አሽራፍ: ከፋጉሎ እና የነቀዘ ሱፍ የተመረዘ የምግብ ዘይት የሚያመርተው ፋብሪካ

አሽራፍ በባሕርዳር ከተማ ሁለት የፋብሪካ ይዞታዎች አሉት፤ በቀበሌ 11 እና በቀበሌ 14:: የመጀመሪያው በ1996 ዓ.ም ከመንግሥት በ500 ሚሊዮን ብር የገዛው የባሕር ዳር የምግብ ዘይት ፋብሪካ ነው:: አቶ ደሳለኝ ለገሰ ደግሞ በቀድሞው የባሕር ዳር የምግብ ዘይት ፋብሪካ በአሁኑ የአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውስጥ መስራት ከጀመሩ 28 ዓመት አስቆጥረዋል:: አቶ ደሳለኝ እንዳሉት አሽራፍ አገርንና ህዝብን በስውር እየጐዳ ነው:: ማህበሩ በአይን የሚታይ የስራ ባህሪ የለውም:: ባሉት የተለያዩ ፋብሪካዎች ሙሉ ስራ የለውም፤ አያመርትም::
“ለምሳሌ” ይላሉ አቶ ደሳለኝ “በምግብ ዘይት ፋብሪካው ዘይት አልፎ አልፎ የሚመረት ቢሆንም የጥራት ችግር አለበት:: ‘ይህ የተበላሸ ዘይት እንዴት ለህዝብ ምግብ ይቀርባል?’ ብለን ስንጠይቅ ‘አይመለከታችሁም፤ የእናንተ ጥያቄ መሆን ያለበት የተባላችሁትን በመስራት ደመወዝ መጠየቅ ነው’ እንባላለን:: ‘ዘይቱ ገደል ይደፋ፤ አይመለከታችሁም’ የሚል ምላሽ በተደጋጋሚ ይሰጣል” ብለዋል::
አቶ አብዮት አማረ በአሽራፍ ስራ ከጀመሩ ስድስት ዓመት ሆኗቸዋል:: እኝህ ግለሰብ እንደገለፁትም አሽራፍ ሰባት ፋብሪካዎች አሉት:: ከእነዚህ ውስጥም የሚሰሩት የውኃ ማሸጊያና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ብቻ ናቸው::

በፋብሪካው ውሰጥ የውኃ ማሸግ ኦፕሬተር የሆኑት ሃያት መሀመድ በበኩላቸው “የአሽራፍ ሰባቱ ፋብሪካዎች ቢሰሩ በርካታ የሰው ኃይልን በሥራ ተጠቃሚ ማድረግ በቻለ ነበር:: ነገር ግን ከሰባት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩት ሁለቱ ብቻ ናቸው:: የድሮው የባሕር ዳር የምግብ ዘይት ፋብሪካ እኮ በውስጡ በርካታ ሠራተኞችን ከመያዙም በላይ ምርቱ ከባሕር ዳር ከተማ ባለፈ ቀሪውን የአገሪቱን ክፍልም እየጠቀመ ነበር:: አሽራፍ የሚያመርተው ግን ለሌላው ቀርቶ ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪም አልሆነም:: ስለዚህ ፋብሪካው የማይሰራ ከሆነ ለሚሰራ ባለ ሀብት መስጠት ተገቢ ነው የሚል አቋም አላቸው::

ወታደር እንግዳ በሬ የመኖሪያ ቤታቸው የአሽራፍ ፋብሪካ በተተከለበት በኩታ ገጠምትነት ይገኛል:: ታዲያ ግለሰቡ የድሮውን የምግብ ዘይት ፋብሪካና አሽራፍ ከያዘው በኋላ ያለውን የምርት ሁኔታ እያነፃፀሩ ይገልፃሉ::

የባሕር ዳር የምግብ ዘይት ፋብሪከ እንደተቆረቆረ ጀምሮ የምግብ ዘይት በብዛት እያመረተ ለከተማው ነዋሪ ያዳርስ ነበር:: የተለያዩ ሱቆችንም በመክፈት ምርቱን በጅምላ ይሸጥ ነበር:: ከዘይት ባለፈ ተረፈ ምርቱን (ፋጉሎውን) ለገበሬዎች በማቅረብ ከብቶች በመኖ ተጠቃሚ ሆነው ነበር:: በተጨማሪም ገበሬው ፋጉሎውን እንደ አፈር ማዳበሪያ በመጠቀም በመሬቱ ላይ ምርት ያፍስበት ነበር:: አሽራፍ ፋብሪካውን ከተረከበው በኋላ ግን ዘይት የሚባል ነገር የለም:: ታዲያ የእኛ ጥያቄ ዘይት ያመርት የነበረው ማሽን የት ሄደ ነው?

