ውስጥ-ለውስጥ! በአቶ ደመቀ እና ወ/ሮ ሙፈሪያት መካከል የጦፈ ውድድር ነበር!

ከቻይና ከተመለስኩ ጀምሮ በተደጋጋሚ ስለ ኦሮማራ ጥምረት ፅሁፎችን ማውጣቴ ይታወሳል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ “የኦሮማራ ጥምረት ሊፈርስ ይችላል” የሚል ስጋት ነው። እንደ እኔ አመለካከት የኦሮማራ ጥምረት ከፈረሰ ጉዳቱ የከፋ ነው። በመጀመሪያ አንድ መጠቀስ ያለበት ነገር አቶ ደመቀ መኮነን ደመቀ በአዴፓ (ብአዴን) ሊቀመንበርነት የመቀጠል ፍላጎት አልነበረውም። ይህንን ለግለሰቡም ሆነ ለፓርቲው ቅርበት ካላቸው ሰዎች ለማረጋገጥ ችያለሁ። “ታዲያ ለምን ሃሳቡን ቀይሮ ተመረጠ?” ለሚለው መልሱ ያለው አዴፓና ደህዴን ጋር ነው። ለምንና እንዴት የሚለውን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

አቶ ደመቀ መኮነን እና ወ/ሮ ሙፈሪያት

በእርግጥ አዴፓ አቶ ደመቀ መኮነን ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሏቸው ነበር። ነገር ግን የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት፣ እንዲሁም ገለልተኛና የሌላ ፓርቲ ደጋፊዎችና አባላት ጭምር አቶ ደመቀ በሊቀመንበርነት እንዲቀጥል ባደረጉት ግፊት በአመራርነት ለመቀጠል መወሰናቸውን ገለፁ። የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሆነው የተመረጡት ሰዎች ስምና ያገኙት ድምፅ ሲገለፅ አቶ ደመቀ ከዶ/ር አምባቸው እና ገዱ አንዳርጋቸው ቀጥሎ ሦስተኛ መሆናቸው ሲታወቅ በአዳራሹ የነበሩት ሰዎች ያሰሙት የተቃውሞ ድምፅ ሁላችንም በቴሌቪዥን የተመለከትነው ጉዳይ ነው።

አቶ ደመቀ ሳይፈልጉ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ የተደረገበት መሰረታዊ ምክንያት የአዴፓ አባላትና ደጋፊዎች የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነትን ቦታ ማጣት የለብንም የሚል ፅኑ አቋም ስለነበራቸው ነው። የድርጅቱ ዋና ሊቀመንበር የመሆን ዕድል የነበራቸው ዶ/ር አምባቸው ደግሞ በፓርቲው አባላት ዘንድ ተወዳጅነት አላቸው። ከውሳጥ አዋቂዎች እንደሰማሁት ከሆነ ዶ/ር አምባቸው የእነ አቶ በረከትን ቡድን በጥያቄ ወጥረው ይይዙ ነበር። ይህን የተመለከቱት እነ በረከት ሆዬ እንደ አቶ መላኩ ፈንታ እስር ቤት ከመወርወር ይሉና ወደ ውጪ ለትምህርት ይልኩታል። ሆኖም ግን “ይሄ ትምክህተኛ’ማ በቂ ገንዘብ እየላክን ደልቶት አይማርም” ብለው የሚላክበትን ገንዘብ አቋርጠውበት ነበር። እሱ ሆይ ከሌሎች የፓርቲው አባላት የጠበቀ ግንኙነት ስለነበረው እነሱ በሚልኩለት ገንዘብ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ መብቃቱን ሰምቼያለሁ።

ከላይ እንደጠቀስኩት ዶ/ር አምባቸው በፓርቲው አባላት ዘንድ እንዲህ ያለ ተወዳጅነት ስላለው የአዴፓ ሊቀመንበር ሆኖ የመመረጥ እድሉ ሰፊ ነበር። ይሁን እንጂ ዶ/ር አምባቸው በሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዘንድ እንደ አቶ ደመቀ እውቅና እና ቅቡልነት የለውም። እንደሚታወቀው ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጡ ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለዚህ በሃዋሳው ጉባኤ አሳሳቢው ነገር “ማን የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ይሆናል?” የሚለው እንደነበር ይታወሳል።

