ዘረኝነት እና ኢትዮጵያ፦ በብሔር ላይ የተመሠረተው የፌደራሊዝም ስርዓት ዘረኝነትን ያስቀጥላል!

በነገሠ ጉተማ

“ሰው መሆን ከዘር ይቀድማል። ስንወለድ ቋንቋ አልነበረንም። ሰው ሆነን ነው የተወለድነው። ኢትዮጵያዊነት የማይገባቸው አሉ። እንዚህ ራሳቸውን ስለማያከብሩ ሌላውንም አያከብሩም። ዘረኝነትን የሚሰብኩ ሰዎች ውስጣቸው ፍቅርና ክብር ለራሳቸው የሌላቸው ናቸው።” አቶ ኦባንግ ሜቶ።
ኢትዮጵያ – ከብዙ አንድ (E pluribus unum)

ኢትዮጵያ የዘውጎችና የባህሎች ውቅር

ኢትዮጵያ ታድላለች። ከ87 ባላነሱ ዘውጎች ተሞልታለች። በባህልና በቋንቋ ቀለሞች አሸብርቃለች። እንደኢትዮጵያ የታደሉ ሀገሮች በዓለም ላይ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ባለብዙው ዘውጎችና ባሕሎች የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች አብሮ ተቋቁሞ፣ ተከባብሮ ፣ተጋብቶና ተዋልዶ፤ አብሮ በልቶ፤ አብሮ ጠጥቶ፤ አብሮ ተርቦ፤ አብሮ ስቆ፤ አብሮ አልቅሶ፤ አብሮ ጨፍሮ፤ አብሮ ሞቶ፤ አብሮ ተቀብሮ፤ አብሮ ጠላትን ተጋፍጦ ደሙን አፍስሶና አሸንፎ የኖረ ሕዝብ ነው።

በኢትዮጵያ ባህሎች ተደበላልቀዋል፤ ቋንቋዎች ጉራማይሌ ሆነዋል፤ እምነቶችም ይፈራረቃሉ። ሆኖም ጠላቶቻችን እና ወራሪዎቻችን ልዩነቶቻችንን እንጂ አንድነታችንን ባለመገንዘብ ሊቀራመቱን ያልሞከሩበት ጊዜ የለም። እንግሊዝ ከግብጾች ጋር አብራ ያደረገችንን የአሉላ አባ ነጋ ጀግንነት ይመሰክራል (1)። ጣሊያን በባለብዙ ዘውግ አርበኞች አባቶቻችን አድዋ (2) ላይ ተዋርዳ የተሸነፈችበትን ቁስሏን ለአርባ ዓመታት ስታመግል ቆይታ ጊዜዋን ጠብቃ የመከፋፈልና ቀጥቅጦ የመግዛት ሕልሟን ለመተግበርና ቅኝ ለመያዝ መጥታ የአምሥት ዓመታት ሰቆቃና የዘረኝነት አረም ትታልን ተመለሰች (3)።

ህወሀትም ጣሊያን ካቆመችበት ቀጥላበት የዘር መርዝ ፈትፍታ ቋቅ እያለን አግታናለች። እኛም ተገደን መርዙን ጠጥተን እርስ በርስ ስንገዳደርና ስንፈላለም ሁኔታውን አመቻችተንላት እንደልቧ እንድትዘርፍና ቀጥቅጣ እንድትገዛን አስችለናታል። ባለፉት 27 ዓመታት ህወሃት ያሰራጨችውን የመለያየት ቁስል አድኖ የሕዝብ ለሕዝብ እምነትን መልሶ ለማጠንከር ጉዞው ውጣ-ውረድና ተግዳሮቶች የተሞላበት መሆኑን አሁን እያየነው ነው። ሕዝቡ ከልቡ አንድ ለመሆን የሚፈልገውን ያህል ከሥር ከሥሩ የሚቦረቡሩትና ዘረኝነትን የሚሰብኩ ጠባብ ድርጅቶችና ጥቅማቸውን ሕዝብ በመነጣጠል ላይ የመሰረቱ ቡድኖች ሊያሰናክሉት ይታገላሉ። ይህንንም ለማከናወን በተዘረጋው መርበብ ተጠቅመው የመከፋፈል ተግባራቸውን ቀጥለዋል። ይህንንም ጥቃት ለማክሰም በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ የመሆን ፍላጎት ላይ ተመርኩዘን የመተማመን፣ የፍቅርንና የአንድነት መንገድን ማዘጋጀት አለብን። ይህንንም አሁኑኑ መጀመር አለብን።

