የእኛ ሰው በቻይና- ክፍል 2፡- የቻይኖች ዓይን እና የጥቁሮች ቆዳ የሁሉንም መልክ አንድ ያስመስላል!

ወደ ቻይና ለመሄድ የተሳፈርንበት አውሮፕላን “Boing Dreamliner” ሲሆን ቤጂንግ ከተማ ለመድረስ የፈጀብን 9 ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ግን የመጣነው በ”Airbus” አውሮፕላን ሲሆን ከቤጂንግ አዲስ አበባ ለመድረስ የፈጀብን 11 ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ነው። ሁለቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ናቸው። በሁለት አውሮፕላን መካከል ይህን ያህል የፍጥነት ልዩነት ይኖራል ብዬ ገምቼ አላውቅም። እንደ ትራንስፖርት መኪና የአውሮፕላንም “1ኛ ደረጃ” እና “2ኛ ደረጃ” እንዳለው የገባኝ ያኔ ነው። ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ስመጣ እንደ ወተት ሲንጠኝ የነበረውን አውሮፕላን ሳስታውስ ደግሞ “3ኛ ደረጃ” ሊኖር እንደሚችል ገመትኩ።

የበረራ ሰዓቱ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት አከባቢ ስለነበር አበዛኛውን የጉዞ ሰዓት ያሳለፍኩት በእንቅልፍ ነው። የበረራ አስተናጋጆቹ ቁርስ ሲያቀርቡ ከጎኔ የነበረው ተጓዥ ቀሰቀሰኝና ቁርስ በላሁ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ቤጂንግ አለም-አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ደረስን። ልክ ከአውሮፕላኑ ስወርድ የሆነ የሚሰነፍጥ ሽታ ሸተተኝ። ቀና ብዬ ዙሪያ ገባውን ስቃኝ አየሩ ልክ እንደ ሐምሌ ወር ጭጋጋማ ነው። ይህ ጭጋግ ግን ደመና ሳይሆን ጭስ ነው። ከታች ያለው ምስል በተሳተፍኩበት ሴሚናር ላይ የቤጅንግን አየር ብክለት ለማሳየት ተብሎ ከቀረቡት ምስሎች ውስጥ የተወሰዱ ናቸው።

ከላይ በምስሉ ላይ እንደሚታየው የቤጂንግ ከተማ አየር ብክለት እጅግ በጣም አስከፊ ነው። በተለይ እንደ እኔ ለሀገሩ ባዳ የሆነ ሰው አየሩን መተንፈስ ይከብዳል። ይህ ብቻ ሳይሆን አየሩ የሆነ የሚያስጠላ ሽታ አለው። አውሮፕላኑ ውስጥ እያለሁ አልሸተተኝም ነበር። የመንገደኞች ተርሚናል ውስጥ ስገባ ደግሞ ሽታው ቆመ። ስለዚህ የቤጅንግ አየር ብክለት እንኳን ለሳንባ ለአፍንጫም ይከብዳል። በዚህ ላይ ደግሞ ሙቀቱ አይጣል ነው። ያለ አየር ማቀዝቀዢያ ሙቀቱን መቋቋም ከባድ ነው።

ቻይና ውስጥ ሁሉም ነገር ትልቅና ብዙ ነው። ከዚህ በፊት በጣም “ትልቅ” ያልከው ነገር ቻይና ስደርስ በጣም ትንሽ ይሆናል። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በጣም ትልቅ ይመስለኝ ነበር። የቤጅንግ አለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ግን በጣም ትልቅ ነው። ቦሌ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም የአየር ማረፊያዎች አንድ ላይ ቢደመሩ የቤጂንግ አለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ግማሽ እንኳን አያክሉም። በአጠቃላይ ሌላ ቦታ በጣም ትልቅ የመሰለህ ነገር ቻይና ስትደርስ በጣም ትንሽ እንደሆነ ትገነዘባለህ።

