ሰበር ዜና፦ ሜቴክ የ150 ቢሊዮን ብር የውጪ ኮንትራት መፈረሙ ታወቀ (የሰነድ ማስረጃ)

የሜቴክ ኃላፊዎች ከፍተኛ ዘረፋና ሌብነት የፈፀሙት ግን ከሀገር ውስጥ ይልቅ ከውጪ ሀገራት ድርጅቶች ጋር በሚፈፅሙት የግዢ ስምምነት አማካኝነት ነው። ሆኖም ግን ሰሞኑን በእነ ሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው ላይ የቀረበው የክስ ማስረጃ ስመለከት የወንጀል ምርመራው በዋናነት በሀገር ውስጥ ግዢዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ከዚህ አንፃር ከሜቴክ ጋር በተያያዘ የሚካሄደው ምርመራ በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ አይደለም የሚል ስጋት በውስጤ ተፈጥሮ ነበር። ዛሬ ጠዋት ልክ ከእንቅልፌ ስነቃ በፌስቡክ የመልዕክት አድራሻ የደረሰኝ መረጃ ግን በጉዳዩ ላይ የነበረኝ ስጋት ወደ ግራ መጋባት ስሜት ቀይሮታል።

በእርግጥ መረጃው የተላከው ከወራት በፊት ነው። በፌስቡክ በየዕለቱ ብዛት ያላቸው መልዕክቶች ስለሚደርሱኝ የተወሰኑትን ሳላያቸው ያልፋሉ። ዛሬ ጠዋት ታዲያ ውስጥ አዋቂው “ምነው ባለፈው አመት ሐምሌ ወር ላይ የሜቴክን ጉድ የሚያሳይ ሰነድ ልኬልህ ዝም አልክ?” የሚል ማስታወሻ ሲልክልኝ ወደኋላ ተመልሼ መልዕክቶቹን መፈተሸ ጀመርኩ። ለካስ ከወራት በፊት የሜቴክን የአምስት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የሜቴክን የግዢ ስምምነት የመረጃ ቋት (Data base for Contract Agreement) ልኮልኛል።

ከሜቴክ ሰራተኞች ሾልኮ የወጣው የግዢ ስምምነት የመረጃ ቋት እ.አ.አ. ከ2010 – 2012 ዓ.ም ባሉት ሦስት አመታት ድርጅቱ የፈፀማቸውን የውጪ ኮንትራት ውሎች በዝርዝር ይዟል። በዚህ ሰነድ “የውጪ ኮንትራት” (Foreign Contract) በሚል ርዕስ ስር፤ የውል ቁጥር፣ የውል ዓይነትና ሁኔታ፣ የተዋዋለው ድርጀት ስምና አድራሻ፣ የኮንትራቱ ዋጋ እና የአከፋፈል ሁኔታ፣ ውሉ የተፈረመበት እና የፀደቀበት ቀን፣… ወዘተ በዝርዝር ያሳያል።

ከላይ በተጠቀሰው የሰነድ ማስረጃ መሰረት ሜቴክ እ.አ.አ. ከ2010 – 2012 ዓ.ም ባሉት ሦስት አመታት ውስጥ ብቻ 244 የውጪ ኮንትራቶችን ፈፅሟል። ከእነዚህ ውስጥ 189 የውጪ ኮንትራቶች የሚከፈለው ዋጋ በዶላር ወይም ዩሮ ተገልጿል። በኮንትራቱ ዋጋ ያልተገለፀባቸው 55 የውጪ ኮንትራቶች ያሉ ሲሆን ከእዚህ ውስጥ 48ቱ ኮንትራቶች የተፈረሙበት ቀን ተገልጿል። 4 ኮንትራቶች አለመፈረማቸው የተገለፀ ሲሆን የተቀሩት 3 ኮንትራቶች ደግሞ መፈረም ወይም አለመፈረማቸው አልተገለፀም። የዋጋ መጠናቸው ከተገለፀባቸው ኮንትራቶች ውስጥ 179 ኮንትራቶች መፈረማቸው የተገለፀ ሲሆን 6 ደግሞ አመፈረማቸው ተገልጿል። የተቀሩት 4 ኮንትራቶች ደግሞ መፈረም ወይም አለመፈረማቸው አልተገለፀም።

ከላይ በተገለፀው መሰረት የ5,140,158,598.44 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ146,288,913,711.6 ቢሊዮን ብር በ21 ሀገራት ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር ኮንትራት ተፈራርሟል። ከዚህ በተጨማሪ የ133,185,622.47 ዩሮ ወይም የ4,320,341,596.17 ብር ኮንትራት በ11 ሀገራት ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር ተፈራርሟል። በአጠቃላይ እ.አ.አ. ከ2010 – 2012 ባሉት ሦስት አመታት ውስጥ ብቻ ሜቴክ በተለያዩ ውጪ ሀገራት ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር የ150,609,255,307.77 ብር ኮንትራት መፈራረሙን ለማወቅ ትችሏል።

የሜቴክ ኃላፊዎች የፈፀሙትን ቅጥ ያጣ ዘረፋና ሌብነት በዝርዝር ለማወቅ ከተፈለገ እነዚህ የ150 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትራት ውል ስምምነቶች በዝርዝር መታየት አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሚከፈለው ዋጋ ሳይገለፅ የተፈረሙ ስምምነቶች አንድ በአንድ መታየት አለባቸው። ይህን ያህል የሀገር ሃብት የወጣባቸው ኮንትራቶች አፈፃፀም እና በዚያ ላይ የሚደረግ ምርመራ በሜቴክ ኃላፊዎች ላይ ለተከፈተው ክስ ተጨባጭ ማስረጃ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። የውጪ ኮንትራቶች ዝርዝር የያዘውን ሰነድ ለሚመለከተው አካል ለማድረስ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ይህን ሊንክ በመጫን ማውረድ ይችላል።

2 thoughts on “ሰበር ዜና፦ ሜቴክ የ150 ቢሊዮን ብር የውጪ ኮንትራት መፈረሙ ታወቀ (የሰነድ ማስረጃ)

  1. በአን ደሀ አገር ላይ አንደዚህ ከሆነማ በንጽጽር ሲታይ ከዚህ በላይ ዘረፋ የ ያለ አይመስለኝም በሀገር ክህደትም ጭምር መጠየቅ አለባቸው። ፍትህ ለጭቁኑ ለተዘረፈው የኢትዮጵያ ህዝብ!

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