ያለሽግግር መንግስት ሀገርን ማሻገር – ለቪዥን ኢትዮጵያ የቀረበ ጥናታዊ ፅሁፍ

መግቢያ

ከዘውዳዊው አገዛዝ መገርሰስ በኋላ ኢትዮጵያ ሁለት የሽግግር መንግስትን ዘመናትን አስተናግዳለች፡፡የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት የፊውዳሉን ስርዓት የተካው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሲሆን ሁለተኛው ኢህአዴግ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ጋብዞ የመሰረተው ከ1983-1987 የቆየው የሽግግር መንግስት ነው፡፡ ሆኖም ሁለት የሽግግር መንግስት ያስተናገደችው ሃገራችን እስከዛሬ ድረስ በተግባር ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መሸጋገር አልቻለችም1፡፡

ይህ ያልተቻለበት ምክንያት በወቅቱ የሽግግር መንግስታቱን ሲመሩ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ሃገርን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ ቅድሚያ የሰጡት የፖለቲካ ስልጣናቸውን በማቆየት ላይ በመሆኑ ነበር፡፡የሽግግር ጊዜውንም ለሃገር ሽግግር ከመስራት ይልቅ የወደፊት ስልጣናቸውን ለማደላደያ እና የፓርቲያቸውን/የቡድናቸውን ፍላጎት ማስጠበቁን በህግ ማዕቀፍ ያፀኑበት ሆኖ አልፏል2፡፡ ሃገራችን የሽግግር መንግስታትን ማስተናዷ ብቻውን ወደዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊመራት አልቻልም፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሃገር ለማሻገር የሽግግር መንግስት የሚል መጠሪያ ያለው መንግስር መሰየሙ ዋነኛ ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡ዋነኛው ጉዳይ በሃገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃገርን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት ነው፡፡

ሁለት የሽግግር መንግስታትን ያሳለፈችው ሃገራችን አሁንም በወሳኝ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡በአሁኑ የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሽግግር ሁኔታ እንጅ የሽግግር መንግስት የለም፡፡ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው ጉዳይም አከራካሪ ሆኖ ይገኛል፡፡በርግጥ አምባገነን መንግስታት ስልጣን ሲለቁ ድርድር ተደርጎ ከሃገሪቱ የተውጣጡ የፖለቲካ ሃይሎች ለመሰረቱት የሽግግር መንግስት አስረክበው የሚለቁበት ሁኔታ በተፈጠረበት ሃገር ወደ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመሻገር የሚደረገው ጉዞ ቀላል ይሆናል3፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ግን ይህ አይደለም፡፡ይልቅስ የህዝብ ትግልን ተከትሎ ኢህአዴግ ውስጥ በተከሰተው ውስጠ-ፓርቲ ትግል ዲሞክራሲያዊ ሃገር ለመመስረት የሚሹ ቡድኖች ስልጣኑን ተረክበው የሽግግር መንግስት ባይሆኑም የሽግግር ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡

ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያደርጉ ሃገራትን ሽግግር ስኬታማ ከሚያደርጉ ቅድመ-ሁኔታዎች ዋነኞቹ፤ በሽግግር ወቅት ሃገሪቱን የሚመሩ መሪዎች ለሽግግሩ ስኬት ያላቸው ቁርጠኝነት፣የፖለቲካ ልዩነቶችን አቻችሎ ፖለቲካዊ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ ዝንባሌ/ችሎታቸው፣ በህዝባቸውና በአለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው3፡፡ አሁን ሃገራችንን የሚመሩ መሪዎች ወደስልጣን በመጡበት አጭር ጊዜ ከወሰዱት እርምጃ በመነሳት እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎችን የሚያሟሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በመሪዎች በኩል የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎች ከሞላ ጎደል የተሟሉበት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን የሽግግር መንግስት የመመስረት ሌላ ከባድ ሥራ ውስጥ መግባት ብዙ ትርፍ ያለው ነገር አይደለም፡፡

በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሃይሎችን አቻችሎ ይዞ የሚጓዝ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ፍላጎት ባሳየበት ሁኔታ የሽግግር መንግስት ወደ ማቋቋም መሄዱ በሃገሪቱ ከገነነው የጎሳ ፖለቲካ ጋር ሲደመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያደላ ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በሃገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ለመፍጠር ያሳየውን ዘንባሌ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሃገሪቱን ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ ዘይቤ ለማሻገር የሚያግዙ ስራዎችን መስራቱ ተመራጭ ይሆናል፡፡

በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ “ሃገር ማሻገር” የሚለው ሃረግ የሚገልፀው የሃገራችን ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ እንዳታራምድ ሲያግዱ የኖሩ ዋና ዋና ችግሮችን በሽግግሩ ወቅት ፈቶ በምርጫ ለሚመጣው መንግስት ችግሯ የተቃለለ ሃገር ማስረከብ የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እሳቤ የሃገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች በታሪክ ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የተደገፉ ስለሆኑ በአንድ መንግስት አቅም የሚፈቱ አይደሉም፡፡እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮች በሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫ የሚመረጠው መንግስት እንዲፈታቸው ማቆየት ተመራጩን መንግስት ህልውናውን በሚፈታተን ችግር ሊከተው፣ ሃገሪቱንም መልሶ ለሌላ ህዝባዊ አመፅ ሊዳርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሃገራችንን ፖለቲካ ዋና ዋና ችግሮች ሳይቃለሉ በምርጫ ለተመረጠው መንግስት መተላለፍ ስለሌለባቸው በሽግግሩ ወቅት በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ትብበር መፈታት አለባቸው፡፡ የእነዚህን ችግሮች ምንነት መዳሰስ እና እንዴት መፈታት እንዳለባቸው መጠቆም የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ አላማ ነው፡፡

ሃገር ማሻገር እንዴት?

ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚደረግ የለውጥ ጉዞ ስኬታማ የሚሆነው ለውጡ እንዲመጣ የህዝብን ትግል ያነሳሱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ድጋሜ አገርሽተው የብጥብጥ ምክንያት እንዳይሆኑ አድርጎ ፖለቲካዊ መልስ መስጠት ሲቻል ነው5፡፡ ለውጥን ያነሳሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለይቶ በተሳካ ሁኔታ የመመለሱ ስራ ደግሞ ከሃገር አቀፍ እስከ አለም አቀፍ የደረሰ የፖለቲካ ሃይሎችን ተሳትፎ የሚፈልግ እንጅ በስልጣን ላይ ባለው አካል ብቻ የሚቻል ነገር አይደለም6፡፡ የሃገሪቱን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በርካታ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ለመመለስ መሞከሩ እርምጃውን ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር በርካታ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ያስችላል፡፡ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሲቪክ ማህበራት፣ምሁራን፣ዓለምአቀፍ የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጥ ትግል እንዲያደርግ የገፋፉ አንኳር ጥያቄዎች በከፊል አሁን በስራ ላይ ባለው ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩ አንዳንድ ድንጋጌዎች የፈጠሯቸው ናቸው7፡፡ የዘር ማንነትን ብቸኛ መገለጫ አድርጎ የሚያስበው ወቅታዊው የሃገራችን ፖለቲካዊ ባህል፣ይህን የሚከተለው የዘር ፌደራሊዝም፣ የሃገሪቱ ክልሎች በፈለጉ ሰዓት ሉዓላዊ መንግስት ሆነው መገንጠልን የሚፈቅደው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ፣የመሬትባለቤትነትን ለብሄር ብሄረሰቦች እና ለመንግስት ሆኖ መደንገጉ ዋነኞቹ ህገ-መንግስት ወለድ የሃገራችን ፖለቲካ ችግሮች ናቸው8፡፡እንዲህ ያሉ ህዝቡን ለትግል ያስነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን መመለስ ካልተቻለ ሃገሪቱ ወደ ሌላ የብጥብጥ ምዕራፍ የማምራት አደጋ ሊገጥማት ይችላል9፡፡ ሃገራችን እያየችው ያለውን የለውጥ ጅማሬ ለማፅናት እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄዎቹ ፈርጀ ብዙ እና የብዙ አካላትን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ በመሆናቸው፤ የሁሉም የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሃይሎችን ተሳትፎ ይፈልጋሉ፡፡

ስለዚህ ጥያቄዎቹ መመለስ ያለባቸው ወደፊት በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ወደ ስልጣን በመጣ አንድ ፓርቲ ሳይሆን በሃገሪቱ ባሉ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ውይይት ተደርጎባቸው በስተመጨረሻው ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርበው መሆን አለበት፡፡ በአንድ የምርጫ ጊዜ የሚመረጥ መንግስት የህዝብን ውክልና የሚያገኘው የፓርቲ ፕሮግራሞቹን ተከትሎ በአምስት አመት ውስጥ እሰራለሁ ያላቸውን ተግባራት ለመከወን እንጅ እንደ ህገ-መንግስት ያሉ የሃገሪቱን ህዝቦች ዕጣ ፋንታ በዘላቂነት የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን አይደለም፡፡

