በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የታጠቁ ወታደሮች ለውይይት ወደ ቤተ-መንግስት ሄዱ!

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ዛሬ በቤተ-መንግስት ዙሪያ የተከሰተውን ግርግር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በቡራዩ አከባቢ ለግዳጅ ተሰማርተው የነበሩ ወታደሮች ወደ ቤተ-መንግስት በአካል በመምጣት ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ ተናግረዋል። የወታደሮቹ ጥያቄ በዋናነት ከደሞወዝ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልፀዋል። ከደሞወዝ ጋር በተያያዘ መምህራን፥ የህክምና ሰራተኞች፥… ወዘተ ተመሳሳይ ጥያቄ እንደሚያነሱ በመጥቀስ የደሞወዝ ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ ተናግረዋል። ሌላው ቀርቶ ቃለ-ምልልስ የሚያደርጉለት ጋዜጠኛ ጭምር በቂ ደሞወዝ እንደማይከፈለው በቀልድ እያዋዙ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ወታደሮቹ በቤተ-መንግስት ተገኝተው ጥያቄያቸውን በቀጥታ ማቅረባቸው እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንደሌለበት ገልፀዋል። በመጨረሻም ጠ/ሚኒስትሩ ከወታደሮቹ ጋር ጠቃሚ መረጃ የተገኘበት ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል ቤተ-መንግስት ውስጥ በወታደሮች ታግተዋል ሲባሉ የነበሩት ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነን ከወታደሮቹ ጋር ተቃቅፈው የተነሱት ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተለቅቋል። በዚህም ብዙዎች እፎይታ እንደተሰማቸው መገመት ይቻላል። ብዙዎች ዛሬ ቀኑን ሙሉ በፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ገፆች ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች በጭራሽ ተቀባይነት የሌላቸውና ህዝቡን ወደ መጥፎ ተግባር የሚመሩ መሆናቸውን ሲገልፁ ይስተዋላል። ጠ/ሚ አብይ በበኩላቸው ትክክለኛ መረጃ ከመንግስት እስኪሰጥ ድረስ ህዝቡ በትዕግስት መጠባበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

አንድ የሀገር መሪ ማንኛውንም ዓይነት ነገር የሚያከናውነው ቀድሞ በተቀመጠለት የግዜ ፕሮግራም ነው። አንደኛ እንደ ሀገር መሪ በቀን ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን ሊያከናውን ስለሚችል ውሎው በፕሮግራም የሚመራ መሆን አለበት። ሁለተኛ የፕሮቶኮልና የጥበቃ ጉዳይ ስላለ አንድ የሀገር መሪ ከተቀመጠለት ፕሮግራም ውጪ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በፈለገው ሰዓትና ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም። ስለዚህ ከሞላ-ጎደል በሁሉም ሀገር ማለት ይቻላል፣ ቀደም ብሎ ፕሮግራም ያላስያዘ የየትኛውም የሥራ ዘርፍ ሰራተኛ፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እየሄደ ሳለ እግረ-መንገዱን ወደ ቤተ-መንግስት ጎራ በማለት ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ጋር መወያየትና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ማግኘት አይችልም።

በእርግጥ እንደ ጠ/ሚ አብይ አገላለፅ ወታደሮቹ ያነሱት ጥያቄ የመምህራን፥ የህክምና ባለሞያዎች፥ ጋዜጠኞች፥ … በአጠቃላይ አብዛኛው የግልና የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጥያቄ ነው። ነገር ግን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራ ለሥራ ከሄዱበት አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲመለሱ እግረ-መንገዳቸውን ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በመሄድ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በአካል ለመገናኘት አይጠይቁም። ጥያቄያቸው ምንም ያህል አንገብጋቢና ከጠ/ሚ አብይ ውጪ በሌላ ምላሽ የማያገኝ ቢሆን፣ ከሃዋሳ ከተማ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች ወደ ሃዋሳ ከተማ ከመመለሳቸው በፊት እግረ-መንገዳቸውን ወደ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ጎራ በማለት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር መወያያት አይችሉም። ሌላው ቀርቶ ጠ/ሚኒስትሩ በፅፈት ቤታቸው ለሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቤተ-መንግስት የተገኙት ጋዜጠኞች አጋጣሚውን በመጠቀም የደሞወዝ ጭማሪ ወይም ሌላ ዓይነት ጥያቄ መጠየቅ አይችሉም።

