አቶ ያሬድ ዘሪሁን፡- ሲሸሽ እንደ ቄስ ለብሶ፣ ሲያዝ እንደ ሌባ አጎንብሶ!

የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ኃላፊ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን እስከ ትላንት ድረስ አላውቀውም ነበር። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ኃላፊ እያለ እንደ ቀድሞ አለቃው አቶ ጌታቸው አሰፋ ከዜጎች እይታ ተደብቆ ይኖር ስለነበረ ይሁን አላውቅም። ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ሆኖ እንደነበር ሰምቼያለሁ። ነገር ግን በወቅቱ እኔ እስር ቤት ስለነበርኩ መሰለኝ ስለ ሰውዬው ሹመትና መሰናበት ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረኝም። ያም ሆነ ይህ ስለ አቶ ያሬድ ዘነበ የሰማሁት ትላንት ነው።

ዛሬ ጠዋት ላይ መታሰሩን ከሰማሁ በኋላ ግለሰቡን በመልክ መለየት አልቻልኩም። በእርግጥ የሰውዬው ምስል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሲተላላፍ ነበር። ሆኖም ግን በቪዲዮና የፎቶ ምስሎች ላይ የግለሰቡ የፊት ገፅታ በትክክል አይታይም። መጀመሪያ ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲወጡ ከነበሩት ምስሎች አብዛኞቹ የተሳሳቱ ነበሩ። በመቀጠል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ይዞ የወጣው OBN ቢሆንም ግለሰቡ የፊት ገፅታውን ላለማሳየት አንገቱን አቀርቅሯል። በመጨረሻም የግለሰቡን ትክክለኛ የፎቶ ምስል የተመለከትኩት ቢቢሲ አማርኛ ይዞት በወጣው ዘገባ ላይ ነው።

አቶ ያሬድ ዘሪሁን ከፖሊስ ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ እና በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋም ያሳየው ባህሪ በጣም አስገራሚና አነጋጋሪ ሆኗል። ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አንገቱን በማቀርቀር የፊት ገፅታውን ከእይታ ለመሰወር ያደረገው ጥረት በተለይ በሀገራችን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። በመቀጠል ግለሰቡ ከአዲስ አበባ ራሱን ደብቆ የወጣበትን ሁኔታ አስመልክቶ የራሴን መላምት ማስቀመጥ እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ በትላንትናው ዕለት የደረሱኝን ሁለት መረጃዎች መነሻ አደርጋለሁ።

አንደኛው መረጃ የአቶ ያሬድ ዘሪሁን “የነፍስ አባት” ተጠርጣሪው እንዲያመልጥ ተባብረዋል በሚል ፍርድ ቤት መቅረባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል ተብሎ በፖሊስ የሚፈለግ የመረጃና ደህንነት ምክትል ኃላፊ የነፍስ አባት እንዳለው ማወቅ በራሱ አስገራሚ ነው። በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፀምበት መስሪያ ቤትን በምክትል ኃላፊነት የሚመራ ሰውዬ የነፍስ አባት ይኖረዋል ብዬ አልጠበቅኩም። የሰዎችን ነፍስና ስጋ ሲያላቅቅ የሚውል ሰውዬ “የነፍስ አባት አለው” ማለት “ሴይጣን ለተንኮሉ በእግዚያብሔር ስም ይምላል” የሚሉት ዓይነት ነው። የሆነው ሆነና፣ “የነፍስ አባቱ እንዴት አድርገው ነው ከፖሊስ እንዲያመልጥ የረዱት?” ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ትላንት አንድ ግለሰብ ከአዲስ አበባ ከተማ ደውሎ የነገረኝ መረጃ በዋቢነት እጠቅሳለሁ።

ይህ ግለሰብ ትላንት አዲስ አበባ አቃቂ አከባቢ በላዳ ታክሲ ተሳፍረው ሲሄዱ የነበሩ ሁለት የሃይማኖት አባቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተ ነገረኝ። ከታክሲው ውስጥም በማዳበሪያ ከረጢት ውስጥ የጦር መሳሪያ እንደያዙ ጨምሮ ነገረኝ። ነገር ግን የሃይማኖት አባቶች የጦር መሳሪያ ሲያዘዋዉሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚለው ዘገባ ለማመን ይከብዳል። ከዚህ በተጨማሪ ልጁ የሰጠኝን መረጃ የማጣራበት ሌላ ምንጭ ስላልነበረኝ ተወኩት። ነገር ግን ዛሬ ጠዋት አቶ ያሬድ ዱከም ውስጥ በሌላ ሰው ስም መታወቂያ በተከራየው የመኝታ ክፍል ውስጥ እንዳለ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ስሰማና ግለሰቡ የፊት ገፅታውን ከፎቶ ካሜራ ለመደበቅ አንገቱን አቀርቅሮ ስመለከት አንድ ነገር ገባኝ።

አቶ ያሬድ ዘሪሁን ከአዲስ አበባ በድብቅ የወጣበትን ሁኔታ ለመገመት ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት መረጃዎች አንድ ላይ ማያያዝ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ተጠርጣሪው ትላንት ከምሽቱ 5፡00 ላይ ዱከም ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ሰር መዋሉ ፖሊስ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ጥብቅ ፍተሻና አሰሳ ላይ እንደነበር ይጠቁማል። በመቀጠል አቃቂ አከባቢ ፖሊስ የሃይማኖት አባቶች ያሉበትን ታክሲ አስቁሞ ጥብቅ ፍተሻ ማድረጉ ደግሞ የሚፈልጉትን ሰው ማንነት ይጠቁማል። ይህ ደግሞ የአቶ ያሬድ የነፍስ አባት ተጠርጣሪው እንዲያመልጥ ተባብረዋል በሚል ተከሰሱ ከሚለው መረጃ ጋር ስታያይዙት ነገሩ ይበልጥ ግልፅ ይሆናል።

በዚህ መሰረት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ኃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን ከፖሊስ ተደብቆ የወጣው የቄስ ወይም የመለኩሴ ልብስ ለብሶ እንደሆነ መገመት ይቻላል። የነፍስ አባቱ ደግሞ የክህነት አልባሳትን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለነፍስ ልጃቸው በመስጠት ይተባበሩታል። ፖሊስ ይህን ቀድሞ ይደርስበትና የነፍስ አባቱን በቁጥጥር ስር ያውላል። በመቀጠል ደግሞ የሃይማኖት ልብስ ለብሰው በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መከታተል ይጀምራል። በመጨረሻም ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት ላይ አሰሳና ክትትሉ ሰምሮለት ተጠርጣሪውን ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቅ በቁጥጥር ስር አውሎታል። እንደ ቄስ ለብሶ ወደ ኬኔያ ለመጏዝ የነበረው ዕቅድ ተጨናግፎ እንደ ሌባ አንገቱን ደፍቶ እስር ቤት ገብቷል፡፡ እንደ ሌባ አቀርቅሮ መግባቱን ሁሉም አይቷል፣ እንደ ቄስ ለብሶ መሸሹ ግን የእኔ ግምት ነው !