ከአምባገነን መንግስታት ውድቀደት በኋላ የሚደረግ ምርጫ የሃገሮችን ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ጉዞ በእጅጉ የሚወስን ነው9፡፡እንዲህ ያለው ምርጫ በስኬት ተከናውኖ የሚመጣው መንግስትም በተረጋጋ ሁኔታ ሃገሪቱን ለመመምራት እንዲችል በተቻለ መጠን ብጥብጥ ሊያስነሱ የሚችሉ ዋና ዋና የህዝብ ጥያቄዎች በሽግግሩ ዘመን መመለስ አለባቸው፡፡እነዚህ ዋነኛ የሃገሪቱ ችግሮች በሃገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ በተሳተፉበት የጋራ ጥረት በሽግግሩ ወቅት ቢፈቱ አዲስ የሚመረጠው መንግስት እነዚህን ችግሮችን ወደ መፍታቱ አስቸጋሪ ስራ ከመሄድ ይልቅ በብጥብጥ የቆየችውን ሃገር መልሰው የሚገነቡ ፖሊሲዎችን አውጥቶ መተግበሩ ላይ እንዲያተኩር ይረዳዋል10፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሃገሪቱን ለለውጥ ያነሳሱ ዋና ዋና የህዝብ ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚመረጠው መንግስት እንዲፈቱ ከተተወ ሃገሪቱ ተመልሳ ወደ ነውጥ የመግባት ከፍ ያለ ዕድል ይኖራታል11፡፡ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሃገሪቱ ከአምባገነን መንግስት ወደ ዲሞክራሲ ለመጓዝ በሽግግር ወቅት እንደመሆኗ ህዝቡ ከለመደው የአምባገነናዊ አስተዳደር በተለየው የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመምራት ራሱን የቻለ ችግር ይጠብቀዋል12፡፡የሚቀጥለው የሃገራችን ምርጫ ሃገሪቱ ወደ ዲሞክራዊያዊ የምርጫ ዘይቤ የምትተላለፍበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡የሚያሸንፈው ማኛውም ፓርቲ(ኢህአዴግን ጨምሮ) ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንግዳ ነው፡፡በምርጫው የሚያሸንፈው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሆነ ደግሞ እንግድነቱ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለሃገር መምራትም ይሆናል፡፡ከሁለቱም ወገን ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስት የሚያስተዳደርው ለዲሞክራሲ እንግዳ የሆነን ህዝብ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ብቻ ቀላል የማይባል ተግዳሮት ይጠብቀዋል፡፡

በዚህ ተግዳሮት ላይ የሃገሪቱ ህዝቦች ለረዥም ዘመን የታገሉባቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ይሄው ተመራጭ መንግስት እንዲፈታ መጠበቅ ሃገሪቱን ወደ አደገኛ ብጥብጥ ሊመራት ይችላል፡፡ስለዚህ በሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫ ወደስልጣን የሚመጣው መንግስት መረከብ ያለበት በታሪክ እየተንከባለሉ የመጡ ሥር-ሰደድ ፖለቲካዊ ችግሮቿ የተቃለሉ ኢትዮጵያን መሆን አለበት፡፡

በሽግግሩ ወቅት መመለስ ያለባቸው መሰረታዊ የሃገራችን ችግሮች ምን ምን ናቸው?

ሃገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ለማሻገር የሚቻለው ህልውናዋን የሚፈታተኑ፣የህዝቦቿን ሰላም የሚያደፈርሱ፣የዲሞክራሲ ግንባታን የሚያግዱ ችግሮቿን በሰፊው ለሁለት ይከፈላሉ፡፡አንደኛው ህገ-መመንግስታዊ ድጋፍ ያላቸው ነገር ግን የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮም ሆነ የሃገሪቱን እንደ ሃገር የመቀጠል ዕድል አደጋ ውስጥ የሚከቱ ችግሮች ሲሆኑ ሁለተኛውዎቹ ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ጋር የሚቆራኙ ችግሮች ናቸው፡፡

ሀ. ህገ-መንግስት ወለድ ችግሮች፤

  1. የዘር ፖለቲካ/የዘር ፌደራሊዝም

በአሁኑ ወቅት በምንኖርባት ዓለም ህዝቦች በዘውጋቸው ሳሆን ሶሻል ዲሞክራሲ፣ሊብራል ዲሞክራሲ፣የወግ አጥባቂዎች በሚሉ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ትግበራ ቀመር ላይ ባተኮሩ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው ማህበራዊ መስተጋብራቸውን እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸውን በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የተነሳ አብዛኛዎቹ የዓለም ሃገራት የዘር ፖለቲካን ካነገበችው ሃገራችን በተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካን ይዘት ዘውግ ብቻ እስከማድረግ የዘለቀችው ሃገራችን፣ በአስፈሪ የጎሳ ግጭት፣በማያቆም የክልሎች የድንበር ጥያቄ፣በኢኮኖሚ እድገት ዝግመት ውስጥ ትገኛለች፡፡

የሃገራችን ፖለቲካ ወቅታዊ ችግር ዋነኛ ምንጭ የዘር ፖለቲካ ነው13፡፡የዘርፖለቲካ/ፌደራልዝም በባህሪው ለዘመናዊ ፖለቲካ ግንባታ የማይመች፣ከዲሞክራሲ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ፣ የሃገርን ዘላቂ ሰላምን በማስፈን በኩል ቀላል የማይባል ተግዳሮት የሚደቅን፣ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መሰናክል የሚፈጥር፣የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስቸግር፣ከተፈጥሯዊው የሰውልጆች ባህሪ ጋርም የማይሄድ ርዕዮተ-ዓለም ነው14፡፡ የዘር ፖለቲካ ከሰውልጆች ተፈሯዊ የእሳቤ ፈለግ ባፈነገጠ ሁኔታ የአንድ ዘር አባላት ሁልጊዜ ተመሳሳይ አቋም እንደ ሚይዙ ታሳቢ ያደርጋል15፡፡

በሃገራችን ህገ-መንግስት የተደነገገው የዘውግ ፖለቲካ ታሳቢ የሚያደርገው ይህኑ ከአንድ አይነት ዘር የሆኑ ሰዎች አንድ አይነት ፍላጎት እና ሃሳብ ይኖራቸዋል የሚለውን እሳቤ ነው፡፡ይህ እሳቤ የዘር ክልል ከመከለል የሚነሳ ችግር አለበት፡፡ የዘውግ ወይም የብሄረሰብ ክፍፍል ማድረግ እና ድንበር ማበጀት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የተለያ ጎሳዎች እና ብሄረሰቦች የአሰፋፈራቸው ግንኙነት በጣም የተወሳሰቡ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ግዛት በዘር ፌደራሊዝም የከለለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የሃገሪቱን ብሄረሰቦች ታሪካዊ ግንኙነቶች በአግባቡ ሳይመረምር እና ሁሉን አቀፍና ህዝቦችን ያካተተ ምክክሮችን ሳያደርግ የተደረገ አከላለል ነው17

በተጨማሪ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 ድንጋጌ መሰረት ፌደሬሽኑ በዘጠኝ ክልሎች ብቻ እንዲኖሩ ያደረገበት መመዘኛው ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ይህየህገመንግስቱ ቁልፍ ችግር ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 ንዑስ ቁጥር 1 ውስጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው እያለ በሃገሪቱ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች ከ85 በላይ በሆኑበት ሁኔታ ስምንት ብሄረሰቦች ብቻ ተመርጠው የራሳቸውን መንግስት ማቋቋማቸውን በህገ-መንግስት ማወጅና ሌሎቹ ብሄረሰቦች ከፈለጉ ወደ ፊት መንግስት ማቋቋም ይችላሉ ብሎ ማለፉ በብሄረሰቦች መሃከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ከመሆኑም በላይ የዘር ፌደራሊዝሙ በበቂ ጥናት እና ትኩረት ያልተሰራ መሆኑን ያሳያል18፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው በአሁኑ ሰዓት የማያባራ የክልል ጥያቄ እየተነሳበት ያለው ደቡብ ክልል ነው፡፡

በክልል ደረጃ ያልተዋቀሩ ብሄሮችም የራሳችን ክልላዊ መንግስት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ የየራሳቸውን ክልሎች ማቋቋም እንደሚችሉ ነው በህገመንግስቱ የተገለፀው19፡፡ ይህን ጥያቄ ለማንሳት የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ ተደርጎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 47 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተቀመጠው ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ህዝብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት በስራ ላይ የሚውለው፤ “ሀ” የክልል መመስረት ጥያቄው በብሄሩ፣ ብሄረሰቡ ወይም ህዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ እና ጥያቄው በፅሁፍ ለክልል ምክርቤት ሲቀርብ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጅ በሃገራችን ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በስተቀር በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ብሄረሰቦች ይህን ለማድረግ የሚያስችል የብሄረሰብ ምክር ቤት የላቸውም20፡፡ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልለ ውስጥ የጉሙዝ/በርታ ብሄረሰብ የራሱ ምክርቤት እንዲኖረው አቅርቦ የነበረው ጥያቄ በክልሉ ምክርቤትም ሆነ በፌደሬሽን ምክርቤት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ነው21፡፡