ዘረኝነትን የምናጠፋው በፍቅርና በሰላም ብቻ ሳይሆን የዘረኝነት አቀንቃኞችን ከነፖሊሲዎቻቸው ከስልጣን በማስወገድ የሕዝቡን የፖሊቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሕብረተሰባዊና ባህላዊ አኩልነት የሚያረጋግጡ ዴሞክራሲያዊ መዋቅሮችን በመፍጠር ነው።

አድዋ

የአድዋ ጦርነት ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ዘውጎች ትግል ውጤት ነው። የሁሉም ዘውጎች ደም ፈሷል

እኛን ኢትዮጵያውያንን ከሁሉም በላይ ታላቅ ከሚያደርጉን ብዙ ባሕሪዎቻችን አንዱ፣ ከሌሎች ሃገሮች በዘረኝነትና በሌሎች እኩይ ተግባራት ሰቆቃ ለደረሰባቸው እጆቻችንን ዘርግተን ተቀብለን ተዋህደን አንድ ሕዝብ የመሆን ችሎታችን ነው። ከታሪክ እንደምንማረው የነብዩ መሐመድ ቤተሰብ (4)፣ የአውሮፓ አይሁዶች (5)፣ ግሪኮች፣ አርመኖች እና ሌሎችም በዘርም ሆነ በሌሎች እኩይ ምክንያቶች ሊያጠፉዋቸው ከሞከሩ አምባገነኖች ሸሽተው ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ መኖርያ ያገኙት ኢትዮጵያ ነው። ከግሪክ አገር የፈለሱና ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ ተቀብላቸው የራሷ ዜጎች ያደረገቻቸው የፋኑሪስ ቤተሰብ ልብ የሚነካ ታሪክ መስቀል በተባለው መጽሐፍ ተዘግቧል። የፋኑሪስ ቤተሰብ ወደኢትዮጵያ የተሰደደው አባታቸው በመጀመሪያ የስደተኞች መናኸሪያ ተብላ ወደምትታወቀው አሜሪካ አገር ተሰዶ በተጓዘበት መርከብ ላይ በተላለፈበት በሽታ ምክንያት አሜሪካን እንዳይገባ ተከልክሎ ኤለስ አይላንድን ሳይረግጥ በመጣበት መርከብ ወደሐገሩ ከመለሱት ብኋላ ነው (6)። ይኸው እኛም ለሌላው እንተርፍ የነበርነው አሁን በተራችን በዘረኝነት መርበብ ተጠልፈን እየተላለቅን እንገኛለን። ይህን ፅሁፍ ሲዘጋጅ በሐረር፣ በደቡብ ሕዝቦች ክልል፤ በቤኒሻንጉልና አካባቢው ከፍተኛ የዘውጎች ግጭቶች የብዙኃን ህይወቶችን እያጠፉ ናቸው።

ዘረኝነት ምንድነው?

የዘረኝነት ትርጉምና አተገባበር ብዛትና ስፋት አለው። በቀላል ትርጉሙ ዘረኝነት አንድ ዘር ወይም ዘውግ ወይም የህዝብ ክፍል በራሱ የበላይነት አምኖ ሌላውን ዘር ወይም ዘውግ በቋንቋው በመልኩ ወይም በተለየ ዘርነቱ ከራሱ ዝቅ አድርጎ አንቋሾና አጥላልቶ የሚያይበት ርዕዮተ ዓለም ነው። በዚህም መልኩ ዘረኝነት አድልዎንና በአይነ ጭፍን አግልሎ መፍረድን ያመጣል (7)።