በአጠቃላይ በየትኛውም ሀገር መምህር፥ ወታደር፥ ጋዜጠኛ ወይም የቤተ-መንግስት ሰራተኛ በፈለገው ሰዓት ወደ ጠ/ሚኒስትሩ በመሄድ ጥያቄውን ማቅረብ አይችልም። በዓለም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ዛሬ ቁጥራቸው ወደ አርባ የሚጠጋ ወታደሮች በራሳቸው ፕሮግራም ወደ ቤተ-መንግስት በመሄድ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር መወያየት ቻሉ። ወታደሮቹ ከምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ጋር ደግሞ ተቃቅፈው ፎቶ ተነሱ። በቤተ መንግስት የተደረገው ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው ተናገሩ። ጠ/ሚኒስትሩ ከወታደሮቹ ጋር የነበረውን አስደሳች ቆይታ የሚያሳዩ የፎቶ ምስሎች ተለቀቁ። በመጨረሻም ወታደሮቹ በቤተ-መንግስት የራት ግብዣ እንደሚደረግላቸው ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ዘገቡ። የተቀረው የህብተሰብ ክፍል በበኩሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መልቀቅ ተገቢነት የለውም እያለ ባለቀ ሰዓት የሰማውን ማራገብ ጀመረ።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ሌላው ቀርቶ የቤተ-መንግስት ሰራተኞች እንኳን ስለራሳቸው ችግር ለመወያየት በፈለጋቸው ግዜ ከሀገሪቱ መሪ ጋር ስብሰባ መቀመጥ አይችልም። ከመምህራን፥ ጋዜጠኞች፤ ሐኪሞች፥ ከቤተ-መንግስት ሰራተኞች፥…ወዘተ በተለየ የዛሬዎቹ ወታደሮች ወደ ቤተ መንግስት በመሄድ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር መወያየት እንችላለን የሚል እምነት ከየት አመጡ? የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው የሌላ መስክ ሰራተኞች ልክ እንደ ወታደሮቹ ወደ ቤተ-መንግስቱ ቢሄዱ ከጥይት ናዳ ቢተርፉ እንኳን ከእስር የማምለጥ እድላቸው በጣም ጠባብ ነው። ታዲያ ወታደሮቹ ወደ ቤተ መንግስት በመግባት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር መገናኘት የቻሉበት ሚስጥር ምንድነው? መልሱ የጦር መሳሪያ ነው!