እንደ ደቡብ ክልል ብሄረሰቦች የራሳቸው ምክርቤት እንዲኖራቸው በተደረገበት ሁኔታ ያለው ችግር ደግሞ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3 ስር ከሀ-ሠ የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች የክልል ጥያቄ የሚያቀርበውን ብሄር ጉዳይ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የሚታየው ጥያቄው በተነሳበት ብሄር ምክርቤት እና በክልሉ ምክርቤት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ በሌሎች ሃገራት ግን አዲስ ክልል ወይም አስተዳደር ለማደራጀት ጥያቄ ሲነሳ ገና ከመጀመሪያው ለማየት የሚችሉት ጥያቄው የተነሳባቸው ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ ፌደራሉን ህገ-መንግስት መሰረት በማድረግ በሶስትዮሽ እንጅ በአካባቢያዊ ምክርቤቶች ብቻ አይደለም፡፡

ለምሳሌ በፌደራል ጀርመን ህገመንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ እንደተገለፀው በፌደራሉ መንግስት ስልጣን ውስጥ አሁን ካሉት የፌደራል አባል መንግስታት በተጨማሪ አዲስ የፌደራል መንግስት ወይም አስተዳደር ማደራጀት እንደሚቻል ያመለክታል፡፡ ይህ ተፈፃሚ የሚሆነው አዲስ አስተዳደር የሚፈልጉ አካባቢዎች ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል የኢኮኖሚ ግንባታ ብቃታቸውና መንግስታዊ ሃላፊነቶችን እንደሌሎች ፌደራል አባል መንግስት ሊወጡ የሚችሉ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣የመሬታቸው ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ አስተዳደር ለማቋቋም ምቹ መሆኑ ሲያስተማምን ፣በህዝቦች መሆከል የባህል ተቀራራቢነት መኖሩ ሲታወቅ እና የኢኮኖሚ ግንባታ ግንኙነቶችም በትክክል ይህንኑ ለማስፈፀም የሚያስችሉ ሆነው ሲገኙ የአስተዳደር ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል ያመለክታል22፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን የአዳዲስ ክልሎች መፈጠር ጥያቄውም መልሱም በክልል ምክርቤት እና በአካባቢያዊ የብሄረሰቦች ምክርቤት ውሳኔ ብቻ እንዲያልቅ ተደንግጓል፡፡ ይህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በተቀመጠበት ሁኔታ ጥያቄው አይነሳ ማለት ህጋዊ አካሄድ አይደለም፡፡ጥያቄው ህገ-መንግስታዊ ስለሆነ መፈቀድ ካለበት ደግሞ ክልሎቹ በተመሰረቱ ማግስት የድንበር፣ተፈጥሮ ሃብት ይገባኛል እና የማንነት ጥያቄን መሰረት ያደረጉ የእርስበርስ ግጭቶች የመከተል እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ይህ ደግሞ የሃገሪቱን እንደ ሃገር መቀጠል ፈተና ላይ የሚጥል ችግር ነው፡፡

ሌላው ትልቅ ችግር በሃገሪቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39 ለሃገሪቱ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተሰጠው ከሃገሪቱ ተገንጥሎ ሉዓላዊ ሃገር የመሆን መብት ነው፡፡ይህን ድንጋጌ በህገ-መንግስት ማስቀመጥ ለሃገር ህልውና አደገኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያ በቀር በሌሎች የዓለም ሃገራት ከዘውግ ጥያቄ ጋር የተያያዙ እንደ መገንጠል ያሉ ጉዳዮች የተለያዩ ዘውግ አባላት ተከባብረው በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ወደሚል ፈለግ ተቀይሯል23፡፡ ሃገራችን ግን ይህን አንቀፅ የህገ-መንግስቷ አካል አድርጋ ቀጥላለች፡፡ የዚህ ምክንያቱ ህገ-መንግስቱ ሲፃፍ የሃገሪቱ ዋነኛ ወሳኝ የፖለቲካ ሃይል የነበረው ህወሃት በተፈጥሮው ስታሊናዊ ማንነት ያለው በመሆኑ እና ፓርቲው በትጥቅ ትግል ወቅት ከፃፈው የፓርቲ ማኒፌስቶች ቅጅ በመሆኑ አንቀፁ እንዲነሳ ፍላጎት ያለው ባለመሆኑ ነው24፡፡

በዚህ ድንጋጌ የአማርኛው ትርጉም ላይ ብሄረሰቦች “ያለምንም ቅደመ-ሁኔታ”፣በእንግሊዝኛው ደግሞ “unconditionnally” ከሃገሪቱ ተገንጥለው የራሳቸውን ሉዓላዊ መንግስት የመመስረት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡በነባራዊው ዓለም ሃገርን መገንጠል የሚያክል ትልቅ እና ውስብስብ ጉዳይ ቀርቶ ማንኛውም ቀላል የሚባል ውሳኔ ያለቅድመ-ሁኔታ ሊደረግ አይችልም፡፡ በተግባር የታየውም ይሄው ነው፡፡ በወረቀት ላይ ያለ ቅድመ-ሁኔታ መገንጠልን የሚፈቅደውን ህገ-መንግስት የፃፈው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በሃያ ሰባት አመቱ ቆይታው የመገንጠልን መብት በተግባር ሲተገብር አልታየም፡፡በምትኩ እንገንጠል ከሚሉ እንደ ኦነግ እና ኦብነግ ያሉ ቡድኖች ጋር ሲዋጋ፣ሲከስ፣ሲያስር ነው የታየው፡፡ ሆኖም የአንቀፁ በህ-መንግስት ላይ ተፅፎ መኖር ሃገሪቱን ለከባድ የህልውና አደጋ መጋበዙ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ በሃገሪቱ ለሚመጡ መንግስታት ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡

በጥቅሉ ሲታይ በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መካከል ለሰላም እና ለጋራ ብልፅግና መታገለን የሚያመቻቹ ሁኔታዎች የሉም፤ጊዜን እና የፖለቲካ ውዝገቦችን እየጠበቁ የተለያዩ ብሄረሰቦች የመገንጠል ጥያቄዎችን ማንሳታቸው የማይቀር ነው25፡፡ ይህ ህገ-መንግስቱን ባስረቀቀው ኢህአዴግ በኩል የዲሞክራሲ መገለጫ ተደርጎ የሚቀርብ ቢሆንም በተቃራኒው ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን የሚያበረታታ ፣ሰላምን እና የጋራ እድገትን የሚያሰናክል አካሄድ ነው25፡፡

በዓለማችን ከኢትዮጵያ በቀር የፌደራል ሥርዓት እያራመደ መገንጠልን በህገ-መንግስቱ የደነገገ ሃገር የለም፤ምክንያቱም የፌደራል ሥርዓት በመስራች መንግስታት መሃከል ያለ ስምምነት ውጤት ነው26፡፡ስለዚህ የመገንጠል ጥያቄን በህገ-መንግስት መደንገግ አስፈላጊ ካለመሆኑም በላይ የራሱን የፌደራሊዝምን ትርጉም የሚያዛባ ነው፡፡ፌደራል ስርዓት እያራመዱ የመገንጠል ጥያቄ ከተነሳ የፌደራሉን መንግስት እድገትና በፌደራሉ መንግስት አባል መንግታት መካከል ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍ የሚያፋልስ፣የሃገርን ህልውናም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡

እስከ መገንጠል በደረሰ ህገ-መንግስታዊ አንቀፆች የሚደገፈው የዘር ፖለቲካ በሃገራቸን በቆየበት የሃያ ሰባት አመት እድሜ በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዘር ግጭትን፣መፈናቀልን፣ሞትን፣ስደትን አስከትሏል፡፡የዘር ፖለቲካን በይፋ የፈቀደው የኢትዮጵያ ህገመንግስት በተግባር ዘር ማፅዳትን ያስከተለ ነው27፡፡ በጉራፈርዳ አማሮች ላይ ፣በሶማሊ እና በኦሮሞ ዘውጎች መካከል፣በጉጅ እና በጌዲኦ፣በቤኒሻንጉል እና በኦሮሞ፣በአማራ እና ትግሬ፣በወላይታ እና ሲዳማ፣ማስቃን እና ማረቆ፣ቀቤና እና ጉራጌ ዘውጎች መሃከል የሚታየው ግጭት መነሻው በህገመንግስት የተደገፈው የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡

በዘውግ ዘይቤ ላይ ብቻ የቆመው ህገ-መንግስት ከሁለት ዘውግ የሚወለዱ/ረሳቸውን በዘውግ ማንነት ለመግለፅ የማይፈልጉ የሃገሪቱን ህዝቦች እንደሌሉ የሚቆጥር ነው፡፡ እነዚህ እንደሌሉ የተቆጠሩ እና ከዘውግ ፖለቲካው የተገለሉ ህዝቦች ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ጥቂት የማይባል ቁጥር ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ባገለለ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነ የፖለቲካ መረጋጋት ማምጣት፣ስር ከሰደደ ድህነት ወጥቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ያስቸግራል፡፡ ለእድገት አካታች ፖለቲካ ያስፈልጋል፡፡እንዲህ ያሉ ችግሮችን ያልፈታች ኢትዮጵያ ህልውናዋም አደጋ ላይ ነውና ሽግግር አደረገች ማለት አይቻልም፡፡ ሃገር ለማሻገር የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት ሁሉንም ሃይሎች ባሳተፈ መንገድ የጎሳ ፖለቲካን የሚያበረታቱ ህገ-መንግስታዊ አንቀፆችን ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡

