ኢትዮጵያ: የገዥ ሀሳብ ትርክት መክሰምና አደጋዎቹ!

በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ባለፉት አስርታት በግልፅ ወደ አደባባይ ወጥተውና በተለያዩ የሀሳብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች ይኸውም በዘመን አመጣሾቹ ማህበራዊ ድህረ ገፇችም (social medias) ይሁን በዋናዎቹ ሚዲያዎች (mainstream medias) በአብዛኛው ጎልተው የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች የትኞቹ ነበሩ ብለን ስንገመግም ፅንፈኛ ወይም የአንድን ወገን ብሶት ብቻ የሚያቀነቅን አስተሳሰብን የሚያንፀባርቁ ሆነው እናገኛቸዋለን:: ይኸውም “የተማረ” ወይም “የተመራመረ” የሚባለው ኢትዮጵያዊ የሚያናፍሰው ትርክት በአብዛኛው ከብሶት በመነጨ ዝንባሌ ‘የኔ ብሔር በዚህ ረገድ ተጨቁኗል በዚያ መልኩ ተበድሏል’ የሚል ይዘት ያለው ነው:: ከዚህ በተረፈ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደፊት ሊያራምዳት የሚችልና በሀሳብ ልዕልና ሚዛን ሲለካ ሚዛን የሚደፋ ወይም በእሳት እንደሚፈተን ወርቅ የጊዜን ፈተና የሚያልፍ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሀሳብ ሆኖ አይገኝም::

ይኽ ለምን ሆነ ብለን የጠየቅን እንደሆነ ደግሞ በአብዛኛው የነዚህ ሀሳቦቾ መተንፈሻና ለህዝብ ማድረሻ መድረኮች ወይም ሚዲያዎች እንዲያስተናግዱ ይፈቀድ የነበረው በቅድምያ በሀገሪቱ ስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት የማያሳጣ ሀሳብ ነው:: ሲቀጥል ደግሞ የዛኑ ስርዖት አስተሳሰቦች የሚደግፍና የሚያጠናክር ሀሳብ ብቻ እንዲሆን ግድ ይል ስለነበር ነው:: ይህ ሂደት በረጅም የግዜ ድግግሞሽ የተሳሳተ ትርክት እንኳ በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ትክክለኛው ትርክት ሆኖ ከፍተኛ ቅቡልነት እንዲኖረው ያደርገዋል::

የገዥ ሀሳብ ትርክቶች መሠረታዊ የስርፀት ሂደት

በማንኛውም ‘የተማረ’ (educated) የሚባል ማህበረሰብ ውስጥ አንድን እሳቤ እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ቢያንስ ከማህበረሰቡ ነባራዊ እውነታ አንፃርና ከሀሳቡ ወቅታዊ ፋይዳ አንፃር ጥያቄ መጠየቅ ወይም ሀሳቡን እንደ ሀሳብ መሞገት የተለመደ ባህል ነው:: ሲልቅ ደግሞ አማራጭ ወይም የተሻለ የሚባል ሌላ አቻ ሀሳብን በማቅረብ መሞገት ደግሞ ‘የሰለጠነ’ (civilized) የሚባል ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ነው:: እነዚህም አካሄዶች ለአንድ ሀሳብ ቅቡልነት አስፈላጊ የማወዳደሪያ ወይም የመመዘኛ መንገዶች ተደርገው ይታያሉ::

