ለውጡ ተቀልብሷል ወይስ አልተቀለበሰም?

በያሬድ ሃይለማሪያም

አንድ አመት እያስቆጠረ ያለው የዶ/ር አብይ አስተዳደር እና የለውጥ ምሪት ገና ከአሁኑ መንገዳገድ ጀምሯል። ለውጡ የተጋረጡበትን ፈተናዎች እና ያፈጠጡ አደጋዎችን ቀደም ሲል ባወጣኋቸው ተከታታይ ጽሁፎች ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ሂደቱን እየተገዳደሩ እና መስመር ሊያስቱትም እየሞከሩ ናቸው ያልኳቸውን ዋና ዋና ኃይሎችም በእነዚህ ጽሑፎች ጠቃቅሻለው። አክራሪ ብሔረተኞች፣ ጨለምተኛና ጭፍን ተቃዋሚዎች፣ እራሱ በመደናበር ላይ ያለው የለውጥ ኃይል እና የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች የጀመሩት የእርስ በርስ ሽኩቻ ዋነኛ ምክንያቶች ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ ኃይሎች ለውጡ በተፈለገው መልኩ እና ሲጀመር በነበረው ፍጥነት እንዳይቀጥል እየተገዳደሩት መሆኑን በሁለት ተከታታይ ጽሁፎች በዝርዝር ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። ችግሮቹ አሁንም አፍጠው እና አግጠው እየወጡ ነው።

ለውጡን በተመለከተ አራት የተለያዩ አስተሳሰቦች ሲንጸባረቁ አስተውያለሁ፤

  • ለውጡ ሙሉ በሙሉ ተቀልብሷል፤
  • ለውጡ ሊቀለበስ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል፤
  • ለውጡ አልተቀለበሰም እንደውም በታቀደለት እና በተቀደደለት ቦይ እየፈሰሰ ነው፤
  • ከመነሻውም ለውጥ የሚባል ነገር የለም፤

የለውጡ ሂደት ላይ እጅግ የተለያዩ ምልከታዎች እየተንጸባረቁ ነው። ይህ ውይይት በበርካታ ሚዲያዎች እና በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይም በጎላ ሁኔታ እየተንጸባረቀ መምጣቱ ሕዝቡ ግራ እንዲጋባ፣ የለውጥ አመራሩም ላይ የነበርው እምነት እንዲቀንስ ወይም እንዲጠፋ እና እርስ በእርስም የመከፋፈል አዝማሚያ እንዲታይ አድርጓል።

የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሃሳቦች አንድ መስመር ላይ ሲሆኑ ከስጋት እና በመሬት ላይ እየሆነ ካለው ነገር በመነሳት የተሰነዘሩ ወይም በለውጥ ኃይሉ ላይ ተስፋ ከመቁረጥ የመነጩ መደምደሚያዎች ናቸው። እነዚህን በቅጡ መመርመር እና ምላሽ ማግኘት የግድ ይላል። የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ደግሞ፤ ለውጡ በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏለ እና ጭርሱኑ ለውጥ የለም የሚሉት ምልከታዎች ከስሜት እና ምኞት በዘለለ በአመክንዮ ያልተደገፉ እና በግልጽ መሬት ላይ የሚታዩ ተጨባጭ እውነታዎችን መሰረት ያላደረጉ ወይም የሚታዩ እውነታዎችን ከመካድ የመነጩ የስሜት አቋሞች ይመስሉኛል። በእነዚህ ሃሳቦች ዙሪያ ውይይት ማድረግ ጊዜ ከማጥፋት ያለፈ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።

በመጀመሪያዎቹ ስጋቶቻችን ላይ በግልጽ ልንነጋገር ይገባል ብዮ አምናለሁ። ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው፤ ታዋቂውን የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ምሁር ፕ/ሮ መስፍን ወልደማሪያምን ጨምሮ ለውጡ በራሱ የለውጥ ሃይሉ ተቀልብሷል የሚል አቋም ተንጸባርቆ አይቻለሁ። ለእዚህም በቂ የሚባሉ ማሳያዎችንም ከግራና ቀኝ ተጠቁመዋል። እኔ ይህን መደምደሚያ ሙሉ በሙሉ አልጋራውም። ስጋታቸው ግን ስጋቴ ነው።

