የተንዛዛ የፍርድ ቤት ቀጠሮን ለማስቀረት አዲስ መመሪያ እና የክትትል አሰራር ሊዘረጋ ነው

በፍርድ ቤቶች ከቀጠሮ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ማስተካከል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

በመጀመሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ተገልጋዮች በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል በዋናነት በቀጠሮ መንዛዛት ምክንያት አፋጣኝ ውሳኔ ያለማግኘት አንዱ ነው ተብሏል።

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ለሚያቀኑ በርካታ ዜጎች የቅሬታ ምንጭ ሲሆን፥ ረጃጅም ቀጠሮዎች ዜጎች በፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይረኩ ከማድረጋቸው በተጨማሪም ጉዳያቸውን በቤታቸው ይዘው እንዲቀመጡ የሚያደርጉ መሆኑም ይነገራል።

አንድ ጉዳይ ምርመራው በፖሊስ አልቆ፣ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶና መረጃዎችን አቅርቦ ፍትህ ለማግኘት የፍርድ ቤት በርን ለበርካታ አመታት የሚረግጡ ዜጎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ለዚህም በፍር ድቤቶቹ የቀጠሮ መርዘምና በአፋጣኝ ውሳኔ አለማግኘት ችግር ሰለባ ነን የሚሉ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ተጠቃሽ ናቸው። ክስተቱ የወንጀል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በፍታብሄር ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ባለጉዳዮችን የሚያካትት መሆኑም ታውቋል።

የተንዛዛ ቀጠሮ እና አወሳሰን ከተከራካሪ ወገኖች በተጨማሪ በጥብቅና ሙያ የተሰማሩ የህግ ባለሙያዎችን ያማረረ ጉዳይ ነው።

መመሪያው በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የወጣ መሆኑን፥ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል። በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን ያማከለ ሲሆን፥ በዋናነት ተገልጋዩ የሚማረርባቸው ረጃጅም የቀጠሮ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም በፍትህ ዘርፉ የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ ያግዛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በያዝነው አመት በፌደራል የመጀመሪያ እና ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል።

በሙከራ ደረጃ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ የተደረገው መመሪያም ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ነው የተባለው። ይህን መመሪያ ተከትሎ ቀጠሮ አሰጣጥን እና አፈጻጸምን የሚከታተል አሰራርም አብሮ እንደሚዘረጋ ነው የተገለጸው።

ዳኞች ላይ የሚደራረብ ጉዳይ መብዛትም ለፈጣን ፍርድ አሰጣጥ ችግር ስለሚሆን የመዝገብና የዳኛ ጥምርታም ሊታሰብበት ይገባል ነው የተባለው።

ምንጭ፦ Waltainfo