የሁለት ስርዓት ወጎች: አፓርታይድና ህወሀት

በሀገራችን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ በዜጎቿ ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በአህጉሪቱ ደረጃ እንኳን ታሪካዊ ሊባል በሚችል መልኩ የተፈፀሙ ህገወጥ የሀገር ሀብት የማሸሽና የተደራጀ የሀገር ዝርፊያ ሴራዎች የደቡብ አፍሪካው የቀድሞው አፓርታይድ ስርዓት በጥቁር የሀገሬው ዜጎች ላይ ዘርግቶ ከነበረው የጭቆናና የአፈና ስርዓት ጋር ከፍተኛ ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል:: አፓርታይድ ከኛው ጉድ ህወሀት ጋር ያላቸውን የመርህ: የግብርና የስርዓት ቁርኝቶች ሲቃኙ ሁለቱም የአንድን ቡድን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ለማረጋገጥ ሌላውን ሲጨቁኑና ሲዘርፉ መኖራቸውን እናያለን::

ሀ) አፓርታይድ: ደቡብ አፍሪካ

አፓርታይድ በዋናነት በዘረኛነቱ የሚገለፅ ስርዓት ሲሆን በዚህም ስርዓት ተቋማዊ በሆነ መልኩ የተዘረጉ ሴራዎች በሀገሪቱ የነጮችን ዘለቄታዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነትን አስጠብቆ ለመቀጠል ያለሙና በጥቁር የሀገሪቱ ዜጎች ላይ የተጠነሰሱና የሚተገበሩ የነበሩ ሲሆን ቀጥሎ የተዘረዘሩ ስልቶችን ይከተል ነበር::

1) የተቀነባበረና መዋቅራዊ በሆነ መልኩ በኢኮኖሚ ማደህየት

በጊዜው ጥቁሮችን ሆን ብሎ በኢኮኖሚ ለማደህየት (systematized economic impoverishment) ይደረግ የነበረው መዋቅራዊ (systemic) እና ተቋማዊ (institutionalized) በሆነ መልኩ ሆኖ ሴራው ብዙ መልክ ነበረው:: ይኸውም ጥቁሮች የፓለቲካ ንቃተ ህሊናቸው (political consciousness) ዝቅተኛ እንዲሆን የህግና የሳይንስ ዘርፎች እንዲሁም ባጠቃላይ ከኢኮኖሚክስ ጋር የተያያዙ ዘርፎች ጥናት ላይ እንዳይሰማሩ በረቀቁ ተቋማዊ አካሄዶች እድሉን ይነፈጉ ነበር:: ይህ መሆኑ በጥቁሮች ነጮች ላይ ሊነሱ የሚችሉ የፖለቲካ ተሳታፊነትና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ሆነ ሌሎች የመብት ጥያቄዎች እንዳይነሱ ለማድረግ ነበር:: ይኽም በህዝብ ብዛት የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን አንድ አስረኛ (4ሚሊየን) ብቻ የነበሩት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የማህበራዊ: ኢኮኖሚያዊና የፓለቲካ የበላይነታቸውን በዘላቂነት አረጋግጠው ለማስቀጠል ከነበራቸው ጥልቅ የመዋቅራዊ አሰራር ስልት የመነጨ ነበር::

ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችንና የማዕድን ክምችት ያለባቸውን መሬቶች ጥቁሮቹን በማፈናቀል እየነጠቁ መውሰድም አንዱ የዚሁ ሴራ ስልት አካል ሆኖ በሰፊው ይተገበር ነበር:: እንደውም በስራ አጋጣሚ በሌላ አገር ያገኘሁት አንድ ግዙፍ አለም አቀፍ ተቋም ይመራ የነበረ ጥቁር የሀገሬው ዜጋ ሲያጫውተኝ እንደነገረኝ ‘አንድ ነጭ ፈረሱን በነባር ጥቁር አባወራዎች መሬት ላይ እንዲጋልብ ይደረግና በፈረስ ጋልቦ መሸፈን የቻለው መሬት በሙሉ ተሰጥቶት ከዚያ መሬት ላይ ጥቁሮቹ እንዲፈናቀሉ ወይም ጭሰኛ ሆነው መሬታቸው ላይ እንዲሰሩ ይደረግ’ እንደነበርና አባቱም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቻቸውን በዚያ መልኩ መነጠቃቸውን ገልፆልኝ ነበር::

