በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ የሚያጠነጥን ዘጋፊ ፊልም ለህዝብ እይታ ሊቀርብ ነው

ባለፉት ዓመታት በእስር ጥላ ስር ይገኙ በነበሩ ዜጎች ላይ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አትኩሮቱን ያደረገ ዘጋቢ ፊልም በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ለእይታ እንደሚበቃ የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ዝናቡ ጡኑ ገለፁ።

አቶ ዝናቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዘጋቢ ፊልሙ እንደየቴሌቭዥን ጣብያዎቹ መርኃ ግብር ዛሬ ወይንም ነገ ለተመልካች ይደርሳል።

መስሪያ ቤታቸው መረጃ እንደማይደብቅ የተናገሩት አቶ ዝናቡ በበርካታ የቴሌቭዥን ጣብያዎች የመታየቱን ፋይዳ በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ከሳምንታት በፊት ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተያይዘ ተፈፅመዋል በተባሉ ከባድ የሙስና ወንጀሎች ዙርያ የሚያጠነጥን ፊልም በመንግሥታዊ እና ከመንግሥት ጋር ይቀራረባሉ በሚባሉ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ታይቶ የመወያያ ርዕስ ሆኖ እንደከረመ አይዘነጋም።

ተቺዎች እርምጃውን “የዘጋቢ ፊልም ፍርድ” ሲሉ የነቀፉት ሲሆን፤ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ያልተረጋገጠን ተጠርጣሪዎች ላይ ቀድሞ ብያኔ ያስተላለፈ ነው ሲሉ ቅዋሜያቸውን ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን በጋዜጠኞች ተጠይቀው የነበሩት አቶ ዝናቡ የፊልሙ ይዘት ለፍርድ ቤት ከተላከው የወንጀል ዝርዝር የተለየ ስላልሆነ በፍትሕ ሂደቱ ላይ ጣልቃ እንደመግባት አይቆጠርም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውም ይታወቃል።

ቢቢሲ ፊልሙ ይተላለፍባቸዋል ከተባሉ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ከአንደኛው ያገኘው መረጃ አንደሚያሳየው ይህ 1ሰዓት ከ15 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውዘጋቢ ፊልም ዛሬ ምሽት ከ2፡30 በኋላ የሚታይ ሲሆን፤ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል የተባሉ ተጠቂዎችን ምስክርነት ያካተተ ነው።

**

ምንጭ፦ BBC|አማርኛ