ህወሓት ለሁለት ተከፍሏል! ሃዋሳ ላይ የተደመረው ቡድን መቀሌ የመሸገውን አሳልፎ ይሰጣል!

በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ፤ “ዶ/ር አብይ እንዴት ሆኖ የህወሓቶችን ሙሉ ድምፅ ማግኘት ቻለ?”፣ “ዶ/ር ደብረፂዮን በዕጪነት በቀረቡበት የምክትል ሊቀመንበርነት ምርጫ አብዛኛው የህወሓት አባላት ድምፃቸውን እንዴት ለአቶ ደመቀ መኮነን ሊሰጡ ቻሉ?” የሚሉት ጥየቄዎች በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በደንብ ያሳያል። በአንድ በኩል በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የህወሓት አባላት ዶ/ር አብይ ሙሉ ድምፅ፣ ለአቶ ደመቀ መኮነን ደግሞ ከራሳቸው ድርጅት ሊቀመንበር የበለጠ ድምፅ በመስጠት መርጠዋቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አክራሪ የህወሓት አመራሮችና አባላት ልሳን የሆነው Tigraionline የተሰኘው ድረገፅ ከወትሮ በተለየ የዶ/ር አብይ መመረጥን ከተቀበለ በኋላ የአቶ ደመቀ መኮነን መመረጥ ለኢህአዴግና ሀገሪቱ ትልቅ ኪሳራ እንደሆነ ፅፏል፡፡

ነገር ግን ይህ ድረገፅ ከ20 ቀን በፊት ባወጣው ፅሁፍ ዶ/ር አብይ ከስልጣን መውረድ አለባቸው ብሎ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ “ጠ/ሚ አብይ ሀገሪቷን ለመምራት ብቃት የለውም፣ ከውጪ ሃይሎች ጋር ተመሳጥሮ ሀገሪቷን ለመበታተን እየሰራ ነው፣ ፍፁም አምባገነን የመሆን ምልክት እያሳየ ነው” የሚሉ ምክንያቶችን አቅርቧል፡፡ በዚህ ፅሁፍ በአቶ ደመቀ መኮነን ላይ የቀረበው ነገር የፌደራል ስርዓቱን ለማፍረስ ከዶ/ር አብይ ጋር በሚስጠር እየሰሩ ነው ([Abiy Ahmed] is secretly working with Gedu Andargachew and Demeke Mekonnen to destroy the federal system…) የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሃዋሳ ላይ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የአክራሪ ህወሓቶች ልሳን የሆነው ድረገፁ ጥቃቱን ከዶ/ር አብይ ወደ አቶ ደመቀ አዙሯል፦

“Prime Minister Abiy Ahmed’s reelection is not surprising given the populism he generated and the anti EPRDF sentiment in Ethiopia, what is surprising is reelection of Demeke Mekonnen. In our view Demeke Mekonnen is one of the architects of the breakdown of law and order in Amara regional state and the rest of country. Demeke should have been brought to justice for what happened to the thousands of people with Tigrai origin, the Agaw people, and the Qemant people in Amara regional state in 2016 and 2106. …Any other person from SNNPR or from Ahmara region would have been better to work with Dr. Abiy Ahmed, but by electing Demeke EPRDF told the Ethiopian people it is still playing games.”

ትላንት ባወጣሁት ፅሁፍ በኢህአዴግ ጉባኤ ተሳታፊ ከነበሩ ውስጥ አዋቂዎች ባገኘሁት መሠረት፣ ህወሓት ቀድሞ ከሚታወቅበትና አብዛኞቻችን ከምንጠብቀው የፀረ-ኦሮማራ አቋምና አመለካከት ተላቅቆ ለዶ/ር አብይ እና አቶ ደመቀ ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ በጉባኤው ወቅት የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ዶ/ር አብይ ባለፉት ጥቂት ወራት ላሳዩት የላቀ አመራር አድናቆታቸውን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው ላይ የተሳተፉ የህወሓት አባላት ለዶ/ር አብይ ሙሉ ድምፅ ሲሰጡ ለአቶ ደመቀ መኮነን ደግሞ ከዶ/ር ደብረፂዮን በላይ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል የአክራሪ ህወሓቶች ልሳን የሆነው Tigraionline ጥቃቱን ከዶ/ር አብይ ወደ አቶ ደመቀ መኮነን አዙሯል፡፡

