የደቡብ ክልል ከ’አሸናፊ ደጋፊነት’ ያልዘለለ የ’ፋርዳ’ ፖለቲካና መዘዙ!

በፈቃዱ በዛብህ
‘ሀዋሳን ማዕከል አድርጎ የሚዘውረው የደቡብ ክልል ፖለቲካ በአሀዳዊ እና ፌዴራላዊ ስርዓት መንታ መንገድ ላይ የሚዋዥቅና አሸናፊን ከመደገፍ ያልዘለለ ሚና ያለው ሆኖ እስከመቼ ይዘልቅ ይሁን? ፤ የ’Scientific’ ፌደራል ሥርዓት አወቃቀር አጥኚ ቡድን ውጤትስ ከክልሉ የወደፊት ህልውና እጣ ፈንታ ጋር ተያይዞ ምን አይነት አንደምታ ያለው ሪፖርት ይዞ ይወጣ ይሁን?’ የሚሉት ጥያቄዎች ለውጡ በክልሉ ከፈጠረው ስሜት እና ተስፋ አንፃር አንገብጋቢ መልስ የሚሹ በመሆን ነጥረው ወጥተዋል::

የአሁኑ የደቡብ ክልል ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ እና ካሉ የገዢ መደቦች እና ስርዓቶች አንጻር ሲታይ ከrole-playing game ሚና ብዙም የዘለለ አይደለም፡፡ ክልሉ በሀገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶችና መስተጋብሮች በአሀዝ ደረጃ ሲታይ ያለው አበርክቶት ቀላል ባይሆንም በሁሉም የመንግስት ስርዓቶች ማለት በሚያስችል ሁኔታ ከተጠቃሚነት እና ተጽእኖ ከመፍጠር አንጻር ሲታይ በጎደለ ከመሙላት ያለፈ ስራ ሲሰራ እምብዛም አይታይም፡፡ ለዚሁም አይነተኛ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በሚደረግ የኢኮኖሚ ፍልሰት የክልሉ ተወላጆች ሁኔታ ተለይቶ ቢታወቅም ይህንን ለመቅረፍ እና የስራ እድልን ከመፍጠር አኳያ በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግስት የሚደረጉ የትልልቅ ፕሮጀክቶች ሁኔታ (ኢንዳስተሪ ፓርክን ጨምሮ) ከፍላጎት ይልቅ ወደ ተደማጭነት ያጋደሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

ይህ እውነታ አንድ ነገር አስታወሰኝ:: ልጅ ሳለን ተቧድነን ኳስ ስንጫወት ቁጥራችን ጎድሎ ከሆነ አንድ ሰው ኳስ ለያዘው ቡድን እንዲያገለግል ሆኖ ይሰየማል፡፡ ሌላኛው ቡድን ኳስ ሲይዝ ደግሞ ይኸው ልጅ አሰላለፉን ቀይሮ በተቃራኒው ይጫወታል፡፡ ይህ “ፋርዳ” ተጫዋች ቶሎ ቶሎ ከሚቀያየረው ሚናው እና የጨዋታው ባህሪ የተነሳ የማን እነደሆነ እስኪቸገር ግራ ይገባዋል፡፡ ‘የኔ ነው’ የሚለው ወዳጅም ጠላትም ያጣል ማለት ነው፡፡ ‘A friend of all is a friend of none’ አንዲሉ ማለት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ብዙ ቦታ አካሎ እንዲጫወት ብዙ ትንፋሽ እና ጉልበት ቢጠበቅበትም በምንም ሁኔታ ግን ‘ጎል ማግባት’ አይፈቀድለትም ነበር፤ ካገባም እንደ ጎል አይቆጠርለትም ነበር:: የደቡብ ክልል የ’ፋርዳ’ ፖለቲካም ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት ይሁን ዛሬ ላይ ከዚህ የተለየ ሚና ሲኖረው አይታይም::

