ከውስጥ አዋቂ የተላከ ደብዳቤ በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ውስጥ የሚፈፀመውን ጉድ አጋለጠ!

ቀን፡- ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም

ለ፦__________________________________
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- የተፈጸመና እየተፈጸመ ያለ ዘረፋ እንዲጣራ እና እርምጃ እንዲወሰድ ስለመጠየቅ

በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር ካሉት ዋና መምሪያዎች መካከል አንዱ የሆነዉ የስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር በሃገራችን ተጠልለዉ የሚገኙ የተለያየ ሃገር ዜግነት ያላቸዉን ስደተኞች ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፤ ተቋሙ በየዓመቱ ለሚያከናዉናቸዉ ሥራዎች የበጀት ምንጩን ከUNHCR, WFP IGAD እና ከሌሎቹም አለም አቀፍ ተቋማት እና ከኤምባሲዎች ሲሆን ለስደተኞች ድጋፍ ለማድረግና የኑሮ ሁኔታቸዉን ለማሻሻል በየዓመቱ የሚመደበዉ በጀት በከፍተኛ ሁኔታ በብሄራዊና መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሲመሩ በነበሩ ሀላፊዎች እና በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ሃላፊዎች ሲመሩ በነበሩና አሁንም በመምራት ላይ ባሉ በከፍተኛ ሁኔታ ላላፉት 10 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ሃብት እየተመዘበረ ይገኛል፤ በዚህም ስደተኞች ማግኘት ያለባቸዉን ጥቅም እንዳያገኙ እና ለሃገራችን በስደተኞች ስም የሚገኘዉን የዉጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ለምዝበራ እና ዝርፊያ ተጋልጦ ይገኛል፤ ይህን ዘረፋ እና ምዝበራ አሁን በሃገራችን ካለዉ ለዉጥ ጋር ተያያዞ መዝባሪዎች ለህግ ይቀርባሉ፤ ለዉጥም ይኖራል የሚል ተስፋ በመላ ሠራተኛዉ ቢኖርም፤ አሁንም ዘረፋዉን ለማስቀጠል በሚመስል መልኩ ዘራፊዎቹና የዘረፋ ተባባሪዎቹ ምደባ እና ሥልጣን ሲሰጣቸዉ እየታየ ይገኛል፤ በመሆኑም ዋና ዋና የዘረፋ እና ምዝበራ መስኮች ከዚህ የሚከተሉት ሲሆኑ፤ ተቋሙ ጉዳዩን አጣርቶ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት ያለን ሲሆን፤ ጉዳዩ አፋጣኝ እርምጃ የማይወሰድበት ከሆነ ያለዉን ምዝበራ በመረጃ እና በማስረጃ በማስደገፍ መላዉ የሃገራችን ህዝቦች እንዲያዉቁት ለሃገር ዉስጥ እና ለዉጭ ሚዲያዎች የምናሳዉቅ መሆኑን እየገለፀን፤ በዚህም ሃገራችን ያላት በስደተኞች አያያዝ እና አስተዳደር ላይ ያላት በጎ ስም ሊጎድፍ ይችላል፡፡ ስለሆነም ክቡር የተቋማችን ዋና ዳይሬክተር ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተዉ የተቋሙ ዋና የዘረፋ ዋና መምሪያ በሆነዉ የስደተኞች ጉዳይ ዋና መምሪያን ስር ነቀል የሪፍርም ሥራ ዉስጥ እንዲገባ እና ግልጽ ግምገማ በማድረግ አጥፊዎቹ በህግ እንዲጠየቁ እየጠየቅን ነጥቦቹ ከዚህ በታች ተቀምጠዋል፡፡

