ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል፡ ከምርጫ በላይ መሳም ይበልጣል!

አብዛኛውን ግዜ የፖለቲካ መሪዎች ንግግር በፕሮቶኮል የታጠረና ስሜት-አልባ ነው። ፖለቲከኞች ከዜጎች ጋር በግልፅ ተገናኝተው አይነጋገሩም፣ ከማህብረሰቡ የዕለት ከእለት ህይወት የተነጠሉ ናቸው። እንዲህ ያሉ የፖለቲካ መሪዎችን በቀላል አማርኛ ለመግለፅ “ሰው-ሰው አይሸቱም!”። ይህ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ “ሰው ሰው የሚሸቱ መሪዎች ያስፈልጉናል” በሚል ርዕስ ካወጣሁት ፅሁፍ የተወሰደ ነው። በወቅቱ እንደ ማሳያ አድርጌ ያቀረብኩት የቀድሞ የአሜሪካ ፕረዜዳንት ባራክ ኦባማን ነበር። ባራክ ኦባማ በተለይ ከህፃናት ልጆች ጋር በተያያዘ ያላቸውን የግል ስብዕና እና ባህሪ በአሜሪካ ማህብረሰብ ስነ-ልቦና ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳረፈ ነው።

Photo – President Obama, White House, Oval office, 2015

ዛሬ ላይ ይህን ፅሁፍ ዳግም እንዳወጣ ያደረገኝ ነገር ሌላ ሰው ሰው የሚሸት መሪ በመገኘቱ ነው። እሱም ጠ/ሚ አብይ አህመድ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ “ዴሞክራሲ ማለት ነፃ ምርጫና የፓርላማ ክርክር ብቻ አይደለም። ከዚያ በተጨማሪ “ሰው-ሰው የሚሸቱ መሪዎች ያስፈልጉናል!” በማለት ገልጩ ነበር። ከዚህ አንፃር ሲታይ የዶ/ር አብይ መምጣት “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” የሚያስብል ነው። በእርግጥ እ.አ.አ. በ2015 የተመረጡት የካናዳው ጠ/ሚኒስትር ¨Justin Trudeau” እና ባለፈው አመት የተመረጡት የፈረንሳዩ ፕረዜዳንት “Emmanuel Macron” ከዶ/ር አብይ ጋር በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ሦስቱም መሪዎች ከሴቶች ጋር በተያያዘ ያላቸው አመለካከት ተመሳሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ሦስቱም መሪዎች የካቢኔ 50% ሴቶች መሆናቸውን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ነገር ግን ዛሬ በበርሊን የነበሩ ሴት ኢትዮጵያዊያን ለዶ/ር አብይ ያሳዩትን ፍቅርና አክብሮት ያህል ማንም አያገኝም። ዛሬ በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዶ/ር አብይን ከሩቅ ሀገር እንደመጣ የልብ ወዳጅ ጉንጭና ትከሻ እያገላበጡ የሳሙትን ያህል የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ በርሊን ቢመጣ እዚያ በሚገኙ ካናዳዊያን አይሳምም። በትላንትናው ዕለት ዶ/ር አብይ ፓሪስን እንዲጎበኝ የጋበዙት የፈረንሳዩ ፕረዜዳንት አዲስ አበባ በሚጡ እዚህ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች እንደ ዶ/ር አብይ አገላብጠው አይስሙትም። በእርግጥ ከዶ/ር አብይን ወደ በርሊን የጋበዙት የጀርመን መሪሃ-መንግስት አንጄላ ሜርክል ዛሬ ዶ/ር አብይ በነበረበት ጎዳና ላይ ቢገኙ ጀርመናዊያን በናፍቆት አቅፈው ሊስሟቸው አይጣደፉም።

የጀርመኗ መርሃተ-መንግስት አንጄላ ሜርክል እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ በጀርመን፣ በርሊን ከተማ

ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መሪዎች የበለፀገ ኢኮኖሚና የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያላቸው ናቸው። ከዶ/ር አብይ በተለየ ሦስቱም በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ የተመረጡ መሪዎች ናቸው። ነገር ግን በሀገር ውስጥ ሆነ በስደት በሚኖሩ ዜጎች ልክ እንደ ዶ/ር አብይ አቅፈው ሊስሟቸው በስስት አይሻሙም። የሦስቱም ሀገራት መሪዎች በስደተኞች ዙሪያ የሚያራምዱት አቋም በአረዓያነት የሚጠቀስ ነው። ከዚህ አንፃር በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከጀርመኖች በላይ ለአንጄላ ሜርክል ፍቅርና ክብር ሊኖራቸው ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጎን ለጎን ቢቆሙ በስደት ከሚኖሩባት ሀገር መሪ ይልቅ ለስደት የዳረጋቸውን ሀገር መሪን በፍቅር አቅፎ መሳም ይመርጣሉ።

