የህወሓት ተሞክሮ፡- ጭቁን ብሔርተኛ ስልጣን ሲይዝ ጨካኝና ጨቋኝ ይሆናል!

አንዳንድ ሰዎች የሚናገሩት እና የሚፅፉትን ስመለከት ይገርመኛል። የአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ የሚያቀነቅኑ የኦሮሞ፥ የአማራ፥ የሲዳማ፥ የወላይታ፥ የሶማሌ ሆነ የስልጤ ፖለቲካ ቡድኖች አቋምና አመለካከት የትግራይ ብሔርተኝነትን ከሚያቀነቅነው ህወሓት ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች፤ “ላለፉት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለታየው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዋና መንስዔው ህወሓት ነው፤ ዛሬም ቢሆን በአራቱም አቅጣጫዎች ከሚከሰቱት የፀጥታ እና አለመረጋጋት ችግሮች በስተጀርባ የህወሓት እጅ አለ” ሲባሉ አይገባቸውም። ምክንያቱም ይህን እውነታ በአግባቡ መገንዘብ ከቻሉ የህወሓትን ስህተትና ውድቀት ለመድገም አይጣደፉም ነበር።

አክራሪ ብሔርተኝነት ትክክል መሆኑን በተግባር ለማረጋገጥ ከህወሓት በላይ ምቹ ዕድልና አጋጣሚ የነበረው ቡድን የለም። ምክንያቱም ህወሓት ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል። በብሔርተኝነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ዘርግቷል፤ በተመሳሳይ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት መስርቷል። በዚህ አቋምና አመለካከት ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ትልቅ ሀገርና ህዝብ አስተዳድሯል። ከህወሓቶች መቅሰም ያለብን ጠቃሚ ልምድና ተሞክሮ፤ ብሔርተኝነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገርን ፈፅሞ ለመምራት የማያስችል በራስ-ወዳድነት እና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ጠባብና ኋላቀር የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት መሆኑን ነው። ይህ ህወሓት በተግባር ያረጋገጠው ሃቅ ነው።

በእርግጥ ብሔርተኝነት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ፋይዳ የለውም እያልኩ አይደለም። በመሰረቱ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ፋይዳ የሌለው ነገር ተግባራዊ አይደረግም። ከዚህ አንፃር ብሔርተኝነት የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። የብሔርተኝነት በአንድ ማህብረሰብ ውስጥ በእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና አለው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የተለያዩ ብሔሮችና ጎሳዎች በሚኖሩባት ሀገር ያለ ብሔርተኝነት ስሜት በሁሉን-አቀፍ የነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር አስቸጋሪና የረጅም ግዜ ጥረት የሚጠይቅ ነው።

ይሁን እንጂ ብሔርተኝነት ህዝባዊ ንቅናቄን ከመቆስቆስ የዘለለ ፋይዳ የለውም። በብሔርተኝነት አመለካከት እንኳን የተለያዩ ብሔሮችን የራስን ማህብረሰብ መምራትና ማስተዳደር አይቻልም። ምክንያቱም ብሔርተኝነት በራስ ወዳድነት እና ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከት ነው። በመሆኑም ህዝብን መምራትና ማስተዳደር ስንጀምር ከሌሎች ብሔሮች ይልቅ ለራሳችን ብሔር ተወላጆች መወገን እና ማድላት እንጀምራለን። በብሔርተኝነት ውስጥ ያለው የጥላቻ ስሜት ሀገርና ህዝብ ማስተዳደር ስንጀምር ወደ ቂም-በቀል ጥቃት ይቀየራል።

በራስ ወዳድነት እና ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ንቅናቄ መጨረሻው ከእኩልነት ይልቅ በአንድ ወገን የበላይነት ይሆናል። በመሆኑም እንደ ህወሓት ያለ አክራሪ ብሔርተኛ ቡድን መጀመሪያ ላይ ይዞት የተነሳው የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ በመጨረሻ ወደ የራሱን የበላይነት እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ይሆናል። ይህን ስርዓት በሚቃወሙ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ አሰቃቂ በደልና ግፍ ይፈፅማል። ስለዚህ የራሱን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲል የሌሎችን መብትና ነፃነት ይጥሳል። በዚህ መሰረት ከስልጣን በፊት ጭቁን የነበረው ብሔርተኛ ቡድን የፖለቲካ ስልጣን ከያዘ በኋላ ጨካኝና ጨቋኝ ይሆናል። በአጠቃላይ ከkህወሓት ተሞክሮ የምንረዳው ነገር ቢኖር ጭቁን ብሔርተኛ ስልጣን ከያዘ በኋላ ጨቋኝና ጨካኝ እንደሚሆን ነው።