የማንነት ፖለቲካ Vs የዜግነት ፖለቲካ

አሁን ባለው የኢትዮጲያ ፖለቲካ ለብዙዎች ግራ አጋቢው ጉዳይ ማንነትን (በተለይ በብሔርን) መሰረት ባደረጉ ፓርቲዎች እና ዜግነትን መሰረት አድርገው በተዋቀሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል “የማይታረቅ” የሚመስለው የፖለቲካ ጉዞ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እንደ አሸን የፈሉትን ፓርቲዎችም ከሁለቱ ጎራ የሸሹ አይደሉም በዚያው ልክም የሁለቱም ደጋፊም ተቀዋሚ የበዛ ነው፡፡

የማንነት ፖለቲካ

በሀገራችን በብዙዎች ዘንድ የማንነት ፖለቲካ መልካም የሆነ እይታ አለው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ለማንነት ፖለቲካ (identity politics) ያለን እሳቤ የተንሸዋረረ ስለሆነ እና ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሀገራችን ማንነትን መሰረት አድርገው የተዋቀሩ ፓርቲዎች ያላቸው ሪኮርድ መልካም ስላልሆነ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በብዙዎች ዘንድ ጎሰኝነት (tribalism) ከማንነት ፖለቲካ (identity politics) ጋር ሲምታታ ይስተዋላል፡፡ ጎሰኝነትን (tribalism) እና የማንነት ፖለቲካ (identity politics ፈጽሞ ይለያያሉ፡፡ የማንነት ፖለቲካ (identity politics) ከ1990ዎቹ ወዲህ እየጎለበተ የመጣ ሲሆን አሁን አሁን በመላው አለም ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ ያለ የፖለቲካ አደረጃጀት ነው፡፡

ማንነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ወይም አደረጃጀትን በተመለከተ ጥሩም መጥፎም ብለን የምንፈርጀው አደረጃጀቱ (how they organize) እና የተደራጀበት ፍሬምዎርክ (what are the framework) የሚሉትን ወሳኝ አሳቦች በማየት ነው፡፡ በዚህ መሰረት በማንነት መደራጀት እንደ ሀገር ጎጂ ወይም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ከላይ የተገለጹትን አሳቦች መሰረት አድርገን ካየን በሀገራችንም ሆነ በአለም ላይ ሁለት አይነት የማንነት ፖለቲካዎችን ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ሰፊ በሆነው ሀገራዊ ማንነት ውስጥ ሆኑ የተጎዳን ቡድን ማንነት ለማስከበር መጣር ወይም በዚያ ስም መደራጀት ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ አሜሪካዊው የጥቁሮች መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ነው፡፡ ሉተር በአሜሪካዊ ማንነት ውስጥ ሆኖ የተገፋውን የጥቁር መብት ለማስከበር ሲታገል እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ይህ አይነት የማንነት ፖለቲካ አደረጃጀት በሀገር ውስጥ ለሚደረገው የአንድነትና የዲሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ነው፡፡

ሁለተኛው የማነነት ፖለቲካ አደረጃጀት ግን “ተመሳሳይ ጠላትን” በመፍጠር የተደራጀ የማንነት ፖለቲካ (common enemy identity politics) ብልን የምንጠራውና የፖለቲካ ህልውናውን ሌላኛውን ቡድን ጠላት በማድረግ የሚንቀሳቀስና ፖለቲካዊ ፍልስፍናውንም “እኛ እና እነሱ” በሚል አሰልፎ “እነሱን” በማጥፋትና በማጥቃት፣ ህልውናቸውን በማቀጨጭ አልፎ ተርፎም ጦርነት በማወጅ የተመሰረተ ማንነት ፖለቲካ አደረጃጀት ነው፡፡ ይህ ለአንድ ሀገር ህልውና መቅሰፍትን ይዞ የሚመጣና በኢደትም አስከፊ ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ አደረጃጀት የመናገር መብትን የሚጋፋና በተለይ በመንጋ ፍትህ (የእኛ) የሚያምንና የተለየ አሳብን የማያስተናግድ አደረጃጀት ነው፡፡