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር (ማዘጋጃ ቤት) የሥራ ባልደረባ የሆኑት አቶ ሲሳይ ወርቁም “አሽራፍ ለህዝብና ለመንግስት የሚጠቅም ሥራ እየሰራ አይደለም:: ቀደም ሲል የነበሩት የድርጅቱ መኪኖች፣ የዘይት መጭመቂያዎችና ሌሎች ማሽኖች የሉም፤ የት ሄዱ? ይፈተሽ!” ብለዋል::

ምርቱ

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ “ዘጠኝ ሊትር የምግብ ዘይት በአሽራፍ የተመረተ ገዛሁ:: አንዱን ጀሪካን /ሶስት ሊትር ይይዛል/ ከፍቼ ወጥ ስሰራበት የተሰራው ወጥ ማይቀመስ መራራ ሆኖ ተገኘ:: የተለየ ባእድ ቃናም አለው:: በመሆኑም ለጤናየ በመስጋት ዘይቱን አስቀምጨዋለሁ” በማለት በምሬት ተናግረዋል:: ለ28 ዓመታት በዚሁ ፋብሪካ ውሰጥ ያገለገሉት አቶ ደሳለኝ ለገሠም “በአሽራፍ የሚመረተው ዘይት ችግር አለበት:: ስንጠይቅም አይመለከታችሁም፤ ገደል ይደፋ እንባላለን” ብለዋል::

አቶ አብዮ አማረ በበኩላቸው “አሽራፍ ለዘይት ማምረቻ የሚጠቀመው ግብዓት ጊዜው ያለፈበት ነው” ብለዋል:: የጥራት ተቆጣጣሪው አቶ ጥጋቡ አስማረም “የአሽራፍ ዘይት ማምረቻ የሚጠቀመው ኬሚካል ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ ዘይቱ ጥራት የለውም፤ መራራም ነው” በማለት ተናግረዋል::

የተደቀነው አደጋ

አቶ አብዮት አማረ እንደጠቆሙት አሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለዘይት ማምረቻነት የሚጠቀመው ኮስቲክ ሶዳ የተበላሸ ነው:: “እንግዲህ አስቡት! አሽራፍ ዘይት የሚያመርተው የተበላሸ ኬሚካል በመጠቀም ነው:: ታዲያ የተበላሸ ኬሚካል አስቀምጦ እየተጠቀመ መሆኑ ሲደረስበት በድብቅ በሌሊት ጭኖ ሊያስወጣ ሲሞክር እጅ ከፈንጅ ተይዟል” ብለዋል:: ሀያት መሀመድ የተባሉ የውኃ ማሸግ ኦፕሬተር እንደተናገሩት “አሽራፍ ለምርት የሚጠቀመው ሶዳ የተሰኘው ኬሚካል የተበላሸ ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል::

በአሽራፍ ውስጥ በጥራት ተቆጣጣሪነት የሰሩት አቶ ጥጋቡ አስማረ በበኩላቸው “አሽራፍ ዘይት የሚያመርተው ጊዜው ያለፈበትን ኬሚካል፣ ጨውና ኮስቲክ ሶዳ እየተጠቀመ ነው:: ይህ ጊዜው ያለፈበት ኬሚካል ላለፉት ስድስት ዓመታት ሥራ ላይ ውሏል:: ታዲያ በዚህ በተበላሸ ኬሚካል ዘይት ስለሚመረት ምርቱን ማህበረሰቡ እየተቀበለው አይደለም:: መራራ ነው:: ይህን ዘይት የተጠቀመ ሰው ከዓለም ተለይቶ ሊሆን ይችላል” ብለዋል::

እኛ ያልተጣራ ዘይት (ክሩድ ኦይል) በሚመረትበት የዓባይ ማዶ ፋብሪካው በተገኘንበት ወቅት ፋብሪካው የዘይቱን ተረፈ ምርት (ፋጉሎ መሰሉን ነገር) ወለል ላይ አስጥቶ መልሶ ዘይት ሊሰራበት ሲያዘጋጀው ተመልክተናል:: ለዘይት መጭመቂያነት የሚጠቀምበት ሱፍም ነቅዞ ነፍሳቱን አስተውለናል::