በእኔ ምልከታ ለውጡ ገና አልተቀለበሰም። ሊቀለበስ የሚችልበት አፋፍ ላይ ደርሷል በሚለው ሃሳብ ግን ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ከላይ የዘረዘርኳቸው ተገዳዳሪ ኃይሎች እርስ በርስ ሲጓተቱ እና አንዳንዴም እየተመጋገቡ ለውጡ ሊቀለበስ የሚችልበትን ስጋት ከፍ አድርገውታል።

እንግዲህ እንደሚባለው ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ ከሆነ ምንድን ነው ቀጣዩ እጣ ፈንታችን? ወይም አልተቀለበሰም ነገር ግን አደጋ ተጋርጦበት ከሆነ ግምገማችን እንዳይቀለበስ ምን ማድረግ እና በምን መልኩ መታደግ ይቻላል? የሚሉት ጥያቄዎች ዋና የመወያያ ነጥቦቻችን ሊሆኑ ይገባል።

+ ተቀልብሷል፤

ለውጡ ተቀልብሷል ማለት የዶ/ር አብይ አስተዳደር ከሽፏል ወይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል አጥፏል ወይም በአቅም ማጣት የተነሳ ቃሉን መጠበቅ ተስኖታል ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት በኢትዮጵያዊነት ስም ድብቅ ተልዕኮ ይዞ ለአጭር ጊዜ አታሎናል። ይህ ማለት የአገሪቱ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ እየተዘወረ ያለው በኦዴፓ ነው። ኦዴፓ ደግሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እያሳየ ያለው ባህሪ እና እየወሰዳቸው ያሉ አንዳንድ እርምጃዎች ድርጅቱ በአክራሪ ኦሮሞ ብሄረተኞች የተጠለፈ ሰለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ እየቀረበ ነው።

አቶ ለማ ዲሞግራፊን አስመልክተው የተናገሩ፣ በተቀነባበር መልኩ በሚመስል ሁኔታ በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ዜጎችን የማፈናቀል እርምጃ፤ በተለይም የለገጣፎ ክስተት፣ የአዲስ አበባ ጥያቄ እና የኮንደሚንየም እጣ አወጣጥን በተመለከ ክልሉ የሰጠው መግለጫ፣ የክልሉ ፖሊሶች እና የጸጥታ ኃይሎች ዱላ እና ሜጫ ከያዙ የቄሮ ወጣቶች ጋር ወደ አደባባይ ወጥተው ሕዝብ እና መንግስትን አስፈራርተው መመለሳቸው እና ቀደም ሲልም በቡራዩ ጭፍጨፋ ላይ ክልሉ ያሳየው ዳተኝነት ተደማምረው ኦዴፓ የህውሃትን ቦታ ለመተካት ደፋ ቀና እያለ ያለ ይሆን የሚል ጥያቄን በብዙዎች ዘንድ አጭሯል። ብዙዎች ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ከኦዴፓ በኩል ለውጡን በመምራት ግንባር ቀደም የሆኑት ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ የሃሳቡ ተጋሪዎች በመሆናቸው ነው ብለው ደምድመዋል። ሕዝብ በእነኚህ ቀንዲል የለውጥ ሃዋሪያ ተደርገው በተወሰዱ ሰዎች ላይ ያለው እምነት በዚህ መልኩ ማቆልቆሉ ለውጡ ተቀልብሷል የሚለውን መደምደሚያ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል።