በነዚህና መሰል በረቀቀ መልኩ በተቀነባበሩ ስልቶች በሀገሪቱ አበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች ጥቁር የሀገሪቱ ዜጎች ከዚህ ግባ የሚባል ሚና እንዳይኖራቸው ነጮቹ ቁልፍ የተባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችን: በተለይም የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ (macro economy) በመቆጣጠር ጥቁሮቹን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ የኢኮኖሚ ባርነት ውስጥ ዘፍቀው በቀላሉ ይገዟቸው ነበር::

2) ከሀገሪቱ ቁልፍ የፓለቲካ ስልጣኖች ማግለል

በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥም ቢሆን የጥቁሮቹ ተሳትፎ ከታማኝ ተላላኪ አስፈፃሚነት የዘለለ አልነበረም:: በዚህም ረገድ ጥቁሮች በሀገሪቱ ወሳኝ የፖለቲካ ስልጣኖችን ላይ እንዳይቆናጠጡ በተደራጀ መልኩ ከውክልና ያለፉ የመንግስት ፖለቲካዊ ሹመቶች አካባቢ እንዳይደርሱ ከፍተኛ አሻጥሮች ይደረጉ ነበር:: በተለይም ደግሞ በዚህ ሁሉ ጫናና ጭቆና አልፈው ማንኛውም አይነት ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ ትግል ለመፈፀም የሚሞክሩ ጥቁር የሀገሪቱ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸው ነበር:: እነዚህ የማያዳግሙ ቅጣቶች ሌሎች ጥቁሮች ተገፋፍተው ወደ ሀገራዊ ነውጥ ሊያመራ የሚችል የትግል አቅጣጫ እንዳይይዝ የለውጥ ትግሉን በአጭሩ ለመቅጨት ያለሙ በመሆናቸው ለሌሎቹ እንደማስተማሪያነት ሲባል የሚደረጉ ስለነበር ለአእምሮ እንኳን የሚዘገንኑና እጅግ አስከፊ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጥቁሮቹ ላይ ይፈፀሙ ነበር::

3) በዘላቂነት የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ መክተት

በተደራራቢ የኢኮኖሚ ባርነትና ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀውንና በአብዛኛው ያልተማረ ጥቁር የሀገሬውን ህዝብ ለዘላቂ ማህበራዊ ቀውሶች መዳረግ ከ’ቀበሌ’ ያለፈና የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ወይንም ደግሞ የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችን በተደራጀ ወይንም ሀገራዊ ቁመና ባለው መልክ እንዳያነሳ ያደርገው ስለነበር በረቀቀ መልኩ ጥቁሮችን በራሳቸው የማህበራዊ ቀውሶች እንዲወጠሩ ማድረግ ሌላው ነጭ የአፓርታይድ ስርአት አራማጆች የተንኮል ሴራ ስልት ነበር::

በአፍሪካ የተለያዩ በቅኝ የተገዙ አገራት በጊዜው የተቀጣጠለውና በኢትዮጵያ ሲደገፍ የነበረው የነፃነት ትግል በየቦታው እየፈጠረ የነበረው ጥቁሮች ከነጮች የጭቆና አገዛዝ ነፃ መውጣት እንደሚችሉ ማየታቸው የፈጠረው ተፅዕኖ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን ባያፋፍመው ኖሮ ምናልባትም ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን እስካሁን በአፓርታይድ አገዛዝ ስር ሊሆኑ ይችሉ ነበር::

በስተመጨረሻም ደቡብ አፍሪካዊያን ከአፓርታይድ ዘረኛ ስርዓት ተላቀው ነፃነታቸውን ቢያውጁም የሀገሪቱ አብላጫ የኢኮኖሚ አቅም በነጮቹ እጅ የቀረ በመሆኑ ከኢኮኖሚ ጫናው ሊገላገሉም ሆነ ይኸው ጦስ ካስከተለባቸው ማህበራዊ ቀውስ ሊላቀቁ አልቻሉም: ምንም እንኳ ሀገራቸው በኢኮኖሚ ካደጉት ሀገራት ተርታ የተሰለፈች ቢሆንም::

ለ) ህወሓት: ኢትዮጵያ

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ህወሀት በዋናነት በብሔርተኝነቱ የሚገለፅ ድርጅት ሲሆን ሲመሰረት የራሱን ብሔር ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ወደ ትግል የገባ ቢሆንም ኋላ ላይ የተፈጠረውን እድል ተጠቅሞ ሀገራዊ ድርጅት: ወይም የፖለቲካ ቡድን መሆን ያልቻለና በነበረው መንደርተኛ አስተሳሰብና መርህ የተነሳ በስተመጨረሻም በጥቂት ግለሰቦች የተፅዕኖ ክልል ውስጥ የወደቀ ድርጅት ሆኗል::