አቶ ነጋልኝ ሁነኛው የዘይት ፋብሪካው ጀኔራል ሜንቴናስ ማናጀር ናቸው:: እሳቸው ደግሞ “በአሁኑ ወቅት በሶስት ጐተራ ከ500 ቶን በላይ መቶ በመቶ ጥራቱን የጠበቀ የሱፍ ግብአት አለን:: ነገር ግን ለዘይት መጭመቂያነት የተገጠመው መሳሪያ ዘመናዊ መሆንና የባለሙያዎች ብቃት ማነስ ተደማምሮ መቶ በመቶ ወደ ስራ እንዳንገባ አድርጐናል እንጂ የግብአት እጥረት በዘይት በኩል የለብንም:: በ24 ሰአት ውስጥ እኮ 36 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ማምረት እንችላለን:: በየክፍሉም የጥራት ማስጠበቂያ ላቦራቶሪዎች አሉን:: ፋጉሎ የመሰለውን ነገር መልሶ ለዘይት መጭመቂያነት ማዋል ክፋት የለውም፤ የምግብ ዘይት ባህርይ ነው” ብለዋል::

በአሽራፍ የሚመረተው የሳፊ ውሃ ፕሮዳክሽን ሱፐርቫይዘር አታልሌ ጎሹ በበኩላቸው “የሳፊ ውኃ ከከርሰ ምድር 104 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ የሚፈልቅ ነው:: ጥራቱ በአገሪቱ የደረጃ መዳቢ ባለሥልጣን በላብራቶሪ፣ በኬሚካል፣ ፊዚካልና ባዮሎጂካል ተፈትሾ የተረጋገጠ ነው” ብለዋል::

ሚስተር ዲያ ባበክር የአሽራፍ ጀኔራል ማናጀር ናቸው:: እሳቸው እንደገለፁት የአሽራፍ ሰባቱ ፋብሪካዎች በሙሉ ሥራ ላይ አይደሉም:: የዘይት መጭመቂያና የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በጥሬ እቃ እጥረት እየሰሩ አይደለም:: የዘይት ግብአትም ከሱዳን እንድናመጣ ተፈቅዶልን ነበር:: ነገር ግን አንድን ኩንታል ከመተማ ባሕር ዳር በ300 ብር ማጓጓዝ ትችላለህ፤ ከገዳሪፍ ባሕር ዳር ግን 425 ዶላር ያስወጣል:: ስለዚህ ግብአት ከውጭ አገር ማስገባቱ አክሳሪ ነው:: ሌላው ደግሞ የስጋ ማቀነባበሪያውን ለማስጀመር ጥራት ያለው ከብት በአማራ ክልል ማግኘት አልተቻለም:: የጁስ ማቀነባበሪያው ግን ለስራ ተዘጋጅቷል:: በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል:: የመኖ ማቀነባበሪያው ደግሞ ስራ የሚጀምረው የዘይት ምርቱን ተከትሎ ነው:: ስለዚህ የአሽራፍ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ያልገቡት በሁለት አበይት ችግሮች ነው:: አንደኛው የጥሬ እቃ አቅርቦት ማጣት ሲሆን ሁለተኛው የኃይል አቅረቦት እጥረት ነው::

ጀኔራል ማናጀሩ ጨምረው እንዳሉት “አሽራፍ የሚያመርተው ሳፊ ውሃ በጥራት በኢትዮጵያ ቀዳሚ ነው:: በህክምና ተቋማት ጭምር ጥራቱ ተረጋግጧል:: ስለዚህም ምርቱ ከአማራ ክልል ባለፈ ለትግራይና አዲስ አበባ እየቀረበ ነው::”
“በጠቅላላው” አሉ ጀኔራል ማናጀሩ “እኛን መንግሥት በብዙ መልኩ ለመደገፍ እየሞከረ ነው:: ነገር ግን የግብርና ውጤት ማግኘት አልተቻለም:: ለዚህ ነው በሙሉ አቅማችን ወደ ምርት ያልገባነው” ብለዋል::

