ሰበር ዜና፦ የጠፉት መርከቦች ቁጥር “አራት” ደረሰ! “ሜቴክ ይቅር በለኝ” ማለት አሁን ነው!

የኢትዮጵያ መርከቦች የሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በህገወጥ ንግድ የተሰማሩበት ሁኔታን ለመገንዘብ ከትላንት ማታ ጀምሮ ጥረት ሳደርግ ነበር። አሁን ላይ ነገሮች በሙሉ ግልፅ ሆነዋል። ትላንት ማታ ባወጣሁት ፅሁፍ ሜቴክ አባይ እና ህዳሴ የተባሉ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦችን ከባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በመግዛትና የኮሞሮስ ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውለበልቡ በማድረግ በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። ሆኖም ግን አንድነት የተባለችዋ የኢትዮጵያ መርከብ “St. Kitts-Nevis” የተባለች የካሪቢያን ደሴት ሰንደቅ ዓላማ ይዛ በህገወጥ ንግድ መሰማራቷን የሚያሳይ መረጃ በማግኘቴ ጉዳዩ ሜቴክ ላይ ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ።

ባለፈው አምባሳደር ሱሊማን ደደፎ በሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰራውን ዘረፋና ሌብነት ስታውቁ “ሜቴክ ይቀር በለኝ ትላላችሁ!” ያሉት ትክክል ነው። በሌሎች ሀገር ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያን መርከቦች ለህገወጥ ንግድ መጠቀም እንደሚቻል ለሜቴክ ያሳየው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መርከቦችን በበላይነት የሚያስተዳድረው መስሪያ ቤት ሁለት መርከቦችን የሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ በማስያዝ በህገወጥ ንግድ ላይ ማሰማራቱን ለማወቅ ተችሏል። እውነትም ነገሩ “ሜቴክ ይቅር በለኝ” ያስብላል።

ነገሩ እንደዚህ ነው። የደርግ መንግስት ነፃነት፣ አንድነት፣ አብዮት እና መንግስቱ ኃይለማሪያም የሚል ስያሜ ያላቸው አራት መርከቦች ይገዛል። በመቀጠል የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አብዮት የተባለችውን መርከብ “ህዳሴ”፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም የተሰኘችውን ደግሞ “አባይ ወንዝ” የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል። ትላንት ባወጣሁት ፅሁፍ ሜቴክ ህዳሴ እና አባይ የተባሉትን መርከቦች “Padma” እና ”Tika” የሚል ስያሜ በመስጠት የኮሞሮስ ሰንደቅ ዓላማን እያውለበለቡ በህገወጥ ንግድ መሰማራታቸው ተገልጿል። ነገር ግን ከሜቴክ በፊት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ “St. Kitts-Nevis” ከተባለችው ሀገር ሰንደቅ ዓላማ በመግዛት በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርቷል።

ነፃነት የተባለችው መርከብ

በዚህ መሰረት የድርጅቱ ኃላፊዎች በህገወጥ ንግድ ዳጎስ ያለ ገቢ ማግኘታቸው ከሜቴክ ጄኔራሎች ጆሮ ይደርሳል። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ህዳሴ እና አባይ የተባሉትን መርከቦች በተመሳሳይ መንገድ በህገወጥ የንግድ ስራ ለማሰማራት መንቀሳቀስ ሲጀምር ሜቴክ ጣልቃ ይገባል። በዚህም ሁለቱን መርከቦች ቆራርጬ ለሌላ ግንባታ አውላለሁ በሚል ይገዛቸዋል። ከዚያ በኋላ ልክ እንደ የባህር ትራንስፖርት ኃላፊዎች ዳጎስ ያለ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። ሆኖም ግን የሜቴክ ጄኔራሎች በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ህገወጥ ንግድ በደንብ አያውቁም። ለዚህ ደግሞ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ አውጥተው እድሳት ማድረጋቸው እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቁ መርከቦችን በመጠጋገን በዓለም አቀፍ ህግ ወደቦችና የንግድ መስመሮች መንቀሳቀስ አይቻልም። ሜቴክ አባይ እና ህዳሴን እንዲያንቀሳቅስ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት መስሪያ ቤት እንኳን ፍቃድ መስጠት አይችልም። የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቁ መርከቦች የኢትዮጵያን የሰንደቅ ዓላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ከተገኘ በሁሉም የኢትዮጵያ መርከቦች ላይ እገዳ ይጣላል። ስለዚህ እነዚህን መርከቦች መጠቀም የሚቻለው የሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማን ለሶስት ወር ያህል በመከራየት ነው።

