ጎረቤት ሀገራት ተደምረዋል! ህወሓት መውጫ አጥቷል!

ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጣ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሄደባቸው የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት መካከል ኬኒያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ናቸው። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በዩጋንዳ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል። በእርግጥ ዶ/ር ወደ ዩጋንዳ የሄደው ስለ ደቡብ ሱዳን ከዩጋንዳው መሪ ዮሪ ሙሴቬኒ ጋር ለመወያየት ነው። ምክንያቱም በተለይ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በስልጣን በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ የነበራትን የመሪነት ሚና አጥታ እንደነበር ነበር። የደቡብ ሱዳን የነፃነት ትግል ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ በጉዳዩ ላይ የነበራትን ሚና ለዩጋንዳ አሳልፋ መስጠቷ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

ዶ/ር አብይ በዩጋንዳ ይፋዊ ጉብኝት ያደረገው ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ የነበራትን ሚና መልሳ እንድታገኝ አስችሏታል። ከጉብኝቱ በኋላ የደቡብ ሱዳን መሪዎችን ፕረዜዳንት ሳልቫ ኬር እና ተቀናቃኛቸው ኤሪካ ማቻርን ወደ አዲስ አበባ በመጥራት እንዲስማሙ አደረጓቸው። ይህን ባደረጉ ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከኢሳያስ አፍወርቂ ጋር የወዳጅነት እና የሰላም ስምምነት ፈረሙ። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የደቡብ ሱዳን ፕረዜዳንት በስደትና በእስር ለሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምህረት ማድረጋቸውን አወጁ።

በዚህ መልኩ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ቀድመው ተደመሩ። አንድ ስሙን የማልጠቅሰው በኤርትራ ሲንቀሳቀስ የነበረ የኢትዮጵያ አማፂ ቡድን ከዶ/ር አብይ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሀገር ለመግባት ፍቃደኛ አልነበረም። ከዚያ ይልቅ ወደ ደቡብ ሱዳን በማቅናት በሀገሪቱ የጦር ካምፕ ለመስራት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም የደቡብ ሱዳን ሳልቫ ኬር “እኔም ተደምሬያለሁ፣ አንተም ብትደመር ይሻላል” በማለት ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገበት ከውስጥ አዋቂዎች ለመረዳት ችያለሁ። ይህ አማፂ ቡድን ወደ አስመራ ተመልሶ ሲሄድ የኢሳያስ መንግስት ከዚህ በኋላ ኤርትራ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደማይችል ያስረዳዋል። በዚህ ምክንያት አማፂ ቡድኑ ከዶ/ር አብይ የቀረበለትን ጥሪ ሳይወድ-በግድ ተቀብሎ ወደ ሀገር ቤት ገብቷል። ይህ እንግዲህ የጎረቤት ሀገራት መደመር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ በግልፅ ይጠቁማል።

ከኤርትራና ደቡብ ሱዳን በመቀጠል የተደመሩት ሀገራት ሶማሊያና ኬኒያ ናቸው። በእርግጥ ዶ/ር አብይ ወደ ኬኒያ እና ሶማሊያ ጉብኝት ያደረገው ወደ ስልጣን የመጣ ሰሞን ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ሀገራት ከህወሓት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እና ትስስር የነበራቸው ሀገራት እንደመሆናቸው መጠን ለመደመር ረጅም ግዜ ወስዶባቸዋል። በአንፃሩ ኤርትራ በህወሓት ተንኮልና አሻጥር ከፍተኛ ግፈት ቀማሽ ስትሆን ደቡብ ሱዳን ደግሞ ከቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ስታገኝ የነበረውን ዲፕሎማሳዊ ድጋፍና ሽምጋይነት ተነፍጓት ለእርስ-በእርስ ግጭትና አለመረጋጋት ተዳርጋለች። በመሆኑም ከህወሓቶች በተለየ ለሀገራቱ ሰላም ቀና እና ቁርጠኛ አቋም ይዞ ከመጣው ዶ/ር አብይ ጋር በቀላሉ መግባባትና መደመር ችለዋል።

ከዚህ አንፃር ሶማሊያና ኬኒያ ቀረቤታቸው ከዶ/ር አብይ ይልቅ ለህወሓት ባለስልጣናት እና የጦር ጄኔራሎች ነበር። ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ረገድ የጋራ አጀንዳ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ባለስልጣናት ከኬኒያ አቻዎቻቸው ጋር ጠንካራ የሆነ የዲፕሎማሲና የጥቅም ትስስር እንዳላቸው ይታወቃል። ኬኒያ ከኢትዮጵያ የምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በሶማሊያ ደግሞ የህወሓት ጄኔራሎች በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ አድራጊ-ፈጣሪ ነበሩ። አንድ የሶማሊያ ባለስልጣን ያለ ኢትዮጵያ ጦር ድጋፍና እገዛ ወደ ስልጣን የመምጣት ሆነ በስልጣን ላይ የመቆየት እድሉ የመነመነ ነበር። በመሆኑ ከኤርትራና ደቡብ ሱዳን አንፃር ኬኒያና ሶማሊያ ራሳቸውን ከህወሓት ተፅዕኖ ለማላቀቅ እና ለመደመር ረዘም ያለ ግዜ ወስዶባቸዋል።

