ህወሓት “የማፊያ ቡድን” መሆኑ ታውቆ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል!

ይህ ፅሁፍ ባለፈው ሳምንት በወሎ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀው የኦሮማራ የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ነው

የኦሮማራ ጥምረት ከተመሰረተ አንድ አመት ሞላው። ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። በተለይ በኦዴፓ እና አዴፓ መካከል የተፈጠረው ጥምረት በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል። የአዲሱ አመራር ሆነ የኦሮማራ መድረክ ዓላማ በሀገራችን ለሚስተዋሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ነው። ሆኖም ግን ባለፈው አንድ አመት ከቅድመ ዝግጅት እና አንዳንድ ጅምር እንቅስቃሴዎች በዘለለ ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይቻልም።

በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ በዘላቂነት ለማስቀጠል እነዚህን ውስብስብ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ያስፍልጋል። በዚህ መሰረት ባለፉት ሦስት አስርት አመታት የተጠራቀሙ እና እርስ-በእርስ የተጠላለፉ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት፤ በመጀመሪያ የችግሮቹን መሰረታዊ መንስዔ በግልፅ መለየት፣ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች ማቅረብ፣ የተግባር ዕቅድ ማዘጋጀት እና የአፈፃፀም መመሪያና ክትትል ስርዓት መዘርጋት አለበት። ለዚህ ደግሞ የኦሮማራ ጥምረት የተመሰረተበት እና የአመራር ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት ተመልሶ ማየት ያስፈልጋል።

ለኦሮማራ ጥምረት ሆነ ለአመራር ለውጡ መነሻ የሆነው በተለያዩ የኦሮሚያና አማራ አከባቢዎች የታየው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ነው። ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ የተቀሰቀሰው፤ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ባለመከበሩ፣ ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ ምክንያት ነው። በየግዜው የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ስለሚከሰቱ የተጠቀሱትን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ አይቻልም። በሌላ በኩል እነዚህን መብቶች እና ነፃነቶች ሙሉ በሙሉ ማስከበር የተሳነው መንግስት በስልጣን ላይ መቆየት አይችልም። ስለዚህ የመንግስት ተቀባይነት እና ድጋፍ የሚወሰነው ነባርና አዳዲስ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በሚያደርገው ያላሳለሰ ጥረት ነው።

ዜጎች የሚያነሷቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ተቀብሎ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት የሚያደርግ መንግስት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ ስለሚኖረው በስልጣን ላይ ይቆያል። በአንፃሩ ከብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል የሚነሱ ጥያቄዎችን በኃይል ለማፈን እና ለማዳፈን ጥረት የሚያደርግ መንግስት እንደ ሁኔታው ጨቋኝ፥ አምባገነን፥ በዝባዥ፥… ወዘተ ይባላል። እንዲህ ያለ መንግስት ከተወሰነ ግዜ በኋላ በህዝብ ምርጫ ወይም በህዝባዊ አመፅ ከስልጣን ይወገዳል።

የዜጎችን የመብትና ነፃነት ጥያቄ ለማፈን ከወታደራዊ ኃይል እና ጉልበት በዘለለ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅም፤ በዚህም የህብረተሰቡን ማህበራዊ እሴቶች በመጣስ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሞራል ውድቀት የሚያስከትል፣ በሀገር ትልቅ ማህበራዊ ኪሳራ የሚያደርስ የፖለቲካ ቡድን፤ የሀገሪቱን ዜጎች በብሔርና ቋንቋ ከፋፍሎ የፖለቲካ ስልጣን የያዘ፣ የብሔርና ጎሳ ግጭት በመቀስቀስ የበላይነቱን ማስቀጠል የሚሻ፣ የሀገሪቱ አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ በከባድ የዘረፋና ሌብነት ተግባር የተሰማራ፣ ሀገሪቱን ለመበታተን አቅዶ ሀገር የሚያስተዳድር የፖለቲካ ቡድን ትክክለኛ መጠሪያው “የማፊያ መንግስት” ነው።

በመሰረቱ በመንግስታዊ መዋቅር እና ተቋማት ውስጥ ሰርጎ በመግባት በህገወጥ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ እና የህግ ተጠያቂነትን ማስቀረት ከጣሊያን ሚላን እስከ አሜሪካ ማንሃታን ከተሞች የተለመደ የማፊያዎች አሰራር ነው። “የማፊያ መንግስት” የሚለው ግን ከሶቬት ህብረት ውድቀት በኋላ የመጣ ነው። የማፊያ ቡድኖች የመንግስት መዋቅርና ተቋማት ውስጥ ሰርገው አይገቡም። ከዚያ ይልቅ በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን የመንግስትን መዋቅርና ስልጣን በመጠቀም የማፊያ ቡድኖች የሚፈፅሙትን ተግባር ይፈፅማል።