ሰንደቅ ዓላማን ከሌላ ሀገር መከራየት “Flag on convenience”(FOC) በመባል ይታወቃል። በዚህ ረገድ ሰንደቅ ዓላማቸውን ለመርከቦች በማከራየት ግንባር ቀደም የሆኑት ሀገራት “Comoros” እና “St. Kitts-Nevis” ይባላሉ። እነዚህ ሀገራት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መርከቦች ለሦስት ወር ያህል በባህር ላይ እንዲንቀሳቀሱ ባንዲራቸውን ያከራያሉ። የአከራዩ ስም፣ ዜግነት እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን የሚያነሱት ኪራዩ ከሶስት ወር ለበለጠ ግዜ ከሆነ ብቻ ነው። በሁለቱ ሀገራት ባንዲራ የማከራየት ወይም “FOC” ተግባር ምን እንደሚመስል በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ከተሰራ ጥናት የሚከተለውን ቀንጭበን ወስደናል።

የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ መርከቦች ደግሞ በተሰጣቸው ሦስት ወራት ውስጥ በህገወጥ ንግድ ይሰማራሉ። ከዚያ በኋላ ወደ ህንድ፣ ፓኪስታን እና ቻይና የመሳሰሉ የኢሲያ ሀገራት ተወስደው አካላቸው ተቆራርጦ ለሌላ ስራ ይውላል። አሁን ባገኘሁት መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ነፃነት እና አንድነት የተባሉትን ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች “Andi 1” እና “Netsa 1” በሚል መጠሪያ የ“St. Kitts-Nevis” ሰንደቅ ዓላማን በመግዛት በህገወጥ ንግድ አሰማርቷል።

የሰንደቅ ዓላማው የተከራየበት ግዜ ሲያበቃ ደግሞ “አንድነት” የተባለችውን መርከብ እ.አ.አ በ04/07/2015 ዓ.ም፣ እንዲሁም “ነፃነትን” ደግሞ እ.አ.አ. 11/07/2015 ዓ.ም “Alang” ለተባለው ለህንድ ኩባንያ መሸጡን ከታች ባለው ምስል ላይ ማየት ይቻላል።

በአጠቃላይ ሜቴክ በመርከብ ግዢና የባህር ትራንስፖርት ዘርፍ የገባው ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ነው። የሀገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት አካል የሆነው ሜቴክ እና የሀገሪቱን የንግድ መርከቦች በበላይነት የሚያስተዳድረው መስሪያ ቤት ከሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ በመግዛት በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበረ ማወቅ በራሱ ያሳፍራል። እነዚህ መርከቦች በየትኛውም ሀገር መንግስት ቢያዙ ተጠያቂ የሚሆነው የሀገሪቱ መንግስት ነው። ምክንያቱም የመርከቦቹ ባለቤት፣ አስተዳዳሪ እና ተጠቃሚ ተብሎ የተመዘገበው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ነው።

3 thoughts on “ሰበር ዜና፦ የጠፉት መርከቦች ቁጥር “አራት” ደረሰ! “ሜቴክ ይቅር በለኝ” ማለት አሁን ነው!

  1. እናመሰግናለን መምህር ስዩም።
    በዚህ አግባብ መንግስት መረጃ ይኖረው ይሆን? ካለው ለምን እርምጃ አይወስድም?

    Like

  2. Why don’t u send those files for PM office or some responsible office dear teacher.it is so amaizing history.nothing remain from our mama Ethiopia!

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