ይሁን እንጂ የሶማሊያ ፕረዜዳንት በባህር ዳር ከተማ የሶማሌ ክልል ፕረዜዳንት ባሉበት ከኢሳያስ አፍወርቂ እና ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በይፋ ተደምረዋል። በተመሳሳይ የኬኒያው ፕረዜዳንት ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ በመጡበት ግዜ ከኢትዮጵያ ፕረዜዳንት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተደምረዋል። አዲሷ የኢትዮጵያ ፕረዜዳንት አምባሳደር ፈትለወርቅ ከኃላፊነታቸው በተጨማሪ በኬኒያ የነበራቸው ቆይታና ልምድ ኬኒያዎች እንዲደመሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል።

ከስድስቱ የኢትዪጵያ ጎረቤት ሀገራት ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተደመሩት ሰሜን ሱዳን እና ጅቡቲ ነበሩ። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው ምክንያት ሰሜን ሱዳን እና ጅቡቲ ከህወሓቶች ጋራ የተበቀ ግንኙነት እና የጥቅም ትስስር አላቸው። ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት 90% የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚካሄደው በአሰብ ወደብ፣ 5% ደግሞ በምፅዋ ወደብ በኩል ሲሆን የተቀረው 5% በጅቡቲ ወደብ በኩል ነበር። ከጦርነቱ በኋላ 95% የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚካሄደው በጅቡቲ ወደብ በኩል ሆነ። በዚህ ምክንያት የጅቡቲ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ላይ የተመሰረተ ሆነ። ከወደብና ተያያዥ አገልግሎቶች ክፍያ በአመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች። ሁለቱ ሀገራት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን በጋራ ከማስተዳደር ጀምሮ የመብራት ኃይል እና ውሃ አገልግሎት አቅርቦት፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መሬት አቅርቦት ስምምነት አላቸው።

በዚህ መሰረት የዶ/ር አብይ አመራር ከኤርትራ ጋር የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት መፈራረሙ ለጅቡቲ የህልውና አደጋ የጋረጠ ነው። አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት የጅቡቲ ወደብን ሲያስተዳድር የነበረው የተባበሩት ዱባይ ኤሜሬት ኩባንያ የስምምነት ውሉን በመጣስ ከሀገሪቱ የተባረረበት ምክንያት ዱባዮች ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስማማት በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ በማለት ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ጥያቄ ቀድማ የተቃወመችው ጅቡቲ መሆኗ እንደ ሌላ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል።

የኤርትራ መንግስት ሶማሊያ እንድትደመር ያላሳለሰ ጥረት ማድረጉ ይታወሳል። የሁለቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ወደ ሶማሊያ በመሄድ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በባህር ዳር ከተማ በኤርትራ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል የሦስትዮሽ ውይይት ለማድረግ በመጨረሻ ሶማሊያ እንድትደመር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። በተመሳሳይ ሰሞኑን የኤርትራው ፕረዜዳንት አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ በጅቡቲ ያደረጉት ጉብኝት የጅቡቲው ፕረዜዳንት ወደ ጅማ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ሊኖረው እንደሚችል መገመት ይቻላል። በዚህ መሰረት የጅቡቲው ፕረዜዳንት በጅማ ተገኝቶ ተደምሯል ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሰሜን ሱዳን መሪዎች በጅማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቃት ፕሮግራም

ዛሬ ከጅቡቲው ፕረዜዳንት ጋር በጅማ የተገኙት የሰሜን ሱዳን ፕረዜዳንት አልበሽር እንደ ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የመደመር አዝማሚያ እያሳዩ ነው። ከህወሓቶች እና ቻይናዎች ጋር ያላቸው የጠበቀ ቁርኝት በቀላሉ ከመደመር ሊያግዳቸው ይችላል። ነገር ግን የመደመር ጽንሰ-ሃሳብ በአብሮነት እና ትብብር መንፈስ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ህወሓት ሲያራምደው ከነበረው በሸርና አሻጥር ፖለቲካ የተሻለ ሆኖ መውጣቱ የማይቀር ነው። የዶ/ር አብይ የዲፕሎማሲ አካሄድ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ሲሆን በአንፃሩ ህወሓቶች ሰሜን ሱዳንን የሚፈልጓት መሸሺያና መሸሸጊያ በማድረግ የራሳቸውን የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ነው። በመሆኑም ከተወሰነ ግዜ በኋላ ሰሜን ሱዳን ከህወሓቶች አሻጥር ይልቅ የዶ/ር አብይን ትብብር በመምረጥ በሙሉ ልብ መደመሯ የማይቀር ነው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት ከሞላ ጎደል ሁሉም ጎረቤት ሀገራት ተደምረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከሀገሪቱ አብላጫ ህዝብ ያላቸው ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብን ጨምሮ እንደ አፋር፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ እና ሶማሌ ያሉ ክልሎች የአመራር ለውጥ በማድረግ መደመራቸውን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ። ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና ጎረቤት ሀገራት በተለያ የመደመር ፍላጎትና ተነሳሽነት የሌለው በወንጀል የሚፈለጉ የቀድሞ ባለስልጣናት መሸሺያና መደበቂያ የሆነው የትግራይ ክልል ነው። ይሄ ቡድን ከትግራይ ክልል ውጪ መሄጃና መደበቂያ ቦታ የለውም። በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ጎረቤት ሀገራት መሸሽና መሸሸግ አይችልም። በዚህ መሰረት ህወሓት ያለው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው። ከዚህ በኋላ ግፊትና ጫና ማድረግ ድመትን በር ዘግቶ እንደ መግረፍ ነው። ድመትን በር ዘግቶ መግረፍ በድንገት ወደ አውሬነት ተቀይራ ልትናከስ ትችላለች። በተመሳሳይ ህወሓትን ከዚህ በላይ መጫን ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ጉዳዩ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ያሻዋል።