ኢህአዴግ በሚመሠረተው “አገር-አቀፍ” ፓርቲ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሊካተቱ እንደሚችሉ ተገለጸ

ዮሃንስ አንበርብር (ሪፖርተር)

በኢሕአዴግ ውሳኔ ብቻ የሚመረጥ የአገር መሪ የመሰየም አካሄድ እንደሚያበቃና የአጋር ድርጅቶች ሲያነሱ የቆዩት የፓለቲካ ውክልና ጥያቄም በዚህ እንደሚመለስ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ … ፓርቲ እያልን አንሄድም። እንደ ኢሕአዴግ ከጫፍ ጫፍ ያሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በነፃነት የሚሳተፉበት አንድ አገራዊ ፓርቲ እንመሠርታለን፤›› ብለዋል።

ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ የኢሕአዴግንና የአጋሮቹን ውህደት በተመለከተ የተከናወነው ጥናት መጠናቀቁን ገልጸው፣ በጥናቱ የተለዩት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ሁሉም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች በቅርቡ ከሚመሩት ማኅበረሰብ ጋር በተናጠል ውይይት ማድረግ እንደሚጀምሩ አስረድተዋል። በውይይት ከዳበረ በኋላም መሟላት የሚገባውን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ በዓመቱ መገባደጃ ላይ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት የሚያስችለው ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል።

በኢሕአዴግና በአጋሮቹ ውህደት በሚወለደው አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ መካተት እንደሚችሉ፣ ለዚህም ኢሕአዴግ በሩን ክፍት እንደሚያደርግ አቶ ሳዳት ገልጸዋል።

በሚመሠረተው አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ ማሟላት የሚጠበቅባቸው፣ የኢሕአዴግን መሠረታዊ ባህሪያት መቀበል እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢሕአዴግና አጋሮቹ የሚያደርጉት ውህደትም ነባር የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባህርያትን ሳይለቅና እነዚህን መሠረታዊ ባህሪያትም ለሚመሠረተው አገር አቀፍ ፓርቲ በማውረስ የሚፈጸም መሆኑን ገለጸዋል፡፡ የብሔርና የቋንቋ ማንነቶች፣ እንዲሁም የፌዴራሊዝም ሥርዓት መርሆች ተጠብቀው፣ ከሚቀጥሉት የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባህርያት መካከል ዋናዎቹ መሆናቸውን ለአብነት ጠቁመዋል።