የዴሞክራሲ ግንባታ እና የምሁራን ሚና (በጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ሊቀርብ” የነበረ ፅሁፍ)

በመሰረቱ በአንድ ሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባት እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ሲቻል ነው። ያለ ምሁራን ተሳትፎና ድጋፍ ደግሞ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም። በዚህ መሰረት፣ በዚህ ፅሁፍ “በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ የምሁራን ሚና ምንድነው?” የሚለውን በዝርዝር እንዳስሳለን።

1. ትምህርት እና ዕውቀት

የአማርኛ መዝገበ-ቃላት “ምሁር” የሚለውን ቃል “በትምህርት፥ በዕውቀት የበሰለ አዕምሮ ያለው ሰው” በማለት ይገልፀዋል። በዚህ መሰረት፣ “ምሁር” ሲባል በትምህርት ዕውቀት የቀሰመ፣ በዚህም ሰፊ ግንዛቤ ያለው፣ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየትና በጥልቀት ማገናዘብ የሚችል ማለት ነው። በመሆኑም ምሁር ለመሆን ትምህርት መማር፣ መመራመርና ማወቅ የግድ ነው።

በመሰረቱ፣ ምሁር ለመሆን መማር ያስፈልጋል፣ በትምህርት ደግሞ ዕውቀት ይገኛል። በዚህም ብዙ የተማረ ሰው ሊኖር ይችላል፣ ብዙ ነገር የሚያውቁ ሰዎች ይኖራሉ። ነገር ግን፣ በትምህርት የሚገኘው ዕውቀት በተግባር ለውጥና መሻሻል ካላመጣ መማር ሆነ ማስተማር ፋይዳ የለውም። በትምህርትና በምርምር የተገኘ ዕውቀት ፋይዳ የሚኖረው በግል ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ትርጉም ያለው ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል ሲሆን ነው።

ትምህርትና ዕውቀት የሰዎችን ሕይወት ሊያሻሽል ይገባል። በመሆኑም በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት። ይህ ለሌሎች ሰዎች ሲባል የሚደረግ አይደለም። ከዚያ ይለቅ፣ በሰዎች ሕይወት እሴት የማይጨምር ነገር ለራሳችን ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ፋይዳ-ቢስ ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይ በራሳችን ሆነ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል የማያመጣ ትምህርትና ዕውቀት ምንም እርካታ የሌለው ፋይዳ-ቢስ ነገር ይሆናል።

2. ማን ነው “ምሁር”?

ስለዚህ ምንም ዓይነት ትምህርት ብንማር፣ ምንም ያህል ዕውቀት ቢኖረን፣ በማህብረሰባችን ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ካላስቻለን ፋይዳ-ቢስ ነው። በአንድ ማህብረሰብ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ብዙ ሰዎች መስማት የማይፈልጉትን ነገር መናገር፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ኋላቀር ልማዶችን እና ባህሎችን መንቀስና መተቸት፣ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ኢ-ፍትሃዊ ተግባራትን በግልፅ መተቸት፣ መንቀፍና የተሻሻሉ አሰራሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ መጠቆም እና በመሳሰሉት ተግባራት መሳተፍ ያስፈልጋል።

“Edward Said” እ.አ.አ በ1993 ዓ.ም “Representations of an Intellectual – Holding Nations and Traditions at Bay” በሚል ርዕስ በሰጠው ትንታኔ፣ “intellectual” ማለት ዕውቀትና ክህሎቱን በመጠቀም የህዝብን ኑሮና አኗኗር ለመቀየር፣ የዜጎችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለማሻሻል አስተዋፅዖ የሚያበረክት ሰው ነው።

“The intellectual is the individual endowed with a faculty for representing, embodying, articulating a message of you, attitude, philosophy or opinion to as well as for a public in public. This role has an edge to it, and cannot be played without the sense of being someone whose place it is, publically, to raise embarrassing questions, to confront orthodoxy and dogma rather than to produce them, to be someone who cannot easily co-opted by governments and corporations.” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual – Lecture 4, Reith Lectures 1993.