የጀርመን፥ ፈረንሳይ ወይም የካናዳ መሪዎችን ዛሬ በአካል የማግኘት እድል ባይኖርህ ነገና ከነገ ወዲያ በእቅድ አሊያም በአጋጣሚ ልታገኛቸው እንደምትችል ታውቃለህ። ስለ መሪዎቹ የዕለት ከእለት እንቅስቃሴ መረጃ ብትፈልግ ከብዙ ሚዲያዎች ማግኘት ትችላለህ። በእርግጥ ስለ ኢትዮጵያ መሪዎች በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃ ልታገኝ ትችላለህ። በአካል የማግኘት እድሉ ሲያጋጥምህ ግን እንደ መሪው ይለያያል። እንደ መለስ ዜናዊ ያለ መሪን በአካል የምታገኘው እሱ ሲፈልግ ብቻ ነው። ከፊቱ ላይ የሚታየው ሳቅና ፈገግታም ለአንተ ሳይሆን ለቪዲዮ ካሜራው ነው። ከዚህ በተረፈ ግን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በመኪና ሲያልፉ የመሪዎቹን መልክ በጨረፍታ እንኳን ማየት አትችልም። ምክንያቱም ከገና በመዓት አጃቢዎች የተከብበው መኪና ወደ አንተ እየተቃረበ ሲመጣ ወታደሮችና ፖሊሶች ፊትህን እንድታዞር በጩኸትና በቁጣ ያዋክቡሃል። እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ መሪዎችን ልክ እንደ ዛሬው በበርሊን ጎዳና ላይ በድንገት ብታገኛቸው ደግሞ ብሶትና አቤቱታህን በተቃውሞ ለመግለፅ እንጂ አቅፈህ ልትስማቸው አትጣደፍም።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ልክ እንደ መለስ ዜናዊ ከህዝቡ በ…ጣ…ም የራቁ፣ በቴሌቭዥንና ራዲዮ ካልሆነ በስተቀር በአካል የማይታዩ፥ የማይጨበጡ፥ የማይዳሰሱ፥ የማይስቁ፥… ወዘተ ናቸው። በሀገር ውስጥ ሆነ በስደት ለሚገኙ ዜጎች የሚናገሩ እንጂ እንደ ሰው የማይናገሩ ናቸው። በእርግጥ የቀድሞ መሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በቅርብ ለሚያቋቸው ሰዎች የሰውነት ባህሪና ስብዕና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንደ ፖለቲካ መሪ ግን ከህዝብ የተነጠሉ አስፈሪ ግዑዝ ፍጥረታት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ምንም ዓይነት የሰውነት ለዛና ወዝ የሌላቸው ግዑዝ ፍጥረታት ናቸው። እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ ዓይነት የሰውነት ወዝና ለዛ ያለው መሪ ሲመጣ ታዲያ ሄደህ ጥምጥም ትልበታለህ። ትከሻውን አቅፈህ፣ ጉንጩን እየሳምክ፣ ጸጉሩን እየዳሰስክ፣ የሀገሪቱ መሪ ልክ እንዳንተ ሰው መሆኑን በተግባር ታረጋግጣለህ። የፖለቲካ ብቃትና ክህሎት ቀስ ብሎ ይደርሳል። በመጀመሪያ የፖለቲካ መሪው ልክ እንዳንተ የሚታይ፥ የሚዳሰስ፥ የሚታቀፍ፥… የሰውነት ወዝና ለዛ ያለው ህያው ፍጡር መሆኑን ማረጋገጥ አለብህ። እንደ ልዩ ፍጡር ስሜትህን የማይጋራህ፣ በደልና ጭቆናን ስትቃወም ለእስርና ስደት የሚዳርጉ መሪዎች በነገሱበት ሀገር አዲስ መሪ ሲመጣ በቅድሚያ ልክ እንዳንተ ሰው መሆኑን በአካል አቅፈህና ዳስሰህ ታረጋግጣለህ። ምክንያቱም ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል!!!

3 thoughts on “ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል፡ ከምርጫ በላይ መሳም ይበልጣል!

 1. ክቡር ጠ/ሚ ከፈረንሳይ ጠ/ሚ የተደረጉ ስምምነቶ እጅግ በጣም ጥሩ ናቸዉ።የምስራቅ አፍሪካ ሰላም ለማስጠበቅ ያደረግከው ስምምነትም አመርቂ ነዉ። ከወገኖችህ ያደረከው ሰላምታ አደንቃሎህ።
  ነገር ግን ሁሉም ከንቱ ነው!! ለምንድነው ብለህ ብትጠይቀኝ?
  መልሱ:የእርሰበርስ ስላም ሳታስጠብቅ አውሮፓ አሜሪካ መካከለኛው ምስራቅ የምትሄደው ከመዝናናት ውጪ ሌላ ትርጉም አይነሮውም።
  Peace to Ethiopians first. Others are secondary !!

  Like

 2. You do not know about HM HSI? To see him you simply walk between the lower and upper palaces at 9:00 in the morning. PS differnciate propaganda based knowledge and hard facts

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