ዘረኝነት ሰፋ ባለው ትርጉሙና ተልእኮው ሲታይ፤ የገዢው ወይም የልሂቃኑ ክፍል ከላይ የተጠቀሱትን የዘር፣ የዘውግ፣ የቋንቋ ልዩነቶችን በመጠቀምና በመከፋፈል የራሱ ዘር ወይም ዘውግ ያልሆነውን ሕዝብ ዝቅ አድርጎ በማስቀመጥ መሠረታዊ መብታቸው የሆኑትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ መዋቅሮች ተካፋዮችና ተጠቃሚዎች እንዳይሆኑ መንፈግ ነው። መንግስቱን የሚቆጣጠረው ዘር ቁልፍ ቁልፍ የመንግሥት መዋቅሮችን በመያዝና ለራሱ ዘር ብልፅግና እንዲውሉ በማድረግ፤ የሌላው ሕዝብ ንብረት የሆኑትን የማምረቻ መሳሪያዎችንና የተፍጥሮ ሀብቶችን ለራሱ በመዝረፍ፤ እውነተኛ ባለቤቶቹ በሁሉም ዘርፍ ከራሱ ዘር ወይም ዘውግ ወይም ሕዝብ እንዲያንሱ በማድረግ የዘረኝነት መርሆውን ይተገብራል። በዘረኛ ሥርዓት የሃገሪቷ እፍታ ሃብት ለገዢው ብሔር ሲመደብ “ሌሎቹ” ብሔሮች በደረቁ አጥንት እንዲጣሉ ይደረጋል። እንደዓብነት ለመጥቀስ ህወሃት በእንደነ ኤፈርት ዓይነት በበጎ አድራጎት መልክ በተደራጁ ግዙፍ ኩባንያዎች ስር የሃገሪቷን ቁልፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፎችን (ፋብሪካዎችን፣ ጥሬ ሀብቶችን፣ ምርቶችን፣ ማዕድናትን፣ ማከፋፈያዎችንና የመሳሰሉትን) በመሰብሰብና የራሳቸውን ማከፋፈያ ዘርፍ አስከመንደር ችርቻሮ ድረስ አቋቁመው በራሳቸው ወገኖች (ዘውጎች) በመቆጣጠር ሌሎቹን ዘውጎች ከሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚነት ለማግለል መቻሏን አይተናል። ሌላው ደግሞ እስከቅርብ ድረስም የመከላከያ አመራሩ ከፍተኛ ስልጣኖችና ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በህወሓት አባላትና ከአንድ ስፍራ በመጡ መንደርተኞች ቁጥጥር ስር መሆኑ ይታወሳል።

ሰው ዘረኝነትን ይማራል እንጂ አብሮት አይወለድም። ሰውን ዘረኝነት ከሚያስተምሩት ጥቂቶቹ፤ ዘረኛ ቤተሰብ፣ ዘረኛ አብሮ አደጎች፤ በዘርኝነት ተግባር ጥቅም ሲሆኑ ከሁሉም በላይ ዘረኝነትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት የሃገሩን ሕዝብ ለመለያየት ዘረኝነትን እንደመሳሪያ ለመጠቀም በትምሕርትና (9) በመሳሰሉት የመንግሥት ተቋሞች አማካይነት ሥር እንዲሰድ ሲያደርግ ነው።

የክልል አገዛዝ የዘረኝነት ዕድሜን ማራዘሚያ መሣሪያ ነው

ፖሊሲው በዘረኝነት ላይ የተመረኮዘ የራሱን ዘውግ ጥቅሞች የሚያስጠብቅ መንግሥት ሌሎቹ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ተባብረው እንዳያምፁበት ከሚጠቀምባቸው አንዱና ዋነኛው ዘይቤ የሃገሪቱን ዘውጎች በየክልላቸው አጉሮ ከፋፍሎ መግዛት ነው። የራሱን ዘር ወይም ዘውግ እንደበላይ ቆጥሮ ሥልጣን ላይ የወጣ ዘር ወይም ብሔር ሌሎቹን ብሔሮች በእውቀት፣ በሰብዓዊ ችሎታ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ብስለታቸው ዝቅተኞች አድርጎ ስለሚቆጥራቸው የሱ ተገዢ እንዲሆኑ ያስገድዳል። አንዱን ዘር ከሌላው ተሻለ አስመስሎ በመስበክም የክፍፍልን፣ የእርስበርስ መናናቅንና መጠላላትን ያስፋፋል። የደቡብ አፍሪቃው የነጮች መንግስት የአፓርታይድ ሕጎችን አውጥቶ የሃገሪቱን ዜጋዎች በዘርና በጎሳ ከፋፍሎና በክራአሎች (በመንደሮች) ከልሎ መግዛት አንዱ ምሳሌ ነው።