በዚህ መሰረት፣ “ምሁር” ማለት በህዝቡ ውስጥ እየኖረ የህዝብን ጥያቄ (መልዕክት)፣ አመለካከት፣ ፍልስፍና ወይም ሃሳብ ለመወከል፣ ለመያዝና ለመግለፅ የሚያስችል ብቃት የተቸረው ግለሰብ ነው። ይህ የምሁራን ድርሻ የራሱ ደረጃ አለው። በአደባባይ አሳፋሪ ጥያቄዎችን ለማንሳት፣ ኋላቀር አመለካከትንና ግትር ቀኖናዊነትን ለመጋፈጥ፣ እንዲሁም ለመንግስት ፍላጎት በቀላሉ እጅ ላለመስጠት ድፍረትና ቁርጠኝነት የሌለው ሰው ይሄን ድርሻ ለመወጣት አይቻለውም።

“ምሁራን” ማለት ሃሳብና አስተያየታቸውን በአደባባይ በመግለፅ የህዝብን ጥያቄ የሚያንፀባርቁ፣ እንዲሁም ኋላ-ቀር አመለካከትና ግትር አቋምን በይፋ የሚሞግቱ ናቸው። በእርግጥ ይህን የሚያደርጉት ከግል ወይም ከተወሰነ ቡድን ጥቅም አኳያ ሳይሆን በመሰረታዊ የነፃነትና የፍትህ መርሆች ላይ በመንተራስ ነው። በየትኛውም ግዜና ቦታ፤ የሰዎች ነፃነት ሲገፈፍና ፍትህ ሲዛባ በይፋ በመናገርና በመፃፍ ተቃውሟቸውን ይገልፃሉ። ነፃነትና እኩልነትን ሲረጋገጥም ድጋፍና ደስታቸውን በይፋ ይገልፃሉ።

በአጠቃላይ፣ ምሁራን በትምህርት ዕውቀት ያገኛሉ፤ በዕውቀት ግለሰባዊ ነፃነትን ይጎናፀፋሉ። እነዚህ የነፃነትን ጣዕም የሚያውቁ በሁሉም ግዜና ቦታ ለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት ይሟገታሉ፣ ድንቁርናና ጭቆናን ፊት-ለፊት ይጋፈጣሉ። በአማርኛ እንዲህ ዓይነት ስብዕና እና ባህሪ ያላቸው ሰዎች “ምሁር” ሳይሆን “ሙር” ይባላሉ። የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ሙር” የሚለውን ቃል “የተማረና ዕውቀት ያለው ሆኖ ወፈፍ ስለሚያደርገው ብዙ የሚለፈልፍና የሚናገር፥ ንግግሩ ግን ፍሬ ነገር ያዘለ ሰው” እንደሆነ ይገልፃል።

3. ገለልተኝነት ወይስ አገልጋይነት

እስር ቤት ሳለሁ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ሲጠይቁኝ የነበረውና በቀጥታ ለመመለስ የተሳነኝ ጥያቄ “ከሰለጠንክበት የመምህርነት ሙያ ውጪ የፖለቲካ ፅሁፎችን እንድትፅፍና እንድታሳትም ማን ፈቀደልህ?” የሚል ነበር። ይህን ጥያቄ “በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት ዴሞክራሲያዊ መብቴ ነው፣ በከፍተኛ ት/ት ተቋማት አዋጅ አንቀፅ 4(3)፣ እንዲሁም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 13(2) መሠረት ማህበራዊ ግዴታዬ ነው” በማለት ለመመለስ ሞክሬ ነበር። ነገር ግን፣ የፖሊሶቹ ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ መብቴንና ማህበራዊ ግዴታዬን እንደ ወንጀል በሚቆጥር የተሳሳተ አመለካከት ስለነበራቸው አልተሳካም። ቦታው ጦላይ የጦር ማሰልጠኛ ባይሆን፣ ከዚያ ይለቅ በአንዱ ዩኒቨርሲቲ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ ለእንዲህ ያለ የተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው ምላሽ ራሱ ጥያቄውን ማስተካከል ነበር። እንደምታውቁት የዚህ ሀገር ፖሊሶች ለጠየቁት ጥያቄ መልስ እንጂ ማስተካከያ አይሹም።

በእርግጥ ሁሉም ፖሊሶች የማህብረሰቡ አካል ናቸው። በእነሱ ጥያቄ ውስጥ ያለው የተሳሳተ እሳቤ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቅ ነው። እንደ እኔ በመምህርነት ወይም በሌላ የሙያ መስክ ከተሰማራ ሰው የሚጠበቀው “ሙያተኝነት” (professionalism) ነው። ምክንያቱም፣ እያንዳንዱ ባለሙያ በሰለጠነበት የሙያ መስክ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይፈለጋል። ብዙውን ግዜ ከመደበኛ ሥራው በተጓዳኝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አይበረታቱም። በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የሚነካካ ከሆነ ፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም።

