የጠ/ሚ አብይ አመራር ከታጠቁ ወታደሮች ይልቅ “የሰይጣን ጠበቆች” ያስፈልጉታል!

በመጀመሪያ ደረጃ “የሰይጣን ጠበቃ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ታሪካዊ አመጣጡን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል። ከዚያ በመቀጠል የጠ/ሚ አብይ አህመድ አመራር ለምን የሰይጣን ጠበቃ እንደሚያስፈልገው እንመለከታለን። የምዕራባዊያን ህዳሴ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትግል ሲደረግ የነበረው በዋናነት ከሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን ጋር ነው። በተለይ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በሰዎች መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ህይወት ላይ ሙሉ ስልጣንና ቁጥጥር ነበራት። በመሆኑም የሰዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በቤተ-ክርስቲያኗ አስተምርሆት መሰረት መከናወን አለባቸው። ከዚህ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለከፍተኛ ቅጣት ይዳርጋል።

በአውሮፓ የህዳሴው ዘመን ልሂቃን ቀዳሚ ተግባር ይህን የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ሥራና አሰራር መተቸት ነበር። በዚህ መልኩ የሚሰነዘር ትችትና ነቀፌታ በመጨረሻ በሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ንቅናቄ እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል። በእርግጥ ይህ ንቅናቄ እ.አ.አ. በ1517 ዓ.ም በጀርመናዊ ማርቲን ሉተር እንደተጀመረ ይነገራል። ነገር ግን፣ ከማርቲን ሉተር በፊት ቢያንስ ለሃያ (20) ግዜ ተጀምሮ ንቅናቄ ተደርጎ የነበረ ሲሆን የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን ሁሉንም በሃይል ማዳፈን ችላ ነበር።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በማርቲን ሉተር መሪነት የተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ ለ21ኛ ግዜ ነው። ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር በ1520ዎቹ የቤተ-ክርስቲያኗን አስተምኽሮት በመተቸት የፃፋቸውን ፅሁፎች እንዲያነሳ (retract) እንዲያደርግ ከጀርመን ንጉሱና የሮማ ጳጳስ ትዕዛዝ ተሰጠው። ማርቲን ሉተር ግን ትዕዛዙን ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበረም። ይህን ተከትሎ ጳጳሱ ከቤተ-ክርስቲያኗ ሲያባርሩት፣ ንጉሱ ደግሞ በወቅቱ በነበረው የጀርመን ህግ የመጨረሻውን ቅጣት፣ የህግ-ከለላን በማንሳት (outlaw) ማርቲን ሉተር በተገኘበት ቦታ እንዲገደል የሚል ፍርድ አሰተላለፉበት።

በዚህ መልኩ በማርቲን ሉተር ላይ የተላለፈው ውሳኔ በመጨረሻ የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያንን ለሁለት ከፈላት። ከዚህ በተጨማሪ ቤተ-ክርስቲያኗ በህዝብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነትና እምነት አሳጣት። በዚህ ምክንያት በህዝቡ ዘንድ ያጣችውን ተቀባይነትና ተዓማኒነት መልሳ ለማግኘት የቤተ-ክርስቲያኗን ሥራና አሰራር ከስህተትና አድልዎ የፀዳ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንፃር በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች ውስጥ፣ ቅድስና የሚሰጣቸው ጳጳሳት በእምነትና ምግባራቸው ደካማ፣ በፈጣሪ ፊት ሞገስና ክብር የሌላቸው ናቸው የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል።

ከላይ የተጠቀሰውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የጳጳሳቱን መንፈሳዊ ፅናትና ሃጢያትን መርምሮ ቅድስና በሚሰጠው የቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ (congregation) ሥራና አሰራር ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግ ይገባል። ያለ ትችትና ነቀፌታ ደግሞ የሲኖዶሱን ሥራና አሰራር ከስህተትና አድልዎ የፀዳ ማድረግ አይቻልም። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲተቹና ሲነቅፉ የነበሩት ሰዎች በፕሮቴስታንት ተሃድሶ ንቅናቄ ከሮማ-ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያ ተገንጥለዋል። በቤተ ክርስቲያኗ የቀሩት ከማንኛውም ዓይነት ትችትና ነቀፌታ የታቀቡ ብፁዓን ብቻ ናቸው።