በዚህ መሠረት፣ መቀለ ላይ የመሸገው አክራሪ ቡድን በTigraionline በኩል የሚፈፅመውን ጥቃት ከዶ/ር አብይ ወደ አቶ ደመቀ መኮነን ሲያዞር ሃዋሳ ላይ፦

  • 1ኛ) የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ለጠ/ሚ አብይ አህመድ ያላቸውን አድናቆትና ክብር በይፋ ገለፁ፣
  • 2ኛ) የህወሓት ተወካዮች ለዶ/ር አብይ ሙሉ ድምፅ ሰጡ፣
  • 3ኛ) አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዶ/ር ደብረፂዮንን ለኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት ዕጩ እንዲሆን ጠቆመ፣
  • 4ኛ) አብዛኞቹ የህወሓት ተወካዮች ድምፃቸውን ከዶ/ር ደብረፂዮን ይልቅ ለአቶ ደመቀ ሰጠ፡፡

እነዚህ ነጥቦች መቀለ ላይ በመሸጉት የእነ ስዩም መስፍን፣ አቦይ ስብሃት፣ አባይ ፀሃዬ፣… ወዘተ በመሣሠሉት ፀረ-ለውጥ አቋም ያላቸው የህወሓት መስራቾች፥ አመራሮች እና በዶ/ር ደብረፂዮን በሚመራው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ያለውን ልዩነት በግልፅ ይጠቁማል፡፡ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት በግልፅ ለመረዳት ደግሞ ዶ/ር ተክለኣብ ሽብሩ “የህወሓት ሐዘን” (TPLF’s Grief) በሚል በድረገፃችን ላይ ያወጣውን ፅሁፍ ዋቢ ማድረግ ተገቢ ነው። እንደ ዶ/ር ተክለኣብ ገለፃ፣ የኦሮማራ ጥምረት በህወሓት ላይ ያደረሰውን ከባድ ሽንፈት ተከትሎ ድርጅቱ በከባድ ሀዘን ውስጥ ወድቋል። ይህ ሀዘን ደግሞ የራሱ የሆኑ ደረጃዎች አሉት። እነሱም፦ ሽንፈቱን መካድ (Denial)፣ ሁለተኛ ንዴት (ብስጭት) (Anger)፣ ሦስተኛ ድርድር (Bargain)፣ አራተኛ ድብርት (Depression) እና አምስተኛ መቀበል (Acceptance) ናቸው።

Elisabeth Kubler Ross. Stages of Grief.

ዶ/ር ተክለኣብ ከላይ የተጠቀሰውን ፅሁፍ ባወጣበት ወቅት ህወሓት ንዴት (Anger) በሚለው የሀዘን ደረጃ እንደሆነ ገልፆ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ አክራሪ የህወሓት መስራችና አመራሮች በልሳናቸው “Tigraionline” ላይ የሚያወጧቸውን ፅሁፎች፣ እንዲሁመ በህወሓት ውስጥ እያቆጠቆጠ የነበረውን መከፋፈል እንደ ማሳያ ጠቅሶ ነበር፡-

“…as a sign of anger and desperation, propaganda to fear-mongering is underway. Tigraionline commentators are floating an idea of drafting 10,000 youths from each 35 Tigray woredas. This, on top of an already existing region’s well trained and equipped Tigray militia, is to establish, 3rd generation Woyane, with a total of 350,000 military personnel. Its mission is to march to Addis Ababa and regain the lost power. …Lastly, as a sign of anger at oneself, TPLF is now divided into two: a reformist group and old guards. While the old guards led by Abay Tsehay, Seyoum Mesfin, and Samora Yenus are to stay the angry course; Arkebe Oqubay, Abraham Tekeste, Getachew Reda and Debretsion Gebremichael represent a change of heart to join the reformists. It is most likely that in the coming months and weeks, this new reformists will lead TPLF into bargaining phase.”