በማህበረሰቡም ውስጥ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ነጥሮ የወጣ ሀሳብ ነው እውቅና የሚሰጠው:: በዚህ መልኩ በጥቂት ልሂቃን (elites) ተመንጭቶ በብዙሀን አዋቂዎች ተተችቶ በዘመን ጠገብና ሀገር በቀልም ሆነ በተውሶ ተወስደው በጎለበቱ እውቀቶች የሀሳቡ ጥራት ይመዘናል:: በዚህ ሂደት ተመዝኖና ግዜውን የጠበቀ ሀሳብ መሆኑ እንዲሁም በግዜው ካለ የማህበረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ: የሀሳቡ ቅቡልነትም ሆነ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት አንፃር ይፈተሻል:: ይህ በሀገር በቀልም ሆነ በተውሶ ተወስደው በጎለበቱ ጥበቦች (wisdom) ተፈትሾ ገዥ ሀሳብ ሆኖ ያለፈ ሀሳብ በሰፊው ህዝብ ዘንድ እንዲንሸራሸርና የዚያ ማህበረተሰብ የግዜው ትርክት አካል እዲሆን ይደረጋል::

ይህ አካሄድ እንደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት የሆኑት ግሪኮች ባህላቸው ነበር:: ለዚህም ነው ግሪኮቹ በአውሮጳ የሰለጠነ አስተሳሰብ ቁንጮ የነበሩት:: ሲቀጥልም ለምዕራቡ አለምም ሆነ ለአለማችን በአጠቃላይ: ዛሬ ላይ አውሮጳዊያኑ የሚመፃደቁበትን የሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብንና የመንግስት አስተዳደርን ያበረከቱት እነሱ ናቸው:: ከሞላ ጎደል በዚህ ሂደት ነው እንግዲህ በአውሮጳና በምዕራቡ አለም በገዥ ሀሳብ የሚያምንና በአንፃራዊነትም ቢሆን እኩልነት ያለው (egalitarian) ህብረተሰብና በዲሞክራሲያዊ የህዝብ አስተዳደር የሚመራ የሰለጠነ ማህበረተሰብ ሊፈጠር የቻለው::

የማህበራዊ ለውጥ መምጣት ታሪካዊ ተግዳሮቶች

የሀገራችንን ታሪካዊ እውነታዎችና ተፈጥረው የነበሩ የማህበራዊ ለውጦች ተግዳሮቶችን ስንቃኝ በመጀመሪያ ማህበረሰቡ በአብዛኛው ሀይማኖተኛ ማህበረሰብ ነው:: ይህ ከመሆኑ አንፃር ባለፉት ዘመናት (በተለይም እስከ ሀያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ) ቤተ-ክህነትና የመንግስት አስተዳደር (the Church and the State) በግልፅ የተለየና ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ የተፅዕኖ ክልል (Sphere of influence) አልነበራቸውም:: እንግዲህ ይህ ባለመኖሩ የተነሳ የማህበረሰባችን የኑሮ ዘይቤ ቅኝትም ሆነ የፖለቲካ ማህበረተሰቡ ትርክት በተፈለገው ደረጃ ሳያድግ ቆይቷል:: አንድም የነዚህ ሁለት ግዙፍ ግን በግልፅ ሊነጣጠሉ ያልቻሉ አካላት (entities) የእርስ በርስ መጠላለፍ ሌላም በሀገራችን ተራማጅ ህብረተሰብ (progressive society) ከነበረውው ዝቅተኛ ቅቡልነት የተነሳ ማህበራዊ አብዮት (social revolution) ብዙም ሳናስተናግን ለረጅም ግዜ ቆይቷል::

ከዚህ ባሻገር በእያንዳንዱ መሠረታዊ ማህበራዊ አብዮት መሀል ያለው ግዜ መርዘም የማህበረተሰብ የለውጥ ፍጥነቱ አዝጋሚ እንዲሆን አድርጎታል:: ይህ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገራችን የአለማችን ቀደምት ስልጣኔ ምንጭ እንዳልነበረች አሁን ወደምንገኝበት የኋላ ቀር ሀገሮች ተርታ ልትሰለፍ ችላለች:: ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው እነ ደቡብ ኮሪያ: ሲንጋፖርና ቻይና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሀገራት የዛሬ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በኢኮኖሚም ሆነ በስልጣኔ በእጅጉ የምንበልጣቸው የነበሩ ሀገሮች መሆናቸው ነው::

ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ህበረተሰብ የመፍጠር የመከኑ እድሎች

ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ማለትም ከንጉሳዊው አገዛዝ መክሰም ጀምሮ የተከሰቱ ሁለት የፖለቲካ አብዮቶችን ነበሩ:: ይኸንንም ተከትሎ የተፈጠሩት የማህበራዊ አብዮቶች ወደ ትክክለኛውና በገዥ ሀሳቦች ላይ ወደተመሰረቱ የፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ ቅኝቶች የመግባት እድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የመከኑ እድሎች (missed opportunities) ሆነው አልፈዋል::

ለዚህም እንደምክንያት ሊወሰዱ ከሚችሉት ለምሳሌ በደርግ አብዮት ወቅት አብዮቱ ከጅምሩ በኮሚኒስት ርዕዮት ስም በውጭ ሀይሎች መጠለፉ (the hijacking of the revolution by foreign actors in the name of communist ideology from its inception on) አንዱ ነው:: በቀጠለው አብዮት ወቅት ደግሞ ያው የቀደመውና በተሳሳተ መስመር ላይ የነበረው የፖለቲካ ስርዓት የስከተለው ሀገራዊ የብሔር ጭቆና ቀውስ የወለደው ብሶት የፈጠረው ፅንፈኛና ብሔር ተኮር የፓለቲካ ስርዓት በቀጣይነት ትክክለኛ (justified) የፖለቲካ መስመር ተደርጎ መወሰዱ ነው::

በሁለቱም አጋጣሚ በግዜው የፖለቲካውን ምህዳር ዘዋሪ የነበሩ ‘ምሁራን’ የአስተሳሰባቸው ቅኝት የተዛባ ከመሆኑ የተነሳ ከተሳሳተ ትርክት ወደ ሌላ የተሳሳተ ትርክት መሸጋገራቸው የመጀመሪያው ስህተት ነበር:: ሲቀጥልም አፍራሽ የፓለቲካ መስመር (deconstructive politics) እንደ ትክክለኛ የፖለቲካው ባህል መያዙ ተራማጅ በሆነ አስተሳሰብ ወደ ገዥ የሀሳብ ፖለቲካ መስመር እንደ ሀገር እንዳይገባ እንቅፋት ሆኖ አልፏል::

ነባራዊና ማህበራዊ ትርክቱን የመቀየር እንቅፋቶች

አሁን ላይ ሀገሪቱ ውስጥ አሳሳቢና ነባራዊ ስጋት ሆኖ የሚገኘው ነገር ይህ ትውልድ ለሶስት አስርታት ያክል በብሔር ተኮር የፖለቲካና ማህበራዊ እሴቶች ትርክት ሲቃኝ ያደገ ትውልድ መሆኑ ሲሆን ይህም ቀጣዩን ግዜ ፈተና የበዛበት ያደርገዋል:: አሁን በቡድን ለዛውም በብሔር ማንነት ላይ ብቻ በተመሰረተ መንጋ የሚያስብ እንጂ በሀሳብ ልዕልና ላይ በተመሰረተ ተራማጅ አስተሳሰብ የሚመራ ትውልድ የሌለበት ግዜ ነው:: ጥቂት ቢኖር እንኳ በአብዛኛው ተቀባይነት የሚኖረው የመንጋው አስተሳሰብ ስለሆነ መንጭቆ በመውጣት ፋይዳ ያለው የአስተሳሰብ መስመር ለመፍጠርም ሆነ ያለውን ትርክት ለመቀየር ጉልበት አይኖረውም::

የሀሳብ ፖለቲካ መጥፋትና የፈጠራቸው ስጋቶች

በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ መንግስታት በተፈራረቁባቸው ዘመናት የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮቶች ሲንፀባረቁ ቆይቷል:: ይህ እንደመሆኑ መሰረታቸውም የዚያኑ ያህል ይለያያል:: ሆኖም በየዘመናቱ የተነሱት የፓለቲካ ስርዓቶች በጊዜው በአብላጫው የሀይል ሚዛን በደፋው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ርዕዮት ወይንም የፓለቲካ መስመር ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ እንጅ በተወዳዳሪ የሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ አልታዩም::