እንዲህ ባለ ማህብረሰብ ውስጥ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት? በዚህ ዙሪያ “Edward Said” የተባለው ልሂቅ “Representations of an Intellectual” በሚል ርዕስ ጥልቅ ትንታኔ የሰጠ ሲሆን የምሁራንን (intellectuals) ችግር እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

“The particular threat to the intellectual today comes from an attitude that I shall be calling professionalism; that is, thinking of your work as an intellectual as something you do for a living, between the hours of nine and five with one eye on the clock, and another cocked at what is considered to be proper, professional behaviour – not rocking the boat, not straying outside the accepted paradigms or limits, making yourself marketable and above all presentable, hence uncontroversial and unpolitical and “objective”” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual – Lecture 4, Reith Lectures 1993.

ከላይ እንደተገለፀው፣ ሙያተኝነት ወይም ፕሮፌሽናሊዝም (professionalism) በአብዛኞቹ የሀገራችን ምሁራን ዘንድ በግልፅ የሚስተዋል ችግር ነው። በእርግጥ ሙያተኝነት በራሱ እንደ ችግር ሊወሰድ አይገባም። እያንዳንዱ ባለሙያ በሰለጠነበት መስክ የሚጠበቅበትን አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነትና ግዴታ አለበት። ስለዚህ፣ ሙያተኛ ከመደበኛ ሥራውና ከሙያ ስነ-ምግባሩ ውጪ ይሁን እያልኩ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እንደ አንድ የተማረ ሰው ሙያተኝነት የተጣለብንን ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት ሊያግደን አይገባም ነው። በአጠቃላይ፣ ሙያና ሙያተኝነት እንደ መደበቂያ፣ ከኃላፊነት መሸሸጊያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።

አንድ የተማረ ሰው በሰለጠነበት ሙያ (profession) ስም ከሚፈፅማቸው ስህተቶች በጣም የከፋው መደበኛ ሥራውን በተለመደው መንገድ እየሰራ፣ በከረመ አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ሃሳብ እያመነዠከ፣ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ድርሻ ሳይወጣ ሲቀርና፣ በዚህም ከማንኛውም ዓይነት ውዝግብና ፖለቲካ ነፃ ለመሆን ሲሞክር ነው። በዚህ መልኩ፣ “እኔ ከውዝግብና ፖለቲካ ነፃ ነኝ” በማለት የሚመፃደቁ ምሁራን የተጣለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደተሳናቸው በራሳቸው ላይ የሚመሰክሩ ናቸው። የተማረ ሰው ከመደበኛ ሥራው ባለፈ ያለበት ማህበራዊ ኃላፊነት ምንድነው?

4. የምሁራን ሚና እና የፖለቲካ ቋንቋ

4.1 የምሁራን ሚና

እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት የብዙሃን ሕይወት በዘርፈ-ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ እርግጥ ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው የማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል ሲኖር ነው። ከዚህ አንፃር ምሁራን ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። “ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲችሉ የምሁራኑ ሚና ምን መሆን አለበት?” የሚለውን አስመልክቶ “Edward Said” የሚከተለውን ትንታኔ ሰጥቷል፡-

“Every intellectual has an audience and a constituency. The issue is whether that audience is there to be satisfied, and hence a client to be kept happy, or whether it is there to be challenged, and hence stirred into outright opposition, or mobilized into greater democratic participation in the society. But in either case, there is no getting around authority and power, and no getting around the intellectual’s relationship to them.” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual, Lecture 4, Reith Lectures 1993.

