በመቀሌ እየተካሄደ ያለው ሰብሰባ እና የህወሓት ህልውና!

መቀሌ ውስጥ እየሆነ ስላለው ነገር እስካሁን ድረስ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን እስካሁን በደረሱን መረጃዎች ላይ ተንተርሰን ስለ ሁኔታው የተወሰኑ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ህወሓቶች እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ ዓዲ-ሓቂ በሚገኘው የሃውልቲ አዳራሽ ስብሰባ ላይ ነበሩ። ይህ ስብሰባ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚካሄድ ነው። የስብሰባውን አጀንዳ አስመልክቶ የጠየቅኳቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሁለት ሰዎች በዋናነት አቶ ጌታቸው አሰፋን ለፌደራል ፖሊስ አሳልፎ ስለ መስጠት እና አለመስጠት እንደሆነ ነግረውኛል። በመሆኑም ተሰብሳቢዎቹ የሚያሳልፉት ውሳኔ የአቶ ጌታቸው አሰፋን ብቻ ሳይሆን የተቀሩትን የህወሓት አባላት ህልውና የሚወስን ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት እንደ ጌታቸው አሰፋ ያሉ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፎ የሚሰጥ ከሆነ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያልተፈለገ ግጭት ከመግባት ይድናል። በዚህም የፌደራሉ መንግስት የበጀት ድጎማን ከማቆም ጀምሮ የሚጣሉ የተለያዩ ማዕቀቦችን፣ እንዲሁም በክልሉ ላይ ብቻ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከመጣል ጀምሮ በክልሉ መንግስት ላይ ከሚወስደው ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃ ራሱን ይታደጋል። በዚህ መሰረት አቶ ጌታቸውን አሳልፎ መስጠት የህወሓትን ህልውና ያረጋግጣል።

በሌላ በኩል አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ መስጠት የህወሓት የነፍስ-አባት የሆኑትን አቦይ ስብሃት ነጋ እና እንደ አቶ ጌታቸው ወንጀል የሚፈለጉ ወይም ወደፊት ተመሳሳይ እጣ-ፈንታ ይገጥመናል የሚል ስጋት ያለባቸው የህወሓት መስራቾችና አመራሮችን ክፉኛ ሊያስቆጣ ይችላል። የሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው እጣ እንዳይገጥማቸው የፈሩ የህወሓት አመራሮች “ጌታቸው አሰፋ ተላልፎ ይሰጥ!” የሚል አቋም በሚያራምዱት አመራሮች ላይ የኃይል እርምጃ እስከመውሰድ ሊደርሱ ይችላሉ። በዚህ ረገድ አቶ ጌታቸው አሰፋ እና አቦይ ስብሃት አይነተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

ከላይ የተጠቀሰውን አስጊ ሁኔታ ለመቆጣጠር ይመስላል የፌደራል ፖሊሶች የተወሰኑ ቀናት ቀደም ብለው መቀሌ ከተማ መግባታቸው ታውቋል። ለስራ ወደ መቀሌ ከተማ የሄዱ ሁለት ግለሰቦች ባለፉት ሁለት ቀናት ብዛት ያላቸው የፌደራል ፖሊሶችን በመቀሌ ከተማ እንደተመለከቱ ነግረውኛል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ፖሊሶች በመቀሌ ከተማ ጥብቅ ፍተሻ እያደረጉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የእነ ጌታቸው አሰፋ ቡድን ባለፈው ሳምንት ከዛላምበሳ አከባቢ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት የመከላከያ አዛዦችን ክፉኛ ማስቆጣቱን አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ግለሰብ ነግሮኛል። ይህን ተከትሎ አከባቢውን ለቅቆ ወደ ሌላ ስምሪት እየተንቀሳቀሰ ከነበረው የሰሜን ዕዝ ጦር ሰራዊት ውስጥ አብዛኛው በመቀሌ አከባቢ ሆኖ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የፌደራል ፖሊስ የመቀሌ ከተማን፣ የመከላከያ ሰራዊት ደግሞ ዙሪያ ገባውን በቅርበት እየተከታተሉ እንደመሆኑ መጠን የእነ ጌታቸው አሰፋ ቡድን ከዚህ ቀደም እንደሚሉት የትግራይ ክልል ልዩ ፖሊስ ወይም በሌላ ኃይል አማካኝነት ያልተፈለገ ግጭት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ያላቸው እድል ጠባብ ነው። ሆኖም ግን ድርጅቱ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፈው እንዲሰጡ ውሳኔ የሚያሳልፍ ከሆነ ግን በማንኛውም አግባብ ግጭት ለማስነሳት ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። በተለይ ደግሞ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፈው ይሰጡ የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ ባቀረቡት እና የድጋፍ በሰጡት የህወሓት አመራሮች ላይ የኃይል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ።

በመሰረቱ ህወሓት አቶ ጌታቸው አሰፋን እንዲህ በቀላሉ አሳልፎ ይሰጣል ብዬ አላስብም። ሆኖም ግን ይህን በምፅፍበት ሰዓት እንኳን ህወሓቶች ስብሰባ ላይ ናቸው። ድርጅቱ በአንዲህ ያለ ውጥረት ውስጥ ስብሰባ ካልተሳሳትኩ በ1977 እና 1993 ዓ.ም፣ እንዲሁም ባለፈው አመት ይመስለኛል። በ1977 እና 1993 ዓ.ም በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ህወሓት ለሁለት ቡድን ተከፍሎ አንዱ አሸናፊ፣ ሌላው ተሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በ2010 ዓ.ም በተካሄደው ስብሰባ የአቦይ ሰብሃት ቡድን ልክ እንዳለፉት ግዜያት አሸናፊ ሆኖ የወጣ መስሎ ነበር። የዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ግን በአቦይ ሰብሃት ቡድን ላይ የህልውና አደጋ ጋርጦበታል። ላለፉት ስምንት ወራት በዶ/ር አብይ አመራር የተጀመረውን ለውጥ በመቀልበስ ህልውናውን ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ህወሓት ልክ እንዳለፈው ግዜ ዛሬም በውጥረት የተሞላ ስብሰባ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህ ስብሰባ መጨረሻ ላይ ግን ልክ እንደ ቀድሞ ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ አንዱ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ይወጣል። የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው አመራሮች በቢጫዋ ሄሌኮፕተር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ አሸናፊው ቡድን የትግራይ ክልልን በለውጥ ጎዳና የመምራት እድል ያገኛል። ችግሩ ህወሓት እነ አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰን አንድነቱን አስጠብቆ የወጣ እንደሆነ ነው። ምክንያቱም በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፎ ላለመስጠት ከወሰነ የዶ/ር አብይ አመራር ቀጥተኛ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል። ይህ ሲሆን እንደ ፖለቲካ ድርጅት የህወሓት ህልውና ያከትማል።