የገዢው ሃይል የራሱን ዘር ሕልውናውንና የበላይነቱን ዘላለማዊ ለማድረግ የዘረኝነትን ተግባር ከመንግሥት መዋቅር ጋር በማስተሳሰር የመከፋፈያ ደንቦችን በማውጣት ተግባራዊ ያደርጋል። ይህንንም ከራሱ ዘር በወጡ ካድሬዎችና የስለላ መርበቦች አማካይነት በሥራ ላይ ያውላቸዋል። ዘረኝነትን ዘላለማዊ ለማድረግ የአገዛዝ ስልጣኑን ለራሱ ትውልድ ያስተላልፋል። አዲሱንም ትውልድ እንዲተኩት ከሕፃንነታቸው ጀምሮ “እናንተ የንፁህ ደም ዘሮች ናችሁና ከሌሎቹ የኛ ዘር ካልሆኑ ሁሉ በተፈጥሮ በተሰጣችሁ መብት የበላይ ናችሁ።” በሚል የዘረኝነት ርዕዮት ኮትኩቶ ማሳደግና ለስልጣን ማዘጋጀት ነው። ለምሳሌ ጀርመኖች የአርያን ዘሮች ነንና የሁሉም የበላይ ነን በማለት በሚሊዮኖች ሕዝቦች ላይ ያደረሱትን ጥፋት አይተናል። በአሜሪካም የነጭን ዘር የበላይነት (white supremacy) እየሰበኩ የአፍሪቃ ዘሮችን በባርነት (slavery) በመግዛት፤ የመጀመሪያዎቹን የሃገሪቷን ነዋሪዎች ከምድራቸው በማባረርና በመጨፍጨፍ የሠሩት ግፍ ጠባሳው ከአራት መቶ ዓመታት በኋላም አልጠፋም። የደቡብ አፍሪቃ ነጮችም በዓለም ላይ አስከፊውን የአፓርታይድ ስርዓት በመጠቀም በተወላጁ የአፍሪቃ ሕዝብ ላይ ያደረሱት ጭቆናና ስነልቦናዊ ጠባሳ አሁንም ጎልቶ ይታያል።

ዘረኝነትና የዘረኝነት አተገባበር በተፈጥሮው ኢዴሞክራሲያዊ፣ ኢፍትኃዊ፣ ኢሰብዓዊ ነው። ዘረኝነትን እንደፖሊሲ ተጠቅሞ ለሰብዓዊ ህልውናና ማንነት የበላይና የበታች ደረጃዎች በመፍጠር ሕዝቡን ማቃቃርና ዘላቂ ልዩነቶችን መፍጠር በዓለም ላይ አዲስ አይደለም። በባርያ ዘመን ነበር፤ በፊውዳል ጊዜም ነበር፤ አሁንም እየተደረገና እኛም አየቀመስነው ነው። አምባገነኖች ባሉበት ሁሉ የተባበረን ህዝብ ማየት አይፈልጉም። የተባበረ ሕዝብ ለገዳዮችና ለጨቋኞች ጠንቅ ነው። በአንፃሩም የተከፋፈለና እርስበርስ በመፋጀት አቅሙ የደቀቀ ሕዝብ ተጠናክሮና ተባብሮ የጋራ ጠላቱን መከላከል ስለማይችል ገዢዎቹ አምባገነኖች ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ዋስትናን ይሰጣቸዋል። ይህንም ዓይነት አገዛዝ በኢትዮጵያ ብች ሳይሆን በመላው አፍሪቃ አይተነዋል። የአውሮፓ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ያሰመሯቸው ክልሎችና ድንበሮች አህጉሩን በማያልቅ የድንበር ጦርነቶች ውስጥ ከቷል።

“የተጨቆን ብሔሮች ነን”

ዘረኞች የበላይነትን እንደመብታቸው የሚያዩትና ሌሎችንም ዝቅ አድርገው መግዛት እንደሚገባቸው ሊያሳምኑን የሚሞክሩበት ሌላው ስልት የራሳቸው ዘር “በሌሎቹ ዘሮች” ለዘመናት እንደተጨቆነና እንደተገዛ አድርጎ በማቅረብና ያ ዓይነቱ ጭቆናዊ አገዛዝ እንዳይደገምባቸው “የነዚህን ‘ሌሎች ጨቋኝ ብሔሮች’ ቅስም ሰብሮ በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው” በማለት ነው ። “አኛን ከሚያጠፉን ቀድመን እናጥፋቸው” የሚል መርሆ የአገዛዛቸው ስልት ይሆናል።

