ይድረስ ለዲያስፖራው ወዳጄ: “አበው ይሙት ዘረኛ ነህ! ኢትዮጵያዊነትም አይገባህም!”

“በመንደርተኛ አስተሳሰብ ተጠበህ: የጎጠኝነትን ፊሽካ የምትነፋ ዘረኝነት እንደ ዲያቢሎስ የተጠናወተህ ከሆንክ ይኽ ፅሁፍ በትክክል ይመለከትሃል!”

By Raphael Addisu በስደት ሀገር የሚኖር ሰው የእንግሊዝኛ መጠሪያው መሆኑን ዘንግተህ የክብር መጠሪያ መስሎህ ራስህን ‘ዲያስፖራ’ እያልክ መጥራት የምትወድ: ከየት መጣህ ብለው ሳይጠይቁህ: የትኛው ብሔር አባል እንደሆንክ ሳትጠየቅ: አገሬ ነውና መብት የለህም ውጣልኝ ሳትባል: በታክስ ከፋይ ዜጎቻቸው ገንዘብ እየደጎሙና ነፃ የትምህርት እድል ሰጥተውህ እያስተማሩህ: በነፃነት ዜግነት ሁሉ ሳይቀር ተሰጥቶህ አንዳንዴም ኑሮ ሲደቁስህ ‘በማህበራዊ ደህንነት ዋስትና’ (social security scheme) አቅርቦቶቻቸው እየተደጎምክ: ማንም ሳይደበድብህ ሳያስርህ በነፃነት ያለሃሳብ አሜሪካ: አውሮጳና አውስትራሊያ የምትኖር ውድ ‘ዲያስፖራው’ ወንድሜ እስቲ ‘በኢትዮጵያዊነት’ ማንነት መነፅር እንወቃቀስ::

የወገንህ ሰቆቃ ተሰምቶህ ጥለህ የኮበለልክበትን የገዛ ቀዬህን እንኳን ተመልሰህ ቢያንስ በገንዘብህ አሊያም በእውቀትህ ለማልማት ደንታ የማይሰጥህ ከሆነ እውነትም ማንነትህ የጠፋብህ: ስለ አገርህ እንኳን በሌላ ሀገር ዜጋ ስትጠየቅ ኢትዮጵያ ከምትባል ውብ አገር መምጣትህን ከመናገር ይልቅ ከጎንደር: ከድሬዳዋ: ከወለጋ: ከአዋሳ ወይንም ከመቀሌ መምጣትህን መናገር የሚቀናህ መንደርተኛ ነህ::

አባቶቹ አጥንታቸውን ከስክሰውላት ደማቸውን አፍስሰውላት ያቆዩለት ሀገሩ ላይ እየሰራ ግብር በመክፈልም ሆነ በእውቀቱና በጉልበቱ ለሀገሪቱ እድገት የበኩሉን ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ በላቡ በሀገሩ የሚኖር ኩሩ ኢትዮጵያዊን ‘ከሀገሬ ውጣ’ ብለህ የምትደነፋ ከሆነ: አድዋ ላይ ለኢትዮጵያዊነት ክብር በተሰዉት አባቶቻችን አጥንት እምልልሀለው የዘረኝነት አዙሪት ናላህን ያዞረብህ በተውሶ ግን የሰለጠነ አስተሳሰብ የሚገዛበት ሀገር ላይ በክብርና በነፃነት በእንግድነት እየኖርክ አስተሳሰብህ ከጎጠኝነት መዝለል ያልቻለ መንገድህም የጠፋብህ ከርታታ: ማህበራዊም ሆነ የህሊና ፈውስ የሚያስፈልግህ በሽተኛ ነህ::
አንተ ለራስህ በተደላደለው ኑሮህ ተንፈልስሰህ በማህበራዊ ድህረገፅ ከኮምፒውተርህና ስማርት ስልክህ በስተጀርባ ተቀምጠህ ሀገር ቤት ያለን ባለ ብሩህ ተስፋ ወጣት ወንድምህን ጭንቅላት በዘረኛ አስተሳሰብህ እየመረዝክ የክፋት ክርፋትህን የምታዝረከርክ ከሆነ አስረግጬ እነግርሀለው የአስተሳሰብ ዝቅጠትህ ከሲዖል ዝቅታ እንኳን የወረደብህ ነህ:: ወንድሙን ከቀዬው እንዲያፈናቅል: አስተሳሰቡም በብሔር ተኮር ጎጠኝነት እንዲቃኝ የምትቀስቀስ ከሆነ አንተ የኢትዮጵያ ጠላት ባንዳ ነህ:: ሌላኛውን ወንድምህንስ ከየትኛው ሀገርህ ነው ውጣልኝ እያልክ ያለኸው?! ከአንተ ብሔር ስላልሆነ ሀገሩ አይደለም ያለህስ ማነው?! ይህንንስ ለማድረግ የሞራል ብቃቱን ከየት አገኘህ?!