  1. የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመሬት ባለቤትነት ከመጨረሻው የውዳዊ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ካሉትሶስት መንግስታት ጋር የታገለ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ የመሬት ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥ አልቻለም28::የፊውዳሉን ስርዓት የተካው የወታደራዊው ስርዓት መሬት ለዓራሹ የሚለውን መፈክር አንግቦ በተደረገ ትግል ወደስልጣን የመጣ እንደመሆኑ መሬትን የህዝብ የግል ሃብት የማድረግ እርምጃ ይወስዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ሆኖም ደርግ የፊውዳላዊውን ስርዓት የመሬት ስሪት ቀየረ እንጅ የመሬት ባለቤትነትን ወደ ህዝብ የግል ንብረትነት አላሻገረም29፡፡ይልቅስ በመሬት ከበርቴው ተይዞ የነበረውን የመሬት ባለቤትነት ወደ ወታደራዊው መንግስት ባለቤትነት ቀየረው፡፡ ደርግ ይህን ሲያደርግ ከፊውዳሉ ስርዓት በተሻለ ለአርሶ አደሩ በመሬት የመጠቀም መብት ሰጥቷል30፡፡

ደርግን የተካው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የመሬት ባለቤትነት እንደ ደርግ ዘመኑ ሁሉ የመንግስት እንደሆነ በሽግግሩ ዘመን አውጆ የሽግግሩ ዘመን ሲልቅያም በህገ-መንግስት ይህንኑ አፅንቷ፡፡በኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ አርሶ አደሩም ሆነ የከተማ ነዋሪ ህዝብ በመሬት የመጠቀም እንጅ የባለቤትነት የመሆን መብት የለውም፡፡መሬትን በመጠቀም መብቱ መሬቱን እያረሰ ወይም እያከራየ መጠቀም ይችላል እንጅ መሸጥ መለወጥ ወይም መሬቱ አስይዞ መበደር አይችልም31፡፡ እንዲህ ያለው ሙሉ ባለቤትነትነ የማይፈቅደው የመሬት ፖሊሲ ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ ከመሆኑም በላይ ገበሬው የግብርና ምርትን ለማሳደግ አስፈላጊ የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት እንዲንከባከብ የማያበረታታ ነው32፡፡

ሌላው ችግር ለአርሶ አደሩ የተሰጠው ማከራይትን እና ማውረስን የጨመረው በመሬት የመጠቀም መብት ራሱ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አይደለም፡፡ በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች አርሶ አደሩ በያዘው መሬት የመተቀም መብቱን ለማስጠበቅ የተለያዩ ቅድመሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ክልል ህገ-መንግስት አርሶ አደሩ መሬቱን ማውረስ የሚችለው በእርሱ ስር ለሚተዳደሩ ራሳቸውን ላልቻሉ ልጆቹ ብቻ እንደሆነ ይደነገግጋል፡፡በተመሳሳይ የአማራ ክልል ህገ-መንግስት አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ እየተጠቀመ የመቆየቱ ነገር መሬቱን ለመንከባከብ በሚያደርገው ጥረት ይወሰናል፡የአፈሩን ለምነት የሚያስጠብቁ እንደ ዛፍ መትከል እና ለመሬቱ ጎጅ ያልሆኑ ሰብሎችን ማብቀል የመሬቱን ባለቤትነት ለላማጣት እንደ ግዴታ ተቀምጦበታል33፡፡

ሌላው ትልቁ የመሬት ፖሊስው ችግር መሬትን የመሸንሸን ፣የማከፋፈል እና አስፈላጊ ሲሆንም የመውሰድ መብት ሙሉ በሙሉ ለመንግስት(ለክልል የፓርቲ ካድሬዎች) መሰጠቱ ነው34፡፡ ይህ አርሶ አደሩ በመሬት ባለቤትነቱ እንዳይተማመን ያደርጋል፡፡ እንዳስፈላጊነቱ መንግስት ካመነበት በየጊዜው የሚደረገው ዳዲስ የመሬት ሽንሸና እንደሚኖር የሚያዙ ክልሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአማራ ክልል እስካሁን ሁለት ጊዜ፣የትግራይ ክልል አንድ ጊዜ የመሬት ሽንሸና አድርጓል፡፡በሽንሸናው ወቅት ለአርሶ አደሮቹ የሚደርሰውን የመሬት መጠን የሚወስኑት አካባቢው ካድሬዎች ናቸው35፡፡ተደጋጋሚ የመሬት ሽንሸናው የአርሶ አደሮችን መሬት መጠን ይበልጥ እያሳነሰው ስለሚሄድ በዘመናዊ ቴክኖሎች ተጠቅመው እንዳያርሱ ይከለክላል፤ይህም ምርታማነት ይበልጥ እንዲያሽቆለቁል ያደርጋል፡፡ እንደ አማራ ክልል ያሉ ክልሎች እስካሁን ሁለት ጊዜ የመሬት ሽንሸና ማድረጋቸው የአርሶ አደሩ በመሬት ባለቤትነቱ እንዳይተማመን ከማድረጉም በላይ ምርታማትን ይቀንሳል፡፡

ከሁሉም የከፋው ደግሞ አርሶ አደሮቹ መንግስት መሬቱን ለልማት በፈለገው ጊዜ ከመሬታቸው መነሳት እንዳለባቸው የሚደነግገው ህግ የሁሉም ክልሎች ህግ መሆኑ ነው35፡፡ ይህ ህግ አርሶ አደሩን አንዳንዴ ያለበቂ/ያለምንም ካሳ ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሎ ለከፋ ችግር እንዲዳረግ ያደርጋል፡፡ ሃገራችን ከሁለት አመት በፊት ያስተናገደቸው ህዝባዊ አመፅ መነሻው ይህ ህግ ነው፡፡ለአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ሲባል አርሶ አደሮች ከቀያቸው ሊያነሳ የሚችል እርምጃ ከመንግስት ሊወሰድ መሆኑ ሲታወቅ በመላው ኦሮሚያ ረዥም ጊዜ የዘለቀ ህዝባዊ አመፅ እንዲደረግ ገፋፍቷል፡፡

በከተሞች በሊዝ የሚሰጠው የመሬት ይዞታም ሆነ በገጠር ያለው ይዞታ በብሄር ፖለቲካው ሳቢያ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ሰዎች ተረጋግተው እንዲሰሩ የሚያስችል አይደለም፡፡የዘር ፌደራሊዝሙ ክልሎችን የተወላጅ ዘውጎች ብቻ ናቸው የሚል እሳቤን ስለፈጠረ ከሃገሪቱ የተለያየ ቦታ ተጉዘው ባልተወለዱበት ክልል የመሬት ይዞታ ያላቸው ሰዎች በመሬቱ የመጠቀም መብታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ በተለያየ ወቅት በከተሞችም ሆነ በገጠር ሰዎች ንብረት ካፈሩ በኋላ ከአካባቢያችን ለቃችሁ ወደክልላችን ሂዱ እየተባሉ ሃብት ንብረታቸውን ተቀምተው ወደ ድህነት እንዲገቡ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የመሬት ፖሊሲው ከዘውግ ፖለቲካው ጋር ተደምሮ የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራት መብት የሚገድብ በመሆኑ ለሃገር እድገት ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡

  1. ሃገራችን የምትመራበት ሥርዓተ-መንግስት

የሽግግር ወቅቱ ካከተመበት ወዲህ ሃገራችን በፓርላመንታዊ የመንግስት እንድትመራ ህገ-መንግስቱ ይደነግጋል36፡፡ በፓርላመንታዊ ስርዓት ከአሸናፊው ፓርቲ የሆነ ጠቅላይ ሚነስትር በፓርላማ ይመረጣል፡፡ጠቅላይሚኒስትሩ/ሯ በኩሉ/ሏ ሚኒስትሮችን ይሾምና/ትሾምና ሹመቱ በፓርላማ ይፀድቃል፡፡በዚህ መንገድ አሸናፊው ፓርቲ የሃገሪቱን ህግ አውጭ እና አስፈፃሚው አካል ይቆጣጠራል፡፡እንዲህ ያለውን አሰራር የሚፈቅደው ፓርላመንታዊ ስርዓት በህግ አውጭው እና በአስፈፃሚው መሃከል ሊኖር የሚችውን ፍትጊያ ስለሚቀንስ ዲሞክራሲን በመሰረቱ ሃገሮች በተለይ የተረጋጋ መንግስት ለመፍጠር ተመራጭ ነው37፡፡ በተጨማሪም ይህ አይነቱ መንግስታዊ ስርዓት ቁጥራቸው በዛ ያሉ ፓርቲዎች እና ብዙ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ለሚራመድበት ሃገር የሚመከር የመንግስት አይነት ነው፡፡ ምክንያቱም በሃገራቱ ፖለቲካ ያለው የሃሳብ ብዝሃነት መብላላት የሚችለው ፓርላማው ውስጥ ስለሆነ ነው38፡፡

