“ሕገወጥ መሣሪያ የሚመጣው ከሱዳን ነው!”

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መነሻው ሱዳን መሆኑን ይፋ አደረገ። ጠ/ዐቃቤ ሕግ ይህንና መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ መታቀዱና ወንጀልን በመከላከልና ስርዓቱን በማስከበር ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ አስገነዘበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ባቀረበው የ100 ቀናት እቅድ ላይ ተወያይቷል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋየ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ህዝቡን ለማርካት የማያቋርጥ የአሰራር ስርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ምን ጊዜም ቢሆን ወደ ማይቀለበስ ደረጃ ለማድረስና የፍትህ ስርዓቱን አሰራር ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ በትጋት እየሰራ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

መንግስት በአዲሱ አደረጃጀት በሚቀጥሉት 100 ቀናት ከጠቅላይ አቃቢ ህግ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የህግና ፍትህ ለውጥ በብቃት መምራት፣ የሚሻሻሉ ህጎችን ማሻሻልና የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት የማክበር በህጉ መሰረት እንዲታረሙ ማድረግ በዋና ዋና ተግባራትነት ተይዘው እንደሚሰሩ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው እቅዱን ካዳመጠ በኋላ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ሊካሱ የሚችሉበት እቅድ ወጥቶ ቢሰራ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጠሩ ግለሰቦችን ከተጠያቂነት አንጻር የተሰራው ስራ ውስንነት ያለው መሆኑ፣ በተለያዩ ክልሎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቢሰራ፣ በፌደራል የሚተዳደሩ ታራሚዎችን ለማነጽና ለማረም የሚጠየቀው ቅሬታ የአገልግሎት ክፍተት መኖሩ፣ ታራሚዎች ያለ ፍትህና ውሳኔ የሚመላለሱበት ሁኔታ ስላለ በቀጣይ በእቅዱ ላይ ተካተው መሰራት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ያቀረቡት የ100 ቀናት እቅድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይና ትርጉም ያላቸውና ስርዓቱን ከማስከበር፣ በተለይ ትልልቅ ወንጀልን ከመከላከል አንጻር እንደሀገርም አስፈላጊና ተገቢ ስለሆኑ በእቅዱ መሰረት መፈጸማቸውን መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ ጸጥታንና ሰላምን ከማስጠበቅ አንጻር ውሳኔና ፍርድ የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተለይም በወንጀል የተጠረጠሩትን ግለሰቦችን ንብረት የማሳገድና የሚመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ አቃቢ ህጉም በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው እንዲካተቱ ያነሳቸውን ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ እንደሚሰራ አስረድተው፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ጉዳት ካደረሱ ተጠርጣሪዎች አንዳንዶቹ ቢያዙም አንዳንድ ግለሰቦች ብሄርንና በሀይማኖትን ተገን በማድረግ ለፖለቲካ ፍጆታ እያዋሉት በመሆኑ ወንጀለኞችን በመያዙ በኩል ቋሚ ኮሚቴው ሊያግዘን ይገባል ብለዋል፡፡

የጦር መሳሪያ ዝውውርን በተመለከተም ህገ-ወጥ መሳሪያ የሚመጣው ከሱዳን መሆኑን ጠቅሰው ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ መታቀዱና በህገ-ወጥ ዝውውር የሚሳተፉ አካላትን ለመያዝ ጥናት እንደሚደርግም አብራርተዋል፡፡

ምንጭ፦ News.et