የለውጥ ኃይሉ መደናበር፤ የጭፍን ደጋፊዎች እዬዬ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፍዘት!

በአቶ ያሬድ ሃይለማሪያም

ባለፈው ሳምንት በግልጽ እንድንወያይባቸው ሁለት ለውጡን እየተፈታተኑ ስላሉ ኃይሎች የራሴን ሃሳብ አካፍዮ ነበር። ዛሬም ግልጽ ውይይትን የሚፈልጉ እና ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡ አገራዊ ጉዳዮችን ለውይይት ማንሳት እፈልጋለሁ።

፩. የለውጡ ኃይል

የለውጥ ኃይሉ በብዙ ነገሮች እየተነቀፈም፤ እየተሞካሸም እዚህ ደርሷል። ሕዝብ ለዚህ ኃይል ከወራት በፊት ይሰጥ የነበረው ድጋፍ እና የነበረው አመኔታ እጅግ እያቆለቆለ መምጣቱን በግልጽ ማይት ይቻላል። ለምን? ትላንት እዝጌር ከሰማ አመጣልን የተባሉት የለውጡ መሪዎች ዛሬ ቀላል የማይባል ተቃውሞን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እያስተናገዱ ነው። ሕዝብ ለምን እምነት ማጣት ጀመረ? ለምንስ ብዙዎች ከደጋፊነት ወደ ተቃዋሚነት እንዲህ በአጭር ጊዜ አመሩ? የሚሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ ማየት የግድ ይላል። የሕዝብ አመኔታ እየሸረሸሩ ከመጡት የለውጡ ኃይል የክሽፈት ምልክቶች መካከል የተወሰኑትን ማንሳት ይቻላል፤

 • ለውጡን የሚመራው አካል ኢትዮጵያን በአንድነት ለማቆየት እና ጠንካራ አገር ሆና እንድትቀጥል ያለውን ህልም እና ታላቅ እራይ በተለያዩ መንገዶች ቢገልጽም መሬት ላይ ያሉ እና ጎልተው እየወጡ ያሉት እውነታዎች ተቃራኒውን መሆኑ እንደ አንድ ዋና ምክንያት ሊገለጽ ይችላል። አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተከፋፈልች መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ሥርዓቱ ይዞት የመጣው የብሔር ፖለቲካ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ክልሎች አገር ሆነዋል። እያንዳንዱ ክልል ከታጣቂ ኃይል አንስቶ እስከ መንግስታዊ አወቃቀር ድረስ የያዙት ቅርጽ በአገር ውስጥ የተፈጠሩና አይደፈሬ የሚመስሉ ትናንሽ አገሮች አድርጓቸዋል።
 • ይህ ብቻ ሳይሆን ክልሎቹ ወይም እነኚህ ትናንሽ አገሮች እርስ በእርሳቸው እና ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት ቅጣንባሩ የጠፋበት ሆኗል። የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደር እንደልቡ የማያዝባቸው ወይም በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ሥልጣን ያጣባቸው ክልሎች ተፈጠዋል።

 • ይህ በክልሎች መካከል ጎልቶ እየታየ ያለው ጤናማ ያልሆነ ፉክክር እና ግብግብ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ውጥረት ከማባባሱም ባሻገር አንዳንድ ሕገ ወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎችም እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።

 • በክሎች መካከል የሚታየው ፉክክር እና መገፋፋት ከድንበር ግጭቶች መበራከት አንስቶ የማህበረሰቡ አሰፋፈሮችን እያዛባ ይገኛል። ለዚህም በትግራይ እና በአማራ ክልል መካከል ያለውን ውጥረት እንዲሁም በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል እንዲሁም ፤ በደቡብ ክልል በአንዳንድ ስፍራዎች የተፈጠሩtን ግጭት ማንሳት ይቻላል።

 • በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ቅራኔዎችን፣ ግጭቶችን እና መፈናቀሎችን ለፖለቲካ ትርፍ የሚጠቀሙ የአገዛዙ አካላት መኖራቸው ደግሞ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ተናገሩት የተባለው ነገር እንደ ትርጓሜው ከሆነ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው እና ለውጡን ይመሩታል በሚባሉ ሰዎችም ጭምር እንዲህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው እና ከባድ ስህተት መፈጸማቸው ሕዝብ በለውጡ ሂደት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደርጋል።