1) ለስደተኞች በተላከ የእርዳታ ገንዘብ ላይ የሚፈፀም ሌብነትና ዘረፋ፤

ለስደተኞች ለምግብ ዕደላ እና ለተለያዩ ወጭዎች ከአለም ምግብ ፕሮግራም /World Food Program/ የሚመደበዉ በጀት ላለፉት 13 ዓመታት በላይ ኦዲት ተደርጎ የማያዉቀውና ለጋሽ ድርጅቱም ገንዘቡን ከመስጠት ዉጭ ምን ላይ እንደዋለ የማይጠይቅና “ድርጅቱ የደህንነት ተቋም ነዉ” በሚል ተልካሻ ምክንያት በመፍራት በየዓመቱ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ለዋናዉ መ/ቤት በሚል በየጊዜዉ በግለሰቦች በተከፈተ አካዉነት ገቢ ሲሆን የነበረ ሲሆን፤ ጉዳዩ አደገኛ እንደሆነ አንዳንድ ተቆርቋሪ ሠራተኛች በማንሳታቸዉ ላለፉት አራት አመታት “የመንግስት አካዉነት ነዉ” በሚል በተከፈተ አካዉነት ገንዘቡ ገቢ እየተደረገ እንዳለ ይህም መረጃዉን በፋይናንስ እና ግዥ መምሪያ ስር የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህም በአሁኑ ሰዓት መምሪያዉን ከሚመሩት ወ/ሮ እየሩሳሌም ቸርነት እጅ ላይ የሚገኝ መሆኑን፡፡

