ሰሚ ያጣው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ሰቆቃ!!

በቀደምት አስርት አመታት “የፍቅር ከተማ” በመባል የምትታወቀው ሀዋሳ ከተማ አሁን አሁን ሰላሟ ከሸሻት ብዙ ወራትን አስቆጥራለች:: ብሔር ተኮር በሆኑ የፍላጎት ግጭቶችና በህግ አግባብ ሊነሱ የሚችሉ የብሔር ይገባኛል ጥያቄዎችን በህገወጥና የከተማዋን ሰላም በሚያውክ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንጋ ቡድኖች መቀስቀሳቸው በመቀጠሉ የነዋሪዎቿ ሰቆቃ ዛሬም ቀጥሏል:: የህግ የበላይነትን ማስፈን ያልተቻለው በአብዛኛው ከአንድ ብሔር ብቻ የተዋቀረው የከተማዋ ወገንተኛ አስተዳደር እስከ ዛሬም ቢሆን የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ: በፈለጉበት በሰላም የመኖርና ሀብት የማፍራት ህገመንግስታዊ መብቶችና በአጠቃላይም የነዋሪዎችዋን ደህንነት ማስከበር ያልቻለበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነው:: የዚህም ሁሉ ምክንያት በሀገሪቱ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ይመስለኛል::

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ወራት ውስጥ በተለይም ከአሰቃቂውና አንድን አዳጊ ወጣት እስከማቃጠል ከዘለቀው: የከተማው ነዋሪ ላይ ያተኮረ የመንጋ ቡድኖች ጥቃትና ሽብር መልስ በስጋት ውስጥ መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል:: እናቶች ገበያ ወጥተው ከጉሊት ሸምተው በሰላም ወደ መኖሪያቸው መመለስ: ልጆቻቸው ወጥተው ከትምህርት ገበታቸው በሰላም ለመመለሳቸው እርግጠኛ ያልሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው:: ወጣት ሴት ልጆች ንብረታቸው ሳይቀማ አካላዊ ጥቃቶች ሳይደርስባቸው እንደ ድሮው በፈለጉበት ጊዜ ወጥተው መግባት የማይታሰብባት ከተማ ከሆነች ሰነባብታለች ሀዋሳ:: የንግድ ቤቶች በየጊዜው በመንጋ ቡድኖች የመዘረፍ ስጋት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ በእጅጉ አውኮታል:: በከተማው የመንግስት አስተዳደርም ቢሆን የነዋሪዎቿ የህግ-ያለህ ጩኸት ሰሚ አጥቶ የመንጋ ቡድኖች ህገወጥ እንቅስቃሴ በከተማው ፖሊስም ጭምር የዝምታ ይሁኝታ ያገኘ ይመስላል::

የከተማዋ ማህበራዊ ቀውስ መንስኤና ውስብስብነት

የሀዋሳን ከተማ ውስብስብ ማህበራዊና ፓለቲካዊ ቀውስ (socio-political crisis) በትክክል ለመረዳት የከተማዋን ከ70 ብሔር ብሔረሰቦች በላይ ያማከለ የነዋሪዎች ስብጥር የማህበራዊ ኑሮ ዘይቤና የፖለቲካ ስነ-ልቦና መረዳት ያስፈልጋል:: በመቀጠልም የሲዳማን ዞን የክልል ይገባኛል ጥያቄ ተከትሎ (ጥያቄው በራሱ ህገመንግስታዊ አግባብ ቢኖረውም) በከተማዋ ላይ የሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ ጉዳዩን የሚያወሳስቡ ነገሮች ናቸው::

በከተማው ዙሪያ ካሉ የዞኑ አካባቢዎች በመሰባሰብ የተደራጀው “ኤጄቶ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የሲዳማ ወጣት የሚያነሳው ህጋዊነቱ አጠያያቂ የሚሆነውና “የከተማዋ ባለቤት እኛ ነን” በሚል የይገባኛል አመለካከት በየጊዜው በከተማዋ የሚነሳው ብጥብጥ ሌላው የተፈጠረው የሰላም እጦትና ማህበራዊ ቀውስ ምክንያት ነው:: አዋሳ ከተማ በደርግ ግዜ የሲዳሞ አውራጃ መቀመጫ ሆና ስታገለግል የቆየች ሲሆን በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ደግሞ ስሟ ተቀይሮ “ሀዋሳ” በመባል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዋና መቀመጫ በመሆን ራሱን በቻለ የከተማ መስተዳድር ስትተዳደር ቆይታለች::

የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ተዋፅኦዎችና እንደምታዎቹ

ሀዋሳ ከተማ ባለፉት 27 አመታት ውስጥ በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች ከአመታዊ የዞን በጀታቸው ከ20% እስከ 30% የሚሆን እየመደቡላት አሁን ላለችበት የእድገት ደረጃ ልትደርስ ችላለች:: የፌዴራል መንግስትም ቢሆን ከተማዋ ካላት የቱሪስት መዳረሻነትና የኢንዳስትሪ መንደርነት አቅም የተነሳ አይኑን ከጣለባት ሰንበትበት ብሏል:: ከዚህም አንፃር የፌዴራል መንግስቱ በብዙ ቢሊየን ብሮች የሚቆጠር ሀብት የከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታና የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ግንባታ ላይ አፍስሷል:: ይህም ከአለም አቀፍ አየር ማረፍያ: የኢንደስትሪ ፓርክ: ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የፌዴራል ተቋማትን ግንባታና ለነዚህ ተቋማት የተደረጉና እየተደረጉ ያሉ የተለያዩ ግብአቶች አቅርቦቶችን ያካትታል::

በዚህም የተነሳ ካላት የተሟላ የመሰረተ ልማት ይዘት አንፃር በክልሉ የተላያዩ ዞኖችም ሆነ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ባለሀብቶችም ጭምር ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሆና ስላገኟት በከፍተኛ ፍጥነት ከሀገሪቱ ሌሎች ከተሞች በበለጠ መልኩ ልታድግ ችላለች:: ይሄ እድገትዋ የፈጠረላት እድል ደግሞ የክልሉ የኢኮኖሚ ማዕከል ከመሆን አልፋ በሀገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካለባቸውና አይን ውስጥ ከሚገቡ ጥቂት ያደጉ ከተሞች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል::

በነዚህና መሰል ምክንያቶች ከተማዋ ልክ እንደ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያና ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና የፌዴራል መንግስት ኢንቨስትመንትና ድጎማ የለማችና ያደገች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተማዋ ላይ እየተነሳ ያለው የይገባኛል ጥያቄ ውስብስብ ይዘት ይኖረዋል:: ወደ ፊት ከተማዋ በማንና በምን አይነት የከተማ አስተዳደር መዋቅር ልትተዳደር ይገባታል የሚለው ዉሳኔም በህገመንግስታዊ አግባብ የከተማው ነዋሪ ሪፈረንደም አካሂዶ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሚወስንበት ጉዳይ ነው:: ቢሆንም አሁን ያለው በተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው በሚንቀሳቀሱና ወጣቱን ለብጥብጥና የፍላጎቶቻቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉ ከሚሹ ቡድኖች ስራ የተነሳ በከተማዋ ነዋሪና በአካባቢው የሲዳማ ተወላጅ ወጣት መካከል እየተፈጠረ ያለው መቃቃር ለዘለቄታዊ የተረጋጋና ሰላማዊ የከተማዋ ማህበረሰብ ኑሮ ከፍተኛ የሆነ እክል የሚፈጥር አካሄድ ነው::

ቀውሱን የማረጋጋትና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ችግሮችና ፈተናዎቹ

በህገ መንግስታዊ አካሄዱ በእንደዚህ አይነት ከ70 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥርና መኖሪያ በሆነች ከተማ የከተማውም ሆነ የክልሉ አስተዳደር ከፍላጎቶች ግጭት (Conflict of Intetests) የተነሳ ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ የከተማዋን ሰላም ማስከበርም ሆነ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ባልቻለበት ሁኔታ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ በመግባት የከተማውን ደህንነት የመቆጣጠር (takeover የማድረግ) ህገመንግስታዊ ስልጣንና ግዴታ (constitutional mandate and responsibility) ቢኖርበትም በግጭቱ መጀመሪያ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ በአንድ ወገን በተወሰደው የዘር ተኮር ጥቃት ወቅት ብቻ ግጭቱን የማርገብ እርምጃ ሲወስድ ተስተውሏል::

