ከመጋቢት እስከ መጋቢት: 15 ምክንያት ለመውቀስ፣ 30 ምክንያት ለማወደስ!

በዳንኤል ሺበሺ (ፖለቲከኛ)

በዶ/ር አቢይ ከሰርን ወይስ አተረፍን? ያሻግሩናል ወይስ ያሳፍሩናል?ይህን ጥያቄ እያሰላሰልን ወደ አንኳር መመዛዘኛ ነጥቦቼ ልውሰዳችሁ፡፡ ሁሉንም ሥራ መዘርዘር ባይቻልም ግን አንኳር አንኳር ነጥቦቹን ከቃላቸው ጋር እናዛምዳለን ፡፡

ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም፣ መስቀል አደባባይ፣ ፎቶ © ስዩም ተሾመ
ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም፣ መስቀል አደባባይ፣ ፎቶ © ስዩም ተሾመ

1ኛ. ጅማሮ!

ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠ/ሚ/ር ሆነው በሕ/ተ/ም/ቤት ተሰየሙና ቃለ-መሃላ ፈፀሙ፡፡

2ኛ. ማዕከላዊ ተዘጋ!

ዓርብ መጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀድሞ ጠሚ ኃማደ ጊዜ የተወሰነ ቢሆንም “ማዕከላዊ” የሚባለው የወንጀል ምርመራ ማዕከል (ቤታችን) በይፋ እንዲዘጋ አዘዙ፡፡ ጥርሳችን ሀጫ በረዶ ሆነልን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአመዛኙ ተቋርጦ የነበረውን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቀጥል አደረጉ፡፡ በመቀጠልም ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያንና ሌሎች በርካታ እስረኞችን በሙሉ ከእስር ለቀቁ፡፡ ዘንድሮማ ተዓምር ነው አልን፡፡

3ኛ. የካቢኔ አሰያየም!

ሐሙስ ሚያዝያ 11ቀን፡ 2010 ዓ.ም. አዲስ ካቢኔ አቋቋሙ ከማለት ጉሊቻ ቀያየሩ ማለት ብቀለንም ግን ካቢኔያቸውን በመበወዝ ፦ እነ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ የግብርና ፣ አቶ ሞቱማ መቃሳ የመከላከያ ፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የትራንስፖርት ፣ አምባ/ር ተሾመ ቶጋ የመን/ት የልማት ድርጅቶች ሚ/ር ፣ ዶ/ር አማን አህመድ የጤና ጥበቃ ፣ ዶ/ር ሒሩት ወ/ማርያም የሠራተኛና ማኅ/ዊ ጉ/ሚ/ር በማድረግ እና ሌሎችንም በማካተት ካቢኔያቸውን ይፋ አደረጉ ፡፡

4ኛ. የመቀሌና የጎንደር ጉዞ!

ዶ/ር አቢይ ወርሃ ሚያዚያ ወደ ሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ተጉዘዋል፡፡ ዓርብ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አህመድ በጎንደር ከተማ ተገኝተው ከጎንደር ሕዝብ ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የወልቃይት የማንነት ጠያቂ ኮሚቴ አባላትንም በተለይ አወያዩ ፡፡

5ኛ. ጉዞ ወደ ሐዋሳ!

ሐሙስ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አህመድ በሐዋሳ ከተማ ተገኝተው ከሐዋሳ ሕዝብ ጋር ተወያዩ፤

6ኛ. ጉዞ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ!

ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ታዋቂና ተወዳጅ ግለሰቦች በተገኙበት (እነ ዶ/ር ምሕረት ደበበ፣ አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና ሌሎችም በታደሙበት በሚሊኒዬም አዳራሽ መሳጭ ንግግር አደረጉ፤

7ኛ. የነፃነት ኃይላት ፍቺ!

ቅዳሜ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ታላቅ ሰው! አቶ #አንዳርጋቸው_ጽጌን ጨምሮ ከ500 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኞች ክስ በማቋረጥ፣ በምህረትና ይቅርታ እንደተደረገላቸው በተገለፀ ከ3-ቀናት በኀላ ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም.
– አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል፡፡
– ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጀዋር መሐመድ (አክቲቪስትና የOMN ሥራ አስኪያጅ)፣ የኢ-ሳት ቴሌቪዢንና ሬዲዮ ጣቢያ ክሶች መቋረጡ ታወጀ ፡፡

8ኛ. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ!

ቅዳሜ ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ተግባራዊ ሆኖ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሣ ለሕ/ተ/ም/ቤት ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለ3 ወራት ያክል ቆይቶ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሣ፡፡ ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር ክብር የተቸረው ውሳኔ ነበር ፡፡

9ኛ. የባለሥልጣናት ስንብት!

ሐሙስ ግንቦት 30ቀን፡ 2010 ዓ.ም. አይነከውን የህወሓቱን ሰው! የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜ/ጄነራል ሳሞራ ዩኑስ ከሥልጣናቸው በክብር ተሰናብተው በምትካቸው ጄነራል ሰዓረ መኮንን ተሾሙ፡፡

10ኛ. የአሸባሪነት ትርጉም!

ሰኞ ሰኔ 11ቀን፡ 2010 ዓ.ም ለሕ/ተ/ም/ቤት ወሳኝ ንግግር ካደረጉ በኋላ ለተጠየቋቸው ሁሉ ጥያቄዎች አስገራሚ ምላሽ ሰጡ ፡፡ “እኛ ነን አሸባሪዎች!” እስከማለት ደረሱ፡፡

11ኛ. ጉዞ ወደ ደቡብ አቅጣጫ!

ማክሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሐዋሳና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ተጉዘው በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ከሕዝብ ጋር ተወያዩ ፡፡ የክልሉን ሕዝቡን ደም ሲመጡ የነበሩና ከሰብዓዊነት ወጥተው የበሰበሱ ካድረዎች በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣን እንዲለቁ ተማጸኗቸው፡፡ በአሰራራቸው መሰረት ቀላል የማይባሉ ካድሬዎች ከሥልጣን ተባረሩ፡፡

12ኛ. የሰኔ 16ቱ ነገር!

ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ አዲሱ ለውጥ ኃይላት (ለዶ/ር አብይ አህመድ) የሕዝብ የድጋፍና ዕውቅና መስጠት ግድ ስለሆነ ታላቅ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ፤ በዕለቱ በተወረወረ ቦምብ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ መቶዎች መቁሰሉ ይታወቃል ፡፡ እንደ ሀገር ከጉድ ያመለጥንበት፡፡

13ኛ. በደኢህዴን ላይ የተወሰደ እርምጃ!

ሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በደቡብ ክልል የብሔረሰብ ግጭትና ውድመት በመበራከቱ ምክንያት የደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከንቅናቄው ሊቀመንበርነት በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ተገደዱ፡፡ ከላይ በተ.ቁ 11 ላይ ከተጠቀሰው ጉዳይ ጋር እንደሚያያዝ መገመት ይቻላል ፡፡

14ኛ. የአስመራው ልዑክ!

ማክሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሁለት አሥርተ ዓመታት ቆይታ በኋላ የኤርትራ መንግሥት ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ በደል እስካልተደገመ ድረስ ሁሉንም ይቅር አልን፡፡

15ኛ. የድጋፍ በባህር ዳር!

ዕሁድ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ከላይ በተ.ቁ 12 ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ ለዶ/ር አብይ አህመድ አመራር ዘለግ ያለ የድጋፍ ሰልፍ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲዬም በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ፤

16ኛ. ጉዞ አሥመራ!

ዕሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አስመራ አቀኑ፤ ይህ ጉዞ ለኤርትራውያኑ ፕሬዚደንት ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ እና ለአዲሳባው ለዶ/ር አቢይ ታሪካዊ ቀን ተብሎ ተመዘገበ ፡፡

16.1. የ40-ምንጮቹ ድጋፍ ሰልፍ!

ሰኞ ሐምሌ 2ቀን 2010 ዓም አርባምንጭ፣ ጎጃም፣ ዳውሮን ጨምሮ በአውሮጳና በሌሎች ክፍለ-ሀገራትና ክፍለ-አህጉራት ፍጹም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ፡፡ በአርባምንጩ ሰልፍ ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዤ ተገኝቼ ንግግር ያደረኩት እኔ (ዳንኤል ሺበሺ) ሲሆን፤ ሕዝቡ ደስታውን ከሀገሩ ፍቅር ጋር በማስተሳሰር ከ1ሺ ሜትር በላይ ርዝሜት ያለውን ባንድራ (አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ወይም ልሙጥ) ይዘው ወደ አደባባይ ወጣ፡፡ ከባንድራው ርዝሜት አንፃር በኢትዮጵያ ታሪክ የኮንሶ ሕዝብ ይዞ ከወጣው ባንድራ ቀጥሎ የ2ኛነትን ደረጃ የያዘ ነበር ፡፡

17ኛ. ፕ/ት ኢሳያስ “ኢሱ!” ወደ ሀገር ቤት መግባት!

ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሁን ጎረቤታቸውንና የቀድሞ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በዶ/ር አቢይ ግብዣ ገቡ ፤
በመቀጠልም ዕሁድ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአንድ ቀን ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ፕሬዚደንቱ በአዲስ አበባ በሚሊኒዬም አዳራሽ ዶ/ር አብይን ጨምሮ በርካታ ኢትየጵያውያን በተገኙበት በአማርኛ ጭምር ንግግር አደረጉ፤ በዚህ ዝግጅት ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ከያንያን እነ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ነዋይ ደበበ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)፣ የቢፍቱ ኦሮሚያ ባንድ፣ የሀረርኛ ሙዚቃ ባንድ፣ እና ማሀሙድ አህመድ ነበሩ ፡፡

18ኛ. አየር መንገድ!

ረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ በአዲስ መልኩ በረራውን እንዲቀጥል ተደረገ፤

19ኛ. ኢትዮ-ቴሌኮም!

ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮ ቴሌኮም በድምጽ ጥሪ፣ በቴክስት መልዕክትና በኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ ትርጉም ያለው የታሪፍ ቅናሽ አደረገ፤

20ኛ. መግለጫ!

ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ለበርካታ ሀገር ቤትና ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች በሀገራዊና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ መግለጫ በመስጠት የመንግሥታቸውን አቋም ገለፁ፤

21ኛ. የኢሌ ነገር!

ሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በፈፀሙት ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር አዋሉ፤ የምሥራቁን ጎማ አስተነፈሱልን ማለት ነው ፡፡

22ኛ. ገቡ!

ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ በወያኔ አገዛዝ ዘመን የተደረጉ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች ፣ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ወዘተ (አንዳንዶቹ ከነ ቫይረሳቸው) ወደ ሀገር ቤት ገቡ ፡፡

22.1. ታላቁ ሰው ታማኝ በየነ!

ቅዳሜ ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የዓለም ሰብዓዊ ፍጡር መብት ተሟጋቹ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከ22 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ በከፍተኛ አቀባበል ተመለሰ፤ በሕይወት ኖሬ እሱን መቀበል በመቻሌ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

22.2. አግ7!

ዕሁድ ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም ፕ/ር በርሃኑ ነጋ’ን ጨምሮ ሌሎች የአርበኞች-ግንቦት ሰባት (አግ7) አመራሮች ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በአአ ስቴዲየም ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፤ ይሁን እንጂ ለኦነግ የተፈቀደው መስቀል አደባባይ ለአግ7ቶቹ መከልከሉ በሕዝብ ዘንድ የተወሰነ ቅሬታ ጥሎ ማለፉ ይታወሳል ፡፡

22.3. ኦነግ!

ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. የኦነግ አመራሮችና ወታደሮች በደማቅ አቀባበል ወደ አገራቸው ሲገቡ በመስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው ፡፡

23ኛ. የፌ/ም/ቤት Vs የማንነት ጥያቄ!