ሆኖም ፓርላመንታዊ ስርዓትን ለረዥም ዘመን ስታካሂድ የኖረችው ሃገራችን ከላይ የተጠቀሱትን ስርዓቱን ቱርፋቶች ልታጣጥም አልቻልችም፡፡ ይልቅስ ፓርላመንታዊ ስርዓቱ ለአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ህጋዊ ሽፋን የሚሰጥ፣ወደ መጨረሻዎቹ አመታት በተለይ የሃሳብ ብዝሃነት ፈፅሞ የጠፋበት፣ህግ አውጭውን ፍፁማዊ በሆነ የህግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ውስጥ የሚከት ሆኖ ኖሯል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የመንግስት ስርዓት ብቻውን የአንድን ሃገር መንግስት አሰራር ዲሞክራሲያዊ ሊያደርገው እንደማይችል ነው፡፡ ይልቅስ ሃገሮች ፓርላመንታዊ ወይም ፕሬዚደንታዊ የመንግስት መዋቅር ከመመስረታቸው የበለጠ ሃገራቱ የሚገኙበት የፖለቲካ ባህል፣የዲሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ በማራመዱ በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው39፡፡ በዓለማችን በሁለቱም አይነት የመንግስት አወቃቀሮች የተመሰረቱ መንግስታት ስኬታማ የሆነም ያልሆነም ዲሞክራሲን የመመስረት ሂደት ማስመዝገባቸው ለሃሳቡ ማጠናከሪያ ነው፡፡

በፕሬዚደንታዊ የመንግስት አወቃቀር ስኬትን ያስመዘገቡ ሃገራት አነስተኛ የፓርቲ ቁጥር ያላቸው እና የዲሞክራሲ ተቋማቶቻቸው ጠንካራ የሆኑ እንደ አሜሪካ ያሉ ሃገራት ናቸው፡፡ሆኖም እንደ አሜሪካ ባሉ ዲሞክራሲ በዳበረባቸው ሃገራትም በፕሬዚደንታዊ የመንግስት አወቃቀር ተፈጥሮ ሳቢያ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አሉ40፡፡ ከነዚህ ውስጥ በህግ አውጭው እና አስፈፃሚው መሃከል በሚኖር ፍትጊያ ምክንያት ህጎችን ለማውጣት፣በጀት ለማፀደቅ፣የአስፈፃሚውን ሹመት ለማፅደቅ መዘግየት ሊኖር መቻሉ ነው፡፡ ሌላው ችግር የፕሬዚደንት ምርጫ የሚደረገው በቀጥታ በህዝብ ተሳትፎ በመሆኑ በፕሬዚደንቱ/ቷ በኩል ጊዜው ሳይደርስ የስጣን መልቀቅ ጥያቄ ቢነሳ ወይም ፕሬዚደንቱ የፓርላማውን አመኔታ በማጣቱ ሳቢያ በኢምፔችመንት የሚወገድበት ሁኔታ ቢፈጠር ወዲያው ሃገራዊ ምርጫ ማድረጉ አስቸጋሪ ስለሚሆን የሃገሪቱ ላለመረጋጋት ልትዳረግ ትችላለች፡፡በዚህ ረገድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ምክንያት ከሃላፊነት ቢነሱ ሃገራዊ ምርጫ ሳያስፈልግ በፓርላማ ወዲያወኑ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም የሚያስችለው ፓርላመንታዊ ስርዓት ተመራጭ ነው፡፡

የሃገሮች የመንግስት መዋቅር ፓርላመንታዊ ወይም ፕሬዚደንታዊ መሆኑ በራሱ እና ለብቻው የሚፈጥረው ችግር እንደሌለ ይልቅስ ችግሩ የሚነሳው ሃገሮች ከቆዩበት የፖለቲካ ባህል እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥልቀታቸው እንደሆነ ከላይ ተገልጧል፡፡ በዚህ ረገድ ሃገራችን በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ስር የቆየች እንደመሆኗ መንግስታዊ አሰራሩም በዚሁ ቅኝት ኖሯል፡፡ ፓርላመንታዊ ስርዓትን ስንከተል የኖርን ብንሆንም ይህንኑ የሚከተሉ ሌሎች ሃገራት የገኙትን የዲሞክራሲ ቱርፋት እና የመልካም አስተዳደር እሴቶች ማግኘት አልቻልንም፡፡ስለዚህ ሃገራችን በአንድ በኩል ጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ሳትገነባ የፓርላመንታዊ ስርዓትን በመከተሏ ሳቢያ በፓርላማ ውስጥ ስር ሰዶ ከኖረው የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት የአሰራር ዘይቤ መውጣት ሲኖርባት በሌላ በኩል በፓርላመንታዊ ስርዓቱ የነበረውን የአስፈፃሚው ከባድ ተፅዕኖ ተላቃ በአስፈፃሚው እና በህግ አውጭው መሃከል ጤናማ የሃሳብ ፍጭት አድርጎ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ መንግስት ሊኖራት ያስፈልጋል፡፡ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ፓርላመንታዊም ፕሬዚደንታዊም የመንግስት አወቃቀሮች ለብቻቸው ሲቆሙ የሚያመጡትን ችግሮች ቀንሶ ነገር ግን የሁለቱንም ቱርፋቶች የሚያስገኝላትን ከፊል ፕሬዚደንታዊ ስርዓትን(Quasi-presidential) የሚከተል የመንግስት መዋቅር ቢኖራት ተመራጭ ይሆናል፡፡

በከፊል ፕሬዚደንታዊ ስርዓት ፕሬዚደንቱ በቀጥታ ሃገራዊ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሲ/ስትመረጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ/ሯ ደግሞ በፓርላማ ብዙ ወንበር በያዘው ፓርቲ አቅራቢነት በፓርላማ ትመረጥ/ይመረጥና ተጠሪነቷ/ቱ ለፓርላማውም ለፕሬዚደንቱ/ቷም ይሆናል፡፡ የካቢኔ እጩዎች በፕሬዚደንቷ/ቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሯ/ሩ ይቀርብና በፓርላማ ይፀድቃል፡፡ይህ በፕሬዚደንታዊ የመንግስት መዋቅር የሚታየውን በህግ አውጭ እና አስፈፃሚ መሃከል ያለውን ፍትጊ ከመቀነሱ ባሻገር ለፕሬዚደንቱ የሚሰጠው ስልጣን ስላለ በፓርላማ ብዙ ወንበር ያለው ፓርቲ አምባገነን እንዳይሆን ሚዛን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡በተጨማሪም ፕሬዚደንቷ/ቱ እና ጠቅላይ ሚነስትሩ/ሯ ከአንድ ፓርቲ ላይሆኑ ስለሚችሉ በሃገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጣብቆ የሚገኘውን የመንግስት እና የገዥ ፓርቲ ጥምር አሰራር ተፅዕኖ ይቀንሰዋል፡፡ በከፊል ፕሬዚዳንታዊው የመንግስት ስርዓት የሃገሪቱ ፕሬዚደንት በሁሉም የሃገሪቱ ህዝቦች የምት/የሚመረጥ በመሆኑ በዘውግ ፖለቲካ ለተከፋፈለችው ሃገራችን ዘውግ ዘለል የመሪ ምርጫ ፈለግ ይዞ ስለሚመጣ ለሃገር አንድነት የሚሰጠው ጥቅም ይኖረዋል፡፡

ለ. ህገ-መንግስታዊ ያልሆኑ ችግሮች

  1. የካድሬ ፖለቲካ የባለሙያ አስፈፃሚዎችን ቦታ መተካቱ

ኢህአዴግ ሲመራው በኖረው የሃያ ሰባት አመት የፖለቲካ ታሪካችን የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈፀም አስፈላጊው ነገር ሙያዊ እውቀት እና ልምድ ሳይሆን የፖለቲካ ታማኝነት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተገኝተው ከመናገራቸውም በላይ በተግባር ሲታይ የኖረ ነው፡፡ በዚህሳቢያ ፓርቲው በተደጋጋሚ ብርቱ የማስፈፀም ችግር እንዳለበት ሲገልፅ ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የሃገሪቱ ህዝብ ለረዥም ዘመን በመንግስት አገልግሎት እንዳይረካ አድርጎት ከመኖሩም በላይ በሃገሩ ተስፋ እንዲያጣ እና ስደትን እንዲመርጥ አድረጎት ኖሯል፡፡ከፖለቲካዊ ታማኝነት በቀር ያለ በቂ እውቀት ስልጣን ላይ የተቀመጡ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከማስፈፀም ውስንነትቸው በተጨማሪ ከመንግስት ባለስልጣን የማይጠበቅ ሌብነት ውስጥ የገቡ እንደሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግስት ሌቦች እንዳስቸገሯቸው በተናገሩበት የፓርላማ ውሎ ገልፀው ነበር፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት የማስፈፀም አቅም ደካማነት እና ሌብነት ህዝቡ አሁን የታየውን ለውጥ ለማምጣት እንዲታገል ገፍቶታል፡፡