በዚህ ምክንያት የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን በሕዝብ ዘንድ ያጣችውን ተቀባይነትና ተዓማኒነት መልሳ ለማግኘት የነበራት ብቸኛ አማራጭ በሲኖዶሱ ውስጥ የሰይጣን ተወካይ እንዲኖር መፍቀድ ነው። በዚህ መሰረት እ.አ.አ. በ1587 ዓ.ም በቤተ-ክርስቲያኗ ሙሉ እውቅና የተሰጠው “Promotor Fidei” በመባል የሚታወቅ የሥራ ክፍል ውስጥ ተመሰረተ። በዚህ የሥራ ክፍል የሚሰራው ደግሞ “የሰይጣን ጠበቃ” (Devils’ Advocate) በመባል ይታወቃል። እ.አ.አ. በ1913 ዓ.ም የታተመው የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሰይጣን ጠበቃን የሥራ ድርሻ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“To prevent any rash decisions concerning miracles or virtues of the candidates for the honor of the altar. All documents of the canonization processes must be submitted to his examination, and the difficulties and doubts that he raises over the virtue and miracles are laid before the congregation and must be satisfactorily answered before any further steps can be taken in the processes. His duty requires him to prepare in writing all possible arguments, even at times seemingly slight against the raising of any one to the honors of the altar…”

የሰይጣን ጠበቃ በተለይ በ18ኛው ክ.ዘመን መጀመሪያ አከባቢ በቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በጣም ወግ አጥባቂ በነበረችው ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሳዊና ዓለማዊ ምግባራቸው እጅግ የላቁ ቅዱሳንን ለመለየት የሰይጣን ጠበቃ ቁልፍ ሚና ነበረው። ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ቅድስና ከመሰጠቱ በፊት የዕጩዎቹ ተዓምራትና ገድሎች በጥሞና እንዲጤኑ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ በቅድስና አሰጣጥ ሂደቱ የተዘጋጁ የሰነድ ማስረጃዎች በሙሉ ለሰይጣን ጠበቃው ገቢ ይደረጋሉ። እሱም እነዚህን የሰነድ ማስረጃዎች በጥሞና በማጤን በዕጩዎቹ መንፈሳዊ ፅናትና ምግባርን መርምሮ ያገኛቸውን ለመወሰን አስቸጋሪ ወይም አጠራጣሪ ጉዳዮችን በዝርዝር ለሲኖዶሱ ያቀርባል። ሲኖዶሱም ቀጣይ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ዕጩዎቹ ከሰይጣን ጠበቃው ለተነሱት ጥያቄዎች አሳማኝ የሆነ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

የሰይጣን ጠበቃ የቤተ-ክርስቲያኗ ሲኖዶስ አባል መሆኑ ባልተጣራ መረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ በጥድፊያ የቅድስና ማዕረግ እንዳይሰጥ፣ እንዲሁም የአሰራር ሂደቱ ግልጽነትና ተዓማኒነት እንዲኖረው አስችሏል። በዚህ መሰረት የሰይጣን ጠበቃ ለቅድስና ማዕረግ በዕጩነት የቀረቡትን ሰዎች ምግባርና የሞራል ልዕልና በጥንቃቄ በመርመር እና መነሳት ያለበትን ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ በማንሳትና አጥጋቢ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ፣ በፈጣሪ ፊት ሞገስ፣ በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ደግሞ ተቀባይነት ያላቸው ዕጩዎች ብቻ የቅድስና ማዕረግ እንዲያገኙ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