አዴፓ (ብአዴን) የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነትን መልቀቅ እንደሌለበት የጋራ አቋም ይዟል። ብዙዎች የማያውቁት ነገር ደግሞ በዚያው ልክ የደህዴን ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር የመሆን ፅኑ ፍላጎት ነበራት። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዘንድ ደግሞ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከዶ/ር አምባቸው የተሻለ ቅቡልነትና ዕውቅና አላት። ስለዚህ አዴፓ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት ቦታውን ላለማጣት ሲል በድርጅቱ የስልጣን መሰላል ላይ ወደላይ እየወጣ የነበረው ዶ/ር አምባቸውን ያስቆምና ወደታች መውረድ የሚሻውን አቶ ደመቀ መኮነን በሊቀመንበርነት እንዲቀጥል ያደርጋል።

በዚህ መልኩ ወ/ሮ ሙፈሪያት ምክትል ሊቀመንበር ሆና ለመመረጥ የነበራት ጠንካራ ፍላጎት አዴፓ ዶ/ር አምባቸውን ትቶ አቶ ደመቀን በሊቀመንበርነት እንዲመርጥ አስገድዶታል። ትላንት ወ/ሮ ሙፈሪያት “ራሳቸውን ከውድድር ያገለሉበት ምክንያት” በሚል አንድ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ከዚያ በኋላ ብዙ ሰዎች “ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን እንዴት አወቅክ?” በማለት በጥያቄ አፋጥጠውኛል። በእውነቱ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከውድድሩ ራሷን ስለማግለሏ የማውቀው ነገር አልነበረም። ቀደም ብሎ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራት በእጩነት ትቀርባለች የሚል ግምት ነበረኝ። በዕጩነት አለመቅረቧን ሳውቅ ደግሞ ራሷን ከውድድር አግልላ ሊሆን እንደሚችል ገምቼ ከላይ የተጠቀሰውን ፅሁፍ አወጣሁ።

በእርግጥ አንዳንዶች’ማ ከእኔም የባሰ አስቂኝ ተረተረት ፅፈዋል። ለምሳሌ “የምክትል ሊቀመንበርነቱን ቦታ ለወንድሜ (ደመቀ) ለቅቄያለሁ” ብላ ስትል “አቶ ደመቀ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ” የሚል ነገር አንብቤያለሁ። በኢህአዴግ ጉባኤ የተሳተፉ አንዳንድ ወዳጆቻችን የነገሩን ግን ሌላ ነው። ወ/ሮ ሙፈሪያት የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆና ለመመረጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ገልፀውልኛል። አቶ ደመቀ የተመረጠበት የመጀመሪያ ምክንያት ቀደም ሲል በተጠቀሰው የድርጅቱ ስሌት አማካኝነት ኢህአዴግ ውስጥ ያለውን እውቅና እና ቅቡልነት በመጠቀም ነው። ሁለተኛ የአቶ ደመቀ ተወዳዳሪ ዶ/ር ደብረፂዮን መሆኑና ባልተጠበቀ መልኩ ከህወሓት አባላት ድምፅ በማግኘቱ ነው። በመጨረሻ ወ/ሮ ሙፈሪያት በእጩነት ባለመቅረቧ የደህዴን ተወካዮች ከዶ/ር ደብረፂዮን ይልቅ ለአቶ ደመቀ ሰጥተዋል። በዚህ ምክንያት አቶ ደመቀ ያገኙት ድምፅ ከፍ ሊል ችሏል። በአጠቃላይ ግን የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ ለመመረጥ በአዴፓ (ብአዴን) እና ደህዴን መካከል የጦፈ ውድድር እንደነበር የውስጥ አዋቂዎቹ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል

3 thoughts on “ውስጥ-ለውስጥ! በአቶ ደመቀ እና ወ/ሮ ሙፈሪያት መካከል የጦፈ ውድድር ነበር!

  1. ምንአለ ጊዜህንም ጊዝያችንንም በይሆናል ባታጠፋዉና ለኛም ባተርፍ? በዚሁ ከቀጠልክ ላንተ መረጃዎች ያለን አመናታ በጣም ይቀንሳል ወዳጄ ይታሰብበት!

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