ነገረ ቴፒ – የፍትሕ አልባ አስተዳደር ተምሳሌት!

በወንድምስሻ አ. አንገሎ

ፍትሕ አልባነት በማንኛውም ግለሰብና ቡድን ቢጀመርም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተባባሪ አያጣም። ችግሩንና መፍትሔውን ከማንነት ጋር ስናገናኘው ደግሞ ደጋፊና ተቃዋሚው የአለሁልህ ዓይነት (አቴንዳንስ/ፌሎውሺፕ) ይሆናል። ቴፒ ችግር እና መፍትሔዎቿ ሳይገናኙ ለ25 ዓመታት ለአራተኛ ጊዜ የአደባባይ ግጭት ውስጥ ገብታለች፡ 1985፣ 1994፣ 2006 እና ከለውጡ ወዲህ ባሉት ወራት። በነዚህ ጊዜያት ከ1,100 በላይ ዜጎች በመንግሥት ኃይሎችና በእርስ በእርስ ግጭት ለሞት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ለስደትና አለመረጋጋት፣ በሚሊየኖች ብር የሚገመት ንብረት ለውድመት፣ አካባቢው ደግሞ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለመኖሪያና ለሥራ የማይመች ሆኖ ቆይቷል። ምክንያቶች ብዙ ቢሆንም ለመፍትሔው ሕጋዊ ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል ስለሆነ ከመንግሥት ጋር ብቻ የተያያዘውን ልጥቀስ።

፩ ግንዛቤ ስለሸካቾ እና ቴጲ/ፒ

አካባቢያዊ ጉዳዮች እና ታሪኮች ላይ የመንግሥት አመራሮች ግልጽነት የላቸውም። /ሕዝቡ ሸካቾ፣ ቦታው ሸካ ነው የሚባለው/ በኃላፊነት የሚመደቡትም ለፖለቲካውና ለክልል አመራሮች ባላቸው ታማኝነት እንጂ በብቃት ወይም ለአካባቢው ሕዝብ ከሚኖራቸው ጠቃሚነት አንጻር አይደለም። ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ አስተዳደር በሸካ ዞን ውስጥ ይገኙ እንጂ አመራሩ እንደራሱ አካል የማየት ፍላጎቱ እጅግ ደካማ ነው። ለሸካ ሕዝብ እቆረቆራለሁ የሚለው አስተዳደር ምን ሠራህ ቢባል የሚጠቅሰው የሸክኛን ቋንቋ ለትምህርት እና ስነጽሑፍ ለማዋል መሞከር ነው። የሸካቾ ነገሥታት፣ ቤተመንግሥቶቹ፣ ቅርሶቹ የት ናቸው የሚል ጠያቂ ቢመጣ በቃል ከመናገር ያለፈ የሚታይ ነገር የለም። የንጉሡን መቀመጫ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ሳይቀር የሞቻ አውራጃ ሆኖ ቢሮ፣ ስልክ፣ ጠላት መከላከያ ገደል ወዘተ ያለው ቤተመንግሥት ጫካ ውጦታል። ከግራኝ አሕመድ የተሰወሩትን ታቦታትና ቅርሶች ለዕውቅና ለማብቃት ጥረት ያደረግነውን ሰዎች መደገፍ አይፈለግም። አመራሩ በየአጋጣሚው ሲጠየቅ ሁሌ መልሱ ችግር፣ የበጀት እጥረት እና ክልል ነክ ምክንያት ያቀርባሉ። “አላሞ” የተባለው የሸካቾ የአምላክ መንፈስ መዋቅር ውስጥ ካሉት ጎሳዎች አንዱ ሆኖ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እናት መገኛ፣ እንዲሁም ቴፒን ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ አልፎ ያለ የሸካቾ ታሪካዊ ቦታ መሆኑን የሚያስተዋውቅ የስነጥበብ የባህል ወይም ቅርስ ምስክር አላስቀመጡም። /ዳንዲ ነጋሶ ግለ ታሪክ/ ዛሬ ላይ ይህ ለሸካቾውም ሆነ ለሌሎች ወገኖች እንግዳ እንደሚሆንባቸው እርግጠኛ ነኝ። ንጉሡ ኃይለሥላሴም አካባቢውን በሞቻ አውራጃ የኪ ወረዳነት አደራጅተው አመራሮችን ሲመድቡ የየኪ ወረዳ ዋና ከተማ የኪ መንደር የነበረች ሲሆን በሂደት ይህ ቀርቶ በወቅቱ ከፍተኛ ቡናና ቅመማ ቅመም በአውሮፕላን በሚጫንባት አዲሷ መንደር ያሁኗ ቴፒ ተዛውሯል።