ሆኖም ከለውጡ በኋላም በህግ ተርጓሚው እና እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ አንዳንድ የዲሞክራሲ ተቋማትን እንዲመሩ ጥቂት ባለሙዎች ከመሾማቸው በዘለለ የመንግስት አስፈፃሚ ክንፍ አሁንም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች እንደተያዘ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ እንዳለችበት ባለ የሽግግር ሁኔታ ባለበት ወቅት በቀድሞው ስርዓት የነበሩ ካድሬዎችን በነበሩበት ማስቀመጥ ሶስት ዋነኛ ጉዳቶች አሉት41፡፡ አንደኛው ስኬታማ ለውጥ ለማድረግ የለውጥ ወቅት በዓለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ጥምር ክንድ የሚመራ አመራር ያስፈልጋል42፡፡ ሁለተኛ በቀድሞው ስርዓት በዋና ዋና ቦታዎች ሲሰሩ ነበሩ ሰዎች ህዝቡን ለለውጥ ባነሳሱ ወንጀሎች ላይ የመሳተፍ ዕድላቸው ከፍ ስለሚል እነሱን በነበሩበት የስልጣን እርከን ላይ የሚያየው ህዝብ የለውጡን እውነተኝነት በመጠራጠር ለሌላ እውነተኛ ለውጥ ለመታከል ሊከጅል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ወደ ሌላ ብጥብጥ እንድታመራ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሶስተኝነት በቀድሞው ስርዓት ያለ እውቀት እና ልምድ በመንግስት ከፍተኛ ስልጣን ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ለውጡ ወንበራቸውን እና ጥቅማቸው ሊያሳጣቸው እንደሚችል አስበው ለለውጠሉ አለመሳካት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚነሱ ግጭቶችን ተከትሎ የቀድሞ ባለስልጣናት መታሰር እና ከስልጣን መነሳት ለለውጡ ቅልበሳ እንደሚሰሩ አመላካች ነው፡፡ስለዚህ ከለውጡ በፊት በፖለቲካ ታማኝነታቸው ብቻ የሲቪልም ሆነ የውትድርና ስልጣን ይዘው የኖሩ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ከስልጣናቸው ተነስተው ስራውን በሚያውቁ ባለሙያዎች መተካት አለባቸው፡፡ በተጨማሪ የሲቪክ ማህበራት(የሙያ፣የወጣቶች፣ የሴቶች..) መሪዎች ካድሬ ባልሆኑ ገለልተኛ ሰዎች መመራት አለባቸው፡፡

በፓርቲ ካድሬዎች እግር የሚተኩት ባለሙያዎች በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የሚገኙ የማንኛውም ፓርቲ ወገንተኝነት የሌላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በውጭ ሃገር የሚገኙ ባለሙያዎች ወደሃገራቸው መጥተው ለተወሰነ ጊዜ ሃገራቸውን የማሻገሩን ስራ በሙያቸው እንዲያግዙ ሃገራዊ ጥሪ ማድረግ ይቻላል፡፡በቀድሞው ስርዓት በብሄራቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ እንዲሰደዱ የተደረጉ ባለሙያዎችን ይቅርታ ጠይቆ በሽግግር ወቅቱ ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ ቢደረግ ይበልጥ ስኬታማ ሽግግር ለማድረግ ይረዳል፡፡

  1. የመንግስት ባለስልጣናት ስለቀደመ ስራቸው ተጠያቂ እየሆኑ ያለበት መንገድ

አምባገነን መንግስታትን የጣለ ህዝብ በወደቀው ስርዓት ለተሰሩ ወንጀሎች እርምት እንዲሰጥ፣ወንጀለኞች ተጠያቂ እንዲሆኑለት፣ለደረሰበት በደል ካሳ እንዲደረግለት ይፈልጋል43፡፡ በሽግግሩ ወቅትም ሆነ ከሽግግር በኋላ ሃገሮች አስተማማኝ ሰላም እንዲኖራቸው ፍትህ እና እውነት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው44፡፡ በሽግግር ወቅት እውነት ተመርኩዞ የሚሰጥ ፍትህ የተጠያቂነትን እና የህግ የበላይነትን ባህል በሃገሪቱ ለማስረፅ ከማገዙም በላይ በቀደመው ስርዓት ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናት ተጠያቂ መደረጋቸው ለአምባገነኑ ስርዓት መፍረስ አስተማማኝ ምልክት ነው45፡፡

ስለዚህ ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረጉ ነገር በከፊል የሚደረግ ከሆነ በቀድሞው አምባገነን ስርዓት መፍረስ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መተማመን በግማሽ ይሆናል፡፡አሁን እንደሚታየው በፍርድቤት መጥሪያ የጣባቸው ወንጀለኛ ባለስልጣናት ከሃገሪቱ ክልሎች በአንዱ መሽገው መቀመጣቸው የለውጡ መንግስት የሃገሪቱን ግዛቶች ሁሉ የማይቆጣጠር ደካማ ነው፤ለውጡም ሊቀለበስ የሚችል ያልፀና ነው የሚል እሳቤ በህዝብ ዘንድ ሊያድር ይችላል፡፡ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ወንጀለኛ እንደሆኑ የሚያውቃቸው የቀድሞ ባለስልጣናት በከፊል ብቻ ተጠያቂ ተደርገው ከፊሎቹ የለውጡን ሃይል ከሚመራው አዲሱ ስርዓት ጋር ሲሰሩ የሚታይ ከሆነ ህዝቡ በለውጡ ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ ሄዶ ቀስበቀስ ወደ ጥርጣሬም ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ ሌላ የትግል ምዕራፍ እንደሚጠብቀው እንዲያስብ አድርጎ ሌላ የብጥብጥ ምዕራፍ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ስለዚህ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረጉ አካሄድ የሚሸፍነው የጊዜ ሁኔታ፣በዋናነት ትኩረት የሚያደርግበት የወንጀል አይነት ሁሉ ግልፅ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ መንግስት የቀድሞ ባለስልጣናትን በሰብዓዊመብት ጥሰት ሲከስ ክሱ በይረርጋ የማይታገድ ስለሆነ ከኢህአዴግ ወደስልጣን መምጣት ጀምሮ በተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ መስሪያ ቤቶችን የመሩ የቀድሞ ባለስልጣና ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡

ሐ. የሽግግር እርምጃዎቹን ለመውሰድ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች እና የቢሆን መፍትሄዎች

ተግዳሮት አንድ፡ ለውጡን የማፅናት/ወደ ታችኛው የመንግስት መዋቅር የማስረግ ችግር

በአሁኑ ወቅት ሃገራችን የጀመረችው የሽግግር ሁኔታ ከላይ የተጠቀሱትን የሃገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሞከረ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ እንኳን ለውጡ ወደታችኛው የመንግስት መዋቅር የሰረገ አይደለም፡፡ይህ ለውጡን ሊቀለብስ የሚችል ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ህገ-መንግስትን ማሻሻልን ጨምሮ በዚህ ፅሁፍ የተነሱ ዋነኛ የፖለቲካ ችግሮች የሚፈታ ሽግግር ለማድረግ ሲሞከር ደግሞ ሽግግሩን በማስረግ እና በማፅናት በኩል የበለጠ ተግዳሮት ሊገጥም እንደሚችል እሙን ነው፡፡ስለዚህ በዚህ ፅሁፍ ላይ ለተነሱ ችግሮች እልባት የሰጠ ሃገር የማሻገር ስራውን በሁሉም ደረጃ ማስረግ የሚያስችል መንገድ መፈለግ አለበት፡፡የለውጡን አላማዎች የሚያስፈም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፣የሲቪክ ማህበራትን፣ታዋቂ ግለሰቦችን፣ከተለያየ የትምህርት መስክ የተውጣጡ ምሁራንን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ማዋቀር ለለውጡ መፅናት እና ለሽግግሩ ስኬት እጅግ አስፈላጊ ነው46፡፡

ይህ ተቋም ለሽግግሩ ስኬት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ለውጡን ለማፅናት፣ሽግግሩን ለማፋጠን ሊያግዙ የሚችሉ ስራዎችን ሁሉ ሊሰራ የሚችልበት ስልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከነዚህ ስልጣኖች ውስጥ በሽግግሩ ወቅት የሚነሱ ብጥብጦችን ምንጭ አጥንቶ፣ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያመጣ መፍትሄ ለመንግስት ማቅረብ አንዱ እና በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊው ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለለውጡ እንቅፋት የሚሆኑ ሃይሎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ፡፡የሃገሪቱ ፖለቲካ ችግር ምንጭ የሆኑ የህግ፣የፖሊሲ ማዕቀፎችን እና ሌሎች የሃገራችን ፖለቲካ ባህል ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች እና መላው ህዝብ በችግሮቹ ምንነት ላይ ከተነጋገረ በኋላ የሚለወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ሌላው የተቋሙ ሃላፊነት ቢሆን ሽግግሩን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ ይረዳል፡፡በዚህ ስራው ተቋሙ የዲሞክራሲ ተቋማትን የመገንባት ስራ ሰራል፣ መከለስ ያለባቸውን ህገ-መንግስታዊ አንቀፆች፣የምርጫ ህጎች፣እየመጣ ያለው ሃገራዊ ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚወስን ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ ውይይቶችን አዘጋጅቶ ብዙሃኑን ያስማማ ሃገራችን ወደዲሞክራሲያዊ ስርዓት የምትሻገርበትን አቅጣጫ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በለውጡ አስፈላጊነት እና ስኬት ላይ ሃገራዊ ውይይቶችን መድረጉ ለለውጡ ከላይ ወደታች ለማስረግ ይረዳል፡፡