ዓርብ ጥቅምት 2ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተነሥተው ለነበሩት የማንነት ዕውቅና ጥያቄዎች በአግባቡና በአፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጫ ሰጠ፤ ይህም ኢህአዴግ የማንነት ጥያቄ መልሼ መዝገቡን ወደ መዝገብ ቤት ካለ በኀላ የተንሰራራ ጉዳይ በመሆኑ ለህወሓት ሌላው መርዶ፤ ሌላው ውርደት፤ ሌላው ውድቀት ነበር፤

24ኛ. 50:50!

ማክሰኞ ጥቅምት 6ቀን፡2011 ዓ.ም 50:50 የተባለለትን የአዳዲስ ሚኒስትሮችን ሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በማቅረብ አስጸድቀዋል፤ ከነዚሀም መካከል 50 በመቶው በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ሆነው ተገኙ፡፡

♥24.1. ሴቷ ርዕሰ ብሔር!

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ አዲስ ሴት ፕሬዚደንት (ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ)ን አገኘናት፤

♥24.2. ኮሚሽን!

ዓርብ ጥቅምት 23ቀን፡ 2011 ዓ.ም. ለአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን የሚያጠና አንድ አዲስ ኮሚሽን እንደሚቋቋም ይፋ ተደረገ፡፡

25ኛ. በፑሻአፕ የመከነው መፈንቅለ-X? ሙከራ!

ጥቅምት? 2011 ዓም እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ፤ ግን ሕግንና ወታደራዊ ዲሲፒሊን በመጣስ የተንቀሳቀሱ ወታደር ናቸው የተባሉት እስከ መንግሥት መናገሻ ብሎም እስከ ጓዳቸው ድረስ ጥሰው በመግባት የከበባ ሙከራ አደረጉ፡፡ ሰውየውም ወታደር ነበረና የተቸራቸውን ፈተና በብልሃት አለፉ፤ ቀለል ባለ ፑሻአፕ፡፡

26ኛ. መፈንቅለ-ሙሰና ሙከራ!

ሰኞ ኅዳር 3ቀን፡ 2011 ዓ.ም. ወደ 60 የሚሆኑ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ባለሥልጣናት (ጄኔራሎች) በከባባድ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ፤ በሙስና ላይ የተነጣጠረች የመጀመሪዋ ጥይት?

27ኛ. መፈንቅለ-ማዕቀብ!

ረቡዕ ኅዳር 5ቀን፡ 2011ዓ.ም. በኤርትራ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ተጥሎ ለረዥም ዓመታት የቆየው ማዕቀብ እንዲነሣ ተደረገ፤ በዚህም የዶ/ር አቢይ እጅ እንዳለበት መገመት ይቻላል፡፡

28ኛ. ብርቱ ካህኗ!

ሐሙስ ሕዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀድሞ ኢህአዴግ መንግሥት ተቀዋሚና የአንድነት ፓርቲ መሥራችና ሊቀመንበሯ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በዶ/ር አብይ አህመድ ተሾሙ፤ ድንቅ! ተባለ፡፡

29ኛ. ተቃውሞ Vs ተፎካካሪ!

ማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አህመድ 80 ከሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያዩ፡፡ ይህም በይዘቱ ለየት ያለ አቀራረብ ነበር ፡፡

30ኛ. የበሪሊን ግንቡ ፈረሰ!

ሰኞ ታኀሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በሁመራ በኩል ያለው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ተከፈተ፤

31ኛ. የነጮቹ አንቱታ!

ዕሁድ ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ጀምሮ 30 ደቂቃዎች የፈጀ ዘጋቢ ፊልም በቢቢሲ BBC የእንግሊዝኛው አገልግሎት ስለ ወጣቱ የኢትዮጵያ መሪ (ዶ/ር አብይ አህመድ) አስደማሚ የለውጥ ጎዳና አስቀኘን “Ethiopia Racing to Reform” (“ኢትዮጵያ ወደ ተሐድሶ ስትገሰግሥ”) በሚል ርዕስ የተሠራው ዘጋቢ ፊልሙ የዚህ ዓይነቱ ተሐድሶ በፍጥነቱና በአስደናቂነቱ በዓለም ወደር የለሽ እንደሆነ በአግራሞት ዘገቡ፡፡ በተያያዘም የአሜሪካው ታይምስ መጽሄት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ዓም በዓለም ከ100 ተጽፅኖ ግለሰቦች ሊስት ውስጥ በማካተት ይፋ አደረገ ፡፡
♥♥♥

“… እናም በዶ/ር አቢይ ከሰርን ወይስ አተረፍን? ያሻግሩናል ወይስ ያሳፍሩናል?

♥♥♥

1ኛ. መስከረም 1ቀን፡ 2011 ዓም የቡራዩ ዋይታ!

የቡራዩን እልቂት (በተለይ ከጋሞ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታ፣ በተወሰኑ አማራ እና ኦሮሚያ አከባቢዎች መጥተው በቡራዩ ከተማ በሚኖሩ ንፁኃን ላይ የደረሰውን ሰቅጣጭ አደጋ እናስተውሳለን፡፡ ለእነዚህ ተጎጂዎች የኦሮሚያውም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት የፀጥታ ሁኔታውን በተወሰነ መልኩ ከማረጋጋቱ በዘለለ ነጥሮ የወጣ የቁስና የገንዘብ ርዳታ አላደረገም፡፡ የፀጥታ ሁኔታውም ቢሆን ረገብ ያለው በተለይም በሚዲያዎቹ ጥረት፣ በቡራዩ ከንቲባ ውስጥ ባሉ በጥቂት ግለሰቦች/ኃላፊዎች፣ በጋሞ አባቶችና በእኛም ጥረት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይሄንን ጉዳይ የሚከታተል ሉለት ዐቢይ ኮሚቴ አለ፤ እኔ በሁለቱም ኮሚቴ ውስጥ አለሁበትና እንደ መንግሥት የሥነ-ልቦና፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ ስለመደረጉን አላስታወስም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የኦሮሚያውን ፕ/ት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ’ን በአካል ቀርቤ ጠይቄ የነበረ ብሆንም በዝምታ አልፈዋል፡፡ ጉዳት አድርሰዋል ከተባሉት ውስጥ አብዘኞቹ በአባጌዳዎች ምልጃ ተለቋል፤ እየተለቀቁም ነው፡፡ በምትኩ የተጎጂ ቤተሰብ አባላት የነበሩ ወጣቶች እየታደኑ እንዲታሰሩና ክስ እንዲመሰረትባቸው ተደርገዋል፡፡ የግጭቱን መንሥኤ መጥቀስ አልሻም፡፡

2ኛ. ቤት ፈረሳ!