ጊዜው ስላለፈበት ኮስቲክ ሶዳ ጀኔራል ማናጀሩ ተጠይቀው ሲመልሱም “ችግሩ ያጋጥማል! በምግብ ማብሰያህ ውስጥ ጥሩ ነው ብለህ የገዛኽው ቲማቲም ሊበላሽ ይችላል:: እንደዚያ አስበው:: ከዚህ ባለፈ ጊዜ ያለፈበትን ኬሚካል ለዘይት መጭመቂያነት አልተጠቀምንም:: በመጋዝን ውስጥ ያስቀመጥነው ልክ እንደተበላሸ ቲማቲም በማንኛውም ጊዜ የትም የምታስወግደው ቁስ አይደለም:: የራሱ የአወጋገድ ስርዓት አለው፤ ስለዚህም የሚመለከተውን ሁሉ እርዳታ ጠይቀናል:: እናም ጊዜ ወሰደ::

“አሽረፍ እኮ የባሕር ዳርን ማህበረሰብ እየጠቀመ ነው:: ከ200 በላይ ቋሚ ሠራተኛ አለው:: በተጨማሪም በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ብር ለአማራ ክልል ግብር ይከፍላል:: በይበልጥ ደግሞ ሰባቱ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ ሲጀምሩ በእጅጉ ይጠቅማል” ብለዋል ጀኔራል ማናጀሩ::

ጀነራል ማናጀሩ ይህን ይበሉ እንጂ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ማዕረግ አማረ ግን የሚሉት ሌላ ነው:: እሳቸው እንደሚሉት ኮስቲክ ሶዳን (ሶዲየም ሀይድሮ ኦክሳይድ) የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎች ዘይትን ለመጭመቅ በጣም ያስፈልጋቸዋል:: ነገር ግን ይህ ኬሚካል በአግባቡ ካልተያዘና በወጉ ጥቅም ላይ ካልዋለ ኮስቲክ ሶዳ ዘይት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል:: በጠቅላላው ይህ ኬሚካል የዘይት ግብአት ባለበት፣ ግብአቱ በሚታጠብበት፣ በሚገረደፍበት፣ በሚፈጭበት፣… አካባቢ መቀመጥ የለበትም:: ጉዳቱ የከፋ ይሆናልና::

የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እይታ
በክልሉ የኢንዱስትሪ ቢሮ የኢንዱስትሪ ዞንና የአካባቢ ክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ገበይ ሀይሌ “የአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተለያዩ ፋብሪካዎችን ተክሎ ሊሰራ 79 ሺህ 944 ካሬ ሜትር መሬት ከባሕር ዳር ከተማ ተረክቧል:: ለአብነትም፦ ቦታውን በ1996 ሲረከበው የሥጋና ዓሣ ማቀነባበሪያ፣ የዘይት፣ የፕላስቲክ፣ የውኃ ማሸግ፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የጁስና ጭማቂ ማቀነባበሪያ እንዲሁም ሌሎችንም ፋብሪካዎች በመክፈት አገልግሎት ሊሰጥ የታለመ ነበር:: ይሁንና ከሰባት ፋብሪካዎች ሥራ የጀመሩት ሁለቱ ብቻ ናቸው” ይላሉ::

የክልሉ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ በቁጥር ኢኮል (አአኢ-54/646) በቀን 24/03/2006 በተፃፈ ደብዳቤ” የአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወደ ማምረት ባለመሸጋገሩ ክልሉ ከድርጅቱ ጋር የገባውን ወል ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል:: ስለሆነም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም ለድርጅቱ የሰጠውን 79 ሺህ 944 ካሬ ሜትር ስፋት ካለው ቦታ ጋር ተያይዞ ያሉ ውሎች የተቋረጡና የመከኑ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ለአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲደርሰው አድርጓል” ይላል::

በአማራ ክልል የቀድሞው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታሁን መኮንን በበኩላቸው “አሽራፍ የውኃ፣ የፕላስቲክና የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ ሥራ ላይ ናቸው:: የስጋ ማቀነባበሪያው ግን ከቆመ አምስት ዓመት ሆኗታል:: ስለዚህ ድርጅቱ ወደ ስራ የገባው በከፊል በመሆኑ ክልሉን በኢንቨስትመንት ረገድ እየጠቀመ ነው ማለት አይቻልም:: ለነገሩ፤ የጥሬ እቃና የመሰረተ ልማት (መብራት) ችግርም ገጥሞታል:: ስለዚህ አስተዳደራዊ ርምጃ ለመውሰድ ባለሀብቱ የውጭ ዜጋ በመሆናቸው ጉዳዩ የፌደራል መንግስት ነው::

