የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ማኅበራዊ ፈውስ በኢትዮጵያ

ትላነት ማታ በመንግሥት ሚዲያዎች የተላለፈው “የፍትሕ ሰቆቃ” የተሰኘው ዶኩመንተሪ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጠርጣሪ የፖለቲካ እስረኞች ላይ በማጎሪያ ቦቶች እና ምርመራ ቤቶች የተፈጸሙ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይዘግባል። ዶኩመንተሪውን ተከትሎ በማሥግበራዊ ሚዲያዎች ዜጎች የተለያዩ ስሜት የበዛባቸውን መልዕክቶች ሲጽፉ ተስተውሏል። 

ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ የነዚህን ዶኩመንተሪ ዘገባዎች ነገር ጽፌያለሁ….

አሁንም አንዳንድ ነገሮችን ልጨምር

በመሠረቱ [በቂ አስፈላጊው የሕዝብ ሚዲያ ተቋማት ቢኖሩ] በመንግሥት ባይሠሩ እመርጣለሁ። ከዚህ በፊትም የተሠሩትን ስለምናውቅ ማለቴ ነው። አሁን የተሻለ ማስረጃ ቢኖርም ቅሉ። 

የብሔር  እና የቡድን ፖለቲካ የሕዝብን አዕምሮ በተቆጣጠረበት በዚህ ጊዜ ደግሞ ፍትሕን ለማስፈን አጥፊዎች ዞር ብለው ወዳላዩት፣ ድሮ ወዳላማከሩት ሕዝብ መወሸቃቸው ስለማይቀር ያንን ለመቅረፍም እንደሆነ በመረዳት የትላንት ማታውን ዘገባ ልረዳው። 


በኢትዮጵያ ውስጥ ትውልዶችን የተሻገረ የሰቆቃ ታሪክ አለ። ብዙዎች የዚህ ክፉ ጽዋ ተቋዳሽ ሆነዋል። የሕይወት፣ የወዳጅ እና ቤተሰብ፣ የጤና እና አካል፣ የሕሊና እና ሥነልቦና ዕጦት፣  የንበረት ‘መነጠቅ” የደረሰባቸው የግፍ ቀማሾች ብዙ ናቸው። የት እንደደረሱ የማይታወቁ ብዙ ሰዎች አሉ። 

እኔ እንኳን ከማውቃቸው ብዙ ታሪኮች የኦህዴድ አባል ሆኖ በኦነግነት ጠርጥረውት አፍነው የወሰዱትን የዋንጫ ተሸላሚ ዕጩ ምሩቅ ከምርቃቱ 3 ወራት ገደማ ሲቀሩት የታገተ እስካሁን የት እንዳለ የማይታወቅ ልጅ አለ። 


አሁን ማሰብ ያለብን ፫ ነገሮች አሉ። 

  • ፩. ፍትሕ 

ኢሕአዴግ የሠራው ግፍ እጅግ ብዙ ነው። ዘግናኝ ነው። አረመኔያዊ ነው። የዚህ ግፍ ተግባሩ ሰለባዎች ፍትሕን ይሻሉ። ስለዚህ ደግሞ ገዳዮቹ፣ አሰቃዮቹ አረመኔ ተግባር ፈፃሚዎች ያለምንም ቅድመሁኔታ፣ ያለምንም መሸፋፈን ለሠሩት ሥራ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። እዚህ ጋር ክርክርም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ተገቢውን የሕግ ዳኝነት ሊያገኙ ይገባል። አለቀ! 

  • ፪. ሰላም

ፍትሕና ሰላም እንደ እውነት እና ምኅረት ናቸው…ለማስታረቅ ፈታኝ ናቸው።

ይህንን የፍትሕ ማስፈን ሥራን ተከትሎ የሀገር ሰላምን የሚያውክ ነገር እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይሻል። በፖለቲካ ውሳኔ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብጥ ረገጣዎችን በፖለቲካ ውሳኔ ምኅረት ማግኘት የሚፈልግ አካል ይኖራል። ያ አካል የሚፈልገውን ካላገኘ እና ቅጣቱ የምር መሆኑን ካወቀ ዝም የሚል አይመስለኝም። የነበረውን መረብ ተጠቅሞ፣ የራሱን ብሔር “ልትጠቃ ነው” ብሎ፣ ሌላም ሌላም ተጠቅሞ ሰላምን የሚያውክ ነገር እንደ bargain chip ሊጠቀም ይችላልና ጥንቃቄ ይደረግ! 