አንድ ሃገር ከአምባገነን አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር ስኬታማነት ወታደሩ፣ፖሊሱ እና ሌሎች ህግ አስከባሪ እና አስፈፃሚ አካላት ትልቅ ሚና አላቸው45፡፡ ለውጡን እና ሽግሩን ስኬታማ በማድረጉ ረገድ እነዚህ አካላት ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በለውጡ አስፈላጊነት ላይ በእውቀት ላይ የቆመ እምነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ይህን እውን ለማድረግ ለሽግግሩን ለማፅናት የሚቋቋመው ተቋም በሃገሪቱ ክልሎች ሁሉም ደረጃ ላሚገኑ የህግ አስከባሪ እና አስፈፃሚ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት የሽግግሩ ተባባሪ እንጅ አደናቃፍ እንዳይሆኑ መስራት ይችላል፡፡ በሃገራችን የሚታዩ ብጥብጦች አንዳንዴ በፖሊሶች ጭምር የሚታገዙ እንደሆኑ የቡራዩው ግድያ ተጎጅ ቤተሰቦች እና የዓይን ምስክሮች የገለፁት ነው፡፡ ሃገራችን በዘውግ ፖለቲካ ውስጥ የኖረች እንደመሆኗ እነዚህ ህግ አስከባሪዎች ጭምር በዘውግ ላይ የተመሰረቱ ግድያዎችን እና ብጥብጦችን ለማስቆም ተነሳሽነት ለማሳየት ተቸግረውል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ይህ አመለካከት ከህግ ማስከበር ጋር እንደማይሄድ፣ለሃገርም እጅግ አደገኛ እንደሆነ በዚሁ የተነሳ እንደ ሩዋንዳ ያሉ ሃገሮች የደረሰባቸውን ጥፋት በሚያሳይ ሁኔታ በማስተማር የሚበጀው ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር መስራቱ እንደሆነ ባስተማር ያስፈልጋል፡፡

ተግዳሮት ሁለት፡ የፖለቲካ ሃይሎች በሽግግሩ ሂደት እና ዓላማ ላይ ስምምነት ማጣት

በሃገራችን በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም አሰላለፋቸውን ዘውግ ተኮር እና ዘውግ ዘለል ብሎ ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ ፖለቲካ የሃገራችን ፖለቲካ ሁነኛ ችግር እነዚህ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ሃይሎች ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ለሃገር ህልውና እንከዋን ቢሆን በጋራ የሚሰሩለት አላማ ሊኖር አለመቻሉ ነው፡፡በሃገሪቱ ስር ሰዶ የኖረው ለዘውጉ ጥቅም የሃገሪቱን መፈራረስ ጭምር ታሳቢ የሚያደርገው የዘውግ ፖለቲካ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የዘውግ ፖለቲካን የሚያራምዱ የሃገራችን የፖለቲካ ሃይሎች የህገ-መንግስቱን መከለስም ሆነ የምርጫውን ዘመን መሸጋገር እንደማይስማሙበት ይናገራሉ፡፡ እንዲህ እያሉም ለዲሞክራሲ ስፍነት እንደሚታገሉ ይገልፃሉ፡፡ዘውግ ዘለል የፖለቲካ ሃይሎችም በበኩላቸው ለዲሞክራሲ ስፍነት እንደታገሉ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ሁለቱን በሰፊ የልዩነት ላይ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ሊያገናኝ የሚችል አንድ እና ብቸኛ ለማለት የሚያስደፍር ነጥብ ነው፡፡

ዘውግ ተኮርም ሆነ ዘውግ ዘለል ፓርቲዎች ለዲሞክራሲ እታገላለሁ ካሉ የዲሞክራሲዲሞክራሲ መርሆዎችን የሚጥስ አካሄድን ማበረታታት የለባችም፡፡ ዲሞክራሲ ማግለል መርሁ አይደለም፡፡ የዘውግ ፖለቲከኞች እንዳይቀየር የሚፈልጉት ህገ-መንግስት ደግሞ ከሁለት እና በላይ ዘውግ የተወለዱ እና/ወይም ራሳቸውን በዘውግ ማንነት የማይገልፁትን በርካታ የሃገሪቱን ህዝቦች ከሃገሪቱ ፖለቲካ የሚያገል ብቻ ሳሆን ለመኖራቸውም እውቅና የማይሰጥ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ዲሞክራሲያዊ ሃገር መገንባት እንደሚቻል ለህዝብ ክፍት የሆነ ፣በሚዲያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሃገራዊ ክርክር ማድረግ ያስፈጋል፡፡ ይህ ክርክር የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ ያላቸው አቋም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በጠራ ሁኔታ እንዲታይ ያደርጋል፤ ሃገራችን ለዲሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር ላይ የተጋረጡ እሳቤዎችም እንዲስተካከሉ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የዲሞክራሲ እነዚህ ሁለት ሃይሎች የፖለቲካ አመለካከት ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ዲሞክራሲያዊት ሃገርን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ መተባበር ይችላሉ፡፡

ተግዳሮት ሶስት፡ የካድሬ ፖለቲካን በባለሙያ በመተካት በኩል ያለ ችግር

ኢህአዴግ ፓርቲን እና መንግስትን አዋህዶ ሲያስተዳድር የኖረ ፓርቲ ነው፡፡ወደስልጣን የመጣው የለውጥ ሃይል በተወሰነ ደረጃ ባለሙዎችን ወደ ዋኛ የስልጣን እርከኖች እያመጣ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም ዋነኛ የማስፈፀም ስልጣኖች በተለይ የፌደራል እና የክልል ካቢኔዎች በፓርቲው ካድሬዎች እንደተያዙ ናቸው፡፡ የለውጥ ሃይሉ እነዚህን የስልጣን ቦታዎች በባለሙያዎች ለመተካት የሚያደርገው ጥረት ከፓርቲው ካድሬዎች ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፤ከፓርቲው መስመር መውጣት ተደርጎም ሊታሰብ ይችላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችው አማራጭ በሌለው የለውጥ እና የሽግግር ወቅት እንደሆነ፣የቀድሞው አካሄድ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ሃገር ለመቀጠል የማያስችል እንደሆነ በፓርቲ ደረጃ ተነጋግሮ አቋም መያዝ ያስፈልጋል፡

መደምደሚያ

በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት የምትጓዝበትን መንገድ በሚወስን ታሪካዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት የሽግግር ወቅቶችን ብናሳለፍም ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መጓዝ አልቻልን፡፡የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በሽግግር ወቅት ስልጣን የያዙ መንግስታት ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ማዕቀፍ መፍጠር ስላልቻሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ስልጣን ከያዘው ከመንግስት በኩል ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩ አንፃር በጎ ዝንባሌ ይታያል፡፡ ስለዚህ የሽግግር መንግስት የመመስረት ነገር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ ሃገሪቱን ከአንድ ፓርቲ አምባገነን አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያሻግሩ ስራዎችን መስራት ይቻላል፡፡

ይህን በጎ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሃገሪቱን ለማሻገር በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳር ለዲሞክራሲ ስፍነት ጋሬጣ ሆነው የቆዩ ችግሮችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ/ፌደራሊዝም፣የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ሃገራችን የምትመራበት የመንግስት ስርዓት፣ኢህአዴግ ለሃያ ሰባት አመት ያራመደው የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ሃገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ እንዳትገባ የከለከሉ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡

ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው የጎሳ ፖለቲካው ሃገሪቱ በማንኛውም ሰዓት የምትፈራርስበትን፣ ክልሎቿም በፈለጉት ሰዓት ወደ ብዙ የዘውግ ክልሎች የሚሸነሸኑበትን ሁኔታ ህግ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ ይህ የህዝቦችን አንድነት፣ የሃገርን ህልውና(ሰላም)እንደ ቅድመ-ሁኔታ ለሚፈልገው የዲሞክራሲ አስተዳደር ምስረታ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት በከባድ ዘውግ ተኮር ግጭት እና የሃገር ውስጥ ስደት በመታመስ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ባልተወገደበት ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አይቻልም፡፡

የመሬት ባለቤትነትን ለብሄር ብሄረሰቦች እና መንግስት የሚሰጠው የሃገራችን ህገ-መንግስት ከዘውግ ፌደራሊዝሙ ጋር ሲጣመር ከትውልድ ቦታቸው ወደሌላ ክልል ሄደው በሚሰሩ የሃገራችን ህዝቦች እና በሄዱበት አካባቢ ተወላጆች ዘንድ ዘውግን ያማከለ ግጭት እንዲነሳ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ለኢኮኖሚ እድገትም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡

የፓርላመንታዊ የመንግስት ስርዓት በራሱ ችግር ባይሆንም ሃገራችን ከኖረችበት ዲሞክራሲ የራቀው የፖለቲካ ባህል አንፃር የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ለማስፈን መንገድ ተደርጎ ኖሯል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት የፓርላመንታዊውንም የፕሬዚደንታዊውንም የመንግስት ስርዓት ጠንካራ ጎኖች ለመጠቀም በሚያስችለው በግማሽ ፕሬዚደንታዊ(Quasi-presidential) ስርዓት ሃገራችን እንድትመራ ቢደረግ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ይህ አይነቱ አስተዳደር በዘውግ በተከፋፈለው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባገኘ በአንድ ተመራጭ ፕሬዚደንት ስር እንዲተዳደር በማድረግ የጎሳ ፖለቲካውን ለማርገብ ያስችላል፡፡