የወፎችን ጎጆ ማፍረስም እንኳ ይዘግንናል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ለገጣፎ ቤት ፈረሳን ልብ ይሏታል፡፡ የእናቶችን እንባ፣ የህፃናትን ጩሄት ፡፡ ይህ የሆነው በዶ/ር አቢይ አንደበት እንደሰማነው ከዚህ በኀላ በድሃው ላይ ጣሪያ አይፈርስም ባሉበት ማግሥት መሆኑ አቅማቸውንና አቋማቸውን እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ስለዚህ እነ ዶ/ር አቢይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጀምሯል እንደ ማለት ነው፡፡

3ኛ. የዴሞግራፒ ለውጥ!

መፈናቀልን እንደ ልማድ እንውሰድ ፡፡ … ነገሩ የዴሞግራፒ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ ከሆነ፤ እኛ የምናውቀው የአየር ንብረት ለውጥን ነው፡፡ የተፈጥሮ ሂደትን በመዝለል በጥድፊያ የሚደረግ የህዝብ አሰፋፈርና የሀብት ሽሚያ ተገቢ አለመሆኑ አያከራከርም ፡፡ እንዲህ አይነት ነገር የሰማነው በዶ/ር አቢይ መንግሥት ዘመን መሆኑ (ከቃላቸው አንፃር) ለነገሩ ክብደት እንድንሰጥ አድርጎናል ፡፡ ከሶማሌ ክልል ተፈናቃይ ኦሮሞዎችን በአዲሳባ ዙሪያ እና በከተማዋ ያሰፈሩበት አግባብ ለዚሁ አንዱ ማሳያ ተደርጓል ፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ አዲሱ አረጋ የሰጡት ማብራሪያ ከዴሞግራፒ/Demography ወይም የአዲስ አበባን ሕዝብ አሰፋፈር ከመቀየር ስልት ጋር ማያያዛቸው ብቻም ሳይሆን ህወሓታዊ ሴራ መልክ መያዙ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያሳዘነ መሆኑ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በአዲሳባ ከተማና በዙሪያዋ የመኖር #ፍጹም መብት ያለው ሲሆን፤ ግን አሰራሩ በሴራና በአድሎዎ መልክ ከሆነ፤ ጠንከር ያለ ጥያቄ ወደነ ዶ/ር አቢይ እንዲወረወር ማድረጉ ግድ ነው የሚሆነው ፡፡

እዚህ ላይ አዲስ አበባን ወደ ፊንፊኔ የመቀየር ዓላማን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተደረገ የጨፌ ኦሮሚያ የእርቅ ህዝባዊ ሸንጎ ላይ አቶ ለማ መገርሳ ለጉባዔ ተሳታፊዎች አዲስ አበባንና ኦሮሚያን ጉዳይ አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች በኦሮሚኛ የሰጧቸው መልሶችን በተመለከተ የዶ/ር አብርሃም አለሙ ትርጉም ቃል በቃል እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

“የከተማ ፖለቲካን (አርበን ፖለቲክስ) ማጤን አለባችሁ፤ ችላ ልትሉት አይገባም፤” ያላችሁት፣ ትክክል ነው፡፡ የከተማ ፖለቲካ (አርበን ፖለቲክስ) ሊጤን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማእከል (ሴንተር ኦፍ ፖለቲክስ) ከተሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሀገር ፖለቲካ የሚወስነውም ከተማ ነው፤ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተማ ውስጥ ፖለቲካ ማለት አንድ ቁጥር ዲሞግራፊ (የህዝብ ስርጭት) ነው፡፡

“እዚያ ላይ አንዱን ወደዚያ መግፋት፣ አንዱን ወደዚህ መጎተት፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን፣ እንደ ኦሮሚያ ብዙ ነገሮች እየሰራን እንዳለን መገንዘብም ያስፈልጋል፤ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የጀመርነው በጣም አበረታች ነው፡፡

ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ500,000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ እንደምንሆነው ሆነን፣ ገፍተንም፣ ምንም ብለን፣ ከዚህም ከዚያም ብለን፣ የገዳ አባቶችንም፣ ሽማግሌዎቻችንንም ይዘን፣ እንደለመድነው እርቅ ፈጥረን፣ አቅፈን፣ ስመን ወደ ነበሩበት ቦታ ልንመልሳቸው እንችል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መመለስ ይቻል ነበር፤ እኛ ግን ልንመልሳቸው አልፈለግንም፡፡ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ለኦሮሞ አንድነት፣ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ዛሬም ችግር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ገጠር አላሰፈርናቸውም፤ ከተማ ነው ያሰፈርናቸው፣ እነዚህን ሰዎች፣ እወቁ፡፡

በአንድ ጊዜ ከ 500, 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6,000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ አይደለም፡፡ እኒህን ከዚያ የተፈናቀሉትን ሰዎች፣ የዚህን አካባቢ ባህል የማያውቁ ሰዎች፣ በብዙ ነገሮች ከአካባቢው ጋር የማይመሳሰሉ፣ ይቸገራል መችም፣ ይቸገር፤ ዛሬ ችግር የማያጣው ቢሆንም፣ ከተቸገረም እዚሁ ከተማ ውስጥ ይቸገር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በእግሩ የሚቆምበት መሬት ይኑረው፤ እሱ ቢቸገርም ለልጆቹ የሚሆን ስለሆነ፣ ብለን ህዝባችንንም አስቸግረን ካለን ነገር ላይ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሰፈርናቸው፡፡