አጥፊውም ፍትሕ አስፋኙም ከአንድ ፓርቲ መሁኑ ደግሞ ነገሩን የከፋ ያደርጓል። 

፫. ዘለቄታዊ የማኅበረሰብ ፈውስ

ፍትሕ ማስፈኑም ሆነ ሌላውም በቀጣይ የመጨረሻ ግባቸው መሆን ያለበት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ዜጎቿ እንደ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ፣ እንደ ሀገራዊ ዕሴቶች ባለቤትነት አበረው በሰላም መቀጠል እንዲችሉ አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ፈውስ ማስፈን መሆን አለበት። ከዚያ ውጪ፣ ወንጀልም፣ መንግሥታዊ ሽብርም፣ ዶኩመንተሪውም፣ እሥርና እንግልትም፣ መንግሥት መቀያየርም ለሀገራችን አዲስ አይደሉም…እንዳይደገሙ ነው መሥራት ያለብን። #NeverAgain ማለት መቻል አለብን። 

ለማኅበረሰባዊ ፈውስ የሚረዱንን ሰሞነኛ ነገር ልናገር። 

  • ሀ. ይህንን መሰል ዶኩመንተሪዎች ስንሰማም ሆነ በሌላ መልክ የዚህን ቡድን ጥፋት ስንሰማ ጉዳዩን የምወስደበት ሁኔታ እና ግብረመልስ [react] የምናደርበት መንገድ ላይ መጠንቀቅ አለብን። ከምንም ቡድን [ብሔር፣ ኃይማኖት] ማገናኘት የለብንም። እንደ ማኅበረሰብ ክፉም ደግም የለም….ያው ነን። በዚህ ሊሸማቀቅና ኀፍረት ሊሰማው የሚገባ ቡድን ቢኖር ግለሰቦቹ እና ያ ጠባብ አጥፊ ቡድን [narrow circle mafia] ነው። ማንንም ወክሎ አላጠፉም…ማንም ለነሱ አይሸማቀቅ….እኛም ከማንም ጋር አናላክክ። ለወደ ፊትም ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ውስብስብ ተጨማሪ የችግር ሰንሰለት መፍጠሩ አይቀርምና።
  • ለ.  የደረሰው ጉዳት ለጆሮ የሚሰቀጥጥ መሆኑን ከድሮም እናውቀዋለን። እኔ ልጅ እያለሁ የማውቃቸው ሰዎች በአደባባይ ተሰቅሏል። ሰብዓዊነትን የገፈፈ፣ አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መዓት ሰዎች ታግተው በተለያዩ አዲስ አበባም ሆነ የክልል ከተሞች ማሰቃያ ቤቶች የግፍ መከራ ሲቀምሱ ነበሩ። እዚያ ውስጥ ከተፈጸሙ ነገሮች ያየናቸው እጅግ ትንሹን ነው።  በተለያዩ የክልል ከተሞች የደረሰውን መች ሰማን? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጸሙትን ብቻ ነው የተዘገበው። ከ1984 ዓ. ም. ጀምሮ የተፈጸመውን አልዘገበም ዶኩመንተሪው። የት እንደገቡ የማይታወቁ ልጆችን የሚናፍቁ እናቶች፣ ጡረታ ያጡ የወላድ መካን አባቶች  ዛሬም አሉ። አንዳቸውንም አላናገሩም። እናት ልጇን ገድለውባት ሬሳ ላይ ቀጭ በይ ተብላለች…ዛሬም በሕይወት አለች ብዬ አስባለሁ። 