በየዓመቱ የተለያዩ ድርጅቶች የሶስትዮሽ ስምምነት በመፈረም ለስደተኞች አገልግሎት እያቀረቡ ካሉ አገር በቀል እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የዉል ስምምነት በመፈጸም ከተበጀተዉ በጀት ዉስጥ ሃላፊዎች ከፍተኛዉን ገንዘብ እየተከፋሉ እንዳሉ፤ ለዚህም እንደማስረጃ የሚቀርቡት ድርጅቶች ዉስጥ ከዋናዉ መ/ቤት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከስደተኛ ፕሮግራም ሥራዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እና የሥራ ልምድ የሌለዉን ማህበረ ረድኤት ትግራይ የተባለ ድርጅት በዶሎ አዶ የስደተኞች ፕሮግራም ላይ እንዲሰራ በማድረግ እ.ኤ.አ በ2017 ከ UNHCR 87 ሚሊዩን ብር እንዲሁም በ2018 ከ UNHCR 64 ሚሊዩን 984 ሽ 563 ብር ከ88 ሳንቲም በማስመደብ ከፍተኛ የምዝበራ ስራ እየተሰራ ይገኛል፤ በድርጅቱ በኩል ገንዘቡን እየሰበሰቡ የሚገኙት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ናቸዉ፡፡ ከላይ ከተጠቀሰዉ በተጨማሪ የ UNHCR ን የሎጂስቲክስ ሥራ የሚያከናዉን AHA የተባለ ድርጅት በማቋቋም እና የተቋሙ ሃፊዎችን የቦርድ አባል በማድረግ ለድርጅቱ በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት እንዲመደብለት በማድረግ ከፍተኛ የሃብት ምዝበራና ዘረፋ እየተካሄደ ይገኛል፤ ካላይ ከተጠቀሱት ድርጅቶች በተጨማሪ በአርቲስት ትርሃስ ታረቀ በቅጽል ስም ኮበሌ በተባለች አርቲስት ዋና ስራ አስኪያጅነት ስም ASDPO የተባለ ድርጅት በማቋቋም እና ምንም አይነት ልምድ ሳይኖረዉ በሞያሌ ተጠልለዉ ለሚገኙ የኬንያ ስደተኞች እንዲሰሩ በሚል በሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ UNHCR በማስመደብ የተመደበዉን ገንዘብ በከፍተኛ መጠን በመመዝበሩ በጀት መዳቢዉ አካል የሆነዉ UNHCR ጉዳዩን በማየት በጀት ለመመደብ ፍቃደኛ ባለመሆኑ በዚህ ዓመት በግዴታ ለማስመደብ ከፍተኛ ማስፈራራት እና ክስ ሲቀርብ ቢቆይም ጉዳዩ እልባት ባለማግኘቱ እስካሁን እልባት ሳያገኝ ቆይቶዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ለማሳያ የቀረቡ እንጂ በተመሳሳይ ብዛት ያላቸዉ ድርጅቶች ጋር ከፍተኛ ዘረፋ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ለስደተኞች አገልግሎት እንዲዉል በየአመቱ ከ UNHCR ለስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር የሚመደበዉ በመቶ ሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ ከዋናዉ መ/ቤት ሃላፊዎች እና በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ሃፊዎች በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት እየተመዘበረ ሲሆን፤ በተለይም ከፍተኛዉ ምዝበራ ለዋናዉ መ/ቤት ለሥራ በሚል ምክንያት በሚሊዮን ብር የተገዙ የነዳጅ ኩፐኖች በሃላፊዎች ትዕዛዝ ወደ ዋናዉ መ/ቤት የሚላክ ሲሆን፤ ከተላከ በኃላ ኩፖኖችን ከነዳጅ ማደያዎች ጋር የኮሚሽን ክፍያ በመክፈል ወደ ገንዘብ ተመንዝሮ ወደ ሃፊዎች አካዉንት የሚገባ ሲሆን፤ በዚህም ለረጅም አመታት ዘረፋዉ ሲካሄድ ቆይቶዋል፤ ጉዳዩን የሚያስፈጽሙ የንብረት ክፍል፤ የተሸከርካሪ ጥገና እና ስምሪት ክፍል በሃፊነት ሲመሩ የነበሩና በአሁኑ ሰዓት እየመሩ ያሉ ግለሰቦች (የግለሰቦቹ ስም አቶ በረከት የዋናዉ መ/ቤት የትራንስርት እና ሎጂስቲክስ መምርያ ሃላፊ፤ አቶ ዳንኤል አየለ የስደተኞች ጉዳይ የአስተዳደር እና ፋይናንስ እንዲሁም የፕሮግራም መምሪያ ሃላፊ የነበሩ፤ አቶ ፍስሃ ትርፌ የጋራጅ ክፍል ሃላፊ፤ አቶ ዘዉዱ ተክሌ የስደተኞች ጉዳይ የንብረት ክፍል ሃላፊ፤ ጉዳዩ ችግር ሊያመጣ ይችላል በማለት ሲቃወሙ የነበሩ ወ/ሮ እየሩሳሌም ቸርነት የፋይናንስ እና ግዥ መምሪያ ሃላፊ፤ በዋናዉ መ/ቤት በኩል የነዳጅ ኩፐኑን የሚቀበሉ አቶ በረከት እና ከዚህ በፊት የዋናዉ መ/ቤት ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩ እና በአሁኑ ሰዓት በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር የምክትል ዳይሬክተሩ አማካሪ በመሆን እየሠሩ የሚገኙት አቶ ተመስገን ናቸዉ፡፡ ከስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ተቀብለዉ የሚያደርሱ ብዛት ያላቸዉ ግለሰቦች ቢሆኑም በዋናነት አቶ ፍስሃ ትርፌ ናቸዉ፤ ከላይ የተጠቀሰዉ የነዳጅ ኩፐን ዝርፊያ በ2008 ዓ.ም በተደረገ የኮሚቴ ማጣራት የተጣራ እና የተረጋገጠ ቢሆንም የበላይ አመራሩ እንዲቆም ትዕዛዝ በመስጠቱ ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀር ተደርጎዋል፡፡

