የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ሲዘምር ህወሓቶች ለጦርነት ይፎክራሉ! ለምን?

የህወሓት አባላትና አመራሮች የሚያሳዩት ባህሪና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም። ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል የተቀበለውን ለውጥ እነሱ ይቃወሙታል። በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ በብዙሃኑ ዘንድ ድጋፍና ተቀባይነት ሲያገኝ ህወሓቶች ግን ሲያጣጥሉትና ሲቃወሙት ይስተዋላል። ብዘሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ስለ ስላም ሲናገር እነሱ ስለ ጦርነት ይዘምራሉ። የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ለውጡን የሚቃወሙበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ለየት (የተለየ) የሚያደርጋቸው ነገር አለ?

የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ ያለው የህወሓት ዓላማና ግብ የአንድ ወገን የበላይነትን ማረጋገጥ መሆኑ ላይ ነው። ህወሓት እንደ ግለሰብ የድርጅቱን አመራሮች፣ እንደ ቡድን የድርጅቱን አባላት፣ እንደ ማህብረሰብ ደግሞ የትግራይን ህዝብ የበላይነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ ነው። ይህ ከደደቢት እስከ ቤተ-መንግስት፣ ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ ድረስ ያለና የነበረ የድርጅቱ መሰረታዊ አቋምና መርህ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የህወሓት ዓላማና ግብ የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ መዋቅር፣ ተቋማትና የአሰራር ሂደቶች በሙሉ የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው። ነገር ግን የትግራይ ህዝብ፣ የህወሓት አባላትና አመራሮች ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አንፃር ሲታይ አናሳ (Minority) ነው። በመሆኑም እንደ ፖለቲካ ድርጅት ሆነ ማህብረሰብ የህወሓት ዓላማና ግብ ብዙሃኑን (Majority) የሀገሪቱን ህዝብና የፖለቲካ ቡድኖች ያገለለ ነው።

በዚህ መሰረት ህወሓት የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገው ነገር በሙሉ የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚፃረር ይሆናል። ህወሓት እንደ ድርጅት የተመሰረተበትን ዓላማና ግብ ለማሳካት ጥረት ባደረገ ቁጥር የብዙሃኑን መብትና ተጠቃሚነት የሚጋፋ ተግባር ይፈፅማል። በየትኛውም የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ የሰዎች መሰረታዊ ፍላጎት በእኩል ዓይነት መታየት ነው። በመሆኑም የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት እና አሰራር ባለበት ሀገር ዜጎች የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሳሉ።

የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተገቢው ግዜና ቦታ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን በህዝባዊ አመጽና ተቃውሞ – በህዝባዊ አብዮት – ይወገዳል። ሆኖም ግን እንደ ህወሓት ያለ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዓላማና ግብ ይዞ ለሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ቡድን ከብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ለሚነሳው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት አይችልም። ምክንያቱም የብዙሃኑ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማስወገድ ሲቻል ብቻ ነው።

በዚህ መሰረት ህወሓት ከብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ለሚነሳበት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚችለው መሰረታዊ ዓላማና ግቡን በመቀየር ወይም ራሱን በራሱ በማጥፋት ነው። በሌላ በኩል ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ለህወሓት አስተዳደር ተገዢ የሚሆነው ፖለቲካዊ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛን አምኖና ተቀብሎ ለመኖር ከወሰነ ብቻ ነው። ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ጭቆና እና ብዝበዛን የሚቃወም ከሆነ ግን እንደ ህወሓት ካለ የፖለቲካ ቡድን ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግጭት ውስጥ ይገባል። በመጨረሻ ከሁለቱ አንዱ አሸናፊ ሆኖ ይወጣል።

ህዝባዊ ንቅናቄው ካሸነፈ፤ የብዙሃኑ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል። በአንፃሩ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተው ስርዓት ይወድቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሦስት አመታት በታየው ህዝባዊ ንቅናቄ አማካኝነት በህወሓት የበላይነት እና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው ስርዓት ወድቋል። በመሆኑም የብዙሃኑ እኩልነት ለህወሓቶች ውድቀት ነው። የብዙሃኑ ፍትህ እና ተጠቃሚነት ለህወሓቶች ፍርድና ተጠያቂነት ይዞ ይመጣል። በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ድጋፍና ተቀባይነት ያገኘው ለውጥ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች በተቃውሞ ያጣጥሉታል። የብዙሃኑን መብትና ነፃነት ያረጋገጠው ለውጥ በህወሓቶች ዘንድ የመገፋትና ፍርሃት ስሜት ይፈጥራል። አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ሰላምና ልማት በሚዘምርበት ወቅት ህወሓቶች ግጭትና ጦርነት ለማስነሳት ጥረት ያደርጋሉ።

One thought on “የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ሲዘምር ህወሓቶች ለጦርነት ይፎክራሉ! ለምን?

  1. በማዕከካከላዊ ዲሞክራሲ ላይ የተመሠርተው የሕወሀት አገዛዝ አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን ቀማኛ (Extractive) ነው። የሕዝብን ሀብት፣ ደህንነት፣ ሠላም ለራሱ ጥቅም የሚመጥ ነው። የተዘረጋው የመምጠጫ ቧንቧ መቀበያው ጫፍ ትግራይ ሲሆን የመምጠጫው መነሻ ጫፍ የሌላው ኢትዮጵያ ክፍል ነው።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