የማፊያ ቡድኖች መሰረታዊ ዓላማ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ እና የራስንና የመንግስትን መዋቅር በመጠቀም ራስን ከህግ ተጠያቂነት መከላከል ነው። በተመሳሳይ የማፊያ መንግስታት የመንግስትን መዋቅር ተጠቅመው በዘረፋና ሌብነት ተግባር ይሰማራሉ፣ የመንግስትን የፀጥታና ደህንነት፣ እንዲሁም የህግ አውጪና ህግ አስፈፃሚውን አካል በመጠቀም ራሳቸውን ከህግ ተጠያቂነት ይከላከላሉ።

እ.አ.አ. በ2012 “Moises Naim” የተባሉ የዘርፉ ምሁር “Foreign Affairs” በተሰኘው ታዋቂ መፅሄት ላይ በሰጡት ትንታኔ የማፊያ መንግስትን መሰረታዊ ባህሪ እና የማፊያ መንግስታትን ዝርዝር እንደሚከተለው ገልፀዋል፡-

“Unlike normal states, mafia states do not just occasionally rely on criminal groups to advance particular foreign policy goals. In a mafia state, high government officials actually become integral players in, if not the leaders of, criminal enterprises, and the defense and promotion of those enterprises’ businesses become official priorities. In mafia states such as Bulgaria, Guinea-Bissau, Montenegro, Myanmar (also called Burma), Ukraine, and Venezuela, the national interest and the interests of organized crime are now inextricably intertwined. Because the policies and resource allocations of mafia states are determined as much by the influence of criminals as by the forces that typically shape state behavior, these states pose a serious challenge to policymakers and analysts of international politics.” Mafia States፡ Organized Crime Takes Office፣ May/June 2012 ESSAY

ከላይ በተገለጸው መሰረት የማፊያ መንግስት ባለስልጣናት ህገወጥ ዘረፋና የገንዘብ ዝውውር የሚፈፀምባቸው ተቋማት ዋና ኃላፊ ባይሆኑ እንኳን እነዚህን ድርጅቶች መከላከልና ማበረታታት በመንግስት ቅድሚያ የተሰጣቸው ተግባራት ይሆናሉ። በማፊያ መንግስት በምትተዳደር ሀገር ውስጥ ብሔራዊ ጥቅም እና የተደራጀ ዘረፋ የሚፈፅመው ቡድን ጥቅም እርስ-በእርሱ የተጠላለፈ ነው። በዚህ ምክንያት የመንግስትን ፖሊሲ እና የበጀት አመዳደብ ከሀገራዊ ጉዳዮች ይልቅ በማፊያ ቡድኑ ጥቅምና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ይሆናል።

በዚህ መሰረት የማፊያ መንግስት የሀገሪቱን መንግስታዊ መዋቅር፣ ሃብት፣ በጀት፣ የፖለቲካ ተፅዕኖ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በመጠቀም ለራሳቸውን፣ ለቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጅ-ዘመዶቻቸው ሃብትና ንብረት ይሰበስባሉ። በዚህ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ዘረፋ ተግባር የሚሰማሩት ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ህግ አውጪዎች፣ የመረጃና ደህንነት ኃላፊዎች፣ የፖሊስ አዛዦች፣ ወታደራዊ ባለስልጣናት፣ አንዳንዴ ደግሞ የሀገሪቱ መሪዎች ወይም ለእነሱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

“How Smugglers, Traffickers, and Copycats are Hijacking the Global Economy” በሚለው መፅሃፋቸው የሚታወቁት ከላይ የተጠቀሱት ምሁር በዚህ አመት መጀመሪያ አከባቢ (እ.አ.አ. 2018) “Francisco Toro” ከተባሉ ሌላ የዘርፉ ምሁር ጋር በመሆን የማፊያ መንግስት በሚያስተዳድረው ሀገርና ህዝብ ላይ ምን ዓይነት ውድቀትና ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል፤ “Venezuela’s Suicide፡ Lessons From a Failed State” በሚል ርዕስ ጥልቅ የሆነ የትንታኔ ፅሁፍ አውጥተዋል። በዚህ ፅሁፍ የማፊያ መንግስት በሀገርና ህዝብ ላይ ምን ዓይነት ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል ሁለት የላቲን አሜሪካ ሀገራትን በንፅፅር አቅርበዋል፡-

“Consider two Latin American countries. The first is one of the region’s oldest and strongest democracies. It boasts a stronger social safety net than any of its neighbors and is making progress on its promise to deliver free health care and higher education to all its citizens. It is a model of social mobility and a magnet for immigrants from across Latin America and Europe. The press is free, and the trade and investment ties with the United States, it serves as the Latin American headquarters for a slew of multinational corporations. It has the best infrastructure in South America. It is still unmistakably a developing country, with its share o corruption, injustice, and dysfunction, but it is well ahead of other poor countries by almost any measure.

