የኦነግ ትጥቅ መፍታትና ማስፈታት፡ ማን ለምን ይታጠቃል? መቼና ለምን ይፈታል?

በኦቦ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ጦር ሰራዊት ትጥቁን መፍታት አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ዙሪያ ሰሞኑን የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶች ሲሰጡ እንደነበር ይታወሳል። አንዳንዶች ከዚህ ቀደም በህወሓት/ኢህአዴግ የደረሰበት በደል፣ እንዲሁም በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች የጦር መሳሪያ የታጠቁ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች መኖራቸውን በመጥቀስ ኦነግ ትጥቁን መፍታት እንደሌለበት ሲገልፁ ይስተዋላል። በሌላ በኩል መንግስት ባለበት ሀገር የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሌላ ሃይል መኖር ከህግ ማስከበርና ከዜጎች ሰላምና ደህንነት አንፃር አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ ድርጅቱ ትጥቁን መፍታት እንዳለበት ይገልፃሉ። በሁለቱም ወገኖች የሚቀርበው ሃሳብና አስተያየት እንዳለ ሆኖ ጉዳዩን ከመንግስት አመሰራረት ጽንሰ-ሃሳብ አንፃር ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል።

በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን መንግስት የሚመሰርቱት የእያንዳንዱንና የሁሉንም ነፃነት ለማስከበር ነው። ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ ግለሰብ ሦስት ዓይነት ነፃነቶች አሉት። እነሱም፣ 1ኛ፡- በነፃነት የማሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ 2ኛ፡- በነፃነት የመስራትና የመንቀሳቀስ መብት፣ እና 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደርና የመምራት መብት ናቸው። መንግስት፥ ህግና ስርዓት በሌለበት ሁኔታ አንድ ግለሰብ በነፃነት ለማሰብ፥ ለመንቀሳቀስና ራሱን በራሱ ለመምራት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሌሎችን መብትና ነፃነት ይገድባል። ሌሎች ደግሞ ነፃነታቸውን ለማስከበር በአፀፋው በሚወስዱት እርምጃ የሌሎች መብት ይገደባል። እንዲህ እያለ በጋራ የሚኖሩ ሰዎች ህይወትና እንቅስቃሴ በሁከት፥ ብጥብጥና ጦርነት ይታወካል። ስለዚህ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ሰላምና ደህንነታቸውን ለማስከበር መንግስት ይመሰርታሉ።

መንግስት የሚመሰረተው እያንዳንዱ ግለሰብ ከሁሉም ሰዎች ጋር የጋራ ስምምነት በማድረግ ነው። ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የሁሉም ሰዎች 1ኛ፡- በነፃነት የማሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ 2ኛ፡- በነፃነት የመስራትና የመንቀሳቀስ መብት እንዲረጋገጥ እያንዳንዱ ግለሰብ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደርና የመምራት መብት” ለመንግስት በከፊል አሳልፎ ይሰጣል። ራስን በራስ ማስተዳደርና መምራት መብት በዋናነት የጦር መሳሪያ የመታጠቅና የራስን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ስልጣንን ያካትታል። መንግስት በመመስረቱ ሂደት እያንዳንዱ ግለሰብ ከሁሉም ሰዎች ጋራ በሚያደርገው ስምምነት የጦር መሳሪያ የመታጠቅና ሰላምና ደህንነቱን የማስከበር ስልጣኑን ለመንግስት አሳልፎ ይሰጣል። መንግስት ደግሞ ይህን ከሁሉም ዜጎች የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ የሁሉንም ሰዎች ሰላምና ደህንነት ያስከብራል ተብሎ ይታመናል።

በዚህ መሰረት መንግስት የሚመሰረተው እያንዳንዱ ግለሰብ የጦር መሳሪያ የመያዝና የራሱን ሰላምና ደህንነት የማስከበር መብትና ስልጣኑን አሳልፎ በመስጠት ነው። መንግስት ደግሞ በበኩሉ የሁሉንም ሰዎች ሰላምና ደህንነት የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት አለበት። የሁሉንም ሰላምና ደህንነት ማስከበር ከተሳነው ግን ዜጎች ለመንግስት የሰጡትን ስልጣን መልሰው ይወስዱታል። በዚህም የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰላምና ደህንነታቸውን በራሳቸው ለማስከበር ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ። ሆኖም ግን የራሳቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት የሌሎችን መብትና ነጻነት የሚፃረር ተግባር ይፈፅማሉ። እነዚህ ደግሞ መብታቸውን ለማስከበር በአፀፈው የሚወስዱት እርምጃ ወደ ግጭት፥ ብጥብጥና ጦርነት ይወስዳል። የሁሉንም ሰላምና ደህንነት እኩል ለማስከበር ዳግም መንግስት ይመሰርታሉ።