እንደ እኔ እምነት ኦዴፓ በሁለት ኃይሎች ቅርምት ውስጥ የወደቀ ይመስለኛል። አንደኛው አክራሪ በሆኑት ብሔረተኞች የሚመራው እና ሁሉን ኬኛ የሚለው የቄሮ ክንፍ ሲሆን የድርጅቱን መዋቅር ከቀበሌ አንስቶ እስከ ክልሉ ምክር ቤት እና ከፍተኛ አመራሮች ድረስ ስር የሰደደ ኃይል ይመስላል። ይህ ኃይል ቀደም ሲልም በተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙ የኦዴፓ ተወካዮች ላይ ያሳድር የነበረውን ተጽእኖ ልብ ይሉዓል። ይህ ኃይል መጀመሪያውም ሆነ መጨረሻው ኦሮሞ እና ኦሮሚያ ስለሆነ ኦዴፓ ኢትዮጵያዊነትን በማጠናከር እረገድ ጀምሮት እና እያሳየ የነበረው ግንባር ቀደምነት አይዋጥለትም። ይህ ቡድን በኢትዮጵያዊነት ስም ኦሮሞነት ሊዋጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለበት በተደጋጋሚ በየመድረኩ ሲገለጽ ተስተውሏል። ቢያንስ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ የበላይነት መስፈን አለበት ብሎ የሚታገል ኃይል መሆኑንም የክልሉ ፖለቲከኞች ያለ ምንም ሃፍረት በመንግስት ሚዲያ ሳይቀር ሲናገሩ ተደምጧል።

ሁለተኛው ኃይል እና ኦዴፓ ውስጥ ቁጥሩ እየመነመነ የመጣው ኃይል እነ ዶ/ር አብይ የሚያራምዱትን ኢትዮጵያዊነትን የማጎልበት እና የኦሮሞ ሕዝብ ልክ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ተከብሮለት እና መብቱም ተጠብቆለት የሚኖርባት ትልቅ አገር ለመፍጠር እና ልዩነቶቻችንን እንደ ውበትና የህብር ኃይል አድርጎ የሚቆጥረው አስተሳሰብ ባለቤት ነው። ይህ ኃይል በአክራሪ ብሔረተኞቹ ዘንድ ክፉኛ ሲወቀስ እና ሲወገዝ ቆይቷል። ከውግዘትም አልፎ አክራሪው ኃይል በሚያራምደው የሃሰት ትርክት የተነሳ በከልሉ ውስጥ ያለውን ድጋፍ እና ቅቡልነት እንዲያጣ ተደርጓል። ይህ ኃይል እንደ ድፎ ዳቦ በኢትዮጵያዊነት እና መቀመጫው በሆነው ክልል ውስጥ እንደ ሰደድ እየሰፋ በመጣው አክራሪ ብሔረተኛነት መካከል ከላይም ከታችም እሳት ላይ የተጣደ ቡድን ነው። ደጋፊዎቹን እና አባላቱን ለማስደሰት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እያስከፋበት እና አመኔታም እያሳጣው፤ ኢትዮጵያዊነትን ባቀነቀነ ቁጥር በክልሉ ያለውን ድጋፍ እያቆለቆለበት አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ኃይል ይመስለኛል።

ሁለቱን ተገዳዳሪ ሃሳቦች፤ አክራሪ ብሔረተኝነትን እና እትዮጵያዊነትን አጣጥሞ መሔድ ለማንም ቀላል አይደለም። የኦዴፓ አመራርም በዚህ እየተፈተነ ይመስለኛል። መሪዎቹ ኢተዮጵያዊነት ላይ ያላቸውን እምነት አጎልብተው እና ለቃላቸው ቆመው ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ከቆሙ ለውጡን በመሪነት የማስቀጠልም ሆነ ኢትዮጵያን እኩልነት፣ ፍትህ እና ርትዕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር ለማድረግ ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ለውጡም የሰመረ ይሆናል። ኦዴፓም ሆነ የክልሉ ልሂቃን ይህን እድል በአግባቡ ሳይጠቀሙበት ከቀሩ እና አሁን በጀመሩት አካሄድ ከትልቋ ኢትዮጵያ ይልቅ ኦሮሚያ ከበለጠችባቸው ለውጡ ይቀለበሳል።