በመቀጠል ዶ/ር ተክለኣብ አክራሪ አመለካከት ያላቸው የህወሓት አመራሮች ከገቡበት ብስጭት ሲወጡ ወደ ድርድር እንደሚመጡ ገልፆ ነበር። ለዚህ ደግሞ እንደ ማሳያ የተቀሰው እንደ Tigraionline ያሉ ድረገፆች ለውጡ አይቀሬ እንደሆነ ሲገነዘቡ በለውጡና የለውጡ መሪዎች ላይ የሚከፍቱትን ዘመቻ ቀስ በቀስ እየቀነሱ እንደሚመጡ ይገልፃል። በዚህ ረገድ ከ20 ቀን በፊት ዶ/ር አብይ ከስልጣን መውረድ አለበት የሚል ፅሁፍ ይዞ የወጣው Tigraionline ዛሬ ደግሞ የዶ/ር አብይ መመረጥ አይቀሬና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚገልፅ ፅሁፍ ይዞ ወጥቷል።

በዚህ መሰረት በአክራሪ የህወሓት ሰዎች “በጠላትነት” ሲፈረጅ የነበረው ዶ/ር አብይ ከህወሓት ሊቀመንበር አድናቆት ሲቸረው፣ የመቀለው ቡድን ልሳን የሆነው Tigraionline ደግሞ አብዛኛው የህወሓት አበላት በሰጡት ድምፅ የተመረጠውን አቶ ደመቀ መኮነን ላይ ዘመቻ ከፍቷል። ይህ እንደ ዶ/ር ተክለኣብ አገላለፅ፣ የህወሓት ሀዘን ከንዴት/ብስጭት (Anger) በመውጣት ወደ ድርድር (Bargain) መግባታቸውን ያሳያል። ይህን የህወሓት ሀዘን (TPLF’s Grief) ደረጃ ዶ/ር ተክለኣብ እንዲህ ይገልፀዋል፦

“Bargaining is an emotional state when grieving person initiate negotiation for restoring aspects of the situation that is lost. It comes in response to feelings of powerless and vulnerable. While blaming others is the main characteristics of the anger phase, taking responsibility and culpability often characterizes the bargain phase. Therefore, in comparison with anger, this is a weaker line of defense designed to protect oneself and in effect settle the loss in a “win-win” solution.”

ከላይ በተገለፀው መሠረት፣ መቀለ የመሸገው
አክራሪ ቡድን ሽንፈት ከሚያስከትለው ድብርት (Depression) ለመውጣት ሲል ራሱን ለድርድር የሚያዘጋጅበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከአምስቱ የሀዘን ደረጃዎች ውስጥ ይህ አክራሪው የህወሓት ቡድን ለውጡን ለመቀበልና በክብር ለመሰናበት የሚሻበት ወቅት ነው፡፡ በሃዋሳው ጉባኤ ተሳታፊ የነበረው የህወሓት ቡድን ግን በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ህልውናውን ለማረጋገጥ ጥረት የሚያደርግበት ነው፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግና በጠ/ሚ አብይ የሚተላለፉ የለውጥ እርምጃዎችን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ አያቅማማም፡፡ በተለይ የዶ/ር ደብረፂዮን ቡድን በወንጀል የሚፈለጉ የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮችን ለፌደራሉ መንግስት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል፡፡ አክራሪ አቋም የነበራቸው አመራሮችም መለሳለስ የሚያሳዩበትና በወንጀል ተግባር ከተሰማሩት ራሳቸውን ማራቅ የሚጀምሩበት ነው፡፡ በአጠቃላይ የዶ/ር ደብረፂዮንን ቡድን ከአክራሪው ቡድን ለመነጠልና የለውጡ አካል ለማድረግ የሚቻልበት ወሳኝ ደረጃ ላይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