የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋ ህዝብ ነው! የጨዋነት ዋጋው ግን በጣም ውድ ነው!

በህዝብ የተቃውሞ ጫና በህወሓት ይመራ የነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር ተሰናብቶ “አዲስ” አስተዳደር ከመጣ አስረኛ ወራችንን ይዘናል:: ይህ “አዲስ” አስተዳደር ወደ ስልጣን የመጣው ‘አብይ’ የሚባል የተባረከ ተስፋን አንግቦልን ነበር:: ‘አዲሱ’ ኢህአዴግ ሆይ የኢትዮጵያ ህዝብ መቼስ ሆደ ሰፊና ተስፈኛ ህዝብ ነውና ምንም ያክል የበደልህ ብዛት ቢያንገሸግሸውም እንደ ‘አብይ’ ያለ ብሩህ ተስፋ በፊቱ ስታሳልፍለት በደልህን ባይረሳም እንኳ ከአብራኬ የወጣህ ነህና አንድ ቀን ተመልሰህ ከቀልብህ ትሆንና ትክሰኝ ይሆናል ብሎ እንደገና እድሉን ሰጥቶሀል:: እድሉን መስጠት ብቻ ሳይሆን አሁን ካንተ የምጠብቀው ይኼን ነው ብሎ ይመክርኻል:: ምን ማድረግ እንዳለብህም መንገዱን ያሳይኻል:: የክፉ ቀን ደራሽ ‘ልጁ’ ነህና በዚህ ሁሉ የለውጥ ውዥንብር ውስጥ ስታልፍ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም:: ምናልባትም ድንገት ግራ ተጋብቶ ይሆናል ‘ልጄ’ ብሎ በአዋቂዎቹ ያስመክርኻል:: አልፎ ተርፎም መቼስ የቤተሰብ ነገርም አይደል ብሎ ‘በቤተዘመድ’ ሸንጎም ግራ ቀኙን እንድትሰማ አድርጎ ምን ማድረግ እንዳለብህ መላውን ይሰጥኻል::

አንዳንዴም የቤተሰብ ነገር ነውና የቤቴ ጉድ ለማን ይነገራል ብሎ ላንተው ለ’አዲሱ’ ኢህአዴግ ብሶቱን ይነግርኻል:: ገበናውን አውጥቶ ያሳይኻል:: ታዲያ አንተ ሚስጥረኛዬ የቤተሰብ አባልና አዋቂ ነህ ብሎ ብሶቱን በዘከዘከልህ ብሶቱን የእድሜ ማራዘሚ: የውርስ ይገባኛል መሞገቻ አድርገህ በወንድሞችህ መሀከል ፀብ መዝሪያ ስታደርገው ደስ አይልም- አበው ይሙት ደስ አይልም:: በስተርጅና ሌሎቹን በመምከሪያህና በማስታረቂያህ ዘመንህ ታላቅ ወንድም (Big Brother) ሆነህ ሌሎቹን መገሰፅ ሲጠበቅብህ ያለ እድሜህ የልጅነት ጨዋታ አማረኝ ስትል (when you fail to act your age) ለሰሚም ለጎረቤትም ደስ አይልም::

አየህ የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድ ወንዝ የአንድ ቀዬ ህዝብ ነውና ወንድሙ ሲታመም ያመዋል:: ‘ልጄ’ ከወደ መሀልና: ከወደ ደቡብ ያሉት ዘመዶቻችን ከኢትዮጵያዊነት የተጣረዘ ባዕድ ወግ ከወዴት መጥቶ እንዳገኛቸው ባናውቅም ታመዋል: አስቸኳይ ህክምናም ስለሚያስፈልጋቸው ፈጥነህ የርዳታ እጅህን ዘርጋላቸው ብሎ በኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ወግ ይማፀንሀል:: ከልጆችህ መሀል የረብሻ አመል ያለበትም ካለ እንድትገስፀው ይነግርሀል:: በኢትዮጵያዊ የአባትነት ወግ ቀጥተኸው አደብ እንድታስገዛለት እድሉን ይሰጥሀል:: ይኸውም ጉዳዩ መንደሩን ሁሉ መረበሽና ሰላም መንሳት ሳይጀምር እንድታረጋጋው እድሉን ሲሰጥህ ማለት ነው:: ከወንዙ ዳር ያለውም ቀዬ ቅር ብሎታልና አደራህን አታስከፋው: ለክፉ ቀን ደራሽ ወንድምህም አይደል ብሎ ፀሀይ ሳትጠልቅ እርቅ እንድታወርድ በጥበብ ይመክርኻል::

የቤተሰቡ አውራ ነህና ቀዬውን እንድታረጋጋ ሰላሙን እንድታስጠብቅ ሀላፊነቱን ሰጥቶኻል:: አንተም ሀላፊነቱ ይገባኛል: ልወጣውም ዘንድ እችላለው ስላልክ እድሉን ሰጥቶሀል:: ‘በጠፋው’ ልጅ የልጅነት ቁርሾ የተነሳ ቤተዘመድ የተላለቀበት ፀብ ተነስቶ መአት በሚመስል አላስፈላጊ ጦርነት ዘመድ ወዳጅ እንደ ቅጠል ረግፎበት በደም የሚፈላለግ የቀዬውን ጎረቤትም አስታርቅልኝ ብሎ ሲጠይቅህ እሺ ብለህ ቁርሾህን ትተህ የታላቅነትህን ስትወጣ በጀ አሁን እውነትም እየካስኸኝ ነው ብሎ ኢትዮጵያዊ ምርቃቱን ለግሶኻል::