የህውሃት ዘመን በኦዴፓ ታድሶ የሚቀጥልበት እድል የለም። ህውሃት ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረችዋ ኢትዮጵያ ዛሬ የለችም። ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች እጅ ነው። ኦዴፓ መንገድ ቢስት አዴፓ እና ሌሎች ኃይሎች አብረውት ካልተመሙ በቀር ለውጡ ሙሉ በሙሉ በአንድ ቡድን እጅ ሊወድቅ አይችልም። ለዚህም አዴፓ እና ኦዴፓ በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው አቋም ልዩነት ብቻ ጥሩ ማሳያ ነው።

+ የመቀልበስ አደጋ

ለውጡ የመቀልበስ አደጋ እንዳንዣበበበት ከላይ እንደጠቀስኩት እና ቀደም ሲል ባወጣዋቸው ጽሑፎች በዝርዝር ስለገለጽኩት እዚህ መድገም አልፈልግም። በዚህ ዙሪያ ማንሳት እና መፈተሽ የሚገባን ነገር አደጋው ሊቀለበስ እና ልንቆጣጠረው የምንችል አይነት ነው ወይስ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ግብአተ ተመሬት እስኪፈጸም ቆመን መታዘብ ብቻ ነው?

እንደ እኔ እምነት እና አቋም የተጋረጠብን አደጋ ልንቋቋመው የምንችል አይነት ነው። ትልቁ እና ዋናው ቁምነገር ከዚህ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ያለን አቋም እና ግንዛቤ ነው።

፩ኛ/ ለውጥ አለ ብለን እናስባለን ወይ?

፪ኛ/ ለውጥስ ካለ ወይም ተጀምሮ ከነበረ የእኛ ነው ብለን በባለቤትነት ስሜት እናየዋለን ወይ? ወይስ የማን ለውጥ?

፫ኛ/ ለውጡ በሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ለውጥ ነው? ወይስ የአንድ የተወሰነ ቡድን?

፬ኛ/ ለውጡን በሚመራው አካል ላይ እምነት አለን ወይ? ከመምራት ብቃት እና ልምድ ማነስ ባለፈ ንጹህ ልቦና እና ቅን አሳቢነት ላይ ጥርጣሬ አለን ወይ?

፭ኛ/ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ መላሽ አካል ወይስ ጥያቄዎቹን የሚመልስ በሕዝብ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመረጥ መንግስታዊ ሥርዓት የሚመጣበትን እድል የሚያመቻች አሸጋጋሪ ኃይል?

የራሴን አቋም በአጭሩ ላስቀምጥና ቀሪውን ለአንባቢያን እና ለተወያዮች ትቼ ጽሑፌን ልዝጋ።

ኢትዮጵያ ዛሬም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። በአንድ አቅጣጫ ዶ/ር አብይ የሚመሩት ኢትዮጵያዊ የለውጥ ሂደት ያለ ሲሆን በተቃርቅኒው የኢህአዴግ አንባገነናዊ ሥርዓት እድሜውን አድሶ በኦዴፓ መሪነት መቀጠል የሚችልበት እድል። በሌላኛው መስመር ደግሞ አክራሪ ብሔረተኞች የሚፈነጩባት እና ክልሎች አገር ለመሆን የሚራኮቱባት አገር ወይም የመጨረሻው አማራጭ የሽግግር መንግስት እንዲመጣ በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር በሁሉም መንገደ መታገል ነው።

እንደ እኔ እምነት የመጀመሪያው አማራጭ፤ እነ ዶ/ር አብይን ስህተቶችቃቸውን እየነገርን፣ ደካማ ጎኖቻቸውን እያሟላን እና እንዲያሻሽሉ እየወተወትን እና አቅጣጫ ሲስቱም ጮኸን እያነቃን የለውጡ ባቡር ሃዲዱን ስቶ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይዞ ገደል እንዳይገባ ወይም ከመንገድ እንዳይቀር ማገዝ ነው። በአጠቃላይ ለውጡ አልተደንናቀፈም። ተባብረን እንዳይቀለበስ ማድረግ አለብን። ኪሳራው የሁላችንም ነው።

አቶ ያሬድ ሃይለማሪያም – የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

One thought on “ለውጡ ተቀልብሷል ወይስ አልተቀለበሰም?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