ከተማዋም የምርትና ትራንስፖርት ማዕከል ለመሆን ያላት የመሬት አቀማመጥና የአየር ሁኔታ ምቹ በመሆኑ ከጊቤ ማዶ ከተሞች ፈጣን ዕድገት አሳየች። የመንግሥት የቡና ልማት ድርጅትም በንጉሡ ዘመን ተጀምሮ በደርግም መስፋፋቱ ዕድገቷን አስፈንጥሮታል። ይህ ሁሉ ዕድገቷና ተስፋዋ ግን በብሔር ፖለቲካው መታወጅ ማግሥት በ1985 ዓም ጀምሮ ተበረዘ። ከዚያ በኋላ የብሔር ፖለቲካና የደካማ አስተዳደር ውጤት እየመጣ በባሕር መሐል በወጀብ እንደምትመታ ትንሽ ጀልባ ሆና ቀረች።

የአለመልማቷና የአለመስፋቷ ምክንያት መንግሥታዊ ለመሆኑ ምንም አስረጅ አይፈልግም። ይህን ለማለባበስ በሚፈልገው አመራርና “የአመራር ለውጥ ከተደረገ ተስፋዋ ይለመልማል” ብሎ በሚታገለው መሀል ሁሌ ነውጽ አለ። ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የግልና የቡድን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ጸቡን የሚያበረታቱም ጥቂት አይደሉም። መደበኛ አስተዳደራዊና ትናንሽ ልማቶችን ከማደናቀፍ ጀምሮ ለዘላቂ ልማቷም እንቅፋት ያስቀመጠ የሰላም እጦት ተደጋጋሚና የተለመደ ነው። የክልሉም ሆና የፌደራል መንግሥት ተቋማት ይህን ለመለወጥ የሚያደርጉት ጥረት ግልጽ አቋምና ብልሀት ይዞ የሚሠራ የዞን አመራር ስላልነበረ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ያመጡት ዘላቂ መፍትሔ የለም። አንዳንዴም ለግላቸው ጥቅም ሲሉ የተሻሉትን አመራሮች የሚያዋክቡ የክልልና የፌደራል ባለሥልጣናትም ነበሩ።

ችግሩ ላይ ለመግባባት እንዲያግዘን ሁለት ዓይነተኛ ምሳሌዎች ልጥቀስ፦ እኔ በዞኑ በአመራርነትና በባለሙያነት ስሠራ እንደማውቀው ዞኑ አካባቢውን ለማልማት ነጻነት አልነበረውም። ሌብነትን መከላከል ያልቻሉና የሚተባበሩ አመራሮችም የችግሩ አካል ናቸው። የህወሓት የጦር ጉዳተኞችን ለማገዝ ተብሎ ያለውን ሥልጣን ብቻ ተጠቅሞ የግሉን ፍላጎት ሊያስፈጽም የነበረ የፌደራል አመራር ወኪል መሬት አንሰጥህም ሲባል ዝቶ በሄደ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የ2006ቱ ግጭት ተከሰተ። በዚህም ተመካኝቶ ሌሎች ግብአቶች ተጨምረውበት የወቅቱን የዞን አመራሮች እስር ቤት ከተታቸው። ምክንያት አርገው ያፈነዱት ግን የቴፒን ጊዜ ጠባቂ ፈንጂ ብሔር ነክ ግጭት የሚል ነው።