ከላይ እንደተጠቀሰው ዘረኝነትን እንደቋሚ የመንግሥት ፖሊሲ አድርጎ ማስፋፋትና ዘላለማዊ ማድረግ ለገዢው መንግሥት በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ለዚህም የተቋቋሙትን የትምህርት መዋቅሮችና በጊዜው የሚሰራውን ሶሻል ሚዲያ መሳሪያዎችን ዘርግቶ ለራሱ ጥቅም ማራዘሚያ ይጠቀምባቸዋል። በተለይም የራስን ዘር የትምህርት ሥርዓትና ጥራት ከሁሉም የላቀ አድርጎ በመገንባትና ዘመናዊ የመማሪያ ቁሳቁሶችን በሰፊው በማቅረብ ቀጣዩ ትውልዶቻቸው ከሌሎቹ የተሻለ የመሪነት ዕውቀትና ልምድ አስታጥቀው ለኃላፊነት ያዘጋጇቸዋል። በትምሕርትና በጤና መስክ የራስን ዘውግ በተሻለና ዘመናዊ በሆነ ተቋም ማዘጋጀትና የሌላውን ሕዝብ ተመሳሳይ ተቋሞች ማጎሳቆል በትምሕርትና በጤንነት ላይ ያተኮረ ዘረኝነት ነው።

ህወሐት የራሷን ዘር “የወርቅ ፍልቃቂ” (8) አድርጋ የራሷን የበላይነትና የሌሎቹን 87 ዘውጎች የበታችነት ፍልስፍና ስታሰራጭ ቆይታለች። የህወሐት አባላት ለራሳቸውና ለዘውጋቸው አዲስ ትውልዶች በሚሰጡት ትምህርትና ስልጠና ስለራሳቸው የበላይነትና ስለሌሎች የአዕምሮ ዝቅተኝነት አምነውበት አንዲያድጉና ካባቶቻቸው የተረከቡት የክልልና የግለላ ፖሊሲ ወደፊት እንዲቀጥሉበት እያደረጉ ነው። የዘረኝነት ፖሊሲውን በመተግበር “ሌሎች” የሃገሪቱ ዘውጎች በሁሉም የሃገሪቷ አውታሮች (ትምሕርት፣ አኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ወዘተ) በእኩልነት እንዳይሳተፉና በዝቅተኝነት ስነልቡና ይዘው ከትውልድ ተውልድ እንዲቆዩ ማድረግ የፖሊሲው መርሆ ነው።

በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ኅብረሰባዊ ቁጥጥር ለኅብረሰባዊ ስነልቦናዊ ጠባሳ ይዳርጋል። ስነልቦናዊ ጠባሳ ደግሞ ወደዝቅተኝነት ወይም ወደሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ይወስዳል (9)።

አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አምባገነንነትና ዘረኝነት በኢትዮጵያ

ዘረኝነት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተሰበጣጥሮ የብዙ ዘውጎች ስብስብስ ለሆነች ሐገራችን አጅግ አስቃቂ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሥልጣንን በአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ሥር አካብቶ ፍፁማዊ የፓርቲውን የበላይነት (hegemony) ሲፈጥር፣ የዘረኝነት ፖሊሲ ሕዝቡን በማለያየትና በማቃቃር ይህ የፓርቲ የበላይነትን ሕልውና ያረጋግጣል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት ብዙ ዘመናት በተለያዩ ገዢዎች ሥር በዘውግና በቋንቋ እንዲከፋፈል ተደርጓል፤ ተገፋፍቶም እርስበርስ እንዲጠላላና እንዲገዳደል ተገዷል። አነስተኛ የመንደር ሽኩቻ ወደትልቅ ሀገር አቀፍ ጠብ ተዛምቷል። ይህ የከፋፍሎ መግዛት ሥርዓት ወደከፍተኛው ደረጃ የደረሰው ባለፉት 27 ዓመታት በህወሐት በሚመራው የኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ነው። በዚህም ምክንያት በክልልና በዘውግ እንዲከፋፈል የተደረገው ሕዝብ የድንበር ጦርነት መፍጠር፤ በክልሉ የሚኖሩትን “ሌሎች” ዘሮችንና ዘውጎችን በማጥቃትና ከኑሮዋቸው ተፈንቅለው እንዲሰደዱ ማድረግ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለዘርኝነት ተፅዕኖ ዳርጓቸዋል። ለዚህም እንደ አብነት የሶማሊያው ፀረ-አማራ ጭፍጨፋ፤ በጋምቤላ የተከናንወነው ጭፍጭፋ፤ የኦሮሞዎች መፈናቀል፤ በበኒሻንጉል ያሉ አማሮችና ኦሮሞውች መፈጀትን መጥቀስ ይበቃል። ይህ ችግር አሁንም ቀጥሏል። በየጊዜውም የሚነሱ “እኛም ክልል እንሁን” የሚሉ ዘውጎች ጥያቄም ቀጥሏል።