በዋናዉ መ/ቤት የነበሩ አመራሮችም ሆኑ በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር የነበሩነ በአሁኑ ሰዓትም ያሉ በአመራር ያሉ አመራሮች በከፍተኛ ሁኔታ የንብረት ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሲሆን በተለይም በንብረትነት ሳይመዘገብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ጄኔሬተሮች እንዲገዙ ትዕዛዝ በመስጠት በመኖሪያ ቤቶቻቸዉ ያስቀመጡ ሲሆን በዚህም ዶ/ር ሃሽም ቶፊቅ፤ አቶ ይሳያስ ወ/ጊወርጊስ፣ አቶ ዘይኑ ጀማል እና ሌሎችም እስከ አሁን ለጄኔሬተር ነዳጅ ጭምር በማስመደብ አላግባብ ለስደተኛ የተመደበን በጀት ለግል ጥቅም እያዋሉ ይገኛሉ፤

በየዓመቱ ከUNHCR ለስደተኞች የሪፈራል ህክምና አገልግሎት የሚመደበዉን በጀት የተቋሙ ሠራተኞች ላልሆኑ ከፍተኛ የህክምና በጀት በመስጠት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ፤ በጀቱን በተለያዩ ስደተኞች ስም ወጭ በማድረግ ከግለሰቦች መብልጸጊያ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ኢ-ሞራላዊ የሆነ ሥራ እየተሠራበት ይገኛል፤ ለአብነትም የሃላፊዎች ቤተሰብ እና ልጆች በስደተኛ ስም በሃገር ዉስጥ ባሉ የግል ሆስፒታሎች እና በዉጭ ህክምና እንዲያገኙ የሚደረጉ ሲገኙበት፤ በተቋሙ የፕሮቴክሽን መምሪያ ሃላፊ የሆነዉ አቶ እስጢፋኖስ ገ/መድህን ባለቤቱን ልጅ በምትወልድበት ጊዜ በስደተኛ ስም በከፍተኛ የግል ሆስፒታል እንድትወልድ የተደረገበት አንድ አብነት ሲሆን፤ ዝርዝር ጉዳዩን በተመለከተ ዶ/ር አለምብርሃኔ በርሄ ፤ ዶ/ር ጎይቶም አደም ኑር የተባሉ የህክምና ስራዉን በበላይነት የሚመሩ ሲሆን፤ የሪፈራል ሥራዉን የሚመሩት አቶ ገብርሃና ለገሰ የተባሉ ሠራተኞች በዝርዝር መረጃዉ ያላቸዉ እና ጥያቄዉ ከቀረበ በዝርዝር የሚያቀርቡት ይሆናል፡፡

2) ተሽከርካሪን በተመለከተ፤

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን UNHCR /United Nation High Comissioner For Refugees/ ለስደተኞች አገልግሎት ላይ የሚዉሉ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በየአመቱ ለድርጀቱ የሚሰጥ ሲሆን፤ “ከUNHCR ከሚሰጡት ተሸከርካሪዎች ከ60% በላይ የሚሆኑት ለብሄራዊ መረጃና እና ደህንነት አገልግሎት ይዉላሉ” በሚል የሚያስቀራቸዉ ሲሆን፤ ተሸከርካሪዎቹ የት እንደሚገቡ የሚያዉቅ የለም፤ ከዚህም በበሳ ለስደተኞች አገልግሎት እንዲሰጡ ለመጠለያ ጣቢያ ተመድበዉ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች በበላይ ሃላፊዎች የቃል ትዕዛዝ ብቻ ማንነታቸዉ ለማይታወቁ ግለሰቦች እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን፤ ለአብነትም በ2007 ዓ.ም ከሽሬ የኤርትራ ስደተኞች ማስተባበሪያ አዲሃሩሽ መጠለያ ጣቢያ የተመደበች እና የሰሌዳ ቁጥር የ.ተ.መ 965 የተመዘገበች ሎንግ ቤዝ ሃርድ ቶፕ ተሽከርካሪ በወቅቱ ሲያሽከረክሩ በነበሩት አሽከርካሪ ወደ ጎንደር እንድትሄድ ከተደረገ በሃላ ለአንድ ግለሰብ አስረክቦ እንዲመጣ በወቅቱ የሽሬ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ በነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በዋናዉ መ/ቤት በዋና ክፍል ሃላፊነት በመስራት ላይ የሚገኙት በአቶ ገ/ሊባኖስ በርሄ ትዕዛዝ አስረክቦ የመጣ ሲሆን ተሽከርካሪዉ የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ አገልግሎት መስጠት እየቻሉ፤ መኪኖችን ለሽያጭ በማቅረብ እና በመሸጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በግለሰቦች የግል አካዉንት የሚገባ ሲሆን ሽያጩን በዋናት የሚያከናዉኑት የትራንስፖርት ሃላፊዉ አቶ በረከት እና የጥገና ክፍል ሃላፊዉ አቶ ፍስሃ ናቸዉ፡፡