ሁለተኛው ዓይነተኛ ምሳሌ የግሌ ምስክርነት ነው። እኔ ከመንግሥት ሥራ ከለቀኩ በኋላ አካባቢውን ለማልማት የሚቻለውን አማራጭ ሁሉ እንሞክር ስለነበረ ከፍተኛ ውጪ አውጥተን ባስጠናነው መሠረት በማሻና አንድራቻ ወረዳዎች የግራናይት ካባ /ኳሪ/፣ በቴፒ ከተማ አካባቢ የላይምስቶን ካባ አግኝተን ጥሬ ምርቱን በየአካባቢው ልናመርትና የፋብሪካ ሥራውን ቴፒ ከተማ ላይ ልናደርግ ፕሮጀክት አቀረብን። ክልሉ ጥናቱን አይቶ ከተስማማ በኋላ መሬት መስጠት የወረዳዎች ሥልጣን በመሆኑ ወረዳዎቹ ሲጠየቁ ብዙ ምክንያት ተፈጥሮ ተንገላታን። አንዱ የተሰጠን አስተያየትና ከርእሳችን ጋር የሚያያዘው ግን ፋብሪካውንም ከቴፒ ወደማሻ ቀይሩት የሚል ነበር። ይህ ግራ አጋቢ ነው። ለከተማው ነዋሪዎች እንኳ የመኖሪያቤት መብራት በሌላት ማሻ ፋብሪካ መትከል ጭፍን ጠባብነት እና የኛን ትርፋማነትም ጉዳዬም ያላለ ሲሆን ዋናው ግን ቴፒን የኔ ከተማ ነች ብሎ የማያስብ ግን ሸካቾ ነኝ የሚል አመራር መኖሩ ነው። እንዲህ ዓይነት ብዙ ጠቃሚ ዕቅዶች ያለአዋጭነት አመክንዮ ከቴፒ የተባረሩና ማሻም ሄደው የተንገላቱ እንደሚኖሩ ሳስብ የቴፒ ተወላጆች እንደዜጋ ብሶት ቢሰማቸው አይገርመኝም። ይህን ብሶታቸውን የሚደግፍንም ሸካቾ እንደ ባንዳ የሚወቀስ ሰው ገጥሞኛል።

፪ ቴፒ እና አስተዳደሯ፡

የሸካ ዞን አስተዳደር በሚያጋጥሙት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ በብሔር መነጽር እያየ ከዘላቂ ጥቅም ይልቅ ሕዝብ ይቃወመኛል ብሎ ውሳኔዎች ላይ ይውሸለሸላል። የተወሰነውን ውሳኔ ሕዝብን በሚጠቅም ደረጃ የሚሠራም አመራር ጥቂት መሆኑ ውሳኔዎቹም ሆነ ተግባሮቹ “ዞኑ ከተማዋን ለመበደል ሆን ብሎ ይሠራል” ለሚሉ ምክንያት ቢሆን አይገርምም። ከዚህ የማያንሰው ችግር ደግሞ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ለግሉ ጥቅም ሲያሰላ አለማፈሩ ነው። ከዚያችው ከትንሽ የመልማት አቅሟ ላይ የሌባው ጭካኔና ብዛት መጨመር ከባድ ፈተና ነው። በቤተሰብ ጭምር ተደራጅተው የቴፒን የቡናና ቅመማ ቅመም ንግድ ለግላቸው ጥቅም የሚያመቻቹት አመራሮች የከተማዋን የልማት ዕቅዶች ፍትሐዊ በማድረግ ማበረታታት፣ መቆጣጠርና ማስፋፋት ሲገባ እነዚህ የሌብነት ቡድኖች ወዳጅ ዘመዳቸውን እየመረጡ የተፈጥሮ ሀብትና የኢንቨስትመንት ጥቅማጥቅሞች ላይ ይመድባሉ። ስለዚህ በቴፒና የኪ ወረዳ ከከተማው እስከ ገጠር ድረስ ይህ ነው የሚባል ሥራ ሠርተው ሕዝቡን ማሳመን አልቻሉም። ይህ ከሌሎች ችግሮች ጋር ሲደመር አካባቢውን ከተፈጥሮ ጸጋዎቹ፣ ታሪኮቹና ምቹ ሁኔታዎች ይልቅ የብሔር መልክ ያለው ጸብና ስጋት እያስፋፋ ሄደ። ከዚህ ጋር አብሮ የሚማገደው ጉዳይ ደግሞ የአካባቢው ነባር ብሔር የሆኑና ለዘመናት አብረው የኖሩት ሸኮ እና መዠንግር ብሔረሰቦች የተበዳዩ አካል ዋና ሆነው መጠቀሳቸው ነው። እነዚህ ወገኖች በቤንች ማጂ ዞንና በጋምቤላው መዠንግር ዞን የታወቀ የብሔር አስተዳደር ማዕከል ያላቸው መሆኑ ለመፍትሔ ይውል የነበረውን መልካም አጋጣሚ ጭራሽ ችግር አድርጎት የዞን አስተዳደርና የአደረጃጀት ሰፊ ክለሳ ጥያቄ ጎልቶ ወጣ።

ከሌላ የሀገሪቱ ክፍል ለሥራ የመጡና በእውነትም አካባቢውን የቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ማእከል መሆኑን እውን ያደረጉትን ወገኖች ስም እየጠቀሱ መጤነት እንጂ ዜግነት እንዳይሰማቸው ያደረጉ መሆናቸውን ለመግባባት ቅን ልቦና ይፈልጋል።