እንደ “Edward Said” አገላለፅ፣ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት መንግስትን በግልፅ መተቸት ነው። ከምሁራን የሚጠበቀው፣ ሁሉንም ነገር በጭፍን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መለየትና መፍትሄ የሚሹ ነገሮችን መጠቆም፣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ችግሮችን በማስታወስ ዳግም እንዳይከሰቱ ማሳሰብ እና የመሳሰሉትን በማድረግ ሕዝብለ ሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ነው።
እያንዳንዱ ምሁር በሙያዊ ገለልተኝነት ስም በስልጣን ላይ ላለ አካል ድጋፍ ሰጪ ሆኖ ከማገልገል ይልቅ በራሱ ሕሊና እየተመራ የተጣለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። ሆኖም ግን፣ ምሁራን በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ከውዝግብና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፣ ምሁራን ከአወዛጋቢነትና ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ሚናቸውን መወጣት አይችሉም።

በመደበኛው ሥራና አሰራር ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት ማህበራዊ ኃላፊነትን ካለመወጣት በተጨማሪ በስልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር በመተባበር በሕዝቡ ላይ በደል እንደመፈፀም ይቆጠራል። ምክንያቱም፣ ያለ ምሁራን ተሳትፎ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አይችልም። ምሁራን ራሳቸውን ከአወዛጋቢና ፖለቲካዊ ከሆኑ ተግባራት ባገለሉበት ሁኔታ ደግሞ ዘላቂ የሆነ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ አይችልም።
ምሁራኑ ከፖለቲካው መድረክ ገለልተኛ በመሆናቸው ምክንያት ተጎጂ የሚሆነው በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው አካል ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ የተሳነው ፖለቲካዊ ስርዓት ሕልውና ሊኖረው አይችልም። ምሁራን ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ከሆኑ በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋ ይመነምናል። በዚህ መሰረት፣ በሙያተኝነት ስም አወዛጋቢና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነፃ ሆኖ ለመንቀሳቀስ መሞከር ፍፁም የሆነ አገልጋይነት እንጂ ትክክለኛ የምሁራን ባህሪ አይደለም።

4.2 የፖለቲካ ቋንቋ

በመንግስት ሚዲያዎች፤ “የፀረ-ሰላም ኃይሎች፥ የነውጥና ብጥብጥ ቀስቃሾች፥ የሽብር ኃይሎች፥…” የሚሉት ለዛ-ቢስ አባባሎች (Cliches)፣ “ሣይቃጠል በቅጠል፥ ፀጉረ-ልውጥ፥…” የመሳሰሉ አሰልቺ ዘይቤዎች (tired metaphors)፣ እንዲሁም “ጥቂት፥ የተወሰኑ፥ አንዳንድ፥…” የሚሉ የጉብሩ-ይዉጣ አገላለፆች (lazy writing) በስፋት ይደመጣሉ። እንደዚህ ያሉት ቃላት፣ አባባሎችና አነጋገሮች እንግሊዛዊው ፀኃፊ “George Orwell” “የፖለቲካ ቋንቋ” (Political language) በማለት ይገልፃቸዋል።

ከላይ የሀገራችን ምሁራን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደረጋቸው ፍርሃት ነው። የፍርሃቱ ዋና ምንጭ ደግሞ የፖለቲካ ቋንቋ ነው። የፖለቲካ ቋንቋ በስፋት በሚነገርበት ሁኔታ ውስጥ አብዛኞቹ ምሁራን “ደጋፊ” ወይም “ተቃዋሚ” ተብለው በጅምላ እንዳይፈረጁ በመስጋት አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባሉ።

እንደ ኢትዮጲያ ባለ ሀገር ደግሞ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ከትችትና ነቀፌታ ባለፈ ለእስራትና ሞት ሊዳርግ ይችላል። ስለዚህ ምሁራን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አሰተያየት በነፃነት መግለፅ ይፈራሉ። ነገር ግን፣ George Orwell”፣ የመንግስትን አቋምና እርምጃ በይፋ ለመቃወም የሚፈሩና “ከፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ” የሚል አቋም ያላቸው ምሁራንን “un-political’ imaginative writers” በማለት ይገልፃቸዋል። እነዚህ ምሁራን ለዛ-ቢስ፥ አሰልቺና የግብሩ-ይውጣ የሆኑ የፖለቲካ ቃላትና አባባሎችን ከሚፅፉትና ከሚያነቡት የመንግስት ጋዜጠኞች ብዙም የተለዩ እንዳልሆኑ ይገልፃል፡-

“And so far as freedom of expression is concerned, there is not much difference between a mere journalist and the most ‘un-political’ imaginative writer. The journalist is unfree, and is conscious of un-freedom, when he is forced to write lies or suppress what seems to him important news: the imaginative writer is un-free when he has to falsify his subjective feelings, which from his point of view are facts. …If he is forced to do so, the only result is that his creative faculties dry up. Nor can he solve the problem by keeping away from controversial topics. There is no such thing as genuinely non-political literature.” George Orwell, Politics And The English Language, 1946.