ይህን ሁሉ ነገር ውሸት ነው ማለት እንዴት ደፈርን? መንግሥት ለፕሮፓጋንዳ ይህንን ስቃይ weaponize እንዳያደርግ መስጋት አንድ ነገር ነው። “ትግርኛ ተናጋሪ ሰዎች አሰቃዩን” መባላቸው አንድ unfortunate ነገር ቢሆንም ግን ትግርኛ ተናጋሪ ከዚህ በኋላ በማንነቱ ይታደናል አያስብልም። ትግርኛ ተናጋሪ ጓደኛ፣ ቤተሰብ እና ወዳጅ ያለን ሰዎች ነን። ማን ነው እነሱን የሚያድናቸው እና የሚያጠፋቸው? አንዲት ሐረገ እየመዘዙ የሰነከለ አካል እያዩ የዘመናት ሰቆቃን መካድ ምንኛ ፈሊጥ ነው። በዚያ ላይ አንተ ነህ አልተባልክም።  በዚህ ማሾፍስ ምንድነው? “Hate Speech በወንጀለኛም አይደረግ..በሕግ ይዳኝ እንጂ” እየተባለ እንዴት በግፍ አካሉን ያጣ ሰው  እያየን “fake ነው”…”ድራማ ነው” ብለን…አልፎስ እንዴት በነሱ ማሾፍ ጀመርን። ልብ በሉ ይህ “ፌክ ነው”..”ድራማ ነው” የሚለው ግለሰብ ነው “ወገኔ ላይ ፕሮፓጋንዳ ተካሄደ” የሚለው። የሚያሳዝነው  ደግሞ ተቀላቢ ግልገል አረመኔ በሰው ቁስል ሲቀልድ የሚያሸበሽለት መንጋውም በዝቷል ፕሮፓጋንዳ እቃወማለሁ…በሰው ፍጡር የግፍ መከራ የሚቀልደውንም አብዝቼ አቃወማለሁ።  ይህ ወደፊት ለማኅበራዊ ፈውስ አይጠቅመንም። 

በዚህ ሰዓት የተቆጣ ማኅበረሰብ አለን። በማኅበራዊ ሚዲያም ያንን ቀጣ የሚያራግብ ሰው አንፈልግም። በዚያም ልክ ደግሞ የፈራም ይኖራል።  “የዘር ማጥፋት አዋጅ ወጣብህ” እየተባለ ማንስ አይፈራም? ስለዚህ ቁጣም ሆነ ፍርሐትን መንዛት ሳይሆን ሕዝብ ከስሜታዊነት ወጥቶ ወደ ልቡ እንዲመለስ ማረጋጋት አለብን።

 ሐ. የተጎጂዎች ካሳ እና መልሶ ማቋቋም ትረስት ፈንድ ወይም  Endowment ያስፈልጋል።

  • የሕይወት፣ የአካል እና የሥነ ልቦና ጤንነት ቀውስ የደረሰባቸው የግፍ ሰለባዎቹን እና ቤተሰቦቻቸውን፣ ልጆቻቸው እና ወላጆቻቸው የት እንደደረሱ የማይታወቁ ቤተሰቦች ተገቢው ካሳና መልሶ ማቋቋሚያ Endowment ሊቋቋምላቸው ይገባል።  ዶኩመንተሪዎቹም መልካቸውን እና ዓላማቸውን ቀይረው ሙሉ መረጃ ከመላ ሀገሪቱ ተሰብስቦ ሊዘጋጁ እና ለፈንድ ማሰባሰቢያ እና ለተጎጂዎች ማቋቋሚያ እንዲውሉ መደረግ አለባቸው። 

ለዘላቂ መፍትሔው የእርቅ ኮሚሽኑም ቶሎ ወደ ሥራ መግባት አለበት። 


 Never Again!
ባጠቃላይ #ፍትሕ ይስፈን። #ሰላም እንዳይናጋ ጥንቀቄ ይደረግ። ለዘለቄታውም #ማኅበረሰባዊ_ፈውስ ይመጣልን ዘንድ ቡድናዊ ትርክቶችን [ጅምላ ፍረጃም ሆነ ለተበዳይ ሰው ርኅራሄ በማሳየት ፈንታ ተበዳይን ጥፋተኛ ማድረግ] እናቁም።  የተቆጣን እናረጋጋው። የፈራን reassure እናድርገው። ለወደፊትም እንዳይደገም NeverAgain እንበለው። 

NEVER AGAIN