መከላከያው፣ እና እዳው…”ትዕግስቱ” እና ፖለቲካዊ ቅሸባ! 

 

በአሜሪካን ሀገር የሕግ አስከባሪ  ተቋማት  [law enforcement agencies] የሚደነቁበት እና ለሥራቸው ክብርና ምስጋና የሚቸርበት ብሔራዊ ቀን አለ። እሱም የኛው ትራጄዲ የተፈጸመበት ዕለት  January 09 ነው፣ በየዓመቱ።  መከላከያው፣ ፖሊሱ እና የደኅንነት አካላቱ ገለልተኛ የሕዝብ አገልጋይ፣ የሕግ እና የፍትሕ አካላት ተደርገው ይወሰዳሉና። 

እንዳለመታደል ሆኖ እኛ ሀገር በዚህ ደረጃ ያደገ የዴሞክራሲ ባሕል ስለሌለን መከላከያው፣ ፖሊሱ እና የደኅንነት አካላቱ እንዲሁም ገከልተኛ እንዲሆኑ የሚጠበቁ ተቋማት እንደሚፈለገው አልሆኑም። 

የሕዝብ አመፁ አዲሱን የአብይ መንግሥት አመራር [ቡድን] ወደ ሥልጠን ሲያመጣ ከዚያም በብዙ መልኩ ሪፎርም ያሻቸዋል ከተባሉት ተቋማት አንዱ ነበር። መከላከያ። እጅግ አስፈላጊ እና ገለተኝነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባት የሌላባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነውና። የሀገር ልጅ ስብስብ ነው። የሀገር ኩራት ነው። የሉዓላዊነት የመጨረሻው ዋስትና ነው[Structurally speaking ማለቴ ነው]። 

 ጠ/ሚ አብይ አህመድም በሪፎርም አጀንዳቸው በፍጥነት እየሄዱበት ካሉ ተቋማት አንዱ ነው። የሁላችንም ወገን እንዲሆን እንፈልጋለንና! እኔ በበኩሌ ልጄም ቢሆን “የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል” ሲባል ኩራት እና አለኝተነት እንዲሰማን፣ እዚያ ውስጥ ማገልገል በደስታ እንዲሆን እመኛለሁ። ያ ሥራ ተሠርቶ አላለቀም። 

ጄነራል ብርሐኑ ጁላ፥ የኢፌዴሪ መከላከያ ኃይል ምክትል ኢታማዦር ሹም እና የወታደራዊ ኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ

ሰሞኑን በምዕራብ ጎንደር ገንደ ውሃ እና ኮኪት የተፈጸመው ግድያ እጅግ የሚያሳዝን፣ ልብ የሚሰብር እና የሚያስቆጭ ነው። በዚህ አለማዘን አይቻልም። በነገራችን ላይ  ገንደ ውሃን ያለፈው ሠራዊት ኮኪት ላይ በጠበቁት እና ባጠቁት ሰዎች ከመከላከያም ሰው ሞቷል። ያም ወገን ነው።

በቅርቡም በምዕራብ ጉጂ 23 ሲቪሊያን፣ በነቀምቴ (ጎንደር ነው ተብሎ የሚዞረው ዘግናኝ ፎቶ እዚያ ነው)ሲሞቱ፣ ትላንት በኮንሶ ሰው ቆስሏል። ይሄንን የምናገረው “እነዚያን ይታገሳል…እነዚህን ያጠቃል” የሚል ዝንባሌ ያላቸው ነገሮችን ስላየሁ ነው። ሞያሌ በተቀሰቀሰው ግጭት በለጠ ሞላ በተባለው ሆቴል ውስጥ ድርድር/ስብሰባ ላይ በነበሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ በተከፈተ ተኩስ 12 ሰው በአንድ ጊዜ ሞቷል። በምዕራብ ኦሮሚያ ከኦነግ ጋር በሚደረገው ውጊያ ሳቢያ የሚሞቱ ንፅሃን ዜጎች በየቀኑ እየሰማን ነው። መከላከያ በነ እንትና ክልል እዮብ ይሆናል፣ እነ እንትናን ይገድላል የሚል ነገር ስላየሁ ነው። የሚያሳዝነው ነገር “ነፃ ሚዲያ” የሚባሉት እነ BBC AMHARIC ጨምሮ ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው ዘገባ ሲየቀርቡ መታየታቸው ነው።  በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚሠራ ፖለቲካዊ ንትርክ ለማንም ይበጃል ብዬ አላስብም። 

በመሠረቱ ማንም መሞት የለበትም። በተለይ ድሃው ሲቪሊያን ለምን ይሙት? የሲቪሊያን ዜጋን ሞት justify የሚያረግ ምክንያት የለም። መከላከያ በዘላምበሳ እና በሽሬ ያሳየው ትዕግስት ሊደነቅ ይገባል። የወጣቱ ጥያቄን በአላስፈላጊ ሰፈጣ እና ግርግር መልክ ማቅረብ ግን ተገቢ አይደለም።  በተሳሳተ መረጃም ቢሆን ሌላው ሕዝብ በንደዚያ ሁኔታ ተመሳሳይ ድርጊት መድገም አለበት ብዬ አላስብም። አንድ ግልፅ እንዲሆን የምፈልገው ግን መከላከያ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው የሚል ሀሳብ እንደሌለኝ ነው። እሱ በሌላ አካል ተጣርቶ ይቅረብ። ከዚህ በፊትም ተናግራለሁ። 