በፍርሃት ምክንያት ሃሳብና ተቃውሞን በይፋ አለመግለፅ መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ላለው ጭቆናና በደል ድጋፍና ትብብር እንደ መስጠት ይቆጠራል። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ምሁር ለበደልና ጭቆና ድጋፉን ከመስጠት ይልቅ ፍርሃቱን መጋፈጥ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ የፍርሃቱ ምንጭ የሆነው የፖለቲካ ቋንቋ መሰረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ከመረዳት ይጀምራል። እንደ “George Orwell” አገላለፅ፣ የፖለቲካ ቋንቋ ውሸትን እውነት፣ ግድያን ክብር በማድረግና ከነጭ-ውሸት ጋር ህብረት እንዳለን ለማስመሰል የተቀረፀ ነው፡-

“Political language is designed to make lies sound truthful and murder respectable, and to give an appearance of solidity to pure wind.”

5. ምሁር እና ብሔር

በእርግጥ የምሁራን ስራና ተግባር በጎሳ፥ ብሔር ወይም ቋንቋ ሊገደብ አይገባም። ሆኖም ግን፣ የመጡበት ማህብረሰብ በጨቋኝ ስርዓት ግፍና በደል ሲፈፀምበት ገለልተኛ ሆነው ማለፍ አይቻላቸውም። ምክንያቱም፣ እያንዳንዱ ምሁር ከተወለደበትና ካደገበት ማህብረሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ከየትኛውም ሙያዊ ግዴታና ስነ-ምግባር የበለጠ ጠንካራ ነው። መሆኑም አንድ ምሁር በተወለደበት ማህብረሰብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን ወደ ጎን ትቶ ማለፍ አይቻልም።
አሁን በኢትዮጲያ እንደሚታየው ዓይነት፣ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲኖር ምሁራን በተዓማኒነታቸው ላይ ምህረት-የለሽ ከሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ። እንደ ማንኛውም ሰው ምሁራን የራሳቸው ሀገር፥ ብሔር፣ ማህብረሰብና ቤተሰብ አላቸው። ምንም ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ቢኖራቸው፣ ምሁራኑን ከቤተሰቦቻቸው፥ ማህብረሰባቸው፣ ብሔርና ሀገራቸው ጋር ከሚያስተሳስረው ተፈጥሯዊ ገመድ በላይ ጠንካራ ሊሆን አይችልም። በዚህ ምክንያት፣ ለምሳሌ በራሳቸው ብሔር ተወላጆች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭቆና ሲደርስ ከሌሎች ብሔር ተወላጆች በላይ ሊሰማቸው፣ ከወትሮው በተለየ ትችትና ተቃውሞ ሊያሰሙ እንደሚችሉ እሙን ነው።

በኢትዮጲያ ታሪክ መንግስታት ከአንዱ ወይም ከሌላው ብሔር የቋንቋ፣ ባህልና ሥልጣን የበላይነት ጋር ተያያዥነት አለው። ስለዚህ፣ የመንግስት አስተዳደራዊ ችግሮች በብሔሮች ላይ የተፈፀሙ በደሎችና ጭቆናዎች ተደርገው የመወሰድ እድላቸው የሰፋ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሕዝቦች መካከል ያለው ልዩነት ሰው ሰራሽ እንጂ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ማሳመን አለባቸው። ነገር ግን፣ በራሳቸው ብሔር ወይም ህዝብ ላይ የተለየ ጥቃትና ጭቆና ሲፈፀም ማህብረሰባቸውን በመወከል ጭቆናን መቃወምና መታገል አለባቸው። ምሁራን ስለ ሁኔታው በይፋ በመናገርና በመፃፍ ለመጡበት ማህብረሰብ አጋርነታቸውን መግለፅ ይጠበቅባቸዋል።