በጊዜና በትክክለኛው ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲ ላይ ተመርኩዞ መፍትሄ ካላገኘ፤ በአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ አገዛዝ የተዘረጋ የዘረኝነት መርሆ የሕዝብን እርስበርስ ጥላቻ ወደዘር ማጥፋት ደረጃ ሊያራምድ ይችላል። የአንድ ሕዝብ በዘር መጠላላት ወደ ዘር ማጥፋት የደረሰባቸው ሐገሮች ብዙ ናቸው። ለአብነት ያህል የጀርመንን፣ የሩዋንዳንና የዩጎስላቪያን ማንሳት ብቻ ይበቃል። በኢትዮጵያም ውስጥ እስካሁን የተፈፀሙት ሐገርን በዘርና በቋንቋ የመላያየትና እርስበርስ የማበጣበጥ እኩይ ተግርባሮች ዘረኝነት ሥር ሰዶ እንዲንሰራፋ ብቻ ሳሆን አንዱ ዘር ሌላውን የሚያጠፋበትን ጥርጊያ መንገድም እያዘጋጁ ነበር። በአሁኑ ሰዓት በየቦታው እየተፈፀሙ ያሉ የክልል ግጭቶች፤ ሕዝብን ከኑሮው አስፈንቅሎ ማባረር፤ በጅምላ መግደልና መገዳደል ሥር የሰደደ ዘረኝነት ፖሊሲ ውጤት ነው።

በፊት ተጀምሮ በህወሐት ዘመን ፍፁማዊ የሆነውን የሃገራችንን የተውሳሰበ ዘረኛ ሥርዓት አፍርሶ ሕዝባዊ ዴሞክራሲን ሥር የማስያዝ ጉዞ በገደል አፋፍ ላይ በወጣች ቀጭን መንገድ አንደመጓዝ ነው። አንድ የተሳሳተ ርምጃ ከገደሉ አዘቅት ውስጥ ይከታል። ሃገራችን ኢትዮጵያም የምትወስዳቸውን ርምጃዎች ሁሉ በከፍተኛ ጥንቃቄ መውሰድ አለባት። አሁን ካለንበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት አየታገልን ሳለን በችኩልነት ተገፋፍተን የበለጠ ገደል ውስጥ መግባት የለብንም።

ዘረኝነትን ለማጥፋት የእያንዳንዱን ግለሰብ ሰብዓዊ መብትና ደሞክራሲያዊ እኩልነትን ያለምንም ገደብ መተግበር

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ሊፈጠርና ሊጠነክር የሚችለው በክልላዊ አጥሮች ወይም በዘውግ ወይም በቋንቋ ወይም በኃይማኖት በመከፋፈልና መለያየት ሳይሆን የእያንዳንዱን ግለሰብ መሰረታዊ ሰበዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር ነው። የዘር ክፍፍልና ግጭት ለማጥፋት የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ የበላይነትን (hegemony) ለምንጊዜውም አስወግዶ የኢትዮጵያ ዘውጎች በአኩልነትና በአንድነት የሚፈጥሩትና በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተና ሁሉንም ሕዝብ ያሳተፈ ዴሚክራሲን መቀየስ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