አለመታደል ሆኖብን ደግሞ የተረጋጋና በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ሁሉንም ባይሆን አብዛኛውን የሀገሪቱን ማህበረሰብ ያማከለ የፖለቲካ ምህዳር ኖሮን አያውቅም:: በገዥ አስተሳሰብና ተራማጅ በሆኑ አመክንዮች ላይ የተመሰረተ የሀሳብ ፖለቲካ በሀገራችን ሁሌም በጥርጣሬ የሚታይ ነው:: ከዚህ በተረፈም በሀገሪቱ ባለው አብዛኛው የፖለቲካ ማህበረሰብ ዘንድም ተመራጭ አቅጣጫ ሆኖ የማይታይ ጉዳይ ነው:: በእርግጥ ይህ ችግር ለኢትዮጵያ ብቻ የተለየ መገለጫ የሆነ ነገር አይደለም:: ይልቁንም በየትኛውም ያላደገ ሀገር እንደተለመደ የማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤ (norm) የሚቆጠር ነው::

የብሔር ፖለቲካና ያስከተላቸው ተግዳሮቶች

በተፈጥሮው ብሔር-ተኮር ወይም የማንነት ፖለቲካ (identity politics) ምንጩ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በተፈፀሙ ጭቆናዎች ምክንያት የሚፈጠር ብሶት ነው:: ይህ ማህበረሰባዊ ብሶት የሚወልደው የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚስባቸው ውሱን የህብረተሰብ ክፍሎችን ነው:: እነዚህም ዝቅተኛ የአስተሳብ ደረጃ ላይ ያለን የህብረተሰብ ክፍልና የአመክንዮ አስተሳሰብን ያላደረጀና በአብዛኛው ስሜታዊነት የሚያጠቃውን ለጋ ወጣት ነው:: በአጠቃላይም ዝቅተኛ የኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ የህብረተሰብ ክፍልን ነው:: ይህም በአብዛኛው የሚማከለው የተፈጠረው የኢኮኖሚ እኩልነት አለመኖር (economic inequality) የሚወክለው ብሔር ስለተጨቆነ እንጂ (እውነታው ይህ ሆነም አልሆነም) እራሱ በህይወት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ወደ አዎንታዊ እድሎችን መቀየር ስላልቻለ እንደሆነ አገናዝቦ ሊቀበል የማይችለውን ነው::

ስለዚህ በዚህ ነባራዊ እውነታ ውስጥ ባለ ሀገርና ማህበረሰብ ውስጥ ማህበራዊ: ሀይማኖታዊም ሆነ እንደ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከሎች ያሉ ሀገራዊ ተቋማት (secular institutions) በአመክንዮ ላይ ያልተመሰረተና በጎጠኛ አስተሳሰብ ያልተቃኘ: የመንጋ ሀሳብ በነፈሰበት የማይነፍስ: በሀሳብ ልዕልና (superior idea) ትርክት የሚያምን እንዲሁም ሂሳዊ አስተሳሰብን (critical thinking) ያጎለበተ ትውልድን ለመፍጠር ከምን ግዜውም በላይ ወጣቱ ትውልድ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል::

ለገዥ ሀሳብ ትርክት መክሰም የምሁራን አስተዋፅኦ

ባለፉት ስርዓቶች የዜጎች የዕውቀት መሸመቻና የልቀት ማዕከል የሆኑት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ አለመሆን ለገዥ ሀሳብ ትርክት መክሰም ዋንኛው ምክንያት ነው:: ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመንግስት ወይንም ስልጣን ላይ ያለም ይሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲ መጫወቻ ሜዳነት በፀዳ መልኩ አለመተዳደራቸው የሀገሪቱ ምሁራን በነፃነት አመክንዮ ላይ የተመሰረተና በገዥ ሀሳብ የበላይነት ላይ ባተኮረ ማህበራዊ ቅኝት ወጣቱን ትውልድ እዳይቀርፁ አደገኛ እክል ሆኖ ቆይቷል::

