መንግስቱ እና መለስ፡ የመሪዎች አመለካከትና ቃላት ሌብነትን ያጠፋል ወይም ያስፋፋል!

ከሙስና እና ሌብነት አንፃር ሲታይ በደርግና ኢህአዴግ መንግስት መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና ምድር ያህል ሰፊ ነው። “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት ከቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ውስጥ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም እና አቶ መለስ ዜናዊን እንደ ማሳያ በወስደን በንፅፅር እንመልከት። ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያም በጣም ጨካኝና ጨፍጫፊ ሲሆን አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ በጣም ዘረኛ እና ጨቋኝ ነው። ሆኖም ግን ኮ/ል መንግስቱ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል ጭፍን ግብዝነት እየተመራ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት መስርቷል። አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ “ኢትዮጵያ ትውድም” በሚል ጭፍን ጥላቻ እየተመራ የሀገሪቱን ህዝብ በብሔርና ጎሳ በመከፋፈል የአፓርታይድ ስርዓት ዘርግቷል። የኮ/ል መንግስቱ ቅጥ-ያጣ ሀገር ወዳድነት፣ የአቶ መለስ ዜናዊ ስር-የሰደደ ጥላቻ በኢትዮጵያዊያን መካከል የእርስ-በእርስ ጥላቻና ግጭት አስከትሏል።

ነገር ግን ምንም ያህል አሉታዊ ቢሆን ጭፍን ሀገር ወዳድነት ጭፍን ከሆነ ጥላቻ ይሻላል። ሀገሩን አጥብቆ የሚወድ መሪ ምንም ያህል ጨካኝና ጨቋኝ ቢሆን ዘረፋና ሌብነትን አያበረታታም። በሚመራው ሀገርና ህዝብ ላይ ስር-የሰደደ ቂምና ጥላቻ ያለው መሪ ግን ጨካኝና ጨቋኝ ከመሆን አልፎ በሀገሪቱ ዘረፋና ሌብነት ሊያስፋፋ ይችላል። በደርግ ዘመን የነበረው ሙስና እና ጉቦ በአብዛኛው ለባለስልጣናት ምግብና መጠጥ ከመጋበዝ አያልፍም ይባል ነበር። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ግን ለራሳቸው ከመብላትና ከመጠጣት አልፈው ህዝቡን የሚላስ-የሚቀመስ የሚያሳጡ ናቸው።

በደርግ ዘመን ዘረፋና ሌብነት በድብቅ የሚፈፀም አሳፋሪና ፀያፍ ምግባር ነው። የኢህአዴግ ዘመን ባለስልጣናት ይህን ወራዳ ተግባር በህዝብ ፊት ያለ ሃፍረት በግልፅ ይፈፅሙታል። እንደ ደርግ ዘመን ጉቦ ከመቀበልና ሙስና ከመስራት ባለፈ በዘረፉት ገንዘብ ትለልቅ ፎቆች ገንብተው ያከራያሉ፣ የቅንጦት መኪና ይነዳሉ፣ ቪላ ቤት ይገነባሉ፣ ልጆቻቸውን በውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ልከው ያስተምራሉ። የሀገሪቱን ህዝብ ሃብትና ንብረት ከመዝረፍና ማጭበርበር፣ እንዲሁም የሀገር አንድነት ከመውደድና ከመጥላት አንፃር በደርግ እና ኢህአዴግ መንግስት መካከል የሰማይና ምድር ያህል የሰፋ ልዩነት አለ። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከስርዓቱ መሪዎች የግል ስብዕና አመለካከት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው።

ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ምንም ያህል ጭፍንና ግብዝ ቢሆን የሀገሩን አንድነትና እድገት እውን ለማድረግ አጥብቆ ይመኛል። በሚመራው ህዝብና መንግስት ውስጥ ሌብነትና ዘረፋ እንዲሰራፋ አይሻም። በተለያየ አጋጣሚ እና ሁኔታ ሌብነትና ዘረፋን በማውገዝ ይናገራል፣ የተግባር እርምጃ ይወስዳል። በመሆኑም የደርግን የስልጣን የበላይነት እና አጀንዳ ካልተቃወሙ በስተቀር ሀገርና ህዝብን በቀናነትና በታታሪነት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያበረታታል።

በአንፃሩ አቶ መለስ ዜናዊ ከኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ከሚጨነቁ ይልቅ የህወሓትን የስልጣን የበላይነት እና የፖለቲካ አጀንዳ የሚያስፈፅሙ አጎብዳጅ እና ተላላኪ የሆኑ ሰዎችን ያበረታታል። ለምሳሌ “የኢህአዴግን ፖሊሲ እስካስፈፀመ ድረስ ትምህርት ያልተማረ ሰው የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስትር ሊሆን ይችላል” እና “እስካልተያዙ ድረስ ሌብነት ስራ ነው” የሚሉትን የአቶ መለስ ዜናዊ አባባሎችን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። አንደ አንድ ሀገር መሪ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በተለያየ መድረኮች ከሙስና እና ሌብነት ጋር ተያይዞ የተናገራቸው ነገሮች፣ በሌብነት እና ዘረፋ ተግባር በተሰማሩ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተቋማት፣ ነጋዴዎች፣ ደላላዎች፣… ወዘተ በህግ አግባብ እንዲጠየቁና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ ባለማድረጉ ምክንያት ሙስና እና ዘረፋ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።