በዶ/ር አብይ ስም የሚቀናጣው መስሪያ ቤት፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት

(ማሳሰቢያ፦ ይህ ፅሁፍ ከላይ የተጠቀሰው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ለድረገፃችን አዘጋጆች የላኩት ደብዳቤ ነው፡፡ የሰራተኞቹ ቅሬታና አቤቱታ መሰማት ስላለበትና የድረገፃችን ተከታታዮች እውነታውን ማወቅ ስላለባቸው አትመንዋል! ነገር ግን ፅሁፉ የፃሃፊውን ሃሳብና አመለካከት እንጂ የድረገፁን ወይም የአዘጋጆቹን አቋም አያንፀባርቅም!)

ቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒትር በአብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በነበረ ጊዜ የተቋቋመ መስሪያ ቤት ነው፡፡ የሀገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን እንዲሰበስብና ዲጂታላይዝ እንዲያደርግ የተቋቋመው ይህ መስሪያ ቤት ወጪ ቅነሳ ተብሎ የኢትዮጵያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማሻሻያ ሲደረግባቸው ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር የአሁኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር መጠቃለል ሲችል አልያም ወደ ኢትዮጵያ ቤተመዛግብት መደረብ ሲችል ወደ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩትነት አደገ፡፡

ይህ ነው የሚባል ስራ ሲሰራ የማይታየው ይህ መስሪያ ቤት በየጊዜው አዳዲስ ሰራተኞችን እየቀጠረ ወደ ስራ ያስገባል፡፡ በርካታ ሰራተኞች ቢኖሩም በግልፅ የተቀመጠ ይሄነው የሚል ስራ የሌለው መስሪያ ቤት ነው፡፡ ስራዎቹ አንድም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አንድም ደግሞ በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት በኩል የሚሰሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የሚቀጠሩ ሰራተኞች በአይቲ የተመረቁና በትውውቅ አልያም በዝምድና የተመረጡ ናቸው፡፡ እህትማማች፤ ወንድና እህት፤ ባልና ሚስት እና ከአንድ አካባቢ የተሰባሰቡ ሰዎች ያሉበት መስሪያ ቤት ነው፡፡

ሰራተኞቹ የደህንነት ስራ እና አብይን የሚቃወሙ ፅሁፎችን የመቃወም እና የማስተባባል ስራ እንደሚሰሩ የሚያሳዩ የተወሰኑ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው መስሪያ ቤቶች እየተቀነሱ ሲመጡ ስራው በውል የማይታወቅ መስሪያ ቤት ወይም ወደ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር ስራ መጠቃለል የሚችል መስሪያ ቤት እንዲቆይ መደረጉ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መስሪያ ቤቱ በአብይ በኩል በልዩ ሁኔታ የሚታይ መስሪያ ቤት መሆኑ ነው፡፡ እዚያ መስሪያ ቤት ውስጥ በፍፁም የዶ/ር አብይን ስም በክፉ ማንሳት ሆነ መውቀስ አይቻልም፡፡ በጭራሽ!!

ሶስተኛ በቅርቡ ለሰራተኞች የተጨመረው የደሞዝ ጭማሪ እውነትም መስሪያ ቤቱ የተለየ የፖለቲካ ስራ እንደሚሰራ ማሳያ ነው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው ይህ ተቋም ለሰራተኞቹ በቅርቡ የፀደቀላቸው ደሞዝ ከፍተኛ ነው፡፡ የቤት ኪራይ፤ የትራንስርታና መቀናጣት የሚመስለው የልጅ የትምህርት ቤት ክፍያ ሳይቀር የተካተተበት የደሞዝ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት የሚከፈላቸው ደሞወዝ እስከ 35 ሺህ ብር ይደርሳል፡፡

በአንድ ድሃ ሀገር ውስጥ ለአንድ ኢንስቲቲዩት ሰራተኞች ይህንን ያክል ደሞዝ እንዲፀድቅ ያረገው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስት ፅ/ቤት ነው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰራተኞች ከ1ሺ 500 ብር ጀምሮ ከፍተኛው የዳይሬክተር ደሞወዝ (በፕሮጀክት ከሚከፈላቸው ውጭ) 6ሺ ብር ነው፡፡ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሰራተኞች እስከ 35ሺ ብር የሚደርስ ደሞወዝ ይከፈላቸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰራተኞች በዚህ ምክንያት የደሞዝ ጭማሪ የሚጠይቅ ፒቲሽን ተፈራርመው አስገብተው የነበረ ሲሆን በሚኒስትሩ በኩል “ሌላ ተልዕኮ አላችሁ” በሚል ቁጣን አስከትሏል፡፡ የሆነው ሆኖ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት መደረብ የሚችል፤ ስራ የሌለው መስሪያ ቤት በአንዲት ድሃ ሀገር ውስጥ ይህን ያክለ የተጋነነ ክፍያ መፍቀድ የአብይ አህመድን አድሏዊ አሰራር የሚያሳይ ስራ ነው፡፡