አብዛኛው የሀረርጌ ሰዎች ናቸው፣ እወቁ፡፡ ቦርደዴ ማስፈር ይቻል ነበር፤ ምስራቅ ሀረርጌ ልናሰፍራቸው እንችል ነበር፡፡ ማስፈር ትክክል ከሆነ እንዲያውም እዚያው አካባቢ ነበር ማስፈር የሚገባው፤ ያን ባህል ነው የሚያውቀው፣ ያን አየር ነው የሚያውቀው፡፡ ወደማያውቀው ባህል እዚህ አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ አሰፈርነው፡፡ ቢቸገር ቢቸገር ሁለት ዓመት ነው ሊቸገር የሚችለው፤ ከዚያ በኋላ ሰው ሆኖ ይወጣዋል፡፡

ይሄ በፖለቲካ ላይ ያለው ፋይዳ፣ ሄዶ ሄዶም በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ስለሚፈይድ፡፡ ወጣቱንም ስራ እናስይዛለን ብለን በንግድ ስም፣ በሌላም ነገር ስም ብዙ ነገር ስናደርግ ነበር፤ እናም አብዛኛውን ከተማ ውስጥ አስገባነው፡፡ ወደ ከተማ ስናስገባው የሚኖርበት ቦታ ኖሮት ነው፡፡ ከ500,000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያን ክልል ሰራተኞች ዘንድሮ መሬት የሰጠናቸው ገጠር ውስጥ አይደለም፤ ይብዛም ይነስም ከተማ ውስጥ ነው የሰጠናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ነው የሰጠናቸው፡፡ ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ነው ብዬ አይደለም፤ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሆኖም ችላ ያልነው ነገር አይደለም፤ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ ስንሰራም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህም በዚሁ ረገድ ቢታይ መልካም ይሆናል ብዬ ነው የማየው” የሚል ምላሽ መሰጠቱን እናስተውሳለን ፡፡

4ኛ. የመምህራን ቅጥር ጉዳይ!

እኔን ጨምሮ በርካቶቻችን ለኦሮሞ ጥቅም ታግለናል፤ አሁንም እየታገልን ነው፡፡ የኦሮሚያን ጥቅም እየተፃረርኩ የኦሮሞ ልጅ መሆን አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ማንም መጠቀም ያለበት በፍትሐዊ ህግ እንጂ በሴራና በድብቅ መሆን እንደሌለበት እምነታችን ነው፡፡ ከ1660 በላይ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ መምህራንን በአአ ት/ቢሮ ኃላፊነት እንዲቀጠሩ የተደረገበት አግባብ በዶ/ር አቢይ ዘመን የተፈፀመ በመሆኑ፤ ይህ ዕድል ለሶማሌው፣ ለጉራጌው፣ ለትግሬው፣ ለወላይታው ወዘተ አለ ወይ ብለን እንዲንይቅ ያደርገናል፡፡

5ኛ. ከንቲባውና መዘዙ!

ማንም ዜጋ በሀገሩ መዲና የመመረጥ እና የመምረጥ መብት አለው፡፡ በጥቅሉ የኢ/ር ታከለ ኡማ ለምን ከንቲባ ሆነ የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡ በአመጣጡ ላይ ካልሆነ በስተቀር፡፡ የሽግግር ተስፋን ተስፋ አድርገን ካልሆነ በስተቀር የዶ/ር አቢይን አመጣጥ ህጋዊ አድርገን የከንቲባውን ሸመት ሕገ ወጥ ማድረግም በራሱ ሚዛንን መሳት ነው የሚመስለኝ ፡፡ ኢንጅነሩ የተሾሙበት መንገድ እያጨቃጨቀ ባለበት ሁኔታ፤ አቶ አዲሱ አረጋ ሲናገሩ … (ቃል በቃል ባይሆንም) ኢ/ር ታከለ ኡማ እዛጋ የተቀመጡት የፊንፊኔ ባለቤትን እንዲያረጋገጡና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዲያስፈጸሙ (ዝርዝሩን ከዶ/ር አብርሃም ትርጉም ማግኘት ይቻላል) ነው የተባለውም በጠቅላያችን ዘመን ሲሆን፤ በሌላ በኩል ይህን የተቃወሙ አዲስ አበቤዎች ባለአደራ (ባልደራስ) በማቋቋም ጉዞ መጀመራቸውና ይህንን ተከትሎ የጠቅለያችን ዛቻ! …የጦርነት! ምናምን ካሉ በኀላ ባልድራሲ ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳን እንዳይሰጥ ከአንዴም ሁለተ መከልከሉ ቃላቸውን የሚፃረር ነበር ፡፡

6ኛ. የጀዋር መንገድ (ዳንዲ)!

በወላይተኛ አንድ አባባል አለ፤ “የዝንጆሮ መንገድ ምንም ቆንጆ ቢሆን መዳረሻው ወደ ገደል ነው” ይባላል፡፡ ጀዋር የራሱ የሆነ በጎ ጎኖች እንዳሉ ሆኖ፤ ማናችም እንደምንረዳው የOMN ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሀመድ መንገድ ይታወቃል፡፡ ይሳካለታል/አይሳካለትም ሌላ ነገር ሆኖ፤ በቅድሚያ የኦሮሚያ መንግሥት መመሥረት፤ ቀጥሎም የፖለቲካና የሚዲያ ሥልጣን መቆጣጠር ሲሆን፤ በመጨረሻም የሃይማኖት በላይነትን ማረጋገጥ መሆኑን ካለመጠርጠር መጠርጠሩ እንደሚሻል አብዘኞቻችን ከተረዳን ቆይተናል ፡፡