ባለፈው አንድ አመት ውስጥ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በየከተሞች የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ በወደቀበትና በነፃነት ወጥቶ መግባትም ሆነ ሰርቶ መኖር አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች የፌዴራል መንግስቱ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያልቻለበት ሁኔታ የተለመደ መገለጫ እየሆነ ሄዷል:: ለዚህም ድሬዳዋ: ሐረር: ጂግጂጋ: አሶሳ: አዋሳ: ወለጋ የተፈጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀሎችና ሞት የዚሁ የዘገየ የፌዴራል መንግስት ምላሽና ለዜጎች ፈጣን ህገመንግስታዊ ከለላ መስጠት አለመቻል (passive reactive response and wait and see approach) አይነተኛ መገለጫ ሲሆን ታይቷል::

በእርግጥ አሁን ያለው የለውጥ መንግስት አስተዳደር ከመሆኑ አንፃር በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በጥንቃቄ መያዝና ተገቢውን የተመከረበት ምላሽ መስጠት ማስፈለጉና ለውጡን በማይቀለበስ መልኩ ለማስቀጠል ከሚያስፈልገው የፖለቲካ ድጋፍ አንፃር ፈጣን ምላሽ መስጠት ያለመቻሉ አሳማኝ ሊሆን ይችላል:: የዚህ አደጋ ግን የዜጎችን ደህነትን ማረጋገጥ አለመቻል እንድምታ ከመፍጠር አልፎ የፌዴራሉ መንግስት በክልሎች ባለ ህብረተሰብ ዘንድ ቅቡልነት የማሳጣት ዝንባሌን ሊፈጥር ይችላል::

ቀውሱን በዘላቂነት ያለመቀልበስ ሀገራዊ እንድምታዎች

በተለይም ደግሞ የሀዋሳውን ሁኔታ (the case of Hawassa) የተለየ የሚያደርገው ከተማዋ የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አብሮነትና ተቻችሎ የመኖር መርህና የወደፊትዋ ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሙከራ ፕሮጀክት(pilot project of the future Ethiopia) መሆንዋ ነው:: ችግሩ እንደዚህ አይነት ዘመን ተሻጋሪ አጀንዳ ያለው “ሀገራዊ ፕሮጀክት” ብቁ ላልሆኑ እጆች መተዉ ሲሆን የዚህ ፕሮጀክት ከውድቀት አፋፍ መገኘት ውጤት (state of near-failure consequence) እንደ ሀገር ወደፊት መተማመንንና የጋራ እሴቶችን የመገንባቱን ሂደት አዳጋችና አደጋ ያንዣበበት ያደርጋዋል የሚል ስጋት አለኝ::

መንግስት እንዳለፉት 27 አመታት ጆሮ ዳባነትን ካልመረጠና የሚሰማ ጆሮና በፍጥነት ወደ ተግባራዊ ምላሽ የሚሸጋገርበት ቁመናና ቁርጠኝነት ላይ ካለ ዛሬም የሀዋሳ ህዝብ ጩኸት ጎልቶ እየተሰማ ነው: በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ጭምር:: ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለህዝብ እሮሮ ጆሮ ዳባ ማለት ለጊዜው የፖለቲካ ስልጣን ማደላደያ ይሆን ይሆናል እንጂ መጨረሻው አገር ማፈራረስ ነው:: በዘለቄታዊ የፖለቲካ ስሌት አንፃር እንኳ ይታይ ቢባል አዋጭነት እንደማይኖረው ከህወሀት ስህተቶች እንደ ሀገር ብዙ መማር ይቻላል:: የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ሰቆቃ የተሞላ የስጋት ኑሮና የመንግስት ጆሮ ዳባነት ጉዳይ በዚህች አጭር የህፍትህ ያለህ አቤቱታ ሊካተት ባይችልም እኔ ለዛሬ በዚሁ ጨርሻለው!!!
ቸር እንሰንብት!

One thought on “ሰሚ ያጣው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ሰቆቃ!!

  1. እባካችሁን ይህን ውስብስብ ችግር ስታስነብቡን ፍርሃት ዋጠኝ! ለምን ብትሉኝ እኔ ያለሁብት ከተማዬ ብዬ የምጠራት ድሬደዋ ዬ ተመሳሳይ ችግር እየተፈጸመ ይገኛል። የመንጋ ሆነው ወጣቶች ጥቃት መፈጸም በተለይ በ01 ቀበሌ መልካ ጀብዱ ውስጥ።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