የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ የህገ-መንግስቱ ወይስ የኢህአዴግ መዋቅር ችግር?

ህገ-መንግስቱን ማርቀቅ ከተጀመረበት እለት አንስቶ እስከ አሁን ባለው የኢትዮጲያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አጨቃጫቂ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የአዲስ አባባ ጉዳይ ነወ፡፡ ህውሃት መራሹ ኢህአዴግ ገና ወደ ስልጣን ከመጣበት እለት አንስቶ የአዲስ አባባን ጉዳይ እንደ time bomb ሊጠቀምበት እንደፈለገ የህገ-መንግስቱ አርቃቂ ጉባሄን የውይይት ቃለ ጉባሄና አሁን ላይ እየተፈጠረ ያለውን እሰጣ ገባ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡

ህገ-መንግስቱና አዲስ አበባ

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባ የማነች የሚል ጉንጭ አልፋ ንትርክ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ በዶ/ር አብይ የሚመራው የኢህአዴግ መንግስትም አዲስ አባባን በተመለከተ በአንድ ወር ውስጥ እርስ በራሳቸው የሚጣረሱ (አዲስ አባባ የነዋሪዎቿ ነች የሚል እና በኦዲፒ መግለጫ የተጠቀሰውን የኦሮሞን የአዲስ አባባ  ባለቤትነት እናረጋግጣለን የሚል) አሳቦችን እያንጸባረቀ ይገኛል፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 49 የአዲስ አባባን ባለቤትነት በግልጽ ለአዲስ አባባ ነዋሪ ሰጥቶ እናገኛለን፡፡

ህገ-መንግስቱ አንቀጽ 49/2 “የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል ፡፡ ዝርዝሩም በህግ ይወሰናል፡፡” በማለት የአዲስ አባባ ከተማ ህዝብ እንደ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞና ሌሎችም ህዝቦች እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሙሉ ስልጣን ሰጥቷል፡፡

አሁን ባለው ብሔር ተኮር የፌዴራል መዋቅር ሁሉም ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን ይህ መብትም ለአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ይሰራል፡፡ በህገ መንግስቱ መሰረት የአዲስ አበባ ህዝብ በራሱ ምርጫ በራሱ ፈቃድና ፍላጎት የሚያስተዳድረውን የመምረጥ መብት ያለው ሲሆን በሌላ አካል አስተዳዳሪ ተመርጦለት የሚቀመጥበት አካሄድ ግን ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡

በአንቀጽ 49 እንደተጠቀሰው አዲስ አባባ ከኦሮሚያ ወይም አማራ ክልሎች እኩል ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግስት እንደሚሆን ከደነገገ በኃላ እንደ ሌሎች ክልሎች የራሷ ወንበር በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዳላት ይጠቅሳል፡፡ በህገ መንግስቱ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አዲስ አባባ የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የሁሉም ኢትዮጲያዊ ዋና ከተማ ናት፡፡

የኢፌድሪ ህገ መንግስት በመርህ ደረጃ የአዲስ አባባን ባለቤትነት ለአዲስ አበቤዎችና ለኢትዮጲያዊያን ሰጥቷል፡፡  በዚህ መሰረት ከአዲስ አባባ ነዋሪ ውጪ አዲስ አበባን “የእኔ ነች” ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

ከዚህ በተቃራኒ አዲስ አባባ ላለፉት አመታት ከትግራይና ከኦሮሚያ በፌዴራል መንግስቱ ወይም በኢህአዴግ ተመርጠውና ተመልምለው በሚሄዱ አስተዳዳሪዎች እየተዳደረች ያለች ሲሆን የካቢኔ አባላቶቹም ከሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች እየሄዱ አዲ አበቤን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሰረት ኢህአዴግ የራሱን ህገ-መንገስት እራሱ እየጣሰው ይገኛል፡፡

የኢህአዴግ መዋቅር፣ እሳቤናና አዲስ አበባ

በመርህ ደረጃ አዲስ አበባን በተመለከተ ህገ መንግስቱ ያን ያህል የሰፋ ችግር አለበት ብዬ አላስብም፡፡ ይልቁንስ አዲስ አበባን በተመለከተና የአዲስ አበባን ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ የችግር ምንጭ የኢህአዴግ መዋቅርና እሳቤዎች ነው፡፡

የመጀመሪያው ችግር ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር እንደመሆኑ መጠን በሀገሪቱ የሚታዩ አብዛኛዎቹን ችግር በአራቱ ፓርቲዎች አይን የመመልከት አባዜ አለበት፡፡ በዚሁ መሰረት ኢህአዴግ ላለፉት 28 አመታት የአዲስ አባባን ህዝብ ከአራቱ ክልሎች የመጡ ጥርቅሞች አድርጎ እየተመለከተ ይገኛል  (በአዲስ አበባ የስልጣን ክፍፍል ለአራቱ ክልል ተወላጆች በኮታ የሚከፋፈለውና አራቱም ክልሎች ወይም ፓርቲዎች ወደ አዲስ አበባ የራሳቸውን ተወካይ በመላክ አዲስ አበባን ግራ እያጋቧት ይገኛሉ)፡፡

ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ በእኔ እምነት የአዲስ አበባ ህዝብ ልክ middle class በሚበዛባቸው ታላላቅ ከተሞች እንደሚታየው ከብሔር ማንነት በዘለለ ብዙ ፍላጎቶችና ማንነቶች አሉት፡፡ ይህንን ፍላጎትና ማንነት ሌሎች ትናንሽ ወይም ታዳጊ አካባቢዎች ላሉ ፍላጎቶች በተሰጠው ምላሽ መሰረት መመለስ ከባድ ነው፡፡ በአምቦ፣ በሃዋሳ፣ በአዴግራት፣ በደብረ-ማርቆስ ፣ በጋምቤላ… አካባቢዎች ጎበዝ የተባለ ፖለቲከኛ አዲስ አበባ ሄዶ እነዛ አካባቢዎች እንዳደረገው ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የስነ-ልቦና መዋቅር እጅግ የተለየ ነው፡፡  የአዲስ አባባን ህዝብ ፍላጎት ለመመለስ የህዝቡን ስነ-ልቦናና ፍላጎት በተገቢው መልኩ የተረዳና ከህዝቡ ጋር የኖረ የአዲስ አበባ ፖለቲካኛ በወንበሩ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

በአዲስ አበባ ከአራቱ ክልሎች ያልሆኑ፣ ለብሔር ማንነት ደንታ የሌላቸው፣ የከተማ ማንነት ያጎለበቱና ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጲያዊያን አሉ፡፡ እነዚህን የኢህአዴግ መዋቅርም ሆነ እሳቤ የተፋቸው ናቸው፡፡

ሁለተኛው የኢህአዴግ ችግር የአዲስ አበባን ህዝብና ከተማ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚያደርገው በብሔር አይን መመልከቱ ነው፡፡ አዲስ አበባ የፖለቲካ መሃከል ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም መሃከል ነው፡፡ ይህ ማለት በሌሎች ያደጉ ኢኮኖሚዎች እንደሚታየው ህዝቡ እራሱን በብሔር ማንነት ከማየት በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ማንነት (Economic identity) አለበት፡፡ ስለዚህ አብዛኛው ህዝብ ኢህአዴግ እንደሚለው ለብሔሩ ሳይሆን ለኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቹ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት ደግሞ ፍላጎቱን የሚያውቅ መሪ ያስፈልገዋል፡፡

ሶስተኛው ችግር ኢህአዴግ አዲስ አበባን የኦሮሞ ልሂቃንን ለማባበል መስዋህት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ላለፉት 50 ዓመታት መሰረት አድርጎ የተነሳባቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጣ ወዲህ ግን የፊንፊኔ ጉዳይ ከጥያቄዎች ዝርዝር ገብቷል፡፡ ኢህአዴግም አብዛኛውን ዘመኑን (ከአርከበ ውጪ) ህገ-መንግስቱ እንደሚለው አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ከመስጠት ይልቅ የኦሮሞ ልሂቃንን ለማስደሰት ለኦሮሞ አሳልፎ ሰጠ፡፡ ይህ ጉዳይ እስካሁን ድረስ ያልተጻፈ ህግ ሆኖ አዲስ አበባን ለማስተዳደር የአዲስ ነዋሪ መሆን ሳይሆን ኦሮሞ መሆንን እንደ ግዴታ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

ኦሮሚያና አዲስ አባባ

ህገ-መንገስቱ እንደሚለው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም የምታገኘው የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ብቻ ነው (በህገ-መንግስቱና በፌዴራል ደረጃ አዲስ አበባም ኦሮሚያም እኩል እንደሆኑ ልብ ይሏል)፡፡ ከዚህ በተረፈ በዝርዝር በህግ ባልተገለጸ ሁኔታ ኦሮሚያ የአዲስ አበባ  ነች ብሎ መናገር አድካሚ ነው፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የኦሮሞም ነች፣ የአማራም ነች ፣ የአፋርም…

በእኔ እይታ ኢህአዴግ ህገ መንግሰቱ እንደሚለው የአዲስ አበባን ጉዳይ ተግባራዊ ቢያደርግ የአዲስ አባባ ጉዳይ በቀላሉ መፍትሔ ያገኛል፡፡ ምክንያቱም በህገ መንግስቱ በግልጽ አዲስ አባባ የአዲስ አበቤዎች ናትና፡፡