3) በህገ – ወጥ መንገድ ኤርትራዊያን ስደተኞችን ወደ አዉሮፓ እና አሜሪካ መላክን በተመለከተ፡-

አብዛኛዉ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ወደ ሶስተኛ ሃገር ለመሄድ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህም በህጋዊና በህገ-ወጥ ጉዞዎች የሚከናወን ነዉ፤ የስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ከ UNHCR ጋር በመሆን እንደ ስደተኞቹ የሚያቀርበት ጉዳይ/Case/ መነሻ በማድረግ ወደ ሶስተኛ ሃገር በሪሴትልመንት/Resettlement/ ተቀባይ ሃገራት በማፈላለግ የሚልክ ሲሆን፤ ትክክለኛ መሄድ የያለባቸዉን ግለሰቦች በማስቀረት እና ዳታ ቤዙን በማስተካል ካለፉት 8 ዓመታት ጀምሮ በአንድ ስደተኛ እስከ 2 መቶ ሽ ብር በማስከፈል ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸም ቆይቶዋል፤ በ2010ዓ.ም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን ደርሶበት የጉዳዩን ተዋናይ የሆነዉ ቀንደኛ ግለሰብ እና ኤርትራዊ ዜግነት ያለዉ እና በስደተኝነት የተመዘገበ አቶ ይሳያስ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ያካሄደ ሲሆን በምርመራዉም ሁለት የተቋሙ ሠራተኞች የሆኑ አቶ አብርሀም እና አቶ ሚካኤል የተባሉ ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራዉን በስፋት ለማካሄድ የተቋሙን ትብብር የጠየቀ ሲሆን፤ ምርመራዉን አቅጣጫዉን ለማሳት ለምርመራዉ ለሚጠየቁ ጥያቂዎችን የተዛባ መረጃ በመስጠት በጉዳዩ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸዉን እና በአሁኑ ሰዓት በምክትል ዳይሬክተርነት የተመደቡትን አቶ እዩብ አወቀ እና የህግ እና ፕሮቴክሽን መምሪያ ሃላፊ የሆኑትን አቶ እስጢፋኖስ ገ/መድህንን እንዲሁም ተባባሪዎቻቸዉ የነበሩት እና በአሁኔ ሰዓት IOM በተባለ የፍልሰተኞች ድርጅት ዉስጥ የሚሰሩትን አቶ አሸናፊ ተፈራ እና አቶ ምርተአብ ቅሩብ የተባሉ የጥቅም ተካፋዎችን እዳያስጠይቅ ለማድረግ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆን፤ መርማሪ ቡድኑ ዋና ዋና ተዋናዮችን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማመኑ አነስተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸዉን አስሮ ማቆየት እና ማስቀጣት ትርጉም የሌለዉ መሆኑን ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ክሱን አቋርጦ የተያዙትን ተጠርጣሪዎች እንዲፈቱ በማድረግ ክሱ ተዘግቶዋል፤ የክስ ፋይሉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዉስጥ ይገኛል፡፡