ነገር ግን፣ በራሳቸው ሀገር፥ ብሔር፣ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ ስለደረሰው ግፍና በደል ከመናገርና ከመዘከር ባለፈ ምሁራን ተጨማሪ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው። የምሁራን በሀገራቸው፥ ብሔር፥ ማህብረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና ከመናገር ባለፈ ተመሣሣይ በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መናገር፣ ማሳወቅ፣ መተቸትና መቃወም ነው።
የምሁር ቁልፍ መለያ ባህሪ በእሱ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ላይ የደረሰው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደገም፣ በራሱ ላይ ሲደርስ የተቃወመው ነገር በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መታገል ነው። በመሆኑም ምሁራን ለብሔርተኝነትና ወገንተኝነት ስሜት ተገዢ መሆን የለባቸውም። እንደ “Edward Said” አገላለፅ፣ ምሁራን ከተጨቆኑ ውገኖች ጎን በመቆም ትችትና ተቃውሟቸውን የማሰማት ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው፡-

“Does the fact of nationality commit the individual intellectual to the public mood for reasons of solidarity, primordial loyalty, or national patriotism? … ‘Never solidarity before criticism’ is the short answer. The intellectual always has a choice either to side with the weaker, the less well-represented, the forgotten or ignored, or to side with the more powerful.” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual, Lecture 4, Reith Lectures 1993.

6. ምሁራን እና መንግስት

6.1 በትችት ለውጥ

ምሁራን ማህብረሰባቸው ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ባላቸው አቅምና ባገኙት አጋጣሚ መረባረብ አለባቸው።ነገር ግን፣ ጨቋኙ ስርዓት ሲወገድና የሚደግፉት የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ይቀየራል።

ጨቋኝ ስርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ኃይል ስለ ቀድሞ ታሪኩ፣ አሁን ላይ ስላለው ሥራና አሰራር፣ ወይም ስለ ወደፊት አቅጣጫና ዕቅዱ ለመግለፅ አስፈላጊ የሆነ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት አሉት። ለዚህ ተግባር የተመደበ የሰው ኃይልና በጀት አለው። ስለዚህ፣ ምሁራኑ የመንግስትን ሥራና ተግባር አጎልቶ በመናገርና በመመስከር የመንግስት ቃልአቀባይ ወይም አፈ-ቀላጤ መሆን የለባቸውም።

ከዚያ ይልቅ፣ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በማህብረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጉልቶ በማውጣት የግንዛቤና አመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

በመሰረቱ ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ምሁራን በሙያቸው ችግሮችን ቀድሞ የመለየትና መፍትሄያቸውን የመረዳት ብቃት አላቸው። የፖለቲካ ስልጣን ከሚጨብጡት ውስጥ አብዛኞቹ ሕዝብን የማደራጀትና የመቀስቀስ አቅም እንጂ እንደ ምሁራን የላቀ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት የላቸውም። ለምሳሌ “John Stuart Mill” ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አመሰራረትና አሰራር በሚተነትነው መፅሃፉ የምሁራንን ድርሻና ኃላፊነት ምን መሆን እንዳለበት እንደሚከተለው ይገልፃል፡-

“….a fair sample of every grade of intellect among the people which is at all entitled to a voice in public affairs. Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business.” Representative Government, Ch.5: Page 8

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር ነው። የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው። ለዚህ ደግሞ በፖለቲካ ቡድኖች እና በምሁራን መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ይኖርበታል።

ከዚህ አንፃር፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና የሚስተካከሉበትን የመፍትሄ ሃሳቦችን በመጠቆም ነው። የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከምሁራን የተሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው የሀገሪቱንና ሕዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል የፖለቲካ አመራር መስጠት፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ስርዓቱን ማሻሻል ነው።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ በመንግስት ሥራዎችና አስራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ይስተካከላሉ። መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። ስራና አሰራሩ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ይኖረዋል። የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጡ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ይሆናል። ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ይኖራል። ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለዘላቂ ልማት፣ ለአስተማማኝ ሰላም እና ለዳበረ ዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል።
በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ምሁራን ሕግ አውጪዎች የሚያፀድቋቸውን አዋጆች፣ የሕግ አስባሪዎች አሰራርና የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነትን፣ የሕግ አስፈፃሚዎች የሚያሳልፏቸውን የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች፣… በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሥራና አሰራርን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከሙያው አንፃር መተንተን፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያነሱ መወያየትና በመንግስትና ሕዝቡ ዘንድ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ፣ መሰረታዊ ችግር ያለባቸው አዋጆች፥ እቅዶችና ውሳኔዎች በተለያዩ የመንግስት አካላት ተግባራዊ ሲደረጉ እያዩ በዝምታ የሚያልፉ ሰዎች እንደ ምሁር የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እየተወጡ አይደለም። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ምሁር ያለውን ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በተለይ የመንግስትን ስራና አሰራር የመተቸት ማህበራዊ ግዴታና ኃላፊነት አለበት።

