ከደጋፊ ጋራ መወያየት ሆነ መግባባት አይችልም!

ከደጋፊዎች ጋር መሰረታዊ የሆነ ተቃርኖ ያለኝ ይመስለኛል። ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከየትኛውም አካል ደጋፊዎች ጋር የምስማማ አይመስለኝም። አሁንማ ቃሉ ራሱ ሲጠራ የሆነ ጎዶሎ፥ የራሱ የሆነ ነገር የሌለው፥ በራሱ መቆም የማይችል፥… ወዘተ የሚል ስሜት ይሰማኛል። ታዲያ ዛሬ የአማርኛ መዝገበ ቃላትን ከፍቼ የቃሉን ፍቺ መፈለግ ጀመርኩ።

በመጀመሪያ “ደገፈ” ማለት “1. ድጋፍ ሆነ። 2. ረዳ፥ አገዘ። 3. ቀደም ሲል የተሰነዘረን ሃሳብ መቀበሉን ወይም ትክክለኛ ሃሳብ መሆኑን በማጠናከር ተናገረ፥ ሃሳብ ሰጠ።” እንደሆነ ይገልፃል። “ደጋፊ” የሚለውን ደግሞ “ረዳት፥ አጋዥ” ይለዋል። በመጨረሻም “ድጋፍ” የሚለውን ቃል “1. እርዳታ፥ እገዛ። 2. አንድ አካል ባለበት ቦታ ሳይነቃነቅ ወይም ሳይወድቅ እንዲቆይ ጥንካሬ የሚሰጥ ሌላ አካል። 3. መከዳ፥ ትራስ። 4. ማጠናከሪያ፥ ተጨማሪ ሃይል።” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል።

ለምሳሌ የመንግስት ደጋፊዎች የፖለቲካ ቡድኑ ከስልጣን እንዳይወርድ ወይም እንዳይወድቅ ድጋፍና እገዛ የሚያደርጉ ናቸው። በመሆኑም ደጋፊዎች ከረዳትነት ወይም አጋዥነት የዘለለ ሚና የላቸውም። ከዙያ ይልቅ ከሚደፉት አካል የተሰነዘሩ ሃሳቦችን ይቀበላሉ፣ ትክክለኛ መሆናቸውን በማጠናከር ይናገራሉ፣ በዚያ ላይ ሃሳብ ይሰጣሉ። ደጋፊዎች የሌሎችን ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ከማጠናከርና ትክክለኝነቱን ከማረጋገጥና በዚያ ዙሪያ ሃሳብ ከመስጠት በስተቀር የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የላቸውም።

በዚህ መሰረት “ደጋፊ” ሲባል በአይኑና በጆሮው የገባውን የሌሎች ሃሳብና አስተያየት በቃልና በፅሁፍ ወደ ሌሎች የሚያስተላልፍ ነው። ደጋፊ ልክ አሸንዳ የሚባለው የውሃ ቱቦ ከጣሪያው ላይ የሚመጣውን ውሃ ወደታች ከማስተላለፍ የዘለለ ፋይዳ የለውም። በአሸንዳ ውስጥ ውሃን ከመሬት ወደ ጣሪያ ማውጣት እንደማይቻል ሁሉ ደጋፊም ከላይ የተሰጠውን ከመድገምና ማጠናከር ባለፈ የራሱን ሃሳብና አስተያየት ወደላይ ወይም ወደጎን ማስተላለፍ አይችልም።

ደጋፊ ከላይ ተቀብሎ ከሚያስተላልፈው ውጪ በራሱ አዲስ ሃሳብ አያፈልቅም፣ የሌሎችን ሃሳብ ተቀብሎ ወደላይ ወይም ወደጎን ማስተላለፍ አይችልም። በመሆኑም ከሚደግፈው የተለየ ሃሳብና አስተያየት አይቀበልም። የራሱ አቋምና አመለካከት የሌለው ሰው በሃሳብ ልዩነት አያምንም። የሌሎችን የሃሳብና አመለካከት ነፃነት አያከብርም። በአጠቃላይ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያለው ሰው ከደጋፊ ጋራ መወያየት ሆነ መግባባት አይችልም!!!