የእኛ ሰው በቻይና- ክፍል 1፡- የቻይና ተጓዦች እና ሁለቱ ሰርጎ-ገቦች

“የእኛ ሰው በቻይና” ተከታታይ ፅሁፍ

በዚህ ዓመት የመስከረም ወር ላይ ከእኔ ጋር 11 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለስልጠና ወደ ቻይና ሄደን ነበር። “የእኛ ሰው በቻይና” በሚል ርዕስ በማቀርበው ተከታታይ ፅሁፍ ለ21 ቀናት ያህል በቻይና በነበረን ቆይታ የታዘብኳቸውን አስገራሚ፥ አስቂኝና አስተማሪ ጉዳዮችን ለአንባቢያን ለማካፈል እሞክራለሁ። ይህ ተከታታይ ፅሁፍ በተለያዩ ማስረጃዎችና ምስሎች የተደገፈ ሲሆን አንባቢያን በግል፣ በማህብረሰብ፣ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ጠቃሚ የሆኑ ተሞክሮዎች ይገኙበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ክፍል አንድ፡- የቻይና ተጓዦችና ሁለቱ ሰርጎ-ገቦች

መቼም “ጉዞ ወደ ቻይና” ሲባል ማን፥ ለምን፥ እንዴት፥… ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች መነሳቸው አይቀርም። ስለዚህ ጉዞ ከመጀመራችን በፊት እነማን፥ ለምንና እንዴት ወደ ቻይና የመሄድ እድል እንዳገኘን መግለፅ ተገቢ ነው። በእርግጥ ጉዳዩ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ስለነበር ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ሆኖም ግን ከጉዞው ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ይፋ ያልወጡ አንዳንድ አስቂኝ ጉዳዮች ስላሉ ወደኋላ መመለሱ አይከፋም።

ወደ ቻይና የመሄዱን እድል ያገኘነው በጠ/ሚ አብይ አህመድ አማካኝነት ነው። ጠ/ሚኒስትሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ መምህራን ጋር ውይይት ባደረጉበት ዕለት በአቦ-ሰጥ (randomly) 15 ወንድ መምህራንን ወደ መድረክ አስወጥተው ፑሽ-አፕ ካሰሩ በኋላ “መስከረም ላይ ወደ ቻይና ትሄዳላችሁ” በማለት ብዙዎችን ማስገረማቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ 35 ሴት መምህራንን ወደ መድረክ ጠርተው እነሱም ወደ ቻይና እንደሚሄዱ ተናግረዋል። ከላይ በተገለጸው የውይይት መድረክ በጠቅላላ 50 መምህራን በቻይና መንግስት ድጋፍ በተዘጋጁ አጫጭር የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ አድርገዋል።

ጠ/ሚ አብይ ወደ መድረክ ከጠሯቸው አስራ አምስት መምህራን ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ። ልክ ፑሻ-አፑ እንዳለቀ አሸናፊ ያሏቸውን ሦስት መምህራንን ወደ እሳቸው እንዲቀርቡ ካደረጉ በኋላ “መስከረም ላይ ወደ ቻይና ትሄዳላችሁ” አሏቸው። ይህን ግዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ “እንዴ… እኛስ!” ብዬ ጮሁክ። ጠ/ሚኒስትሩ ጩኸቴን ሰምተው ይሁን ወይም ቀደም ብለው የወሰኑት ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር አልችልም። ነገር ግን ወዲያው ወደኋላ ዞር በማለት “ስንት ናችሁ? አስራ አምስት!? በቃ ሁላችሁም ወደ ቻይና ትሄዳላችሁ” አሉን። ከዚያ ለተወሰነች ቅፅበት ዓይን-ለዓይን ትኩር ብለው ከተመለከቱኝ በኋላ “ስም ዝርዝራቸውን ፃፍና ለፕሮቶኮሉ ስጠው” አሉኝ።

ከመድረኩ እንደ ወረድኩ የሰዎቹን ስም፥ ስልክ ቁጥርና የመጡበትን ዩኒቨርሲቲ መመዝገብ ጀመርኩ። ሁሉም ስማቸውን ለማስመዝገብ ከብበውኛል። እኔም አቀርቅሬ እየመዘገብኩ ሳለ አንድ ከዚህ ቀደም የማውቀው ስም ተነገረኝ። ቀና ብዬ ስመለከት መቐለ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ድግሪ አብሮኝ የተማረ የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው። “እንዴ… አንተ መድረክ ላይ ነበርክ እንዴ?” ስለው “አልነበርኩም! ግን በቃ መዝግበኝ! አብረን ቻይና እንሂድ?” አለኝ። ከጠ/ሚኒስትሩ በተጨማሪ ፕሮቶኮሉም “ስዩም…ከ15 እንዳይበልጥ” ብሎ አስጠንቅቆኛል። በቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ተግባር ተበሳጨሁና “ትቀልዳለህ እንዴ!?” ብዬ ስሙን ሰረዝኩት።

ከዚያ በኋላ “ጸጉረ-ልውጦችን” በአንክሮ እየተከታተልኩ የመምህራኑን ስም መመዝገብ ቀጠልኩ። ልክ 12ኛውን መምህር መዝግቤ ቀና ስል በዙሪያዬ ማንም የለም። ከዛ ራሴን 13ኛ ላይ መዘገብኩና ያልተመዘገቡትን ሁለት መምህራን በዓይኔ መፈለግ ጀመርኩ። ይህን ግዜ ነገሩ የገባው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ ዳንኤል መኮንን “ስዬ…ስዬ” ብሎ ጠራኝ። ወደ እሱ ቀረብ ስል “እኔን መዝግበኝ” አለኝ። በሁኔታው ተገርሜ “ተው ዳኒ አትቀልድ!” ብዬው ልሄድ ስል “ቆይ… 15 ሰው መዝግብ አይደል የተባልከው?” አለኝ። አሁንም “አዎ” ብዬ ልሄድ ስል “ታዲያ መድረክ ላይ የወጣችሁት እኮ 13 ብቻ ናችሁ” አለኝ።