ታዲያ የቀዬው “የታች’ ሰፈር ‘ጎረምሶች’ ደርሰው ‘የላይ’ ሰፈር ሰዎች የግጦሽ ማሳችን ላይ ከብቶቻቸውን አሰማርተውብናልና በማለት ቱግ ብለው እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ለፀብ የወጡ እንደሆን በሀገሬው ቱባ ወግ በቀዬው ልማድ የቤተዘመድ የተከበሩ ሽማግሌዎች ተሰባስበው አንተም ተው አንተም ተው ብለው ያስታርቃሉ:: ያለ ቀዬው ከብቶቹን ያሰማራውንም በቀዬው የሽማግሌዎች ፍርድ ሸንጎ ተመጣጣኝ ቅጣት ይሰጠዋል:: በዚሁ ጠብ ያለ ወንዙ ወግ ልማድ ወንድሙን የጎዳ የበደለ ካለም ያጠፋው ግለሰብ አስፈላጊውን ቅጣት ተቀጥቶ እንዲታረም ይደረጋል እንጂ የተበደለው ወገን ጩኸት ዝምታ ተችሮት ያጠፋው ወገን ደግሞ ምንም እንዳላጠፋና ይባስ ብሎም ቀዬውን ያለማ ይመስል ለሌላ ሹመት አይታጭም:: ሁለቱ መንደሮቹ በፀብ እንዳይከርሙ ሲባል እርቅ ቢወርድም እንኳ::

የኢትዮጵያ ህዝብ ግፍ የሚያንገሸግሸው የልጆቹ ሞት: መፈናቀልና አንዱ ከሌላው ይሄ መሬት የኔ ነው: ያኛው ደግሞ ያንተ ነው በሚል ተራና የማይረባ ቁርሾ የእርስ በርስ ግጭት ሰላሙን የመነጠቅ ትዕግስት የሌለው ነውና የልጅነትህን ሲመክሩህ ተመከር:: ሲናገርህ ሲቆጣህ ‘ልጄ’ ነህ ብሎ ነውና አቤት ብለህ ስማ:: የሚበጅህም በእቅፍህ ያኔ ሳይገባህ የሰበሰብካቸው የተንኮል ልጆች ካሉ ብትገስፃቸውና ቀጥተህ መስመር ብታስይዛቸው ነው:: በመንጋው ተኩላ እየሰደዱ በግርግር የሚያተርፉ ያኔ የተሳሳተ መስመር ላይ እያለህ የተወዳጀሀቸው ካሉም ፈልፍለህ እያወጣህ ቤትህን ብታፀዳ ነው የሚሻልህ:: ሁለተኛ እድል ሰጥቶሀልና አታባክነው ጎበዝ! ይኸን ህዝብ በውል ካወቅኸው በጣም አሳማኝና በቂ ምክንያት ቢኖረው እንጅ በታሪኩም ቢሆን ሁለተኛ እድል ሲሰጥ አይታወቅም::

እኔ እምፈራልህ ይህ የዋህ ህዝብ እሮሮውን ማሰማት የተወ ለታ ነው:: የቀዬህን ነዋሪ በውል አውቀህ ከሆነ ዝምታን የመረጠ ግዜ በቅቶታል ማለት ነው:: ከዚያ በኋላ መልስ ካንተ እየፈለገ አይደለም ማለት ነው:: ከዚያ በኋላ ‘ልጅነትህን’ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል ማለት ነው:: ከዚያ በኋላ በቤተዘመድ ሽማግሌ አያስመክርህም ማለት ነው:: ከዚያ ወዲያ ብሶቱን ሀላፊነቱ እንደተጣለበት አንድ የቤተሰብ አባል ጠርቶህ አይነግርህም ማለት ነው:: የዛኔ አንተ ለዚህ ጨዋ ህዝብ ባዳ ሆነሀል ማለት ነው:: አየህ ያ መቼም እራስህን ልታገኘው የማትፈልግበት መጥፎ ቦታ ነው:: እኔም እንደዛ አይነት ቦታ ላይ እንድትገኝ ከቶውንም ልመኝልህ አልችልም:: የቀዬዬን ህዝብ በደንብ አድርጌ አውቀዋለዋ! ብቻ ፈጣሪ ልቡናና የሚያደምጥ ጆሮ ለተግባራዊ ምላሽም የፈጠኑ እግሮች ይስጥህ እያልኩ ለዛሬ በዚሁ ልሰናበት:: እንደው ዳግም በዚሁ ጉዳይ ከተመለስሁ ለዚህ የዋህ ግን ብልህ ህዝብ የልቡን አድርሰህለት: ቀዬህም ኮርቶብህ: የአባቶች ቡራኬ በዝቶልህ ባይ እመርጣለው:: ቸር እንሰንብት::