የኦሮሚያው ቃለ አቀባይ በአደባባይ ሲናገሩ እኛ የጀዋር’ን መንገድ እንደግፋለን! ያሉበትን እናስተውሳለን፡፡ የአዲሳባ ባለቤትነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን የአፍሪካዊያን ነው በሚባልበት በአሁኑ ወቅት፤ ጀዋር ከሚረጨው እሬት አደብ እንዲገዛና አትበጥብጠን! ማለት ሲገባ ጭራሽ የእነ ጀዋርን ኮቴ እንከተላለን ማለት እና ይህንን ተከትለው እነ ክቡር ፕ/ት ለማ መገርሳ’ም የእንደግፋለን ሀሳባቸውን በመግለጫም ጭምር ማረጋገጣቸው፤ እና ይህን ሀሳብ ዶ/ር አቢይ አህመድ በሊቀመንበርነት የሚመራው ፓርቲ (ኦዴፓ) ለስኬቱ ተግተው እንደሚሰራ አቋም የተያዘበትን ሁኔታ ሲታይ ምን እየተሰራ ነው? እንድንል ብንገፋፋ ልንወቀስ አይገባም፡፡

7ኛ. የጃዋር መንገድና የድሃው ጎጆ!

በዶ/ር አቢይ የሚመራው ኦዴፓ ኩዬፈጬ ኮንዴሚኒየም ለባለ ዕጣዎች ለጊዜው ቢሆንም እንዳይተላለፍ መታገዱ አሳዛኝ ነበር፤ የጀዋርን ዕቅድ ማስፈፀም ወይም በጥቅሻ እንደመግባባት ነው፡፡ የልማት ተነሽ ገበሬዎች ካሣ አነሰኝ ጥያቄ ካለባቸው፤ መጠየቅ ያለባቸው መሬቱን የቀማቸው ወይም ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው አካል እንጂ ድሃው የአዲሳባ ነዋሪ እንዲሆን ዳር ዳር ማለታቸው ሁለተ እንድናስብ ያደርገናል “በሬሳችን ላይ!” ያለው ጀዋር መሆኑ አይዘነጋም ፡፡

8ኛ. የወሰን/የድንበር ነገር!

በአንድ በኩል፤ የአዲሳባ እና የኦሮሚያ ወሰን ጉዳይን በተመለከተ ተነጋግረው ችካል ቸካይ? መላምት መቺ የተባሉ ስድስት አባላትን ያቀፈ አንድ ኮሚቴ በዶ/ር አቢይ ተቋቋሟል፡፡ ተደራዳሪውም አደራዳሪውም ሁለቱም የኦሮሚያ ተወላጆች የሆኑ ባለሥልጣናት ሆነው ተሰይሟል፤ በኦሮሚያ በኩል የኦሮሚያ ም/ፕሬዚዳንት በወ/ሮ ጣይባ የሚመራ፤ በአዲሳባ በኩል በም/ከንቲባ ታከለ ኡማ እንዲመራ የተደረገበት ሁኔታ ለጥርጣሬ ያጋለጠ ነበር፡፡ በሌላ በኩል እንደ ሀገር ተመሳሳይ ጥያቄዎችን የሚያጠና በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን፤ ሁለቱንም አካላት ያቋቋሙት ዶ/ር አቢይ በመሆናቸው ነገረ-ሥራቸው ለህዝቡ ግራ ቢገባው አይፈረድበትም ፡፡

9ኛ. የመታወቂያ እደላ ጉዳይ!

በእኔ እምነት ለኦሮሞ ሀገሩ ኦሮሚያ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ ሁሉ እንጂ፡፡ በኬኒያም ሆነ በአሜሪካና በአውሮጳም ሰፋፊ ይዞታ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ያውም ሁሉም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብቱ ተጠብቆለት፡፡ የነገሩ ምንጭ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ላልሆኑ ከገጠሪቱ ኦሮሚያ አከባቢዎች በመጥራት በገፍ መታወቂያ እየታደለ ነው የሚባለው ጉዳይ ሲሆን፤ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበረ አይካድም፡፡ ርግጠኛ ነኝ ማንም አዕምሮ ያለው ዜጋ ኦሮሞ ለምን የአአ መታወቂያ አገኘ እያለ አይደለም፡፡ እንደ ዴሞግራፒው ሁሉ ሴራና ሽፍጥ እየተሰራ ነው የሚል ነበር፡፡ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፤ ግን ከዚህ ቀደም ሲል የትኛውም አገዛዝ ዘመን ያልተሰራ ነገር በመሆኑ እነ ዶ/ር አቢይ’ን ክፉኛ ለትችት ማዳረጉ አይካድም ፡፡

10ኛ. ህወሓት Vs ኦዴፓ!

ኦህዴድ አብዘኛውን ስልጣን ማግበስበሱና ብዙዎችን ወደ ጥግ ገፍቷል ስለሚባለው ጉዳይ፦ ሹመትን በተመለከተ (በተለይም ወሳኝ ቦታ) በአአ ከተማ ከቀበሌያት እስከ ከንቲባ ቢሮ እና የፌዴራል መዋቅሮችን ሹመት፣ ምደባ እና መሰል ስብጥር ሲመዘን ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች አዳልቷል ያሉ ሁሉ ህወሓትን በኦዴፓ እንደመተካት አድርገው መውሰዳቸው አይካድም፡፡ ይህ ድርጊት ከእነ ዶ/ር አቢይ ዓይን የተሰወረ ነው ለማለት ለማንም ፈተና ቢሆንበት አይፈረድበትም ፡፡

11ኛ. ልዩ ጥቅም!

የአንድ ሀገር ልጆች ከአንዱ የተለየ ጥቅም መጠየቅ ጤናማነት አይመስለኝም፡፡ የመሪነትን ሚና ወደ ጎን በማድረግ? ወይም ቸል በማለት የኦሮሚያ አዲሳባ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ዶ/ር አቢይ ዝምታ’ን ወይም መሀል ሰፋርነትን መርጠዋል፤ ወይም እኔ ነገሮችን በጥልቀት የመረዳት ችግር አለብኝ ማለት ነው ፡፡

12ኛ. የቄሮ ነገር!