የቤተ-መንግስቱ ጥበቃዎች ወታደሮቹን በጥይት ሆነ በእስራት ሊመልሷቸው እንደማይችሉ ያውቃሉ። ወታደሮቹም በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት የሄዱበት ምክንያት ከጥበቃዎች የሚመጣባቸውን ማንኛውንም ዓይነት በራሳቸው መመከት እንደሚችሉ በማመን ነው። ወታደርን ከመምህር የሚለየው በታጠቀው የጦር መሳሪያ ነው። ይህ የጦር መሳሪያ የተሰጠው የሀገርና የህዝብን ሰላም ለማስከበር እንጂ የቤተ-መንግስትን ደጃፍ ለመርገጥ አይደለም። እነዚህ ወታደሮች በእጃቸው ላይ ያለውን የጦር መሳሪያ ተጠቅመው ቤተ መንግስት በመግባት ልክ ጠ/ሚኒስትሩን እንዳነጋገሩት ሁሉ ከስልጣን ሊፈነቅሉት አይችሉም ነበር? ዛሬ እነዚህ ወታደሮች ያደረጉትን ነገር ነገ ከየትኛውም አከባቢ ተነስቶ በአዲስ አበባ በኩል የሚያልፉ ወታደሮች ላለማድረጋቸው ምን ዋስትና አለ? ከዚህ አንፃር የዛሬዎቹ ወታደሮች የፈጸሙት ተግባር በምንም አግባብ ቢሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ በኋላም ማንኛውም የታጠቀ ኃይል በተመሳሳይ ድርጊት እንዳይሰማራ አስፈላጊው የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ ከ40 በላይ ወታደሮች ከቡራዩ ወደ ሃዋሳ የሚያደርጉትን የጉዞ አቅጣጫ በመቀየር ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ሲመጡ የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች የማን ጎፈሬ ያበጥሩ ነበር? እነዚህ ወታደሮች የደሞወዝ ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት ጠዋት ላይ ነው። በዚህ ምክንያት በቤተ-መንግስቱ አከባቢ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ትብቅ ፍተሸና ቁጥጥር ሲደረግ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገለጽ ቆይቷል። በድጋሜ ከሰዓት በኋላ በቤተ-መንግስት አከባቢ ግርግር በመነሳቱ ምክንያት በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ከመኪኖቻቸውና ከሚሰሩበት ቢሮ እንዲወጡ ተደርገዋል። ወደ ሃዋሳ የሚሄዱ ወታደሮች መንገዳቸውን ቀይረው ወደ ቤተ መንግስት መሄዳቸው ሳያንስ ከጠዋት ጀምሮ ጉዳዩ መፍትሄ ሳያገኝ የቀረበት ምክንያት ምንድነው? በመከላከያ ሚኒስቴር ከታች እስከ ላይ ያለው የዕዝ ሰንሰለትና ጄኔራሎች ቀኑን ሙሉ ምን ሲሰሩ ነበር?

በመጨረሻ አብዛኞቹ የፖለቲካ መሪዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ዛሬ በታየው ግርግር ዙሪያ ያልተጣሩ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች መልቀቅ አግባብ እንዳልሆነ ሲገልፁ ይስተዋላል። ነገር ግን ጠ/ሚኒስትሩ ራሱ በኋላ ላይ በሰጠው መግለጫ መጀመሪያ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ጥርት ያለ መረጃ እንዳልነበር ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ አንድም የመንግስት ኃላፊ ሆነ ሚዲያዎች ጉዳዩን በማጣራት እውነታውን ለህዝብ ለማሳወቅ ያደረጉት ነገር የለም። ከዚያ ይልቅ በቤተ መንግስት ዙሪያ የተነሳው ግርግር እያየለ ሲሄድ መንግስት የወሰደው እርምጃ ዋና የመረጃ ምንጭ ኢንተርኔትን መዝጋት ነው። የመረጃ ምንጭ በተዘጋበት ሆነ መረጃ የሚሰጥ ኃላፊ ሆነ ሚዲያ በሌለበት የታጠቁ ወታደሮች ከቤተ መንግስቱ ጥበቃዎች ጋር ተፋጥጠዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ወታደሮቹ በዚህ መልኩ ወደ ቤተ መንግስት የሄዱት ስለ ታጠቁና ስለ ታጠቁ ብቻ ነው። ሳይታጠቁ ቢሄዱ ኖሮ እንደ ማንኛውም ሰራተኛ ለጥይት ወይም ለእስር ስለሚዳረጉ ግርግር አያስነሱም ነበር። ከኢትዮጵያ በስተቀር ወታደሮች ለግዳጅ ከተሰማሩበት ሲመለሱ እግረ-መንገዳቸውን ወደ ቤተ መንግስት በመሄድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሞወዝ ጭማሪና ሌሎች ጥያቄዎች እንደሚያቀርቡ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም። እስካሁን ድረስ ባለው ተሞክሮ የሚያሳየው ወታደሮች ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ቤተ-መንግስት የሚሄዱት ለደሞወዝ ጭማሪ ሳይሆን ለመፈንቅለ-መንግስት እንደሆነ ነው። ስለዚህ “ዛሬ ወታደሮቹ በቤተ-መንግስት ተገኝተው ያቀረቡት የደሞወዝ ጭማሪ ጥያቄ ነው” ብሎ ማለፍ የሚቻለው በቢሆን ዓለም እሳቤ ብቻ ነው።

