ለውጡን በዘላቂነት ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት?

በለውጥ ንቅናቄ ውስጥ ሦስት ዓይነት ኃይሎች አሉ። እነሱም አንደኛ፡- የለውጥ አቀንቃኝ ቡድን፣ ሁለተኛ፡- ጸረ-ለውጥ ቡድን፣ ሦስተኛ፡- ግራ-የገባው ቡድን ናቸው። በለውጥ ንቅናቄ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በመሳተፍ የራሱን አስተዋፅዖ ማብርከት የቻለ ቡድን “የለውጥ ቡድን” ነው። በሌላ በኩል የለውጥ እንቅስቃሴ በማንኛውም መልኩ ለማፈን ሆነ ለማደናቀፍ ጥረት የሚያደርግ “ፀረ-ለውጥ” ቡድን ነው። በመጨረሻም የለውጥ እና ፀረ-ለውጥ ቡድኖች በሚያደርጉት ትግል ሚናውን በግልፅ መለየትና የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት የተሳነው ቡድን “መሃል-ሰፋሪ” ነው።

ለውጥ የሚመጣው ወይም የሚጨናገፈው በእነዚህ ሶስት ኃይሎች መካከል በሚፈጠር የኃይል ስብጥር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የለውጡ ኃይል የታሰበውን ለውጥ ለማምጣት ወይም ለውጡ እንዳይጨናገፍ ያለውን አቅምና ችሎታ አሟጥጦ መጠቀም አለበት። ሁለተኛ መሃል-ሰፋሪ የሆነውን ቡድን በአብዛኛው የለውጡ ደጋፊ እንዲሆን ወይም ለውጡን እንዲቀበል ማድረግ ይጠይቃል። በመጨረሻም ጸረ-ለውጥ አቋም ከሚያራምደው ቡድን ውስጥ የተወሰኑት ለውጡን ባይደግፉት እንኳን ለውጡን ከማደናቀፍ ተግባር እንዲቆጠቡ ማድረግ አለበት። በዚህ መሰረት ስኬታማ ለውጥ ማምጠት የሚቻለው የራስን የለውጥ አጀንዳ በማቀንቀን ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የፀረ-ለውጡን ቡድን እንቅስቃሴ ቀድሞ በመቆጣጠርና የመሃል-ሰፋሪውን ድጋፍ በማጠናከር ነው።

ከዚህ አንፃር የዶ/ር አብይ አመራር፤ አንደኛ፡- ወደፊት የሚመጣውን የለውጥ ምንነት፣ የለውጡ አካሄድ እና በተጨባጭ የሚያመጣውን ውጤት በግልፅ ማስቀመጥና በብዙሃኑ ዘንድ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ሁለተኛ፡- እንደ ደህዴን ያሉ መሃል-ሰፋሪዎችን የለውጡ ደጋፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ በመጨረሻም እንደ ህወሓት ያሉ ቡድኖችን ጸረ-ለውጥ እንቅስቃሴዎች በቅድሚያ መገመትና መቆጣጠር መቻል አለበት።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ለውጡ ምንነት፣ አካሄድና ውጤት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ የለውም። መሃል-ሰፋሪው ቡድን በግራ-መጋባት ውስጥ በለውጡ እና ጸረ-ለውጡ ቡድኖች መካከል እየዋዠቀ ሲሆን እንደ ህወሓት ያሉ ጸረ-ለውጥ ቡድኖች ለውጥ ለመቀልበስ ወይም ለማደናቀፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ ለማድረግ ትንፋሻቸውን አሰባስበዋል። ስለዚህ የዶ/ር አብይ አመራር ለውጥ ለማስቀጠል የለውጡን ዓላማና ግብ ጠንቅቆ ማወቅና ማሳወቅ፣ የጸረ-ለውጡን እንቅስቃሴ ቀድሞ ማወቅና መቆጣጠር፣ እንዲሁም መሃል-ሰፋሪውን ወገን የለውጡ አካልና ተጠቃሚ ማድረግ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ለውጡ ባይቀለበስ እንኳን በዘላቂነት ማስቀጠል አዳጋች ይሆናል።