የመፍትሔ ጥቆማዎች በግል መፍትሔ ብሎ መጠቆም እንደ አንድ ዜጋ አስተያየት እንጂ የግልም ሆነ የቡድን አቋም ተደርጎ የማይወሰድና ለውይይት ክፍት የሆነ፣ ከሌሎች ሀሳቦችም ጋር ተቀምሮ የተሻለ የመጨረሻ ሀሳብ ለማቅረብ የሚረዳ ነው ብዬ አስባለሁ። በዘመናችን አስቸጋሪ የሆነብን የግልን ሀሳብ አለማክበር ተከትሎ የኔን ሀሳብ ታርጋ መለጠፍና አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ መግባት የኋላቀርነታችን መገለጫ ከመሆን አያልፍም። ምንም ሥልጣን ስለሌለኝም ለሚመለከታቸው አመራሮች የራሱን ቅን ሀሳብ ማቅረብ የሁሉም ድርሻ ነው።

1/ መልካም አስተዳደር፦

የመጀመሪያው እና ዋናው ከሀገሪቱ ችግር ጋር የተሰናሰለው ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ ብቃትና ቅንነት፣ ሀቀኝነትና ባለራዕይነት ያስፈልጋል። ሀገራችን ለሁሉም ዜጋ ትበቃለች። ድንበር ማስመርና የግል ክልል ፍለጋ የምናስቀድመው አብሮ መኖር የሚሰጠንንም አቅም /ሲነርጂ/ ካለማወቅ ይጀምራል። አካባቢው ከፍተኛ የመሠረተ ልማት፣ የማኅበራዊ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ቅርበት እጅግ የጎዳው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የምትገኘዋን ሀብት በብቃት መጠቀም አለመቻል ከባድ እንቅፋት ነው። ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠርና አልሚዎችን በአስተማማኝነት አበረታቶ መጋበዝም ቅንነት ይፈልጋል። ክልል ተብዬው የሐዋሳ መንግሥትም ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ የአካባቢውን ርቀት ታሲቢ ያደረገ የሀብትና የጊዜ አጠቃቀም አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት እንጂ ለግማሽ ቀን ስብሰባ ሳይቀር 1ሺህ ኪሎሜትር እየተጓዙ የአካባቢውን ልማት መምራት አይቻልም።

2/ ጊዜያዊ የአደረጃጀት ለውጥ፦

አሁን ሸካ ዞን ተብሎ ያለው አደረጃጀት በታሪካዊም ሆነ ወቅታዊ እሳቤዎች ትርጉም የሌለው በመሆኑ ከሐዋሳው መንግሥት እስኪለይና የተሻለ አደረጃጀት እስኪፈጠር ድረስ ሁለት ጊዜያዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ።

ሀ/ የማሻ ከተማ፦ ይህ የማሻ ከተማ አስተዳደር ከዞኑ ሕዝብ ውስጥ አምስት ከመቶ ወይም ከ10ሺህ የማይበልጥ ሕዝብ የሚያስተዳድርና ራሱን በገቢ ያልቻለ ሆኖ እያለ የዞን አስተዳደር ማዕከል በመሆኑ ብቻ ከዞኑ ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከሃያ በመቶ በላይ የሚጠቀም በካቢኔ የሚተዳደር መዋቅር ተደርቷል። አብዛኛውም በጀት ከቀመር መርሖች ውጪ በድጎማ መልክ የሚመደብ ነው። ይህንን የከተማ አስተዳደር መዋቅር ማጠፍ ምንም ቅድመሁኔታ የማይፈልግ፣ ግን ፍቱን መፍትሔ ነው ብዬ አምናለሁ። የከተማ አስተዳደሩ ቀርቶ የማዘጋጃ ቤቱ ዓመታዊ የልማት ዕቅዶች ቢደጎሙ ለማሻ ከተማም ስንቱ ልማት በተሠራ ነበር፡ ከሌቦቹ ከተረፈ።

ለ/ የቴፒ ከተማ፦ ከተማዋን ወደው የመጡትና የሚኖሩባት፣ በተለይ ደግሞ እዚያው ተወልደው የተደራጁባት ዜጎች ከሕገመንግሥታዊ መብታቸው ባሻገር ቴፒን ቴፒ ያደረጓት እነዚህ ወገኖች ናቸው። በብሔር ማንነትታቸው ታይተው ነባር ብሔር አልነበራችሁም ተብሎ የሚታሰብ ወይም የሚተገበር ማንኛውም አካሄድ ሕገወጥ መሆኑን ዐውቆ ሕግ የሚያከብርና የሚያስከብር፡ ቅንና ቆራጥ አመራር መመደብ፣ ከዞኑ ጋር ያለውንም የአስተዳደር ግንኙነት ግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ፣ ብቃትንና ሁሉን ሕዝብ የሚያከብር ቢሆን ትልቅ እረፍት ይሰጣል ብዬ አምናለሁ።