በመሰረቱ የዜጎችን የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ማክበርና ማስከበር የተሳነው መንግስት እውነታን በአግባቡ መስማትና ማየት አይችልም። የተለየ ሃሳብና አመለካከትን አለማክበር “ሁሉንም ነገር እኔ አውቃለሁ” – (infallibility) ከሚል ግብዝነት የመነጨ የአምባገነንነት መለያ ባህሪ ነው። በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን ማስከበር ሲሳነው ደግሞ በሥራና አሰራሩ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና ማስተካከል ይሳነዋል። ክፍተቶቹን መለየት ቢችል እንኳን በመጀመሪያ ችግሩን በፈጠረው አመለካከትና አሳቤ ውስጥ ሆኖ የሚወስደው የመፍትሄ እርምጃ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል ወይም ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። በመሆኑም የመጀመሪያ ስህተቱን ለማስተካከል የወሰደው እርምጃ ሌላ ስህተት ይሆናል። የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን ማክበርና ማስከበር የተሳነው መንግስት በዚህ መልኩ በስህተት ላይ ስህተት እየደረበ ራሱን ለውድቀት ይዳርጋል።

በመሆኑም የጠ/ሚ አብይ አመራር ራሱን ከተደራራቢ ስህተትና ከማይቀረው ውድቀት ለመታደግ ያለው ብቸኛ አማራጭ የሰይጣን ጠበቃ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የሰይጣን ጠበቃን ሚና የሚጫወቱት ጋዜጠኞች፥ ፀኃፊዎች፥ ጦማሪያን፥ ፖሊከኞች፥ የመብት አቀንቃኞች፥ የማህብረሰብ መሪዎች፥ ምሁራን፥…ወዘተ ናቸው። ከዚህ አንፃር ከጠ/ሚ አብይ አመራር የሚጠበቀው የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን ማክበርና ማስከበር ነው። ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት መግለፅ ከተሳናቸው የመንግስት ሥራና አሰራር በስህተት የተሞላ ይሆናል። በመሆኑም ከላይ በተገለጸው መልኩ ራሱን ለውድቀት ይዳርጋል።

በአጠቃላይ ጋዜጠኞች፥ ፀኃፊዎች፥ ጦማሪያን፥ ፖሊከኞች፥ የመብት አቀንቃኞች፥ የማህብረሰብ መሪዎች፥ ምሁራን፥…ወዘተ በፅሁፍና በቃል የሚሰጧቸው ሃሳቦችና አስተያየቶች የመንግስት ተግባራትን አግባብነትና በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ያሳያሉ። ያለ በቂ መረጃና ማስረጃ በጥድፊያ ውሳኔ እንዳይሰጥ፣ የመንግስት ተቋማትና ኃላፊዎች ሥራና አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው፤ ቅጣት ሆነ ሽልማት፣ ሹመት ሆነ ሽረት፣… ከአድልዎና ወገንተኝነት የፀዳ እንዲሆን፤ በዚህም የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የጠ/ሚ አመራር ከብዙ የታጠቁ ወታደሮች ይልቅ ብዙ የሰይጣን ጠበቆች ያስፈልጉታል። ምክንያቱም የመንግስት ተቀባይነትና ህልውና የተመሠረተው የዜጎችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ማድረግ የሚቻለው የሰይጣን ጠበቆች በሚሰጡት ነፃ ሃሳብና አስተያየት እንጂ በወታደራዊ ጉልበት አይደለም፡፡ በመሆኑም የጠ/ሚ አብይ አመራር ከብዙ የታጠቁ ወታደሮች ይልቅ ብዙ የሰይጣን ጠበቆች ያስፈልጉታል፡፡

One thought on “የጠ/ሚ አብይ አመራር ከታጠቁ ወታደሮች ይልቅ “የሰይጣን ጠበቆች” ያስፈልጉታል!

  1. ጉዳዩ አይከፋም፣ ነገርግን በጠ/ሚ ላይ ያለዉን አመናታ ማጣቱን አጉልቶ ለማሳየት የታሰበ በማር የተለወሰ እንዳይሆን ስጋት አለኝ።
    ትርጉም ለDevil’s Advocate የተሰጠዉ ከዚህ የተሻለ ቢፉለግ ዩሚመረጥ ይመስለኛል።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