ሌላ ሀገር ብዙ የመሰለህ ነገር ቻይና ስትደርስ በጣም ትንሽ እንደሆነ ትገነዘባለህ። የቻይና ህዝብ 1.37 ቢሊዮን ነው። የቤጂንግ ከተማ ነዋሪዎች ብዛት 34 ሚሊዮን ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች ብዛት ከብዙ ሀገራት ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ይበልጣል። ሌላው ቀርቶ በቤጂንግ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ብቻ የሚመርመሰመሰው ሰው ብዛት በእኛ ሀገር የአንድ ከተማ ህዝብን ያክላል። ከዚህ በተጨማሪ የከተማዋ ስፋት በጣም አስገራሚ ነው። አስጎብኚያችን እንደ ነገረችን ከሆነ የቤጂንግ ከተማ ስፋት አንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ 180 ኪሎ ሜትር ይሆናል። ስለዚህ የቤጂንግ ስፋት ከአዲስ አበባ እስከ አሰላ ይደርሳል ማለት ነው።
ሌላው በጣም ያስገረመኝ ነገር የቻይናዎች የፊት መልክ ነው። ቻይና ከደረስኩ በኋላ የገባኝ ነገር የቻይናዎች መልክ ልክ እንደ ዜብራ ነው። ከርቀት ሲያዩት ሁሉም ዜብራዎች ላይ ያለው የጥቁርና ነጭ መስመር አንድ ዓይነት ይመስላል። ነገር ግን እያንዳንዱ ዜብራ ላይ ያለው ጥቁርና ነጭ መስመር አሰማመር (Pattern) የተለያየ ነው። በተመሳሳይ የቻይናዎች መልክ ዓይነት ይመስለኝ ነበር። ብዙ ግዜ “አንዱን ቻይናዊ ከሌላው እንዴት ይለዩታል?” እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ነበር።

ቻይናዎች አንድ ዓይነት መልክ ያላቸው የሚመስለን ምን አልባት ትኩረታችን ከፊት ገፅታቸው ይልቅ ትናንሽ አይኖቻቸው ላይ ስለሆነ ይመስለኛል። እዚያው መሃላቸው ቆመህ ስትመለከታቸው ግን የእያንዳንዱ ቻይናዊ መልክ ከሌላኛው የተለየ ነው። በቃ ልክ እኛ የኢትዮጵያዊያን መልክ እንደሚለያየው ሁሉ የቻይናዎችም መልክ የተለያየ ነው። ቻንግቹን ከተማ አንድ የገበያ አዳራሽ መግቢያ ላይ አንድ ቻይናዊ ጎረምሳ “Hey Nigger” ካለኝ በኋላ ግን እነሱም እንደኛ ጥቁሮች በሙሉ አንድ ዓይነት መልክ እንዳለን አድርገው እንደሚያስቡ ገባኝ። ስለዚህ ልክ እኛ ትናንሽ ዓይኖቻቸው ላይ ትኩረት እንደምናደርግ ሁሉ ቻይናዎችም ቆዳችን ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ይመስለኛል። ራስህን ጥቁር፥ ጠይም ወይም ቀይ ነኝ ብትል ያ ቻይናዊ ጎረምሳ “Nigger” ጥቁርነትህን በግልፅ ይነግርሃል። ምን አልባትም እኔ በፊት ቻይናዎች ሁሉ አንድ ዓይነት እንደሚመስሉኝ ሁሉ ለቻይናዎች ጥቁሮች በሙሉ አንድ ዓይነት እንመስላቸዋለን።

One thought on “የእኛ ሰው በቻይና- ክፍል 2፡- የቻይኖች ዓይን እና የጥቁሮች ቆዳ የሁሉንም መልክ አንድ ያስመስላል!

  1. ወንድሜ: Nigger ብሎ መጥራቱ ጥቁርነትህን ለመጥቀስ አይደለም። የበታችነትህን፣ ብርያ መሆንህን አዋርዶ ሲነግርህ ነውና ሲንቋሽሽህ ነው። አንተ እሱን ቻይና ብለህ ብትጠራውና እሱ በአፀፋው Nigger ብሎ ቢጠራህ እኩል አይደለም። የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነህና ድህረገጽህን ከፍተህ Nigger ስለሚባለው ቃል ትርጉምና ታሪካዊ መሠረቱን ብትመረምር ላንትም ሆነ ለተማሪዎችህ ቻይናዎች ምን ያህል ዘረኞችና ራሳቸውን ካንተ የበላይ አድርጉው እንደሚያዩ ልታስርዳ ትችላለህ። ሠላም ሁን።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