በሀገራችን ላይ ባለፉት ሁለት አስርታት በላይ የተጠነሰሰው ሴራ የአንድ ብሔርን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት አስጠብቆ ቢያንስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያክል ለማስቀጠል ያለመና በስልትም ሆነ በአካሄድ ከአፓርታይዱ ስርአት ብዙም የተለየ ነገር ያልነበረው ነው ማለት ይቻላል:: ይልቁንም በከፋ ደረጃ በጥልቀትና በጥንቃቄ የተጠነሰሱ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና በዘላቂነት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ለመከፋፈል የተሰሩ ሴራዎች መኖራቸው የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል::

በሀገራችን ህዝብ ላይ የተጠነሰሰው ሴራ ውጤታማነቱን መሰረት ያደረገበት ዋና እሳቤ (core assumption) የሀገሪቱ የተለያዩ ከ80 በላይ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸው ላይ በማተኮር ማለቂያ ወደ ሌለው ግጭትና አለመግባባት ይገባሉ የሚል ነበር:: ይህንንም አጀንዳ ከግብ ለማድረስ በወጣቱና አዲሱ ትውልድ ላይ ታሪክን አጣሞ ከማስተማር ጀምሮ ሌላው ብሔር ታሪካዊ ጠላቱና ለህልውናው አስጊ እንደሆነ አድርጎ እንዲቀበል እስከማድረግ ከሁለት አስርታት በላይ የተሰራው ስራ ቀላል የሚባል አልነበረም:: ውጤቱም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አሁን ላይ እያየነው ያለው አዲሱና ወጣቱ: ዘመናዊና የሰለጠነ አስተሳሰብ ሊኖረው የሚገባው ትውልድ በጎጣዊና መንደርተኛ አስተሳሰብ ተወጥሮ በየመንደሩ አንዱ ሌላውን ሲያፈናቅልና: በየከፍተኛ ተቋማቱ የገዛ ሀገሩን የነገ ተስፋ የሆነ ወጣት በዱላ ሲያሯሩጥ ማየታችን ነው:: እነዚህንም ውጤቶች ለማምጣት ህወሀት የተከተላቸው ስልቶች የሚከተሉት ናቸው:

1) ሀገሪቱን በብሔር ተኮር የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ መክተት

የፖለቲካ የበላይነቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ባለው ውጥን ይህን ብሔር ተኮር የፖለቲካ ስርዓት ለመዘርጋት የተጠቀመው ስልት የረቀቀ ከመሆኑም በላይ ህገመንግስታዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ስርዓት በመዘርጋት መጀመሩ የጭቆና ስርዓቱ ከህዝብ የመነጨ እንዲመስልና በቀጣይነት ለረጅም አመታት ለማስቀጠል የነበረውን ውጥን ያሳያል::

ለዚህም ከፍተኛ የሆነ የማስረፅ ስራ በመስራት ከሀገራዊ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔር ተኮር እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር በብሔር ባዋቀረው መንግስታዊ መዋቅሩ አማካኝነት ለግል ጥቅማቸው የተገዙና ለግዜያዊ የፖለቲካ ስልጣን በቀላሉ የሚደለሉ ግለሰቦችን አድኖ በመመልመል ተላላኪ የስውር አጀንዳው ማስፈፀሚያ በማድረግ ስልጣኑን ለሶስት አስርታት ለሚጠጋ ግዜ ሊያስቀጥል ችሏል:: ይኸውም ልክ እንደ አፓርታይዱ ስርዓት ቁልፍ የወታደራዊ: የደህንነትና የፖለቲካ ስልጣኑን በታማኝ የራሱ ብሔር ተወላጆች በማስያዥ ሌላውን በተላላኪ የብሔሩ ተወላጅ በእጅ አዙር ሲያስተዳድር ኖሯል:: እዚህ ጋር የአፓርታይድ ስርዓትም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ ቁልፍ የፖለቲካ: ወታደራዊና የደህንነት ስልጣኖች በቀንደኛ የስርዓቱ አቀንቃኝ ነጮች ብቻ እንዲያዙ ማድረጉን ልብ ይሏል::

ይኸም ተቀናቃኝ ያልነበረው የፖለቲካ ስልጣን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አውታሮች ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠር ከማድረጉም በላይ ሀገሪቱን እንደፈለገ ያለ ጠያቂ እንዲበዘብዝ መንገድ ጠረገለት (በግለሰቦችም ይሁን በተደራጁ የኢኮኖሚ ማፊያ ቡድኖቹ በኩል)::