ቄሮን የፈጠሩት እነ ኦቦ ለማ ናቸው፤ ወይም ቲም ለማ፡፡ ይሁን እንጂ በሰላማዊ መንገድ የፍትህ ጥያቄ ከማንሳት በዘለለ መልኩ ወንጀል እየፈፀሙ በመምጣታቸው ከሕዝቡ አሜነታን እያጡ መጥተዋል፤ እንደ አጋር ኃይል ሳይሆን እንደ ሥጋት እየተቆጠሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ክቡር አቶ ለማ መገርሳ (ኦዴፓ) ፣ ቄሮ፣ ጀዋር እና ሌሎች የኦሮሞ ብሄርተኞች እና አሸባሪው ህወሓት በጋራ እየተናበቡ እንደምሰሩ ለመረዳት ብዙ ማሰብን የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ የዶ/ር አቢይ መንግሥት የሥጋት ኃይሎችን አቅፈዋል፤ እንዲያው እየደገፉና እያሰማሩ ነው የሚሉም አሉ፡፡ የእርሳቸውን መምጣት ተከትሎ ክልሉ ከሌላው ክልል በአንፃራዊነት የተሻለ የፀጥታ ሁኔታን መፍጠር የነበርበት ቢሆንም የባሰ ሁኔታዎችን እያየን ነው ፡፡ የሰላም እጦቱ በእርሳቸው አመራር ዘመን እና በኦዴፓ ሊቀመንበርነታቸው ላይ ተዳምረው ማወዛገቡን መቀጠሉ እንደነበረ ሆኖ በኦሮሚያ ውስጥ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለማስታገስና ወንጀለኞችን ወደ ህግ ፊት ለማቅረብ ስስ ልብ እንዳላቸው እንድንገምት ማድረጎናል፤

13ኛ. የጌዲኦ ነገር!

ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ፣ ቤታቸው በላያቸው ላይ ፈረሰባቸው፣ ተዘረፉ ወዘተ ሲባል ብዙም ላይገርመን ይችላል፤ ምክንያቱም ለምደነዋልና ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ለሚኖሩ ለጌዲኦ ሕዝብ ሰማዩ እንደተደፋባቸው፤ ምድርቷ እንደጨከነባቸው፤ ሀገር የበሬ ግንባር እንደሆነባቸው፤ የመንግሥት ርኀራኄ እንደራቀባቸው፤ ተመልክተናል፤ አሁን የእኔ ጥያቄ ለምን ይህ/ያ ሆነ የምል አይደለም ፡፡ በጌዲኦ ሕዝብ ሰቆቃ ላይ በቂ መረጃ እያለው ወይም መኖር ሲገባው መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ? ለምን ሐቁን ለመሸሸግ መረጠ? የሚል ነው፡፡ ከሚዲያዎች ብርቱ ወቀሳ በኀላ ዘግይተው ቢሆንም ጠ/ሚሩን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት እስከ ቦታው ተጉዘው የጎበኟቸው ቢሆንም ግን ለዶ/ር አቢይና ለመንግሥታቸው የጎን ውጋት ሆኖ መቀጠሉ፤

14ኛ. የኢ-ሰብዓዊነት ጥግ!

የሻሸመኔውና የጎጃሙ ሀክሞች ግድያ የሁላችንም ልብ ሰብሯል፡፡ ከዚህ ህመም ገና ሳናገግም (በቀጥታ በእርሳቸው ትዕዛዝ ባይሆንም) ግን የሰው ልጅ ከተገደለ በኀላ አስክሬን እየተቃጠለ ያለው (ማክሰኞ መጋቢት 10ቀን፡ 2011 ዓም ኦዴፓ በሚያስተዳድረው ክልል ምዕ/ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ ሁምነ ዋቀዮ ቀበሌ ውስጥ 2-የውጭ እና 3-ኢትዮጵያዊያን በአጠቃላይ አምስት ሰዎች የተገደሉት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው) እና ክቡርነታቸው “እኔ ወደዚያ መሄድ አልችልም” ያሉበት ወለጋ’ም ይሁን፤ በሻሸመኔ ከተማ የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ የተሰቀለበት ሁኔታ እርሳቸው በሊቀመንበርነት በሚመሩት ብሄረሰብ ውስጥ እና በሀገር መሪነት ዘመን በመሆኑ፤

15ኛ. አድሎዎነትን ማስተናገድ!

እነ ዶ/ር አቢይ አርፍደውም ቢሆን ለውጥ እንዲመጣ ከእኛ ጋር የጣሩትን ያህል ለውጡን ለማስቀጠል ቁጥቁጥ ርምጃዎችን መውሰዳቸው፤ ነባር የኢህአዴግ ወንጀለኞችን፤ የሀገር ሀብት የሆነውን ባንክ የዘረፉትን፣ አዲሱ የኦህዴድ ኃይላት ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ዜጎችን ያፈናቀሉትን፤ ቤት ንብረታቸውን የዘረፉና ያወደሙ በተለይም የኦነግ አባላትንና ራሳቸው የፈጠሯቸው ቄሮዎችን ባላየ ሙድ ማለፋቸው፤ በሌላ አገላለጽ በኦሮሚያ ውስጥ የተፈፀሙ ወንጀሎችን የመሸፋፈን አዝማሚያ፤ ትላንት ሀገሪቱን የጎዱትን የሥልጣን ቦታና የነዋሪነት አከባቢ እንዲቀየሩ በማድረግ ሸፋፍነውና አቅፈው ለመሻገር መሞከራቸውን ደማምረንና አስልተን ስናይ ለለውጡ እንቅፋት ሆነው የተገኙት ራሳቸው ዶ/ር አቢይ መሆናቸውን ያሳብቃል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው እርሳቸውም እንደሚሉት በመረጃና በዕውቀት ማነስ ወይም በሁኔታዎች ጫና ምክንያት ሊሆን ቢችልም ግን ምክንያታቸው የቅጣት ማቅለያ ቢሆን እንጂ ከቅጣት ነፃ አያደርጋቸውም ፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለብን ነገር ቢኖር፦ የኦነግ አባላትንም ሆነ ቄሮዎችን (የኦሮሚያ ወጣቶችን) ሁሉ ወንጀለኛ ማድረግም ተገቢ አይደለም፡፡ ኦነግ እንደ ፓርቲ የራሱ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው በመሆኑ ወደ ተራ ውንብድና ውስጥ ይገባል ብለን ማሰብም አይቻልም ፡፡ ግን በኦነግ ስም የሚነግዱ ካሉ ኦነግም ሆነ ኦዴፓ ቸል ማለታቸው እንድንሰጋ ቢያደርግ ስህተት አይሆንም፡፡

16ኛ. ያለመተማመን ውጤት!