“የወታደሮቹ እንቅስቃሴ ቀላል ስለሆነ የተዛባ መረጃ ማሰራጨት ተገቢ አይደለም” የሚሉ አካላት አሁን ላይ ነገሩ እናንተ እንደምትሉት ቀላል ከሆነ ቀኑን ሙሉ ይህን መናገር ለምን ከበዳቸው? የተሳሳተ መረጃ እንዳይወጣ የፈለገ አካል ትክክለኛውን መረጃ በትክክለኛው ቦታና ግዜ ማድረስ ነው። አሁን ከመሸ በኋላ የወታደሮቹ እንቅስቃሴ “መፈቅለ-መንግስት አይደለም” እያሉ የሚናገሩት ሰዎች ቀኑን ሙሉ አንደበታቸውን ምን ዘጋው? በአጠቃላይ ጠ/ሚኒስትሩ ለህዝብ መግለጫ የሰጡበት ምክንያት፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ከወታደሮቹ ጋር ተቃቅፎ ፎቶ የተነሱበት፣ በሌላ ሳይሆን ቀኑን ሙሉ የተሳሳተ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለተለቀቀ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የመንግስት ኃላፊዎች ሆኑ ሚዲያዎች አስፈላጊውን መረጃ ለህዝብ ማቅረብ ስላልቻሉ ነው። በራሳቸው ድክመት የተፈጠረውን ችግር “በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች….” እያሉ ወቀሳ ማብዛት አይቻልም። ማህበራዊ ሚዲያ ባኖር ኖሮ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን ይቅርና ወታደሮቹ ቤተ-መንግስት አከባቢ ደርሰው እንደነበር እንኳን አይገልፁም ነበር።

One thought on “በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የታጠቁ ወታደሮች ለውይይት ወደ ቤተ-መንግስት ሄዱ!

  1. አዎ! ታይቶ የማይታወቅ፣ ቢደረግም ለመንግሥት ግልበጣ ብቻ ነዉ። አስገራሚ አስደንጋጭና አስፈሪ ነበር። ዋናዉ በፀጥታ፣ በደህንነት፣ በመከላከያና በመንግሥት ተቋም ዉስጥ ያለዉን የጎላ ችግር በአጠቃላይ ያለመደመርና የዳተኝነትና እምብተኝነት እንዳለና በጠ/ሚ ሕይወቱና በሃገሪቷ ህልዉና ላይ ከባድና የከፋ የመከራ ጥላ እንዳንዣበበና ያደረገና የሚያሳይ ነዉ። ጠ/ሚሩን አስቸጋሪና ተፈታታኝ ሁኔታ ዉስጥ የከተተ ለተደራራብ ችግር የሚዳርግ ሃገሪቷን ወደ ባሰ ችግር የመዝፈቅ ብቃት ስላለዉ ጠ/ሚሩ … ሳይደርቅ በቅጠሉ… እንደሚባለዉ በዚህ በኩል ትኩረት በጣም ያስፈልጋል እየተደረገ ያለዉን ባላዉቅም። ወታደር የሥነሥርዓት ተገዥ ወደደም ጠላ መሆን አለበት፣ ያለበለዚያ መለዮዉን ቁጭ ያርግ። ይህ ችግር ቅድሚያ ተሰጥቶ መታየትና መተግበር የሚያስፈልገዉና ጊዜ መሰጠት የለበትም።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