2) መዋቅራዊ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን መዘርጋት

በመላው ሀገሪቱ የፖለቲካ የበላይነቱን ተጠቅሞ በዘረጋው የኢኮኖሚ መረብ አባላቶቹና ተላላኪ የጥቅም ጀሌዎቹ ዋነኛ አስፈፃሚዎችና ተጠቃሚዎች ነበሩ:: በዚህም የዜጎችን ፍትሀዊና እኩልነትን የተላበሰ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ህገመንግስታዊ መብት በመቀልበስ ታሪካዊ ለሆኑ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በተደራጁ ሀይሎች ለተደረጉ የሀገር ሀብት ዝርፊያና የሀገር ሀብትን በትሪሊዮን በሚቆጠሩ ብሮች በማሸሽ ከባድ የሚባል የሀገር ክህደት ፈፅሞአል:: የአፓርታይድ ስርዓት በዚህ ረገድ የተሻለ ሆነ የተገኘበት ነገር ቢኖር ከሀገር ሀብት አለማሸሹ ሲሆን ይህም የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ የአፓርታይድ ስርዓት ከወደቀ በኋላ እንኳ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረጉ ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት አብቅቷታል::እዚህ ጋር በቀጥታ ከአፓርታይድ ስርዓት ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ከ90% በላይ የሚሆነው ሰፋፊና ለም የእርሻ መሬት የተያዘው በህወሀት አባላትና ተላላኪ ጀሌዎቻቸው መሆኑ ሲሆን ይኸውም ባለመሬቶቹን የክልሉ ነዋሪዎች በማፈናቀል መሆኑ ነው:: በአጠቃላይ የተፈጠረው የስርዓቱ ማሽን የሀገሪቱን አብዛኛውን ኢኮኖሚ (በዋናነት ማክሮ ኢኮኖሚውን) እንዲቆጣጠሩ ያደረገ ከመሆኑም አልፎ ሌላው የሀገሪቱ ህብረተሰብ ክፍል በተቀነባበረ ሴራ ከጉልህ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴዎች እንዲወጣ የተደረገበት ሂደት ነው የነበረው::

3) ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ማህበራዊ ቀውሶች መፍጠር

አሁንም ሆነ ባለፈው አመት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተስተዋሉት ብሔር ተኮር ጥቃቶችም ሆነ ግጭቶች እንዲሁም የዜጎች መፈናቀሎች ሀገሪቱን ከዚህ በፊት በታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ ማህበራዊ ቀውስ የከተቷት ሲሆን ይኸም በቀጣይነት የሀገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ጉዳይ ሆኗል:: አሁን ባለበት ሁኔታ ሀገሪቷ በአጭር ግዜ ውስጥ ከዚህ ቀውስ ውስጥ ትወጣለች ብሎ መገመት እጅግ አዳጋች ነው:: የዚህ ማህበራዊ ቀውስ ዋነኛና መሠረታዊ መነሻው ህወሀት ሶስት አስርት አመታት እንኳ ባልሞላ ግዜ ውስጥ የዘራው ብሔር ተኮር የሆነ የማህበራዊ ግንኙነት መርህና የፖለቲካ መዋቅር ናቸው:: ጎጠኛ አስተሳሰቦች በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የአስተሳሰብ ከፍታዎችን እንዲቆናጠጡ የተሰራው ሴራ ፍሬውን አፍርቶ መጥገብ ከጀመርን ሰነባብተናል:: ይህም ህወሀት ሀገሪቷን በብሔር ልኬት በተሰፉ አስተሳሰቦች በመከፋፈል ዘለቄታዊ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ የበላይነቱን ለማረጋገጥ የዘየደው ዋነኛ ወጥመድ ነው:: የሚያሳዝነው ግን የሀገሪቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ህወሀት በሰፋላቸው የአስተሳሰብና ማህበራዊ ግንኙነት ልኬት ውስጥ እራሳቸውን በፈቃደኝነት በማስገባት ጭንቅላታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው (burying their heads in the sand) መገኘታቸው ነው::

2 thoughts on “የሁለት ስርዓት ወጎች: አፓርታይድና ህወሀት

  1. ቆንጆ ፣ ነው!!!
    ለግንዛቤያችን ፣ መስፋት ፣ ስለሚረዳ ፣ በሚቀጥለው ፣ፅሁፍህ፣ ጽዮናዊነትና፣ ህወሓትን ፣ ብትተነትንልን፣ እናመሰግነሀለን

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