The second country is one o Latin America’s most impoverished nations and its newest dictatorship. Its schools lie half deserted. The health system has been devastated by decades of underinvestment, corruption, and neglect; long-vanquished diseases, such as malaria and measles, have returned. Only a tiny elite can afford enough to eat. An epidemic of violence has made it one o the most murderous countries in the world. It is the source of Latin America’s largest refugee migration in a generation, with millions of citizens feeing in the last few years alone. Hardly anyone (aside from other autocratic governments) recognizes its sham elections, and the small portion o the media not under direct state control still follows the official line for fear o reprisals. By the end of 2018, its economy will have shrunk by about half in the last five years. It is a major cocaine trafficking hub, and key power brokers in its political elite have been indicted in the United States on drug charges. Prices double every 25 days. The main airport is largely deserted, used by just a handful of holdout airlines bringing few passengers to and from the outside world.” Venezuela’s Suicide Lessons From a Failed State: ESSAY November/December 2018 Issue

ከላይ ለንፅፅር የቀረቡት ሀገራት ፍፁም የተለያዩ ይመስላሉ። ምክንያቱም የመጀመሪያዋ ሀገር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከላቲን አሜሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም ናት። ሁለተኛዋ ደግሞ በሁሉም ረገድ ከላቲን አሜሪካ ሀገራት የመጨረሻ ናት። ስለዚህ ሁለቱን ሀገራት አንድ ናቸው ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ነገር ግን እውነታው ይሄ ነው – በንፅፅር የቀረበችው አንድ ቬኔዙዌላ ናት። የመጀመሪያዋ በ1970ዎቹ የነበረችው ቬኔዙዌላ ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ የዛሬዋ ቬኔዙዋላ ነች።

እንደ “Moises Naim” አገላለፅ ቬኔዙዌላ ከላቲን አሜሪካ መሪነት ወደ ጭራነት የተቀየረችበት መሰረታዊ ምክንያት “የማፊያ መንግስት” ነው። በዚህ መልኩ ቬኔዙዌላን ለከፋ ውድቀት የዳረጋት የማፊያ መንግስት ላለፉት 27 አመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ከነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ እና ቬኔዙዌላን ሲያስተዳድሩ በነበሩት የማፊያ መንግስታት መካከል ያለው ተመሳሳይነት ከማስገረም አልፎ ያስደነግጣል። የሀገራቱ መሪዎች የሚያራምዱት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት፣ እንደ አሜሪካና ቻይና ካሉ ሃያላን ሀገራት ጋር የነበራቸው የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም በሀገራቱ ላይ ያደረሱት ማህበራዊ ቀውስ እና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ፍፁም ተመሳሳይ ነው።

ኢትዮጵያ ከቬኔዙዌላ የምትለየው የላቲን አሜሪካዋ ሀገር ከገባችበት የውድቀት ገደል አፋፍ ላይ በቋፍ ተንጠልጥላ የተረፈች መሆኑ ነው። በመሆኑም የተጀመረውን ለውጥ በፍጥነት ማስቀጠል ካልተቻለ በስተቀር ኢትዮጵያም ቬኔዙዌላ ከገባችበት መቀመቅ ውስጥ መግባቷ አይቀርም። በመሆኑም የቬኔዙዌላን አወዳደቅ በጥሞና በማጤን በህወሓት የሚመራው የማፊያ መንግስት በሀገሪቱና ህዝቡ ላይ ያስከተለው ውስብስብ የሆኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በግልፅ መለየትና መገንዘብ ያስፈልጋል።

በዚህ መሰረት አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መንደፍ እና ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ኢትዮጵያም የቬኔዙዌላ እጣ-ፈንታ እንደሚገጥማት አልጠራጠርም። ስለዚህ የኦሮማራ ጥምረት ሆነ የአዲሱ አመራር በህወሓት መሪነት የተዘረጋው የማፊያ መንግስት በሀገሪቱና ህዝቡ ላይ ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር በማጥናት፣ ይህ ፀረ-ለውጥ ቡድን ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈፅማቸውን አፍራሽ ተግባራት መለየት፣ እንዲሁም በዚህ ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥና የለውጥ እርምጃ መውሰድ አለበት።