ለካስ ቀድም የጠቀስኩት መምህር ሊመዘገብ የመጣው ይህቺን አይቶ ኖሯል። ዶ/ር አብይ “አስራ አምስት ናችሁ” ያለን በግምት ሲሆን በትክክል መድረክ ላይ የነበሩት ግን አስራ ሶስት መምህራን ብቻ ናቸው። ጠ/ሚኒስትሩና ፕሮቶኮሉ ያሳሰቡኝ የተመዝጋቢው ቁጥር “ከአስራ አምስት እንዳይበልጥ” ብለው ነው። የተመዘገቡት ሰዎች ደግሞ አስራ ሦስት ብቻ ናቸው። ስለዚህ ዶ/ር አብይ ለአስራ አመስት ሰው እድል ሰጥቶ አስራ ሦስት ሰው ብቻ ከተመዘገበ ቀሪዎቹን ሁለት ሰዎች በራሴ ለመምረጥ ወሰንኩ። የቅድሙ መምህር እውነታውን ሳይነግረኝ ሊያታልለኝ ስለሞከረ እሱን አልመዘግብም አልኩኝ። ስለዚህ ዳኒኤል መኮንን የመጀመሪያ ተመራጭ ሆነና 14ኛ ላይ ተመዘገበ።

የቀረችውን አንድ ዕድል ለማን እንደምሰጥ ግራ ገብቶኝ ሳማትር ዓይኔ አንድ ቁመቱ አጠር ያለ መምህር ላይ አረፈ። ይህ መምህር የተቀመጠው እኔ ከነበርኩበት የአዳራሹ ፎቅ ላይ የመጨረሻ ኃላ መስመር ላይ ነው። በዚህ ላይ ቁመቱ አጭር ስለሆነ ወንበር ላይ ተቀምጦ የመድረኩን መሪ ዶ/ር አብይን መመልከት አይችልም። ስለዚህ ሙሉ ውይይቱን ቆሞ ነው ሲከታተል የነበረው። እጄ ላይ የቀረችውን የጉዞ እድል ለእሱ ለመስጠት ወሰንኩ። ከዛ ወደ ቆመበት ሄጄ “ስምህን፥ ስልክ ቁጥርህንና የመጣህበትን ዩኒቨርሲቲ ንገረኝ?” አልኩት። ገርሞት እያየኝ “ዶ/ር ካሳሁን በቀለ፣ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ” አለኝና ስልክ ቁጥሩን ነገረኝ። በሻይ ዕረፍት ላይ የስም ዝርዝሩን ለማስረከብ እየሄድኩ ሳለ ዶ/ር ካሳሁን “ቆይ ግን ለምንድነው ስሜን የመዘገብከው?” ብሎ ሲጠይቀኝ “ወደ ቻይና ትሄዳለህ” አልኩት። ከዛ ነገረ ስራዬ ገርሞት መሰለኝ ከት… ብሎ ሳቀ። በዚህ መልኩ ሰርጎ-ገቦች ከእኛ ጋራ ወደ ቻይና የመሄድ እድል አገኙ።

ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው ምደባ ደግሞ የመጀመሪያ አምስቱ መምህራን ¨2018 Seminar on Enhancing Universities Management for Developing Countries” በሚለው ላይ ተመደቡ። ከተራ ቁጥር 6-15 ያሉት መምህራን ደግሞ ¨2018 Seminar for Education Officials of Developing Countries” በሚለው ሴሚናር እንድካፈል ተመደብን። ከአስራችን ውስጥ አንዱ አቶ ተሰማ አያሌው የተባለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆን ከእኛ ጋር አልሄደም። በመሆኑም የተቀረነው ዘጠኝ መምህራን በቻንግቹን ከተማ በተዘጋጀው ሴሚናር ለመካፈል ወደ ቻይና አቀናን። ቻይና ቤጂንግ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ ደግሞ ሁለት ሴት መምህራን ከእኛ ጋር ወደ ቻንግቹን ከተማ እንደሚሄዱ ነግረውን ተቀላቀሉን። በአጠቃላይ ወደ ቻንግቹን ከተማ የሄዱት ዘጠኝ ወንዶች እና ሁለት ሴቶች፣ በድምሩ 11 መምህራን ናቸው።

ፎቶ ከግራ ወደ ቀኝ:-

ታምራት በቀለ፣ ብርሃኑ ሲመኝ፣ ተክላይ አባይ፣ ካሳሁን በቀለ፣ ዳንኤል መኮንን፣ ስዩም ተሾመ፣ ቅድስና ሰብስቤ፣ የሰራሽ (…)፣ ዮናስ በቀለ፣ ሞገስ ዘውዱ እና በረከት ወሌ

One thought on “የእኛ ሰው በቻይና- ክፍል 1፡- የቻይና ተጓዦች እና ሁለቱ ሰርጎ-ገቦች

  1. Since, I have been following Ethiopian Poltics I found this site has the best place to learn. Specially I became a fond of Seyoume Teshome’s articles. Although I am Ethiopian I spent more than half my age in US never followed current affair about Ethiopia until Dr. Abiy showed up. I left Ethiopia in 1995 after high school.
    I enjoy article like this and one of Seyoum master piece and an eye opener for me of 8 serious article under “ye china geboch”. Seyome thank you very much for all your contribution. Since I don’t get my news feed from Facebook this has been a place for me. Keep up the good work, just know there is one admirer in Las Vegas.
    -Haile G

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