ያለንበት የሽግግር ወቅት እውቀት ያላቸውን ዜጎች አስተዋፅኦ የሚሻ ስለሆነ ኢህአዴግ የኖረበት በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሃገር የማስተዳደር ዘይቤ ተቀይሮ በካድሬዎቹ ቦታ እውቀት እና ሰፊ ዓለም አቀፍ/ሃገር አቀፍ ልምድ ባላቸው ሰዎች መተካት አለበት፡፡ በተጨማሪም በቀድሞው አስተዳደር ሁኔታ ወንጀል የሰሩ የመንግስት ባለስልጣናት ያለምንም አድሎ ለህግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ በህዝቡ ዘንድ ለለውጡ እውነተኝነት ማመሳከሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነገር ነው፡፡ የፍድቤት መጥሪያ ወጥቶባቸው እያለ በትግራይ ክልል ተደብቀው የሚገኙ ባለስልጣናት ተይዘው ወደፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ መንግስት የሃገሪቱን ክልሎች ሁሉ ማስተዳደር የማይችል ተደርጎ ሊወሰድና ሌላ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጡን ሆነ ሽግግሩን ይጎዳል፡፡

እነዚህን ችግሮች መርምሮ በቀጣይ ዘመናት በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ህልውና እንዳይኖራቸው ማድረግ በአሁኑ ወቅት ለሃገራችን ሽግግር የሚያስፈልግ ዋነኛ ስራ ነው፡፡ችግሮቹን አቃሎ ወይም ፈትቶ በሚቀጥለው ምርጫ ወደስልጣን ለሚመጣው መንግስት ለዲሞክራሲ መንገድ የጠረገች ሃገር ማስረከብ ከተቻለ የሚመጣው መንግስት ስራ ዲሞክራሲ ስር እንዲሰድ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት እና ሃሪቱን ከድህነት የሚያወጡ ፖሊሲዎችን መተግበር ይሆናል፡፡ ይህ ሃገሪቱ ከአምባገነንነት አዙሪት ወጥታ ወደ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባሕል ግንባታ እንድትገባ ያስችላታል፡፡

ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ሃገራችን ያላት ብቸኛ መንገድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መመስረት ብቻ እንደሆነ በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች እና በህዝቡ ዘንድ መስማማት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ስምምነቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር ችግር የሆኑ ታሪካዊ፣ህገ-መንግስታዊ እና የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ እና አስተዳደር ባህል እንዲቀየሩ ማስቻል አለበት፡፡ይህን ለማድረግ የሽግግሩን/ለውጡን የሚያስፈፅም ሃገራዊ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ተቋሙ የተልዕኮውን ትልቅነት የሚመጥን ስልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡የለውጡን አላማ በሁሉም ደረጃ ማስረፅ፣በሃገራችን ዲሞክራሲን ለመገንባት ደንቃራ በሆኑ ችግሮች ላይ ሃገራዊ ውይይት አድርጎ እንዲለወጡ መስራት፣ የለውጡን ተግዳሮቶች ተከታትሎ ማስወገድ፣የምርጫ ህጎችን ማሻሻል፣የሃገራችን ቀጣይ ምርጫ መደረግ ያለበትን ቀን ለመወሰን የሚያስችል ሃገራዊ ውይይት ማካሄድ ከስልጣኖቸ መካከል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዚህ ተቋም ከነዚህ ስልጣኖች ጋር መምጣት አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአንድ በኩል በርካታ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ችግር ያለባትን ሃገር በመምራት በሌላ በኩል ለውጡን በመምራት እና የሃገሪቱን ሽግግር በማፅናት ሁለት ትልልቅ ሚናዎች ከመወጠር ይታደገዋል፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

End notes

1 Crisis Group, Ethiopia: Ethnic Federalism and its Discontents, Africa Report No 153, November 4, 2009,Nirobi/Brussels, P.29 ; African Studies Center, Political Culture in Ethiopia: A balance sheet of post 1991 ethnically based Federalism, Info sheet, April 8,2010, p.3-4

2 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.167;

3 Geddes, et al, Autocratic Breakdown and regime transition; perspective on politics,2014, p. 37

4 lowenthal and Bitar, From Authoritarian rule to democratic governance: Learning from political leaders, Stockholm,2015, P.50-53

5 Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, Berghof Handbook dialogue, 2006, p. 4

6 Ibid,P.5-7

7 Alem Habtu, Multiethnic Federalism in Ethiopia: A study of the secession clauses in the constitution, Queens college,2005, p.11-23; John Young, Regionalism and democracy in Ethiopia, Third world quarterly, vol 19፣ No 2, p. 195-203; ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ገፅ. 253-259;Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014,p.78-82; African Studies Center,P.1-2;

8 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 256

9 Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, 2006, p. 4 and 5

10 Ibid, p.10

11 Anna Louise, Factors Affecting Success or Failure of Political transitions, Helpdesk Report, 2017, p.6-8

12 Gracia, Addressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, 2006, p.2-9

13 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 249፤ Crisis Group, Ethiopia: Ethnic Federalism and its Discontents, Africa Report No 153, November 4, 2009, p.3-4

14 Ibid, p.249-53; African Studies Center, Political Culture in Ethiopia: A balance sheet of post 1991 ethnically based Federalism, Info sheet, April 8,2010, p.1-3

15 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 250

16 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.25

17 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ.258፤

18 Ibid, p. 258-260፤ Alem Habtu, Multiethnic Federalism in Ethiopia: A study of the secession clauses in the constitution, Queens college,2005, p.319

19 የኢትዮጵያ ህገመንግስት፣ 1995፣ አንቀፅ 47፣ ንዑስ ቁጥር 3፣ ከ “ሀ” – “ሠ”

20 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.156

21 Ibid

22ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 258-259

23 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.155

24 Ibid,165-187

25 Yash Ghai, Autonomy and Ethnicity: Negotiating competing clams in multi-ethnic states, Cambridge University Press,2000,p.11 ; Murat Somer, Cascade of ethnic polarization: Lessons from Yugoslavia, annals of the American academy of political and social science,Vol.573,Sage Publication,2001,p.128-129; ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 254-255

26 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.165-168

27 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 252

28 Wibke Crewett et.al, Land Tenure in Ethiopia: Continuity and Change, Shifting Rulers, and the Quest for State Control, CGIAR System wide Program on Collective Action and Property Rights (CAPRi), C/- International Food Policy Research Institute, Working Paper No. 91,2008, pp.5-19

29 Daniel Ambaye, Land Rights Expropriation, Stockholm, Springer publication, 2015, p.29

30 Belay Zerga, Land Resources, Uses and Ownership in Ethiopia : Past, present and Future, International Journal of Scientific research and engineering Trends, V.2,Issue 1, 2016, P.19

31 Desalegn Rahmato, Searching for tenure security?: The land system and new policy initiatives in Ethiopia, FSS Discussion paper, 2000, p.2

32 USAID/Ethiopia, Ethiopia Land Policy and Administration Assesment,Report,2004, P.ix

33 Desalegn Rahmato, Searching for tenure security?: the land system and new policy initiatives in Ethiopia, FSS Discussion paper, 2000, p.4

34 Belay Zerga, Land Resources, Uses and Ownership in Ethiopia : Past, present and Future, International Journal of Scientific research and engineering Trends, V.2,Issue 1, 2016, P.20 and 22

35 Ibid, P.20

36 የኢትዮጵያ ህገመንግስት፣1987፣ አንቀፅ ….

37Kaare Strøm et.al, Delegation and Accountability in Parliamentary Democracies, Oxford University press, 2006, P. 3-8

38 Scott Mainwaring, presedentialism, multiparty systems, and democracy: the difficult equation, University of Notre Dame, working paper #144, 1990 p.3

39 José A. Cheibub, Presidentialism, Parliamentarism, and Democracy, University of Illinois Cambridge University Press,2007, p.2

40 Scott Mainwaring, presedentialism, multiparty systems, and democracy: the difficult equation, University of Notre Dame, working paper #144, 1990 p.6

41 Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, Berghof Handbook dialogue, 2006, p. 4

42 Ibid, P.5

43 Sanam Naraghi et.al, Transitional Justice and Reconciliation, A toolkit for advocacy and action, 2007,p.1

44 Julie Macfarlane, working towards restorative justice in Ethiopia, cardozo j. of conflict resolution ,2007,vol. p.487.

45 Sanam Naraghi et.al, Transitional Justice and Reconciliation, A toolkit for advocacy and action, 2007,P.2-3

46 Sarsar,M.C, Tunisia: Revolution as a new form of political transition persuasion, Italian Institute of International Political studies, Analysis N.o 194, 2013,p.3-4

47 Awad, Breaking out of Authoritarianism: 18 months of political transition in Egypt, Constellations, 2013, p.289

One thought on “ያለሽግግር መንግስት ሀገርን ማሻገር – ለቪዥን ኢትዮጵያ የቀረበ ጥናታዊ ፅሁፍ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