የእኛ ሰው በቻይና – ክፍል 3: የቻይና “ጣጣ” በኢኮኖሚዋ ልክ አድጏል!

በክፍል ሁለት አስራ አንድ መምህራን ከአዲስ አበባ ተነስተው ቤጅንግ ዓለም-አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሳቸውን ገልጬ ነበር። ቀጣዩ ጉዟችን ወደ ሰሜናዊ ምስራቅ ቻይና ቻንግቹን ከተማ ሲሆን ከቤጂንግ በአውሮፕላን አንድ ሰዓት ተኩል አከባቢ ይፈጃል። ቻይና ሶሻሊስት ሀገር እንደመሆኗ የቻይና አየር መንገድ የሀገሪቱን አየር ትራንስፖርት በበላይነት ይቆጣጠራል የሚለው የብዙዎቻችን ግምት ነው። ነገር ግን ከቤጂንግ ወደ ቻንግቹን የሄድነው በደቡባዊ ቻይና አየር መንገድ (Southern China Airlines) ነው። በእርግጥ ልክ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገሪቱን ባንድራ የያዘው የቻይና አየር መንገድ (Air China) አለ። ከእሱ በተጨማሪ ግን በሌላው ዓለም ታዋቂ ከሆኑ አየር መንገዶች በተጨማሪ ቅድም የተጠቀስኩት ደቡባዊ ቻይና አየር መንገድ (Southern China Airlines)፣ ምስራቃዊ ቻይና አየር መንገድ (Eastern China Airlines)፣ ማዕከላዊ ቻይና አየር መንገድ (Central China Airlines)፣ ሻንጋይ አየር መንገድ (Shanghai Airlines) እና ሌሎች የማላስታውሳቸው በአብዛኛው ቻይና ውስጥና በአከባቢው ሀገራት የሚበርሩ አየር መንገዶች አሉ።

ከሌሎቹ አየር መንገዶች በተለየ የቻይና አየር መንገድ (Air China) አገልግሎት ጥራት ከሌሎቹ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው። በጣም ያስገረመኝ ደግሞ ከበረራ አስተናጋጆቹ ጋር አብሮ የሚሰራው የጸጥታ ሰራተኛ ነው። ሌሎች አየር መንገዶችም የፀጥታ ሰራተኛ ሊኖራቸው ይችላል። ይሄ ግን ከአስተናጋጆቹ እኩል በድምፅ ማጉያ ይናገራል፣ በተሳፋሪዎች መካከል እየዞረ ነገሮችን ይቆጣጠራል። የበረራ አስተናጋጆቹ በበረራ ወቅት መደረግ ያለባቸውና የሌለባቸውን ነገሮች ከተናገሩ በኋላ ይህ የጸጥታ ሰራተኛ አስተናጋጆቹ የተናገሩት በአግባቡ ተግባራዊ በማያደርግ ተሳፋሪ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ በድምፅ ማጉያ ይናገራል። ለምሳሌ አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት የበረራ አስተናጋጆቹ ተሳፋሪዎች ቀበቶ ማሰራቸውን ካረጋገጡ በኋላ እሱም ተሳፋሪዎችን መቀመጫ እየዞረ ይቆጣጠራል። እንዲህ ያለ ነገር ስመለከት ይሄ የመጀመሪያ ነው።

በቻይና ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አከባቢ ቻንግቹን ከተማ ደረስን። ያረፍንበት ሆቴል “HolidayInn Express” የሚባል ዘመናዊ ሆቴል ሲሆን ሴሚናሩ የተዘጋጀበት ቦታ ደግሞ እዚያው ሆቴሉ 2ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነው። የመስክ ጉብኝት ሲኖር በአውሮፕላን ወይም በአውቶቢስ እንሄዳለን። ከዚያ በተረፈ ግን በሆቴሉ ምድር ቤት ላይ ምግብ እንበላለን፣ ሁለተኛ ፎቅ ላይ እንሰበሰባለን፣ ከ3ኛ-7ኛ ፎቅ ባሉት የመኝታ ክፍሎች ደግሞ እናርፋለን።

የእኔ መኝታ ክፍል 7ኛ ፎቅ ላይ ስለሆነ በአሳንሱር (ሊፍት) ስወጣና ስወርድ በህንፃው ላይ ያሉትን ፎቆች እቆጥራለሁ። አሳንሱሩ ላይ ከተገጠሙት የፎቅ ቁጥሮች ውስጥ 4 ቁጥር የለችም። ውጪ ወጥቼ በህንፃው ላይ ያሉትን ፎቆች ስቆጥራቸው 6 ብቻ ናቸው። አሳንሱሩ ግን ከአንድ 1-7ኛ ፎቅ ይልና 4ን ይዘላታል። በኋላ ሌሎች ህንፃዎች ላይ የተገጠሙትን አሳንሱሮች ስመለከት ሁሉም “4ኛ” ፎቅ የሚባል ነገር የላቸውም። ነገሩ ገርሞኝ ስጠይቅ ለካስ እንደ አሜሪካኖች 13 ቁጥር በቻይናዎች ዘንድ “4” የመጥፎ ዕድል ቁጥር (Bad Luck Number) ናት። ስለዚህ 4ኛ የሚል ካለ አሳንሱሩ ይቆማል ይሁን ህንፃው ይፈርሳል ለእኔ አይገባኝም። ብቻ ግን ቻይናዎች 4ን የመሰለ ደርባባ ቁጥር የመጥፎ እድል ምልክት ማድረጋቸው አስገርሞኛል።