ከላይ በተገለጸው መሰረት የመንግስት አመሰራረት በዋናነት ከጦር መሳሪያ ትጥቅ እና ከዜጎች ሰላምና ደህንነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የሁሉም ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ ከመንግስት በስተቀር የጦር መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ሊኖር አይገባም። ይሁን እንጂ የተለየ የደህንነት ስጋት ያለባቸው ግለሰቦች ከመንግስት እውቅና ፍቃድ በመጠየቅ የጦር መሳሪያ ሊታጠቁ ይችላሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት መንግስት የሁሉንም ዜጎች ሰላምና ደህንነት በጋራ የማስከበር ስልጣንና ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም የእያንዳንዱን ግለሰብ የደህንነት ስጋትና አደጋ መቆጣጠርና መከላከል አይችልም። በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር የሚችለው በተናጠል ሳይሆን በጋራ ነው። በግል የተለየ የደህንነት ስጋት ያለባቸው ግለሰቦች ደግሞ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁ ፍቃድ ይሰጣቸዋል።

የተፈቀደው የጦር መሳሪያ የራሳቸውን ደህንነት ከማስከበር አልፎ በሌሎች ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት የደህንነት ስጋትና አደጋ መፍጠር የለበትም። በዚህ ረገድ የተጣለበትን ግዴታ መወጣት የተሳነው ግለሰብ የተሰጠው ፍቃድ ተቀምቶ በህግ ይጠየቃል። በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የጦር መሳሪያ የታጠቁ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ ከማህብረሰቡ የቆየ ልማድ ጋር የተቆራኘ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ነገር ግን በምንም አግባብ ቢሆን በየትኛውም አከባቢ ዜጎች ከመንግስት እውቅና እና ፍቃድ ውጪ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የለባቸውም። ምክንያቱም ከመንግስት እውቅና እና ፍቃድ ውጪ የሚገኝ የጦር መሳሪያ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የደህንነት ስጋት ይፈጥራል። በግላቸው የተለየ የደህንነት ስጋት የሌለባቸው ሰዎች በህግ አግባብ ከተቀመጠው መስፈርት ውጩ የጦር መሳሪያ የሚታጠቁ ከሆነ ውሎ አድሮ በአከባቢው ሁከት፥ ብጥብጥና ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል። ይህ ደግሞ ለማህብረሰቡም ሆነ ለመንግስት ፋይዳ የለውም።

ይሁን እንጂ ከመንግስት ፍቃድና እውቅና ውጪ ዜጎች የጦር መሳሪያ ሊታጠቁ የሚችሉበት አንድ ብቸኛ አጋጣሚ አለ። እሱም መንግስት፣ 1ኛ፡- በነፃነት የማሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ 2ኛ፡- በነፃነት የመስራትና የመንቀሳቀስ መብት፣ 3ኛ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ከተሳነው፣ እንዲሁም በእጁ ላይ የተሰጠውን ስልጣንና ጦር መሳሪያ በመጠቀም የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚፃረር ተግባር ሲፈፅም ዜጎች የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰላምና ደህንነታቸውን በራሳቸው ማስከበር ይችላሉ። ይህ ደግሞ በመንግስት አመሰራረት ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጎች በጋራ ስምምነት ለመንግስት የሰጡትን ስልጣንና ውክልና በማንሳት የሚደረግ ነው።