እስከ አሁን የነበሩ ስርዓቶች በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ህዝቦች ላይ ትተው ያለፉትን የአሉታዊ ተጽእኖ ትርክትን ለታሪክ ትተን አሁን በሀገሪቷ ላይ ያለውን ብሔር ተኮር የፌዴራል ስርዓትን እንኳን ብንመለከት ከነጉድለቱ ክልሉ ላይ ሲደርስ ሊተገበር የማይቻልበት (የማይፈቀድበት) ሁኔታ የመሬት ላይ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ በኢህአዴግ የሚመራው ‘አንጃ’ ክልሉ ላይ በፖለቲካ ተሳትፏቸውም ይሁን ለገዢው መንግስት እና ፓርቲ ባላቸው የፖለቲካ ታማኝነት እየተሰፈረ በሚሰጥ ይሁኝታ የጥቂት ብሄሮች የስልጣን ውክልና እንደ ዋነኛ መሳሪያ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡ ይበልጥ ትክክለኛ ለመሆን ያክል ደግሞ (To be politically more correct) በአብዛኛው የአንድን ብሔር የፖለቲካ የበላይነት በግብር በሚያንፀባርቁና በስልጣን ክፍፍሉም በግልፅ ይህንኑ እውነታ በሚወከሉ ካድሬዎች የፖለቲካ የግል ጥቅም ከሚመነጭ ታማኝ አስፈፃሚነታቸው የተነሳ ከማዕከላዊ መንግስት በሚጫንባቸው የስልጣን መዘውር ክልሉ በተፈለገበት ሲሾር የነበር ሲሆን አሁንም የቀጠለበት እውነታ ነው ያለው::

ይህ አሰላለፍ ከተሽዋሚዎች የግል ጥቅም በዘለል እንወክለዋለን (ይወክሏቸዋል) ለሚሉት ሕዝብ ባይጠቅምም ከገዢው ስርዓት ፍላጎት እና ጥቅም አንጻር ሲታይ ግን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ክልሉ በአንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ሆኖ ስርዓቱን እና ግለሰብ ተሹዋሚዎችን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታዎች በገሀድ እየተቀየሩ ከመጡበት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ለውጡ እና ለውጡ ይዟቸው የመጡት ያልተለመዱ ነገሮች ግን የክልሉ ህዝብ ከተፈጥሮኣዊ እና ታሪካዊ ባህሪው በተቃረነ በሚመስል መልኩ ልዩነትን ፈላጊ እና ጠያቂ አድርጎት በሁሉም ማህበረስብ መግባባት ላይ ያልተደረሱ አንድነቶችን (False harmonies) ተፈታትኖ በሚያሳዝን ሁኔታ የብዙ ንፁሀን ዜጎች ሕይወት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በአሳዛኝ ሁኔታ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም ሳያንስ የዚህ እኩይ ተግባር አስፈጻሚ እንደነበሩ በመንግስት የተነገረባቸው ሰዎች በክልሉ መነግስት ሹመት እንዲያገኙ ሆነው ሁሉንም ሰው ግራ አጋብቷል፡፡

አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ የአንድነት እና የፌደራል ስርዓቶች ከሁሉም ጎልተው የወጡ የወደፊት አማራጮች መስለው ቢታዩም ቅሉ የየስርዐቶቹ ደጋፊዎች በአብዛኛው እና በሚያስገርም ሁኔታ ውክልናቸው ብሔር ተኮር መሆኑ ለደቡብ ክልል አሁንም ከለመደው ‘አሸናፊን ከመደገፍ’ ሚናው በዘለል ሶስተኛ አማራጭ ይዞ ለመቅረብ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ይሆኑበታል፡፡ ይህ የፍላጎት እንዲሁም የአቅም ውስንነትን ያጠቃልላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በውስጡ ያሉ የተለያዩ ብሔሮች ባላቸው ታሪካዊ ፤ ባህላዊ እንዲሁም የዘውግ አረዳድ ተዛምዶ እና ተቃርኖ ከሁለቱ አሰላለፎች ጎራ በአንዱ እንዲሰለፉ ይጠበቃል፡፡ ይህም የክልሉን ሕዘቦች በራሳቸው ሀሳብ ከመሰባሰብ ይልቅ ለነገሰ እነዲያጨበጭቡ ይገፋፋቸዋል ይከፋፍላቸዋልም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ከተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ተሰጥቶት የፌደራል ስርኣቱን እንዲያጠና የተላከው የ“Scientific” ጥናት ቡድን ውጤት በሀገሪቷ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ እና በደቡብ ክልል በተለይ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ውጤት በጉጉት ይጠበቃል፡፡

One thought on “የደቡብ ክልል ከ’አሸናፊ ደጋፊነት’ ያልዘለለ የ’ፋርዳ’ ፖለቲካና መዘዙ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