በልምዱ ውስጥ ካለፉት ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች እንደምንማረው የሕዝቡን ሕልውናና መሰረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስከብር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ሂደቱና እድገቱ ረጅምና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የተወሳሰበ ጉዞ ይሆናል። ሕዝባዊ የሆነ ዴሞክራሲ ፍጹማዊ ሥርዓት ስላልሆነና በተግባርና በተመክሮ እየተሻሻለ የሚራመድ ሥርዓት ስለሆነ የእድገት ጉዞው የመውደቅና የመነሳት፣ የመውጣትና የመውረድ፣ የመቀልበስ ወይም የመሻሻል እውነታዎች የሞላበት ሂደት ነው። የሂደቱ መሳካት ዋና መለኪያው በመሰናክሎች መፈተኑ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ተሳታፊነትን ደጋፍ እየተሻሻለና እየጠንከረ የሚበለፅግ ሥርዓት መሆኑ ነው። ሁሉን አቀፍ የሆነ ዴሞክራሲ ያልተቋረጠ የሕዝቡ ታሪካዊ ተመክሮ ታክሎበት ያድጋል ወደፊትም ይራመዳል። ከጥሩው ሥራ ብቻ ሳይሆን ከመጥፎውም እየተማረ እያረመ ወደፊት ይጓዛል። እውነተኛ የሕዝብ መሪዎች የእድገት ውጣና ውረድ እንዲሁም ወደወደፊትና ወደኋላ መመላለሶች የማይቀሩ እውነታዎች መሆናቸውን ተረድተው ሕዝቡን ያዘጋጁታል።

የሁሉም ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብት ሲከበርና ግለሰባዊ እኩልነት ሲጠነክር ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚው፣ የፖለቲካው፣ የተፈጥሮ ሐብቱ፣ የኅብረተሰብ ባህልና ብልፅግና ተካፋይ እንዲሆንና በአንድነት አንዲያድግ መንገዱን ይከፍታል። ሕዝቡም ከሚያባዝተው የመላያያ መርዝ አድኖ እንድነትን ለመፍጠር የሚችለው ሁላችንም በአሉታዊ መንገድ የተለያዩ ሃሳቦቻችንን በአንድ ላይ አዳምረን የሕዝቦችን ውህደታዊ ጥበብ ስንፈትልና ስንሸምን ነው።

በሰማንያ ሰባት ዘውጎች ባህሎችና ቋንቋዎች ያሸበረቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተፈላልጎ እንደጥበብ መዋሃዱን አላቋረጠም፤ አያቋርጥምም። ከመለያየታችን ይልቅ መዋሃድችን ያጠነክረናልና በተፍጥሮም ውህደቱን እንመርጣለን። የጥበብ ቀሚስን ወይም ነጠላን የሚያሳምረው እያንዳንዱ ክር ለብቻው ሆኖ አይደለም ግን እያንዳንዱ ክር ከሌሎች ጋር ተሰበጣጥሮና ተዋህዶ ነው። እኛን የሚያስፈልገን ሰብዓዊነታችንንና የመፋቀር ችሎታንን ያደበዘዘውን የዘረንነት መርዝ ከነሰንኮፉ ነቅለን ለመዳን የሚያስችለን፤ በግልፅ የመወያያ፣ ይቅርታ መጠያየቂያና ይቅርታ መደራረጊያ ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ የሆነ የሰውና የተፈጥሮ ሃብት አላት። የተማሩትና የተመራመሩት ልጆቿም እንኳን ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለመላው ዓለም የሚተርፍ አኩሪ እውቀትና ልምድ አካብተዋል፤ በተግባርም እያሳዩ ናቸው። ይህንን የሕዝብ ካፒታል በማስተባበር እውቀቱንና ልምዱን በየዘርፉ ለሃገራችን ደሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቡናዊና ሌሎችንም የሕዝቡን አንድነት የሚያጠነክሩ መስመርቶችን መመስረት ካለውም ጥሩውንም ማጠናከር እንዲችሉ መረባብረብ ነው።

ማጣቀሻዎች

  1. Erlich, Haggai; Ras Alula and the Scramble for Africa

  2. Raymond Jones – The Battle of Adwa: African victory in the age of Empire

  3. Anthony Mockler; Haile Selassie’s War

  4. Najib Mohammed፡The haven of the first Hijra (migration) – https://www.soundvision.com/article/the-haven-of-the-first-hijra-migration

  5. https://ecadforum.com/2019/01/27/ethiopia-tried-to-save-jews-from-holocaust-in-1943/amp/

  6. Fanouris, Melinda and Lukas; Meskel – An Ethiopian Family Saga 1926-1981

  7. https://en.wikipedia.org/wiki/Racism

  8. ኤርሚያስ ለገሰ – የመለስ ልቃቂት

  9. Michelle Alexander – The new Jim Crow

  10. ፕሮፌሰር ወሰኔ ይፍሩ – ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር (ለውይይት የቀረበ)