4) የሠራተኞች ቅጥርን በተመለከተ፤

ተቋሙ የሰራተኞች ቅጥር እና ዝዉዉር የሚፈጽምበት መመሪያ ቢኖረዉም ከመምሪያዉ ዉጭ በመሆነ መልኩ ከሌሎች መስሪያቤቶች በጡረታ የተገለሉ ሠዋችን እስከ ምክትል መምሪያ ሃላፊነት ደረጃ እስከመመደብ የተደረሰበት ለአብነት ኮ/ል ገነት ገ/እግዜብሄር የተባሉ ግለሰብ በአቶ ጌታቸዉ አሰፋ እና በአቶ ይሳያስ ወ/ጊወርጊስ ትዕዛዝ እንዲቀጠሩ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት የሰዉ ሃይል እና ንብረት አስተዳደር ም/መምሪያ ሃላፊ ሆነዉ እየሠሩ ይገኛሉ፤ በተቋሙ የሌሉ ሠራተኞች እንደተቀጠሩ በማስመስል በሌሉ ሰዎች በፔሮል በመትከል ደምወዝ መክፈል ለአብነት በጋምቤላ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሌሉ ስምንት (08) የIT ባለሙያዎች ለእያንዳንዳቸዉ 20 ሽ ብር የወር ደምወዝ እየተከፈለ ይገኛል፤ የጋምቤላ ማስተባበሪያ አመራሮች በጉዳዩ ላይ ያስጠይቀኛል የሚል ጉዳይ ቢያነሱም ሰሚ ባለማግኘታቸዉ፤ በቅርቡም በደምወዝ ወቅት በየወሩ እየተደወለ ደምወዙ የሚገባበት የባልክ አካዉንት እየተቀያየረ በመሆኑ ደምወዝ ለማስገባት እንደተቸገሩ ይገልጻሉ፡፡ በአለም ምግብ ፕሮግራም በጀት በዋና መ/ቤት ደረጃ የቡድን መሪ በሚል ከ22 ሽ ብር በላይ ለአንድ በተቋሙ ለሌለ ግለሰብ እየከፈለ ይገኛል፤ በዚህም የአለም ምግብ ፕሮግራም ግለሰቡን እንደማያዉቅ እና በጀት እንደማይለቅ በቅርቡ በስብሰባ ላይ የገለጸበት ሁኔታ አለ፤ እነዚህና የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ ባሉ መደቦች የመመደብ እና ባልተገቡ ግለሰቦች የማስያዝ እንዲሁም በሌሉ ሰዎች ደምወዝ የመክፈል ድርጊት በሌሎችም ዞኖች እና ካፖች በስፋት የሚስተዋል ነዉ፡:

