“የስብሃት ማፊያ ቡድን” ክፍል 1፡ ህወሓት – ጨቋኝ ቡድን ወይስ ወራሪ ጠላት?

1) ጨቋኝ ቡድን እና ወራሪ ጠላት

አንድ መንግስት በሚመራው ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ በጭካኔ የተሞላ ግፍና በደል የሚፈፅም የፖለቲካ ቡድን አምባገነን ወይም ጨቋኝ ብቻ ሊባል አይችልም። የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት በሚያፈርስ መልኩ ዘረፋና ሌብነት የሚፈፅም ቡድን ሙሰኛ ወይም በዝባዥ ብቻ ሊባል አይችልም። እንደ ህወሓት በሰው ልጅ ላይ ጨካኝ እና በሀገሩ ላይ ዘራፊ የሆነ መንግስት ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። አብዛኞቹ አምባገነን መንግስታት በዜጎች ላይ ግፍና በደል የሚፈፅሙት የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚል ሰበብ ነው። ስለዚህ በዜጎች ላይ ጨቋኝ እና ጨካኝ ቢሆኑም ለሚመሩት ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በፅናት የሚታገሉ ናቸው። በሌላ በኩል ለሚያስተዳደሩት ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ደንታ-ቢስ የሆነና በዜጎች ላይ በጭካኔ የተሞላ ግፍና በደል የሚፈፅም መንግስት ከአምባገነንና ጨቋኝ ይልቅ “የውጪ ወራሪ ኃይል” የሚለው የተሻለ ገላጭ እና ትክክል ነው።

የሀገርን ሉዓላዊነት በመድፈር የመጣ ወራሪ ኃይል ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቡ አይጨነቅም። ምክንያቱም ለሀገሪቱ ሉዓላዊነትና ነፃነት የሚጨነቅ ቢሆን ኖሮ ሲጀመር ወረራ አይፈፅምም። ከዚህ በተጨማሪ ለሀገሪቱ ዜጎች ተቆርቋሪና ወዳጅ ቢሆን እንኳን ህዝቡ የወራሪዎቹን ወዳጅነትና ተቆርቋሪነት አሻም። ከዚህ አንፃር ህወሓት በዜጎች ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅም ቢሆንም እንደ ሌሎች ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት በሚያስተዳድረው ሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ ፅኑ አቋም የለውም። ለዚህ ደግሞ ለኤርትራ የተሰጡት የአሰብ ወደብ እና ባድመ፣ ለሱዳን የተሰጠው የጎንደር፥ መተማ መሬት፣ በብድር ዕዳ ምክንያት የሀገሪቱ ሉዓላዊ ሃብትና ንብረት አደጋ ላይ የወደቀበት አግባብ፣… ወዘተ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በሌላ በኩል ህወሓት የውጪ ወራሪ ኃይል ነው እንዳይባል የኢትዮጵያ የታሪክና የስልጣኔ እምብርት ከሆነችው ትግራይ የመጣ የፖለቲካ ቡድን ነው። ታዲያ የሀገር ዘራፊና ከሃዲ፣ ለዜጎች ጨካኝና ጨቋኝ የሆነ ቡድን ምንድነው?

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “A Political History of the Tigray People`s Liberation Front 1975-1991” በሚል ርዕስ በፃፉት የሶስተኛ ድግሪ ሟሟያ ጥናታዊ ፅሁፍ የህወሓትን መስራቾች እና ቁልፍ የሆነ የአመራርነት ሚና የነበራቸውን ሰዎች ስምና የህይወት ታሪክ በአጭሩ ገልፀዋል። ከህወሓት መስራቾች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ስሁል አየለ ነው። ይህ ሰው ገና በ14 አመቱ የአጎቱን እግር በመከተል ፋሽስት ኢጣሊያን ለመታገል ወደ ጫካ የገባ፣ በ1950ዎቹ አጋማሽ በቀዳማይ ወያነ ትግል የተሳተፈ፣ ለሁለት የምርጫ ዘመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኖ አገልግሏል። በመጨረሻም በቀድሞ የአፄ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ (በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪ ከነበሩ 7 የትግራይ ተወላጆች ጋር በመሆን የትጥቅ ጀምሯል።

ከስሁል ጋር የትጥቅ ትግል ከጀመሩት ተማሪዎች፤ አጋዚ ገሰሰ፣ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሓዬ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር አረጋዊ በፅሁፋቸው የትጥቅ ትግሉ መስራች ያልሆኑ ነገር ግን ህወሓት ውስጥ ወሳኝ የሆነ የአመራርነት ሚና ከነበራቸው በሚል ሶስት ሰዎችን ይጠቅሳል። እነሱም፡- ሙሴ ተክሌ፣ ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው። የትጥቅ ትግሉ በተጀመረ ጥቂት አመታት ውስጥ አዛውንቱ ስሁል አየለ በሽፍታዎች ተገደለ፣ ወጣቱ አጋዚ ገሰሰ በደርግ ወታደሮች ተገደለ፣ እንዲሁም ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር በነበረው ቆይታ ጠቃሚ የውጊያ ልምድና ችሎታ የነበረው ሙሴ ተክሌ በውጊያ ላይ ሲመራው ከነበረ የህወሓት ታጣቂ ቡድን ከጀርባ በተተኮሰ ጥይት ተገደለ።