“ከዚህ በፊትም በ2006/07 ዓ.ም ወደ ሥራ እንዲገባ ግፊት ቢደረግም ባለመግባታቸው የተሰጣቸው መሬት ተነስቶ ነበር:: ነገር ግን ባለሀብቱ በጤና እክል ምክንያት ወደ ሥራ አለመግባታቸው ተረጋግጦና ችግራቸውንም ለማስተካከል ተግባብተን መሬቱ ተመልሶላቸዋል::
“ነገር ግን አሽራፍ አሁን ያለበትን ችግር ይዞ መቀጠል አለበት ብሎ ማሰብ ጤነኛ ሀሳብ አይደለም፤ ድጋፍ ተሰጧቸዋል:: የእኛ ጉዳት እየታየ ይታሰብበታል” ብለዋል፤ አቶ ጌታሁን::

የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሙያዎች የአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን በተመለከተ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረቡት ሪፖርት አሽራፍ ካሉት ፋብሪካዎች መካከል የውኃና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች የ24 ሰዓት ሥራ ያከናውናሉ:: የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካውም እየሰራ ነው:: በአንፃሩ የዘይት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ አይሰራም:: የሥጋ ፋብሪካው ይባሱን መስራት ያቆመው የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ በቀን የሚፈልገውን ከስድስት ሺህ በላይ ጥራት ያለው ከብት ማግኘት አለመቻሉ ነው:: የዘይት ፋብሪካውም በቀን አንድ ሺህ 500 ቶን ግብአት ማግኘት ባለመቻሉ በመሉ አቅሙ ወደ ስራ አልገባም::

በፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮጀክቶች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል አሰፋ እንደገለፁት አሽራፍ ለስጋ ማቀነባበሪያው የግብአት ችግሩን እንዲፈታ ፋብሪካውን ወደ ሌላ አካባቢ እንዲያዞር ምክር ተሰጥቶት ነበር፤ ግን አልፈጸመም:: በዚህ ጉዳይ ችግር ማንሳት የለበትም:: ከዚህ ውጭ ግን መስራት ያለበትን ነገር በተፈለገው ጊዜና መጠን እየሰራ አይደለም:: ስለዚህ ለአሽራፍ የተለየ ስምምነት ስለሌለው የአማራ ክልል መንግሥት መሬቱን አልሰራህበትም ብሎ ርምጃ የመውሰድ መብት አለው:: ክልሉ የሊዝ ውሉን ለማቋረጡ ማረጋገጫ ካገኘን እኛም የኢንቨስትመንት ውሉን እናቋርጣለን:: ውሉን የመሰረዝና የማስጠበቅ መብት የክልሉ ነው:: እኛ ተቃውሞ የለንም::

ሕጉ ምን ይላል?

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ምስጋናው ጋሻው እንደገለፁት የውጭ አገር ባለሀብቶች ወደ አገሪቱ የሚገቡት አገሪቱ በገባችው ዓለም ዓቀፍ የኢንቨስትመንት ማበረታቻና የጥበቃ ስምምነት ውል መሠረት ነው:: አሽራፍን በተመለከተም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በገባችው የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል:: ስለዚሀ አሽራፍ ካጠፋ የአማራ ክልል በቀጥታ ርምጃ መውሰድ አይችልም:: ይህ ሲባል ግን ወደ ሥራ ያልገባን ፣ በአካባቢ ላይ ብክለት ያደረሰን፣ የሰራተኛ መብትን የጣሰን የውጭ አገር ባለሀብት ለረጅም ጊዜ እሽሩሩ እያለ ይቀጥል ማለት አይደለም:: ክልሉ የፌዴራል መንግሥቱን ርምጃ እንዲወስድ በጥናት አስደግፎ በማቅረብ ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል::

በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለ ሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቆዬ “በ2010 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ አንዳንድ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ‘ከአሽራፍ የገዛነው የምግብ ዘይት የመምረር ባህሪ አለው:: ይሸታልም’ አሉን:: ይህን ጥቆማ ይዘን አጣራን፤ እውነትም ሆኖ አገኘነው:: ድርጅቱ ግን ምርቱ የመጨረሻውን ደረጃ ሳይጠብቅ /እየቀረው/ ለገብያ በመውጣቱ ነው:: ስለዚህ ችግር ያለበት ምርት ስለሚታወቅ ገበያ ላይ እየሰበሰብነው ነው፤ አሉንና ተስማማን:: “አሁን ደግሞ አሽራፍ ለምርት የሚጠቀምበት ኬሚካል ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ከህዝብ ጥቆማ ደረሶን ስናጣራ እውነት ሆኖ አገኘነው፤ ጉዳዩም በሂደት ላይ ነው” ብለዋል::