በመሰረቱ የተማረውና በሀሳብ ፍጭት ወደ ላቀ አመክንዯዊ አስተሳሰብ በመሸጋገር ማህበራዊ ስልጣኔን በሀገር በቀል እውቀትና ብልሀት (indigenous local knowledge and wisdom) ታግዞ ወደ ህብረተሰቡ የማስረፅ ሀገራዊ ግዴታ እና ሀላፊነት እንዳለበት የሚታወቅ ነው:: ሆኖም ይህ ሀገራዊ ሀላፊነት ያለበት ምሁር ከፖለቲካውም ሆነ ለህዝብ ተደራሽነት ካላቸው መገናኛ ብዙሀን እራሱን በማግለሉ ምክንያት በአብዛኛው ያልተማረው የህብረተሰብ ክፍል አሉታዊ ይዘት ላላቸውና በጥቂት ጥራዝ ነጠቅና በግል ጥቅም በሚነዱ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለሚቀነቀኑ አፍራሽ ትርክቶች ተጋላጭ ሊሆን ችሏል:: ስለዚህ የሀገራችን ምሁር ቢገባውም ባይገባውም ሳይማር ያስተማረውን ሆደ ሰፊ ህዝብ እዳ የበላ: ማህፀንዋ ሳይደርቅ ሀገሩን ልጅ አልባ መካን ያደረገ የተማረ መሀይም ነው::

ቀጣይ ሀገራዊ እድሎችና አስፈላጊ ጥንቃቄዎች

ከዚህ በኋላ እንደ ሀገር የመዝለቅ እድል በአግባቡ ለመጠቀም እያንዳንዱ የተማረ ዜጋ ህብረተሰቡ ውስጥ በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ ገዥ ሀሳብ ማህበራዊ ትርክትን የማስረፅ ግዜ የማያስቀጥር ሀገራዊ ሀላፊነቱን መወጣት ግድ ይለዋል:: መንግስትም ቢሆን ከብሔር ተኮር የፖለቲካ ትርክት በመውጣት ሀገራዊ ተቋማትንና መገናኛ ብዙሀንን የነፃና ጤነኛ አስተሳሰቦች መንሸራሸሪያ የማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነት አለበት::

እንደ ሀገር ታላቅ ሀገር ሆኖ የመቆየቱ ሚስጥር በብሔር ተኮርና ጎጠኛ አስተሳሰቦች ሳይከፋፈሉ አንድነትንና ሀገራዊ ህብረትን በማንኛውም መንገድ በማስጠበቅ (maintaing national unity and coexistance by all means) መቀጠል ብቻ ነው:: በርግጥም ያኔ እንደ ሀገር እንደገና ታላቅ ሀገር የምንሆንበት እድል እየተፈጠርልን ይሄዳል:: ለዚህ ሀገራዊ ትልም እንቅፋት የሚሆን ነባራዊ አደጋ እውነታ (the truth of a present and imminent threat) ጥሩ ማሳያ የሚሆኑን እስከ ቅርብ አመታት ድረስ ከኢትዮጵያ ባልተናነሰ የረጅም ዘመን የታላቅነት ታሪክ ያላቸው ዛሬ ላይ ግን በእርስ በርስ ጦርነት ፈራርሰው ህዝባቸው አለም ላይ እንደ አሸዋ በስደተኝነት በየሀገሩ ተበትኖ የሚገኙት እንደ ሶሪያ ያሉ ታላላቅ ሀገራት ናቸው:: ይኽን ከመሰለ መንገድ ደግሞ የኢትዮጵያ አምላክ ሀገራችንን ይሰውርልን እኛም ሳንዘናጋ ግዴታችንን እንወጣ:: ቸር እንሰንብት::

One thought on “ኢትዮጵያ: የገዥ ሀሳብ ትርክት መክሰምና አደጋዎቹ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