ሰበር ዜና! በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች በየትኛውም የኢትዮጵያ አከባቢ የመዘዋወር፣ የመኖር እና ዜግነት የመጠየቅ መብት ተሰጣቸው! (አዋጁ ደርሶናል)

በዛሬው ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር ——/2010” ማፅደቁ ተገልጿል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ፤ በመረጠው የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፣ መንጃ ፍቃድ የማውጣት፣ የመታወቂያና የውጪ ቪዛ (የጉዞ ሰነድ) የማግኘት፣ የባንክ ሂሳብ የመክፈትና ገንዘብ የማንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር ተዋህደው የመኖር እና የኢትዮጵያን ዜግነት የመጠየቅ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡

 • በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅን እንደገና ለማውጣት የቀረበ የረቂቅ አዋጅ ለማንበብ ይህን PDF ማያያዣ ይጫኑ!
 • በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማንበብ PDF ማያያዣ ይጫኑ!

ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና መብቶች የሚደነግጉትን አንቀፇች ከታች በዝርዝር ቀርበዋል፦

  27. የመዘዋወር ነፃነት

  1/ ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ለውጪ አገር ዜጎች በአጠቃላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆኑ ሕጎች ተግባራዊ በማድረግ በመረጠው የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት አለው፡፡

  2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ቢኖርም አገልግሎቱ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎችና አካባቢዎች ሊያመቻች ይችላል፡፡ የሚያመቻቸው የመኖሪያ ቦታ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከመጡበት የዜግነት ወይም የቀድሞ መደበኛ መኖሪያ አገር ተገቢው ርቀት እንዲኖረው በማድረግ መሆን አለበት፡፡

  3/ አገልግሎቱ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማስቻል ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል፡፡

  30. የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ

  1/ አግባብነት ባላቸው ሕጎች የተቀመጡ ድንጋጌዎች የሚጠይቋቸውን መስፈርቶች በማሟላት በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ የውጭ አገር ወይም ዓለም አቀፍ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የያዘ

  ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ በኢትዮጵያ ተመጣጣኝ ምድብ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እንዲሰጠው ሊያመለክትና ሊሰጠው ይችላል፡፡

  2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ሕጋዊ የውጭ አገር ወይም ዓለም አቀፍ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የያዘ ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ በኢትዮጵያ ተመጣጣኝ ምድብ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማግኘት እንዲችል ለመርዳት አስፈላጊውን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና ለመውሰድ ፈቃደኛ ሆኖ ከተገኘ አግባብ ባላቸው ሕጎች የተቀመጡት መስፈርቶች ሊነሱለት ይችላሉ፡፡

  3/ በሌላ ሕግ ተቃራኒ ድንጋጌ ቢኖርም ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ አግባብ ባላቸው ሌሎች ሕጐች የተቀመጡ መሥፈርቶችን በማሟላት በአገልግሎቱ የሚሰጥ ማንነቱን የሚገልጽ የመታወቂያ ሰነድ በመጠቀም የኢትዮጵያ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት የማመልከት እና ተፈላጊውን መመዘኛ ካሟላ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የማግኘት መብት አለው፡፡

  31. የመታወቂያ ወረቀት እና የጉዞ ሰነድ

  1/ ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ማንነቱን የሚገልጽ የመታወቂያ ሰነድ ይሰጠዋል፡፡

  2/ ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዞ ለማድረግ ለአገልግሎቱ በጽሑፍ በማመልከት የጉዞ ሰነድ ማግኘት ይችላል፡፡

  3/ ዕውቅና ያገኙ ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች የጉዞ ሰነድ ዝግጅት፣ ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ እና አሰጣጥ እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ዝርዝሮች አግባብነት ባላቸው የኢሚግሬሽን ሕጎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ በተመለከተው መሠረት ይወሰናል፡፡

  32. የባንክ አገልግሎት ስለማግኘት

  ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ በአገልግሎቱ የተሰጠውን መታወቂያ ሰነድ በመጠቀም የባንክ ሒሳብ ደብተር የመክፈት፣ ገንዘብ የማስቀመጥ፣ የማውጣት፣ የማስተላለፍና የመሳሰሉ የባንክ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አለው፡፡

  33. የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ስለማግኘት

  ማንኛውም እውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ በአገልግሎቱ የተሰጠውን መታወቂያ ሰነድ በመጠቀም የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት የማግኘት መብት አለው፡፡

  40. ከዜጎች ጋር ስለማዋሃድ

  ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩ ስደተኞች ከአገሪቱ ዜጎች ጋር ተዋህደው ለመኖር ሲጠይቁ በቡድንም ይሁን በተናጥል ከዜጎች ጋር ተዋህደው የሚኖሩበትን ሁኔታ አገልግሎቱ ሊያመቻች ይችላል፡፡

  41. ዜግነት ስለማግኘት

  ዜግነትን በሚመለከቱ አግባብነት ያላቸው የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን መስፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም እውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ የኢትዮጵያን ዜግነት በሕግ ለማግኘት ማመልከት ይችላል፡፡