የሠራተኛ አያያዝ

ስማቸውን ቢገልፁ “የከፋ ችግር ይደርስብኛል” ብለው የሰጉ አንድ የአሽራፍ ሠራተኛ እንደገለፁት በዚህ ተቋም ውሰጥ መስራት የጀመሩት የዛሬ 10 ዓመት ነው:: ይሁን እንጂ የሚከፈላቸው በቀን 40 ብር ብቻ ነው:: በጥራት ቁጥጥር የሥራ መደብ ላይ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩት አቶ ጥጋቡ አስማረ “ዘይት እንዲህ መመረት የለበትም በማለቴ ተባረርሁ፤ ‘ለምን?’ ብየ ስጠይቅ ‘ቀሪ አብዝተሃል’ አሉኝ:: ለቀረሁበት ደግሞ ከህጋዊ የጤና ተቋም የህክምና ወረቀት ባቀርብም ተቀባይነት አጣሁ:: ለነገሩ ጥቆማየ ፍሬ አፍርቶ ብዙ ህዝብ ሊጐዳ የነበረ ነገር ሲያዝ በማየቴ ደስታየ ከፍተኛ ነው ብለዋል::

አቶ ወርቁ ቸኮል በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ የተቀጠሩት በ1982 ዓ.ም ነው፤ 22 ዓመት ሙሉ ሰርተዋል:: ነገር ግን ባላወቁት ምክንያት ከ128 ሠራተኞች ጋር ከሥራ ገበታቸው ላይ ተባረዋል:: “ድርጅቱ ሲያባርረን የስራ የአገልግሎት ካሳ ወይም ጡረታ ሊሰጠን ይገባ ነበር:: 22 ዓመት አገልግለን ጉልበታችን ሲዝል በመባረራችን ኑሯችን ተዛባ፤ ልጆቻችን ተጉላሉ:: በጠቅላላው አሽራፍ አልጠቀመንም” ብለዋል::

አቶ ሰለሞን ታደሰ በአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሠራተኛ አስተዳደር ኃላፊ ናቸው:: እሳቸው እንደገለፁት አሽራፍ የአገሪቱን የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/96 ግዴታን ያከበረ ነው:: በመሆኑም የሰራተኞችን መብት የጠበቀም ነው:: የትኛውንም ሰብአዊ መብት የሚጥስ ተግባር አልፈፀመም፤ ይልቁንም ሰራተኛው ያልነበረውን የሰራተኛ ማህበር እንዲያቋቋም አድርጓል:: በዚህም ሰራተኛው ስለመብቱ እንዲጠይቅ በሩን ከፍቷል:: “ይሁንና” አሉ አቶ ሰለሞን “አሽራፍ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሥራ አልጀመረም ነበር:: በመሆኑም ደመወዝ የሚከፍለው ከተቀማጭ ሂሳቡ ላይ ነው:: ስለዚህ ሰራተኛው ላነሳው የደመወዝ ጥያቄ በድርድር እንዲዘገይ ተግባብተናል:: ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ ግን ወደ ሥራ በመግባታችን የደመወዝ ጥያቄው የሚፈታበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል::
አቶ ሰለሞን ጨምረው እንደገለፁት ከዚህ ውጭ መረጃ ሰጠ ተብሎ የተባረረ ሰራተኛ የለም:: አንድ ሰራተኛ ግን ከአምስት ቀናት በላይ በመቅረቱና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የሥራ ውሉ ተቋርጧል:: ሌላው መታወቅ ያለበት “በርካታ ሰራተኞች ሲቀነሱ ይቀመጥላቸው የነበረው የጡረታ ገንዘብ (ፕሮቪደንት ፈንድ) ተከፍሏቸው ነው” ብለዋል::

በአሽራፍ አግሪካልቸራል እና ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከተቋቋመበት ዓላማ ተገቢውን ተልእኮ አላሳካም:: ይህ ደግሞ ያለን ሰፊ ሀብት በተገቢው ሁኔታ አለመጠቅምን ያሳያል:: ከዚህ አኳያ በቀጣይ ከመጠባባቅ ችግሩን በደንብ መርምሮ መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ ነው::

(ሙሉጌታ ሙጨ) በኩር ሕዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም ሙሉ የበኩር ጋዜጣን ፒዲኤፍ በhttp://www.amharaweb.com/Bekur ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ምንጭ፦ አብመድ