ያለመተማመን ሲበቅል ጥርጣሬ ያባብሳል፡፡ ወደ ሌላ አማራጭ እንድናማትር ያደርጋል፡፡ ቀደም ሲል በፌዴራሊዝም ጉዳይ አንደራደርም አሉን፤ እኛም በምክንያት ተቃውምን፡፡ በመቀጠልም በአአ ህዝብ ላይ ጽንፈኛና ጠቅላይ አስተሳሰብ እየመጣ ነው ብለው የሰጉና ብሎም የቡራዩ፣ የጌዲኦ፣ በሶማሌ ክልል በኦሮሞ ተወላጆች ወዘተ ላይ የተፈፀመ አይነት ዕጣ እንዳይገጥመን ብለው የሰጉ የአአ ምሁራን ተሰባስበው የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ (ባልድራስ) ም/ቤት የሚል ስብስብ ማሰባሰብ ጀመሩ ፡፡ ይህንን ተከትሎ ክቡርነታቸው #ከጦርነት ጋር አዛመዱ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አገላለፅ ዶ/ር አቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በንግግር ደረጃ ሁለተኛው ስህተት ይመስለኛል፡፡ በፌዴራሊዝሙ አንደራደርም ካሉት ጋር ስደመር ማለቴ ነው ፡፡ እናም የእነ እስክንድርን እንቅስቃሰን ከጦርነት ጋር ማዛመዳቸው ተገቢነት የሌለው ሀሳብ በመሆኑ ከድንጋጥያችን የተነሳ ምናልባትም የአፍ ወለምታ በመውሰድ ከስር ስር እያረምን አሁንም የተለመደውን ድጋፍ ማድረግን የመረጥን ብዙዎች ብንሆንም ለእርሳቸው ግን ነጥብ እንደመጣል መቆጠሩ አይቀርም ፡፡

ማጠቃለያ፦

አዎን! ለዶ/ር ያለባቸውን አጠቃላይ ውጥንቅጥና ጫና አብዘኛው ሕዝብ ይረዳል የምል እምነት አለኝ፡፡ እኛስ ደግሞ ጭንቀታችንን ወደ ማን መውሰድ አለብን? ወለጋም ሆነ አዷዋ ሀገራችንና ሀገሮዎት አይደለም እንዴ!? እርሳቸው በፈሩበትና ለአፍታ ደረስ ብለው ለመመለስ በሚሰጉት ክልሎዎ/አከባቢ ተራው ዜጋ እንደት መንቀሳቀስ ይችላል? እንደት መኖር ይችላል?

ወደ ማጠቃለያዬ ከመድረሴ በፊት ከላይ የተጠቀሱና ያልተጠቀሱ ነገሮችን ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ መለካት ግድ አለኝ፡፡ የሰውዬውን ስብዕና፣ የወሰዷቸውን ደፋር እርምጃዎችን፣የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታና የተደቀነባቸውን ሁለንተናዊ ፈተና መከለስ ጀመርኩትኝ፡፡ እንዲሁም የህዝባችን የሥልጣኔና የንቃት ወሰንም ማጠን ነበረብኝ፤ የዜጎችን ድህነትና የመሃይምነት ጥልቀት ማገናዘብም ግድ ይላል፤ ሰልጥኛለሁ ተምሪያለሁ የሚሉትን ከወረቀት በዘለለ ጥልቀት ያለው ዕውቀት፣ የሥልጣን ጥማትና የፍላጎት ስፋትን ጨምሮ ከሁሉም በላይ ሰዎች ነንና ፍጹማን ያለመሆናችንን ጭምር ማሰብ ነበረብኝ፡፡

ከዚህ አስጨናቂ ጥያቄ በኀላ በዶ/ር አቢይ ከሰርን ወይስ አተረፍን? ላልኩት ጥያቄ ምላሼ #አትርፈናል የምል ነው ፡፡ ያሻግሩናል ወይስ ያሳፍሩናል? የሚለው ጥያቄ በራሱ ትንቢታዊ ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን ነገን መጠበቅ ግድ ማለቱ የማይቀር ነው፡፡ እናም እንቅጩን ለመናገር አሁንም ጊዜው ገና እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን አምባገነን ይሆናሉ ብዬ አሁንም አላስብም ፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያሰቡትና ከመጡ በኀላ ያቃታቸው ነገር እንዳለ እረዳለሁ ፡፡ ይህም የሆነው በእርሳቸው ክፋት ሳይሆን ከሁኔታዎች ክፋት ይመስለኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ በእርሳቸው በኩል የተሻለ የተስፋ ብርሃን ይታየኛል፡፡

አንዳንድ መረጃዎችን ላጋራኝ ትንሹ ወንድሜን ሀብታሙ ኃ/ጊዮርጊስ’ን አመስግኜ ልሰናበታችሁ፡፡ ሰላም!

Daniel Shibeshi.
Blessing!

One thought on “ከመጋቢት እስከ መጋቢት: 15 ምክንያት ለመውቀስ፣ 30 ምክንያት ለማወደስ!

  1. Critical analysis, free from biasness. ለነ አብይ ብደርሳቸው መልካም ነበር ። if they have the moral to correct their errors. ማታለል ከአሁን ወዲያ የትም አየደርስም ። Jowar’s project for sure will not work. Oromia has to work for unity for its own sake. If something happen it will the most vulnerable region…b/c it is a center of divergent economic interest

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