ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያዎች በመሀል አዲስ አበባ 36 ሔክታር መሬት ተዘጋጀ

ውድነህ ዘነበ (ሪፖርተር)

ለገሃር አካባቢ በተዘጋጀው መሬት አነስተኛ ከተማ ይገነባል ተብሏል

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትዕዛዝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶች የሚሰጥ 36 ሔክታር መሬት አዘጋጀ፡፡፡

ይህ ሰፊ መሬት የተዘጋጀው በመሀል አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ክፍላተ ከተሞች አንዱ በሆነው ቂርቆስ ለገሃር ባቡር ጣቢያ አካባቢ ነው፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አልጋ ወራሽ ሼክ መሐመድን ቢን ዛይድ የሚመራ የልዑካን ቡድን፣ በቅርቡ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ሲመጣ ይካሄዳሉ ከተባሉ ኩነቶች መካከል የ36 ሔክታር መሬት ርክክብ ጉዳይ አንዱ ሲሆን፣ በንጉሣዊ ቤተሰቦች የተቋቋሙ ግዙፍ ኩባንያዎች በሚረከቡት ቦታ ላይ አነስተኛ ከተማ ይገነባሉ ተብሏል፡፡ ይህ 36 ሔክታር መሬት የሚያካልለው ዕድሜ ጠገቡ የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ይዞታ የሆነውን ለገሃር ባቡር ጣቢያ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን (የአሁኑ ገቢዎች ሚኒስቴር) መጋዘኖችና 1,500 ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች ያረፉበት ነው፡፡

ለኩባንያዎቹ ተላልፈው በሚሰጡት ቦታዎች ላይ የሚገኙ 1,500 ነዋሪዎች፣ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው የሚፈናቀሉ ሳይሆኑ በፕሮጀክቶቹ ይታቀፋሉ ተብሏል፡፡

በቦታው ላይ ይገነባል የተባለው አነስተኛ ከተማ አፓርትመንቶች፣ ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ አረንጓዴ ቦታዎችና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የሚያካትት መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ በመንደርደር ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በዚህ መነሻ በተለይ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸውን የሚያሻሽሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

በቅርብ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ድጋፍ ያደረገች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን አቅርባለች፡፡

በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሀል ከተማ ሰፊ መሬት ማዘጋጀቱም፣ የዚሁ ግዙፍ ዕቅድ አካል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተጨማሪም የኳታር መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኳታር ንጉሣዊ ቤተሰቦች ኩባንያ ለሆነው ኢዝዳን ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሜክሲኮ ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ ላይ ከገነት ሆቴል ዝቅ ብሎ ስድስት ሔክታር መሬት አስረክቧል፡፡

ኢዝዳን ግሩፕ በተረከበው ቦታ ላይ ሆቴሎችና አፓርትመንቶችን ያካተተ ግዙፍ ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት እያካሄደ ነው ተብሏል፡፡

ምንጨ፦ ሪፖርተር

One thought on “ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያዎች በመሀል አዲስ አበባ 36 ሔክታር መሬት ተዘጋጀ

  1. ቦታዉ ቀደም ተብሎ የተሰጠ እንጂ አሁን ጠ/ሚ ከመጡ ማለት ከመጋቢት በሗላ የሆነ አይደለም ። ለወጥ ያለ ነገር ቢኖር ነዋሪዎቹ እዚያዉ የሚኖሩበት ሁኔታ መካተቱ ነዉ። ለገሃርና ዙሪያዉ እንዲሁም አሁን ከተከለለዉ በላይ ያለዉ መከተቱ እርግጠኛቱን ማን ነዉ የሚያዉቀዉ?

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