በዚህ ሴሚናር ለመካፈል ከኢትዮጵያ ከሄድነው 11 ሰዎች በተጨማሪ ከግብፅ 1፣ ከቦክስዋና 1፣ ከአርሜኒያ 1፣ ከኢንዶኖዢያ 2፣ ከደቡብ ሱዳን 6፣ ከማላዊ 5፣ ከሰርኒያም 10 (ካሪያቢያን አከባቢ የምትገኝ ሀገር ናት) እና ከትሬነዳድና ትቤጎ 5 ሰዎች መጥተዋል። በአጠቃላይ በዚህ ሴሚናር ተካፋይ የነበሩት 42 ሰዎች ከታች በምስሉ ላይ የሚታዩት ናቸው። ከኢትዮጵያ የሄድነው በሙሉ በግልና በመንግስት ዩኒቨርሲቲ የምናስተምር መምህራን ስንሆን ከማላዊ የመጡት ደግሞ ሶስት የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የትምህርት ሚኒስትር ሰራተኞች ናቸው። የተቀሩት በአብዛኛው ከትምህርት ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያላቸው የቢሮ ሰራተኞች እና መምህራን ስብጥር ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደቡብ ሱዳን እና ቦክስዋና በትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዳሬክተርነት ደረጃ የሚሰሩ ሰዎች መጥተዋል።

የአውሮፕላኑ ጉዞ በጣም አድካ ስለነበር ቻንግቹን በደረስን ማግስት እረፍት እንድናደርግ ተወሰነ። ከእኔ ጋር ከሄዱት ውስጥ አብዛኞቹ አውሮፕላን ላይ እንቅልፍ የመተኛት ልማድ አልነበራቸውም። በመሆኑም ከአዲስ አበባ ተነስተው ቻንግቹን ለመድረስ ከአንድ ቀን ተኩል (36 ሰዓታት) በላይ ያለ እንቅልፍ ተጉዘዋል። አንዳንዶቹ በቻይና አቆጣጠር ሌሊት ስድስት ሰዓት ተኝተው ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት የነቁ አሉ።

እራት ከበላን በኋላ ከተገኘ ቢራ ለመጠጣት፣ የሚጠጣበት ቦታ ካልተገኘም ከሱፐርማርኬት ገዝተን ለመምጣት ከተማው ውስጥ መዞር ጀመርን። ቢራ የሚጠጣበት ሆቴል ወይም የምንገዛበት ቦታ አሳዩን ብለን ለመጠየቅ እንዴት አንድ እንግሊዘኛ የሚናገር ሰው ይጠፋል? በሄድክበት ሁሉ በእንግሊዘኛ ስታናግረው በቻይንኛ ይመልስልሃል። ምን እንዳልከው ሳይሰማህ በማትሰማው ቋንቋ ይመልስልሃል።

ከተወሰነ ግዜ በኋላ አብዛኞቻችን በእንግሊዘኛ እንደማንግባባ አውቀን መጠየቅ ተውን። ለቻይናዎቹ እንግሊዘኛ ሆነ አማርኛ ልዩነት የለውም። ምክንያቱም በሁለቱም ቋንቋዎች ብትጠይቋቸው መልሳቸው የማታውቁት ቻይንኛ ነው። ይህን ግዜ ወዳጄ ዳንኤል መኮነን በእንግሊዘኛ መጠየቁን ትቶ ዝም ብሎ በአማርኛ ጀመር። “ስማ… ሱፐርማርኬት የት እንዳለ ታውቃለህ?” ይላቸዋል። እነሱም ልክ እንደ ቅድሙ በቻይንኛ ይመልሳሉ። ከዛ ይቀጥልና “አማርኛ ትችላለህ? ዶ/ር አብይን ታውቀዋለህ?… ወዘተ እያለ ይጠይቃቸዋል። እነሱ ግን ያው በቻይንኛ የሆነ ነገር ያወራሉ። ይሄ በጣም የሚያስቅ አጋጣሚ ነበር። ቻንግቹን በቆየንበት ግዜ በአማርኛ ጮክ ብለን ቻይናዎችን ጨምሮ አብረውን ያሉትን የሌላ ሀገር ዜጎችን እናማለን፣ እንፎግራለን፥…ወዘተ።

ቻይና ውስጥ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ ቻይናዊያን ብዛት ከጠቅላላው የእንግሊዝ ህዝብ ብዛት ይበልጣል የሚል ነገር የሆነ ቦታ እንዳነበብኩ ትዝ ይለኛል። ታዲያ ከእነዚህ ውስጥ እንዴት አንዱ እንኳን በድንገት መንገድ ላይ አይገኝም ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ወዲያው ግን በ1.37 ቢሊዮን በሚሆነው የቻይና ህዝብ ውስጥ 60 ሚሊዮን የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ውቂያኖስ ውስጥ እንዳረፈች አንዲት የቀለም ጠብታ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ቻይና ውስጥ መኖራቸውን ትሰማለህ እንጂ በአካል የት እንዳሉ አታውቅም፥ አታያቸውም። ለምሳሌ ቻይና ውስጥ የሚገኙ ግብረሰዶማዊያ ብዛት 70 ሚሊዮን እንደሆነ “CGTN” የተሰኘው የቻይና ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ኔትዎርክ ባቀረበው ዘገባ ላይ ሰምቻለሁ። ስለ ግብረሰዶማዊያን መብት መከበር በሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲዘገብ እሰማለሁ ብዬ በፍፁም አልጠበቅኩም። በዘገባው መሰረት እኮ ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ 5 ፐርሰንቱ ግብረሰዶማዊ ነው። ኦሯ…የቻይና ኢኮኖሚዋ ብቻ ሳይሆን ጣጣዋም በዚያው ልክ አድጓል!