ከላይ በተገለጸው መልኩ ዜጎች በግል ወይም በቡድን የጦር መሳሪያ የሚታጠቁት፤ አንደኛ፡- በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎችን መብትና ነፃነት ማስከበር ስለተሳነው ነው፣ ሁለተኛ፡- መንግስት በራሱ ወይም በሌላ ምክንያት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ስለተሳነው ነው። ይህ ከሆነ መንግስት ዜጎች በጋራ ስምምነት የጣሉበትን ግዴታና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ተስኖታል። በመሆኑም ዜጎች በግል ሆነ በቡድን የጦር መሳሪያ የሚታጠቁት የተጣለበትን ግዴታና ኃላፊነት መወጣት የተሳነውን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ አዲስ መንግስት ለማቋቋም ነው።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) የትጥቅ ትግል የጀመረበት መሰረታዊ ምክንያት የኦሮሞን ተወላጆች መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ማስከበር የተሳነውን መንግስት በማስወገድ አዲስ መንግስታዊ ስርዓት ለመዘርጋት ነው። ሆኖም ግን አሁን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ድርጅቱ ወደ የትጥቅ ትግሉን በማቆም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ገብቷል። ይህ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ያስከብራል፤ ኦነግ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ በሚያደርገው የፖለቲካ ትግል የኦሮሞን ህዝብ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው።

በዚህ መሰረት የጠ/ሚ አብይ አህመድ አመራር መንግስት ሲሆን ኦነግ ደግሞ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ይሆናል። ቀደም ሲል በተገለጸው መሰረት መንግስት ባለበት ሀገር የጦር መሳሪያ የታጠቀ የፖለቲካ ቡድን ሊኖር አይችልም። ኦነግ ትጥቅ አልፈታም የሚል አቋም ካለው በሌላ አነጋገር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አልተቀበለም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ከስምምነቱ በኋላም የድርጅቱ ዓላማ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በማስወገድ አዲስ መንግስት መመስረት ነው። በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ታጥቀዋል በሚል ሰበብ ትጥቅ አልፈታም ማለት ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም የተጠቀሱት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የጦር መሳሪያ የታጠቁት በግል ያለባቸውን የደህንነት ስጋት ለመከላከል እንጂ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ አይደለም። በመሆኑም ትጥቅ አልፈታም የሚለው አካሄድ በምንም አግባብ ተቀባይነት የለውም።

One thought on “የኦነግ ትጥቅ መፍታትና ማስፈታት፡ ማን ለምን ይታጠቃል? መቼና ለምን ይፈታል?

 1. ትጥቅ ማን ጋር እንዳለ ሁሉም ያውቃል ፣ የሚዲያ በኦነግ የማይረባ ትጥቅ ላይ ማተኮር ፣ በጣም ያጠያይቃል፣ ድርጅቱ፣ ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፣ እራሱን ለፖሮፓጋንዳ፣ ጥቃት ያጋለጠ ፣ ነው

  የ ኦነግ መፍታት አለ መፍታት ፣ ለውጥ አያመጣም ፣ ማንኛውም ህገወጥ ትጥቅን፣ ማስፈታት የመንግሥት ግዴታ፣ ነው፣ እንዳላችሁትም፣ የዜጎችን ፣ ሠላምና ደህንነት መጠበቅም፣ እንደዚሁ ፣ የመንግሥት ግዴታ ነው፣ አብዛኛዎቹ ፣ የሚደርሱት ችግሮች ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። የሚታየው ግን ጭፍን ድጋፍ ነው፣ ለነአብይ፣

  ሁሉም ተስፋ አስቆራጭ ናቸው ፣ በተለይ ተቃዋሚዎች ፣ ከነሱ ብዙ ስለሚጠበቅ ፣ የሚያሳዝነው ለውጡ መሪ የለውም ፣ ለነአብይ፣(ኢህአዴግ) በጎ ፈቃድ ተትተል፣

  የተቀናጀ የጋራ አመራር መስርተው፣ ለውጡን፣ አቅጣጫ ያሲዛሉ ብለን ስንጠብቅ ፣ በአ/አ ባለቤትነት፣ ላይ ፣ በበቡራዩ ጉዳይ (የመንግሥት ሐላፊነት ነው) ፣መወነጃጀል፣ በመሳሰሉት ነገሮች በማተኮር ፣ መሪዎች ብቻ እንዳልሆኑ ሳይሆን በነሱ በኩል ለውጥ እንደማይመጣ አመልካች ነው፣

  ሃገሬ ኢትዮጵያ ባይ ባይ፣

  ፈጣሪ ፣ በራሱ ፣ ጊዜ፣መልሱን ይሰጣል

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