6.2 በድጋፍ ውድቀት

በእርግጥ እንደ ማንኛውም ዜጋ ምሁራን የመንግስት ስልጣንና ኃላፊነት ተረክበው መስራት ይችላሉ። ይህ ሲሆን እንደ ባለስልጣን የመንግስትን ሥራና ተግባር ደግፈው ሃሳብና አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። የመንግስት ተሿሚ ወይም ባለስልጣን ካልሆኑ ግን ምሁራን ራሳቸውን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት መለየት ይጠበቅባቸዋል።

ምሁራን በዜጎች ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የመንግስት ስራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉት፣ በአጠቃላይ እንደ ምሁር የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉት ራሳቸውን ከመንግስት ሲነጥሉ ነው። ልክ እንደ የመንግስት ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን በማጣጣል የመንግስትን ጥሩ ምግባር አጉልተው ለማውጣት የሚጥሩ ከሆነ፣ በሕዝብና መንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። ምሁራን በደጋፊነት ስም ራሳቸውን ከመንግስት ጋር ማጣበቃቸው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት “John Stuart Mill” እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“….There are no means of combining these benefits except by separating the functions which guarantee the one from those which essentially require the other; by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs, and devolving the former on the representatives of the Many, while securing for the latter, under strict responsibility to the nation, the acquired knowledge and practised intelligence of a specially trained and experienced Few.” Representative Government, Ch.5: P.59

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን፤ የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄዎችና ቅሬታዎችን እንዳይሰማ፣ እንዲሁም የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ምሁራን የመንግስትን እርምጃዎችን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሙያተኝነት ስም ገለልተኛ መስለው ለማለፍ መሞከራቸው በራሱ በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን እንደመደገፍ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በገለልተኝነት (neutrality) ስም መንግስትን ከመተቸት የሚቆጠቡ ምሁራን “የመንግስት ደጋፊ ነን” ከሚሉት በምንም የተለዩ አይደሉም። ምክንያቱም እንደ ምሁር ከማህብረሰቡ የተጣለባቸውን ግዴታና ኃላፊነት አየተወጡ አይደለም።

ስለዚህ ሁሉም ምሁራን በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስከትሉትን ጭቅጭቅና ውዝግብ በመፍራት ማህበራዊ ግዴታቸውን የማይወጡ፣ በተለይ ደግሞ የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን እያጣጣሉ፣ የመንግስትን ስራና ተግባር እያጋነኑ የሚያቀርቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎች በላይ የመንግስት ጠበቃና ደጋፊ ለመሆን መጣር ፍፁም ኣላዋቂነት ነው።

ምሁራን መንግስትን በመደገፍ ወይም በመፍራት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስርዓቱን ከመተቸት ይልቅ የመንግስት ቃለ-አቀባይ ከሆነ፣ በሌላ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት የአስተዳደር ሥራቸውን ከመስራት ይልቅ የምሁራኑን ሃሳብና ዕውቀት፥ ዓይነትና ይዘት መወሰን ከጀምሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይጨናገፋል፣ አምባገነናዊ ስርዓት ይነግሳል።

ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ከመግለፅ የሚቆጠቡ ወይም ደግሞ መንግስትን ለማሞገስ የሚታትሩ ሰዎች እንደ “ምሁር” ያለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ በአግባቡ መወጣት የተሳናቸው ናቸው። ምክንያቱም አምባገነኖች የፖለቲካ ስልጣን የሚጨብጡት የእነሱን ዝምታና ፍርሃት በመጠቀም ነው።

በአጠቃላይ በአንድ ሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚጠፋው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ሲጣስ ነው። የዜጎች መብትና ነፃነት የሚጣሰው ደግሞ ምሁራን በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋለውን ክፍተት መለየትና መተቸት፣ እንዲሻሻል ጥረት ማድረግ ስለተሳናቸው ነው። ስለዚህ የዜጎች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው ምሁራን ከመደበኛ ሥራና ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የተጣለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ በአግባቡ መወጣት ሲችሉ ነው።