ለሕዝብ በደረሰ የተሳሳተ መረጃ ሱር ኮንስትራክሽን መኪኖች የጦር መሣሪያን ይዞ ወደ ሌላ ክልል እየሄደ ነው በሚል የተነሳው ግጭት ነው ምክንያቱ። ይሄ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎች ሀገራችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል። በ’ንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎች ሰው ተዘቅዝቆ ሞቷል፣ የቆሎ ተማሪ በቤተ ክርስቲያን ተደብድቦ ተገድሏል፣ ለምርምር የሄዱ ዶክተራል ተማሪዎች ተገድሏል፣ መኪኖች ተቃጥሏል፣ ንብረት ወድሟል። አሁን በዚህ ላይ መሥራት ያለብን ይመስለኛል።  

 የፍላጎት ልዩነት እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠላትነት አለ ብዬ አላስብም። ባንድ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እና ተቋማዊ መልክ ይዞ የሚደረግ ጭቆና አለ ብዬ አላምንም። አድልዎች የሉም አላልኩም። 

ማጠቃለያ

፩. ድርጊቱ ዘግናኝ ነው። በተገቢው የሕግ አካል ተጣርቶ ፍትሕ እንዲገኝ ምኞቴ ነው። ከተጎዱት እግዚአዝሔር ይማራቸው። ቤተሰብ ያጡት እሱ ያፅናናቸው። ፍትሕም ይስጣቸው!

፪. መከላከያ ያን ክልል ታግሶ ያንን ደግሞ ያጠቃል የሚለው ከባድ ነው። ወደፊትም ጠቃሚ ነው ብዬ አሳስብም። መከላከያ ሪፎርሙ አልቆ ሕዝባዊ ቁመና ይኖረው ዘንድ ሁላችንም የየራሳችንን ድርሻ እንወጣ። 

፫. የሀሰት ወሬ እያሰራጩ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ  እና የትላንቱንም ወሬ ያሰራጩ እና ይሄንን ከባድ ትራጄዲ ያስከተሉ ሰዎች ዛሬ ተነሥተው ተቆርቋሪ መሆናቸው እጅግ የሚቀፍ ነው። ነጋዴዎች ናቸው፣ የፖለቲካ ነጋዴዎች። በሰው ደም ተረማምደው ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ዕዳዎች ናቸው። ይህ በክልል፣ በብሔረሰብ (ethnicity) የተገደበ አይደለም። ሁሉም ውስጥ አሉ። እነዙህ ሰዎች አደብ ሊገዙ ይገባል። ዘግናኝ የሟች ሬሳን ከ”ተዋሱበት” ክልል ውስጥ ምንም እንዳልፈጠረ አድርገው ይልቁንም ጨቋኝ “ባለጊዜ” ለማድረግ መሞከራቸው እጀግ ሲበዛ subhuman ያረጋቸዋል። ዕዳዎቻችን ናቸው። 

፬. መከላከያን እና ሌላን ሀገራዊ ተቋም attack ማድረግ እና ሥም ማጥፋት ዞሮ ዞሮ ሀገሪቷን ነው የሚጎዳው። የወያኔ መንግሥት ምሥረታ ስህተቶች አንዱ የቀድሞውን መከላከያ በጠላትነት ፈርጆ [“የደርግ ወታደር” የሚል ሥም በመስጠት] ማፍረሱ ነው። ይህ ሊሆን አይገባም።  ለምሳሌ “የኢሕኤዴግ ወታደር”፣ “የወያኔ ወታደር” ፣ አሁን አሁን ደግሞ “የኦዲፒ ወታደር”፣ “የአብይ ወታደር” ብሎ መጥራት ለሕዝቡ ጥቅሙ ምንድነው? እዚያ ልጁን የላከው ድሃው አባት ምን ይሰማው? ለወታደር ሞራልስ ጥሩ ነው ወይ? አስፈላጊው ሪፎርም እና እንዶክትሪኔሽን ተካሂዶ መንግሥታዊ ለውጦችን እና ቡድናዊ የፖለቲካ ጡዘቶን መቋቋም እንዲችል ማድረግ ነው የሚያዋጣው። እጅግ ብዙ ሐብት፣ ረጅም ጊዜ እና ብዙ የሠለጠነ የሰው ኃይል የሚያስፈልግ ተቋም ከመሆኑም በላይ ለሀገር ልዓላዊነት ትልቁ እና የመጨረሻ ዋስትና ነውና። እኛ ለመከላከያችን ያለንን የአሁኑን ምልከታችንን ግብጽ እንዳታውቅ፣ አልሸበብ እንዳይሰማ እመኛለሁ። መከላከያ በየቦታው በመንጋ ጩኽት የሚቆም [ሥጋቱ ይገባኛል] ከቡድናዊ ንብረት ጥበቃ እና ብሔረሰብ interest ጋር መጋጨት እና ሥራው መከልከል ያለበት መሆን የለበትም። 

በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያ በየወረዳው የሚከሰተውን ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሹ ግጭቶችን ለማብረድ መላኩ መዘዝ አለው። ባንድ በኩል የክልሎች ፖሊሶች እና ልዩ ኃይሎች ሥራ ነው። መከላከያ የፖሊስ ሥራ ውስጥ መግባት የለበትም። በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ግጭቶች ወታደር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም። 

 

መንግሥቱ አሰፋ ነኝ

ቸር ጊዜ!