ሐ/ የዞኑ የዘገዩ የልማት ጥያቄዎች፦ በሀገራችን በየአካባቢው ያለው ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ለሚጠቀሱት ችግሮች አባባሽ የመሆን አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ አሁን በተጀመረው የልማት ማስፈጸሚያ የሀብት ምንጭ አማራጮች ጭምር በመጠቀም የማካካሻ ሥራ ይፈልጋል። የጎሬ-ቴፒ-ሚዛን መንገድን ማፋጠን፣ ቴፒን ማዕከል ያደረጉት የአውሮፕላንና የደረቅ ወደብ ግንባታዎች፣ የባሮና ገባ ወንዞች የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት፣ የማሻ ከተማ ሰብስቴሽን፣ የማሻ ሰሌኖኖ መንገድ ወዘተ ከኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸው ባሻገር አካባቢውን ከዓለምና ከቴክኖሎጂው አርቆ ከሀገሪቱ ተለይቶ ወደኋላ ያስቀረው ምክንያቶችን ከማስቀረት ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥሩንና መልካም አስተዳደሩን ያሳልጣል። ብቃት ያላቸው አመራሮች ከተመደቡም የቱሪዝም አማራጮቹ ጥቂት አይደሉምና ሠፊ የሕዝብ ተሳትፎና የኢንቨስትመንት ዕቅዶች ተዘጋጅተው የግል ባለሀብቶችን መጋበዝ ይገባል። ይህ በራሱ ሌላ ትልቅ አቅም ይሆናል።
ይህንንና መሰል አቅጣጫዎችን ቢከተል ነባሮቹ ብሔረሰቦች ሸካቾ፣ ሸኮና መዠንግር እንደጥንቱ አብሮነታቸውን ይዘው የመኖር፣ ሌሎችም እንደቀድሞው ዘመን በፍቅርና በትብብር ተጋብተው ተዋልደው መኖራቸውን ይዘው ይቀጥላሉ እንጂ ይህን ያህል አስቸጋሪ ጉዳይ በአካባቢው የለም ብዬ አምናለሁ። የትኛውም ብሔር ከሌላው ጋር ከሰበብ ያለፈ በቂ የግጭት ምክንያት የለውም። ሚዲያውም ይህን በበቂ መረጃ ተደግፎ ቢሠራ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሌላው ቢቀር ከተማውን አምነው ከየሀገሪቱ ጥግ ለሚመጡት የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቴፒ ካምፓስ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሲባል እንኳ መልካም ሥራዎችን በማጉላት ተማሪዎቹና ማኅበረሰቡ የአካባቢው አምባሳደር እንዲሆኑ መሥራት ይገባል።

(መውጫ፦ የሸካቾ ሕዝብን ታሪክና ሀገራዊ ድርሻውን ግን በዚህ ጽሑፍ በጉልህ ማካተት ያልፈለኩት ሌላ ችግር የሚፈጥር ብዥታ ላለማምጣትና በሕዝብም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ያልተግባባንባቸው ተያያዥ ጉዳዮችን የሚቀሰቅስ ስለሆነ ነው። ሸካቾ በታሪኩ በመንግሥት ደረጃ የተበደለውና የከፋ ጉዳት የደረሰበት በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ በበቂ ምስክር ማስረዳት ይቻላል። ይህ መንግሥት ለሀገር በሚጠቅም ደረጃ መፍትሔ መስጠት ከፈለገ ቁጭ ብለን የምንመክርበት ጉዳይ ነው። ሲፈልግ ካፋቾና ሸካቾ አንድ ናቸው ብሎ ቋንቋውን ለማዳቀል፣ ሲፈልግ ደግሞ ከሽናሻ ጋር ዝምድና እንዳላቸው በጥናት ተረጋገጠ እያሉ ማዶና ማዶ እያመላለሱ ማደናገሩን ማቆም፣ እውነታውን በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ቦታ ሰጥቶ መሰነድ፣ ከዚህም አያይዞ በቀጣይ የአስተዳደር አደረጃጀት ለውጥ ማድረግ አለበት።)


ለፀሃፊው ሃሳብና አስተያየት መስጠት ከፈለጋችሁ በዚህ የኢሜል አድራሻ መላክ ይቻላል፦ wendemseshaa@gmail.com