እዚህ ላይ በግልጽ ለማስቀመጥ የአቶ ለማ ትልቁ ስህተት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እና ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔርት ተወላጆችን አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ማስፈራቸው ሳይሆን ከዚህ እርምጃ ጀርባ ያለው ምክንያታቸው የማህበራዊ ምህንድስና እቅዳቸው አካል መሆኑ ነው። እንደ ንግግራቸው ከሆነ የሰፈራው ዋና አላማ የዜጎችን ህይወት መታደግ ላይ ያነጣጠረ የበጎ አድራጎት ሥራው ሳይሆን በወደፊቱ የከተማዋ ፖለቲካ ላይ የሚፈጥረውን እንድምታ ተቀዳሚ ምክንያት ማድረጋቸው ነው።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ሥፍራ ሂዶ የመኖር መብት ስላለው ሰዎቹ ወደዚህ ሥፍራ እንዲመጡ መደረጉ በራሱ በምንም መልኩ ስህተት ሊሆን አይችልም። የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ ለእንዲ ያለ የፖለቲካ ግብ ማስፈጸሚያ ነት ለማዋል መታሰቡ እና ይህ አይነቱ ጠባብ እና ነውረኛ አስተሳሰብ ተፈጻሚ የሆነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ድጋፍ ካገኙት ከአቶ ለማ መገርሳ መሆኑ በለውጡ ኃይሎች ላይ ሕዝብ አሳድሮት የነበረውን ትልቅ እምነት የሚሸረሽር ነው። እንደ አቶ ለማ አገላለጽ ክልሉ እነዚህን ተፈናቃዮች በሚኖሩበት አካባቢ ወይም አቅራቢያ ስፍራ ላይ ሊያሰፍር የሚችልበት እድሉ እና ምቹ ሁኔታ ቢኖርም የአዲስ አበባን የፖለቲካ አቅጣጫ ለማቀየር እርዳታ በሚሹ ወገኖች ላይ መዶለት ሰብአዊነት የጎደለው እና አሁንም አገሪቱ በሸር ፖለቲካ መተብተቧን ነው ይሚያሳየው።

በአገሪቱ በርካታ ክፍሎች በመቶ ሺዎች እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎችስ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

 • ሌላው የለውጥ ኃይሉ የሚወቀስበት አንዱ እና ዋነኛ ነጥብ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሕግ እና ሥርዓትን በአግባቡ ማስፈን እና ማስከበር አለመቻሉ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ለዘላቂ ሰላም በሚል ሕግና ሥርዓት ሲፋለሱ መንግስት የሚያሳያቸው ትዕግስቶች ቀላል ያልሆነ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ኪሳራ አስከትሏል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጠንከር ያለ እና አንዳንዴም ከልክ ያለፈ የኃይል እርምጃ ሲወስዱ ተስተውሏል።
 • ለሕዝብ ጥያቄዎች፣ ሕዝብን ስጋት እና ጥርጣሬ ላይ ለጣሉ ጉዳዮች አፋጣኝ የሆነ ማብራሪያ እና ምላሽ አለመስጠት፤ በተወሰኑ ጉዳዮችም ላይ ነገሮችን መሸፋፈን፤

 • በለውጥ ኃይሉ እና ለውጡን ይገፉ በነበሩ አንዳንድ ኃይሎች መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽ አለመሆኑ እና የመንግስትን ሚና አንዳንድ ጎልተው የወጡና አይነኬ የሚመስሉ ግለሰቦች ሲከውኑ ማየት። አልፎ አልፎም የለውጥ ኃይሉን ያንቀሳቅሱ የነበሩ ሰዎች እና ቡድኖች ከሕግ በላይ፣ ከመንግስት ተሿሚዎች በላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው መታየት እና ለሚያከናውኗቸውም ተግባራት ተጠያቂ አለመሆን፤

 • ላላፉትን በርካታ አመታት ሰብአዊ መብቶችን በመጣስ የጎላ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎችን ተጠያቂ በማድረግ እረገድ ግልጽ የሆነ እና ወጥነት ያለው አሰራር አለመከተል። ያልተደመረ ይከሰሳል፣ ይታሰራል ወይም የእስር ማዘዣ ይወጣበታል፤ የተደመረን ማን ይነካዋል የሚመስል እና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና ግብተአዊ የሚመስል አካሄድ፤
  አንድ ሰሞን የመብት ጥሰት የፈሰሙ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና ተጠያቂ የማድረጉ እርምጃ ዛሬ ወሬውም የለም። ዋና ዋናዎቹ የመጥ እረጋጮች በቁጥጥር ስር ዋሉ ወይስ ጉዳዮ ለፖለቲካ ግብ መጠቀሚያነት ያለው ፋይዳ አከተመ?

 • በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እና ጥሰት አድራሽ የሆኑ አካላትን ጉዳይ የመሸፋፈን እና ነገሮችን የማድበስበስ አዝማሚያ ተደጋግሞ መስተዋሉ። ለዚህም በቡራዩ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተደረገው ጭፍሸፋ በአግባቡ በገለልተኛ ወገን ሳይጣራ መቅረቱ እና ታስሩ በተባሉት አጥፊዎች ላይ እየተወሰደ ያለውም ሕጋዊ እርምጃ ከሕዝብ ጆሮ መራቁ። እንዲሁም በቅርቡ በለገጣፎ የተፈጸመው ዜጎችን የማፈናቀሉ እርምጃ በአካባቢው ባለሥልጣናት መበረታታቱ፤

 • በእዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የለውጡ ኃይል ከሕዝብ አግኝቶት የነበረውን ድጋፍ እና ቅቡልነብት በተወሰነ ደረጃ እያጣ የመጣ ይመላል። ከአሥር ወር በፊት የአብይን እና የለማን ቲሸርት ለብሰው ለድጋፍ በየአደባባዩ የወጡ ሚሊዎኖች ዛሬም በዛው መጠን መኖራቸው እጅግ ያጠራጥራል።

  ፪. የለውጥ ኃይሉ ደጋፌዎች

  ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢፈታተኗቸውም የለውጥ ኃይሉን አሁንም በሙሉ ልብ የሚደግፉ ብዙዎች ናቸው። ገሚሱ አሁንም በዚህ ኃይል ላይ ተስፋ አንቆርጥም፤ እነዚህ ችግሮች በሽግግር ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳራቶች ናቸው። ይህን ለውጥ ችግሮቹን እያረምን ልናስቀጥለው ይገባል። ከዚያ የተሻለ አማራጭ የለንም። ኢትዮጵያኝን ከከፋ አደጋ ለመታደግ እና እንደ አገር እንድትቀጥል ለማድረግ ያለው ቀሪ እና ብቸኛ አማራጭ የለውጡን ኃይሉ ችግሩቹን እየነቀስን እና እንዲታረም ጫና እያደረገን ድጋፋችን እንቀጥል የሚሉ ናቸው። እኔም የዚህን ጎራ እሳቤ እጋራለሁ።

  ሁለተኛው ኃይል በውስጡ የተጠናወተው የካድሬነት ባህሪ አለቅ ያለው እና መንግስት ምንም ይስራ ምን ሊወቀስ አይገባውም ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚሟገት ኃይል ነው። አብይን ወይም ለማን የተቸ የኦሮሞ ጠላት ነው ይልሃል ሲፈልግ። ወይም ደብረጺዎንን ወይም ገዱን የነካ የትግሬ ወይም የአማራ ጠላት ነው ብሎ ያስባል። ይህ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ከቆየው የካድሬነት ባህሪ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። ከእኔ ድርጅት ወይም ከእኔ መሪ ውጭ ያለው መንገደ ሁሉ ሞት ወይም ገደል ነው ብሎ እንደ ተሰገረ በቅሎ የፊቱን ብቻ እያየ የሚያስብ ሰው ሙግት ነው። እንዲህ ያሉ ደጋፊዎች አደናጋሪ ከመሆናቸውም በላይ ለዲሞክራሲያዊ ባህል እድገጥ ጠንቆች ናቸው።

  ፫. ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች

  የተቃዋሚዎቻችን ነገር ዛሬም በቅጡ ሊፈተሽ ይገባል። ከብዛታቸው እና ከጥራታቸው ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ነገር ለጊዜው ወደጎን ልተወውና የለውጡን አቅጣጫ በማስመር እረገድ ያላቸውን ሚና መፈተሽ ተገቢ ነው። እስከ አሁን ድረስ ይህ ለውጥ ምን አቅጣጫ ይዞ መሄድ እንዳለበት የራሱን ፍኖተ ካርታ ነድፎ ሕዝብን ለማሳመን፣ ለማነቃቃት እና በመንግስት ላይ በጎ ጫና ለመፍጠር የተንቀሳቀሰ ኃይል እንብዛም አልተመለከትኩም። አብዛኛዎቹ ድርጅቶች መንግስት በቀደደላቸው ቦይ እንድ ጅረት እየፈሰሱ ይመስላል። በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ምን መልክ መያዝ እንዳለበት የሃሳብ እና የድርጊት ቅደም ተከተሎችን አስቀምጦ መንግስት ይህን የሽግግር ወቅት በዚህ አቅጣጫ ሊመራው ይገባል ብሎ ምክር እና ንድፈ ሃሳቦችን እንደ አማራጭ ያቀረበ ኃይል መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። ካለም ሕዝብ ሊያውቀው እና ሊወያይበት ይገባል። ሁሉም ኃይሎች ማለት ይቻላ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዙርያ ተኮልኩለው ዋነኛ ትኩረታቸውን ቀጣዩ ምርጫ ላይ ያደረጉ ይመስላል።

  በእኔ እምነት ቀጣዩ ምርጫ ብዙ የሚጓጓለት ነገር ይዞ ይመጣል ብዮ አላስብም። ግን አንድ ትልቅ ምዕራፍ ዘግተን ሌላ አዲስ እና ብሩህ የፖለቲካ ምዕራፍ የምንከፍትበት ይሆናል የሚል እምነት ግን አለኝ።

  በቸር እንሰንብት!