2) ወደ ነፈሰበት የሚነፍሱት ስዩምና አባይ

በህወሓት ውስጥ የትግራይ ማርክስት-ሌኒኒስት ሊግ – ትማሌሊ (Marxist-Leninist League of Tigrai – MLLT) የሚል የተለየ ቡድን መመስረቱን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ሶስት የድርጅቱ መስራቾች፤ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ድርጅቱን ጥለው በመውጣት ተሰደዱ። እንደ አረጋዊ በርሄ አገላለፅ፣ ትማሌሊ ከተመሰረተ በኋላ ከህወሓት መስራቾች ውስጥ የቀሩት ከአቶ ስብሃት ነጋ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አክራሪ ብሔርተኛ አመላካከት ያለው አቶ ስዩም መስፍን እና ወደ ነፈሰበት የሚነፍሰው ወይም የራስ አቋም የሌለው አቶ አባይ ፀሓዬ ናቸው።

የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን ዓለም “ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነች” ብሎ ህዝብ ካስጨፈረ በኋላ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ግን ለኤርትራ መወሰኑ ይታወሳል። ለኤርትራ የተወሰነበት መሰረታዊ ምክንያት የአቶ ስዩም መስፍን አቅምና ብቃት ማነስ ነው። ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ የባድመ እና አከባቢው ነዋሪዎች ስም ዝርዝር በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የመረጃ ቋት ውስጥ ይገኛል። ባድመ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን ለማሳየት የባድመ ነዋሪዎችን ስም ዝርዝር ይዞ መሄድ ብቻ በቂ ነበር። አቶ ስዩም መስፍን ባድመ የኢትዮጵያ አካል መሆኗን ለማሳየት ያቀረበው በ1900 ዓ.ም (እ.አ.አ.) በአፄ ሚኒሊክ የተፈረሙ የድንበር ስምምነቶችን ነበር። በእንዲህ ያለ የድንቁርና ደረጃ ላይ የሚገኝ ግለሰብ የህወሓት መስራችና አንጋፋ መሪ ይባላል።

በተመሳሳይ በ1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት ሲከፈል አቶ አባይ ፀሓዬ በመጀመሪያ ከእነ ተወልደ ቡድን ጋር የነበሩ ሲሆን የእነ ተወልደ ቡድን ሲመታ ይቅርታ ጠይቀው ወደ መለስ ቡድን መመለሳቸው ይታወሳል። ይህ የአቶ አባይ ፀሓዬን ትክክለኛ ባህሪ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ግንባር ቀደሙን ሚና የተወጡት አቶ አባይ ፀሓዬ መሆናቸው አይካድም። ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ አቶ አባይ ፀሓዬ በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ሃሳብና አስተያየት በሰጠ ቁጥር ህወሓት አንድ ነጥብ ይጥላል። ስለዚህ የህወሓት መስራቾች በሙሉ በሞትና ስደት ከትግሉ ሲወጡ ድርጅቱ በሁለት ሰዎች ቁጥጥር ስር ወደቀ። እነሱም አቶ ስብሃት ነጋ እና አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው።

10 thoughts on ““የስብሃት ማፊያ ቡድን” ክፍል 1፡ ህወሓት – ጨቋኝ ቡድን ወይስ ወራሪ ጠላት?

  1. በጥንካሬ የምወስድላቸው የስቴቬን ኮዚ ‘ዘ ሰቭን ኢፌክቲቢ ሃቢት’ እንዳለው መድረሻውን አውቀው መንገዳቸውን መጀመራቸው ነው። ለዝርፊያ የተጀመረ ወረራ ወራሪ ቡድን የሚፈፅመውን ጭፍጨፋ ፈፅመው 65 ቢሊዮን ዘረፉ። በቃ የታቀደውም የሆነውም ይህ ነው። ዝርፊያው ገና ነው ካሉ ነገም አንተንም ህዝቡንም ይጨፈጭፋሉ። እኛም መዘርፍ ስለማይሰለቸን እንጨፋጨፍላቸዋለን፤ እንጨፈጨፋላቸዋለን። በጠቅላላው ይህ ስርአት መቆም ካለበት 27 አመት ስልጣን ላይ እንዱቀመጡ ጠጠር ያቀበልን ሁሉአደባባይ ወጥተን መቀጣት እለብን። የህዝቡን እንባ ማድረቅ የምንችለው በይቅርታ አይደለም ከርቸሌን ጎብኝተን አንገት መድፋት አለብን። ዛሬም የህዝብ እንባንና ዋይታ ሳይበግራቸው ለወንበር የሚደራደሩ አሉ። በሞቱ፣ በተደፈሩ፣ በተኮላሹ፣ ባበዱ፣ ወዘተ የዜጎች ቁስል የመጣ ለውጥ ላይ እነሱን ወይም ዘመዶቻቸውን ነው እያየን ያለነው። የለውጡ ቲም የበላይነት እስኪይዝ ብለን ዝም ብለን እንጂ የወንጀለኞቹ ተባባሪ ዛሬም ፃታ ቀይረው ባለበት አሉ። አዎን ሁላችንም ይቅርታ የማይገባን ወንጀለኞች ነን። ለእስር ዝግጁ መሆን የሚገባን የወራሪ ወንበዴ 27 አመት ስልጣን ላይ እንዲቆይ ተባባረነዋል።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