አየህ ይህ የድብርትህ ማሳለፊያ የምታደርገው የሀገር ቤት ወጣት በሚስኪን ግን ኩሩዋ እናቱ የጉሊት ንግድና በኩሩውና ወኔያም አባቱ የቀን ስራ ገቢዎች የሚተዳደርን: ለራሱ የወደፊት መፃኢ እድል ፈንታ እንኳ ማሰብ የተሳነውን ወጣት ቢሆን እንኳ: ገና በልጅነቱ ኳስ በካልሲ ብጣሽ ሰርቶ ብሔርህ ምንድነው ሳይባባል በጣፋጭ አንደበቱ እተኮላተፈ አማርኛውን ከኦሮሚፋ: ሲዳምኛውን ከወላይትኛ: ትግርኛውን ከአማርኛ እየቀላቀለ ከገዛ የሌላ ብሔር ወንድሙ ጋር በፍቅር ሲጫወት ያደገ ጨቅላ ወጣት ንፁህና በኢትዮጵያዊነት የተባረከ አእምሮው ያለው ወጣት ነው::
ታዲያ ይህ ተስፈኛ ወጣት ከአንተ የሚፈልገውም ጠንክሮ ተምሮ ነገ ራሱን በአስተሳሰብ አጎልብቶ ለሀገርና ለወገኑ የሚጠቅም ትውልድ የሚሆንበትን መንገድ እንድታሳየው በሞራልም ሆነ በገንዘብ ይህን ህልሙን ከግብ እንዲያደርስ በቻልከው ሁሉ እንድትደግፈው ነው:: ታላቅ ወንድሙ (Big Brother) እንድትሆነው ነው:: ምክንያቱም አንተ የሰለጠነ አስተሳሰብ የሚገዛበት ሀገር ውስጥ ስለኖርክ ብቻ አስተሳሰብህ ሰልጥኖአል: ከእሱም የተሻለም ታውቃለህ ብሎ ያስባልና:: ደግሞም የተሻለ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ እንድትሆንም የሞራል ግዴታ አለብህ:: አንተ አልገባህ ይሆናል እንጂ በሌላ በምንም ከመገለፅህ በፊት በሰውነትህ ነው የምትገለፀው:: ሰውነት ደግሞ ሌላኛውን ሰው የሆነውን ወንድምህን በማክበርና በመቀበል እንዲሁም በደንብ ከገባህ ደግሞ Celebrate በማድረግ ይገለፃል::

የአዳምና ሔዋን መገኛ ከሆነችው የኢትዮጵያ ምድር ከተገኘህ ደግሞ ይህ ሀቅ የኦክስጅን ያክል በደምህ ተዋህዶ ያለ እውነት ነው:: አየህ ኢትዮጵያዊነት መወለድ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከምንም በላይ የአስተሳሰብ ልዕልና መገለጫ ነው:: ኢትዮጵያዊነት የአስተሳሰብ ቁንጮ: የሰውነት ከፍታ ነው:: ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞነት: አማራነት: ትግራዋይነት: ጉራጌነት: ሲዳማነት: ወላይታነት: ሀድያነት: ከምባታነት: ጋሞነት: አፋርነት: ሱማሌነት: ጋምቤላነት እንዲሁም የተቀሩት ሁሉም የብሔር ማንነቶች ስብጥር መገለጫ ነው::

ኢትዮጵያዊነት ውበት ነው:: ኢትዮጵያዊነት ፍቅርን ምላሽ ሳይጠብቁ መስጠት: የኔ ያንተ ነው በመባባል አብሮ ጠጥቶና በልቶ መኖር ነው:: ዳሩ ግን እኔ ኢትዮጵያዊነትን ልሰብክህ አይደለም: ለዛ እንኳ የሞራል ብቃቱም የለኝም: በዚህች ትንሽ ዘመኔም የሞራል ብቃቱ ያለው ኢትዮጵያዊ አላየሁም አልሰማሁምም:: ግን አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኜ እነግርሀለው፡፡ የአንተ ድርጊት በኢትዮጵያዊነት ስብዕና ሚዛን ፀያፍ የሚባል ምግባር ነው:: አንተን በተመለከተ ብዙ ብነግርህ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህች አጭር መጣጥፍ ስለማልጨርሰው ለአሁን በዚህ ይብቃኝ፡፡ ምናልባት ሌላ ግዜ እድሜ ሰጥቶኝ አንተም አስተሳሰብህ በአንድ እርምጃም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያዊ የአስተሳሰብ ከፍታ አድጎ እንገናኝ ይሆናል::