5) በስደተኞች ላይ ሰብዓዊና መብት ጥሰት መፈጸም፡-

ተቋሙ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮያ ተጠልለዉ ለሚገኙ ስደተኞች ሰበሰዓዊና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በየዓመቱ የሚሰጠዉን በጀት፤ ለስደተኞች ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲዉል የተደረገ ሲሆን፤ በተለይም የኤርትራ ስደተኞች የተለያየ ስም በመስጠት (የሻዕቢያ ተላላኪ እና ለስለላ የመጣ በሚል) በተቋሙ በጀት ድብቅ እስር ቤት ከግለሰቦች በመከራየት ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምባቸዉ ቆይቶዋል፤ የድብቅ እስር ቤቱ ከሚገኝባቸዉ ቦታዎች ለአብነት በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ አዲ- አቡን የተባለ ቦታ ሲሆን፤ በወቅቱ ጉዳዩን ሲያስፈፅሙ የነበሩ አቶ እስጢኖስ ገ/መድህን የህግ እና ፕሮቴክሽን መምሪያ ሃላፊ፤ አቶ ከበደ አባይነህ በወቅቱ የሽሬ ዞን አስተባባሪ የነበሩና በአሁኑ ወቅት ሰዉ ሃይል መምሪያ ሃላፊ ናቸዉ፤ በወቅቱ በዞኑ እና በእንዳባጉና ማጣሪያ ጣቢያ ሲሰሩ የነበሩ እና በድብቅ እስር ቤቱ በጊዜዊነት ተመድበዉ የነበሩ ጉዳዩን በዝርዝር ማስረዳት የሚችሉ ናቸዉ፡፡ ይህ ግርፋት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ለወራት ከቀጠለ በኃላ፤ ወደ ትግራይ ክልል ፍርድ ቤት በማቅረብ የተወሰኑትን በማስቀጣት፤ መረጃ አልተገኘባቸዉም የተባሉትን ስደተኞች አለም አቀፍ ህግን በመጣስ የተሠጣዉ የስደተኝነት እዉቅና ሳይሰረዝ፤ የግል ተሸከርካሪዎችን በመከራየት በግዴታ ወደ ሞያሌ ኬኒያ በመዉሰድ እንዲጣሉ ተደርጎዋል፤ ይህም አንድ ስደተኛ ተገዶ ማስወጣት /Refloument / አይቻልም የሚለዉን አለም አቀፍ ህግ የጣሰ ነዉ፡፡ በእስር ላይ የሚገኙም በትግራይ ክልል በተለያየ እስር ቤቶች ታስረዉ ይገኛሉ፡፡

በተለያዩ የሙስና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሃገራት በዲፕሎማትነት የተመደቡና ለጉዞ ዝግታቸዉን አጠናቀዉ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፤ ከእነዚህም ዉስጥ፡-

  1. አቶ እስጢፋኖስ ገ/መድህን ፡- የስደተኞች ህግ እና ፕሮቴክሽን መምሪያ ሃላፊ – በኩባ ዲፕሎማት ሆነዉ የተመደቡ፡፡
  2. አቶ ሃይለስላሴ ገ/ማሪያም በመምሪያዉ ምክትል ሃላፌ ከዚህ በፊት በ1997 የአዲስ አበባ ደህንነት ኃለፊ ሆነዉ የሠሩ – በእስራኤል ዲፕሎማት ሆነዉ የተመደቡ፡፡
  3. አቶ ተመስገን ከዚህ በፊት የብሄራዊ መደረጃና ደህንነት አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአቶ ጌታቸዉ አሰፋ ረዳት የነበሩ በአሁኑ ወቅት የስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር የምክትል ዳይሬክተሩ አማካሪ በመሆን እየሠሩ የሚገኙት- በደቡብ ሱዳን ዲፕሎማት ሆነዉ የተመደቡ፡፡
  4. አቶ ከበደ አባይነህ – የሰዉ ሃብት መምሪያ ሃላፊ – በስዊድን ዲፕሎማት ሆነዉ የተመደቡ፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ የተነሱት ጉዳዮች ለአብነት እንደማሳያ እንጂ ባለፉት 3 አመታት እና ከዚያም በፊት በስደተኛ ስም የመጣን ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ ምዝበራና ሌብነት እየተፈጸመበት የሚገኝ ሲሆን፤ የተቋሙ ሠራተኞች ጉዳዩን እንዳያወጡ ከፍተኛ ማስፈራራት እና ቅጣት በመቅጣት ሊያዳፍኑት ሞክረዋል፤ በአሁኑ ሰዓት ሃገራች በከፍተኛ ለዉጥ ዉስጥ በመሆኗ እና ዘረፋዉን፤ ማስቆሚያ ወቅት ነዉ በሚል ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጣራ እና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፤ እንዲሁም ዘረፋዉ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

ከሠላምታ ጋር

ከተቋሙ ሠራተኞች

ግልባጭ
ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የህዝብ አቤቱታዎችና ጥቆማዎች መቀበያ ማጣራት ዘርፍ
ፓ.ሳ.ቁ 1031
አዲስ አበባ