የኢትዮጲያን የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ከተጀመረበት 1960ዎቹ ወዲህ የተቋቋሙ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የመጀመሪውን አደረጃጀት ከመጠቀም ይልቅ “አንድ ጠላትን” በመፍጠር ሂደት የተዋቀሩ ናቸው፡፡ ህውሃት ፣ኦነግ እና ኦብነግ ለዚህ ተጠቃሾች ሲሆኑ “colonial thesis” በመባል የሚታወቀውንና ኢትዮጲያና ገዢዎቿ (በተለይ ሚኒሊክ) ቀኝ ገዢ ናቸው ቀኝ ገዢውም “እኛን” ጨቁኖናል በሚለው ህሳቤ ተመስርተው እና ለድል በቅተው በህውሃት በመመራት ላለፉት 27 ዓመታም በዚሁ ትርክ መቆየታቸው አሁን ላለንበት ልዩነት ዋነኛ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

ከማንነት ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ ይዘውት የሚነሱት ጥያቄ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ አደረጃጀቶች ደጋፊን ያበዛልኛል ፣ተቀባይነትን ይጨምርልኛል በሚሉት መንገድ ይዋቀራል፡፡ ከእነዚህ አወቃቀሮች አንዱ ደግሞ ማንነትን መሰረት አድርጎ መደራጀትን ያካትታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን በማንነት የሚደራጁ ፓርቲዎች ከሌላው እኩል የመታየት ጥያቄ (isothymos) ይዘው ሲነሱ ሌሎቹ ደግሞ ባለፈው ስለተበደልን ወይም የተሻለ ነገር ስላደረግን ከሌላው በበለጠ እንታይ (megalothymos) የሚል ጥያቄን ይዘው ይነሳሉ:: ይህ ጥያቄ ለእኩልነት ቦታ የለውም ምክንያቱም እኛ ከእነሱ እንበልጣለን የሚል ነውና፡፡

የሊብራል ዲሞክራሲ ድክመት

ለቡድን መብት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም በተዳከመበትና ራሺያ ተበታትና ለግለሰብ መብት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሊብራሊዝም ሲያሸንፍ ሊብራሊዝምን በማድነቅ “The end of history and the last man” በሚል ስለ ሊብራሊዝም አሸናፊነትና ታላቅነት በመዘከር ግሩም መጽሀፍ ያስነበቡን ፍራንሰስ ፉኮያማ ከሶስት አስርት አመታት በኃላ ሊብራሊዝም ሊመልሰው ያልቻለውንና በአለም እየሰፋ የመጣውን የማንነት ፖለቲካ የሚዘረዝር መጽሐፍ “identity the demand for dignity politics of resentment” በሚል ርዕስ በ2018 አስነበቡ፡፡ በፍራንሰስ ፎኮያማ እምነት እያንዳንዱ ሰው በውስጡ የታወቀ ማንነት አለው፡፡ ይህ ማንነት ደግሞ ግለሰባዊ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚጋራው ውስጣዊ ማንነት (thymos) ሲሆን ይህ ማንነት በሌሎች እውቅናን እና ክብርን የሚፈልግና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ባለፉት አመታት ሊብራል ዲሞክራሲ ይህንን የማንነት እውቅናን ጥያቄ መመለስ ባለመቻሉ ትልቁ ፈተና ገጥሞታል፡፡

ሊብራል ዲሞክራሲ በባህሪው የግለሰብ መብትን (ዜግነት) መሰረት ያደረገ ርዕዮተ አለም ነው፡፡ ነገር ግን አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይን ጨምሮ በብዙ የአውሮፓ ሀገራት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ወይም ከግለሰብ ይልቅ የቡድንን ጥያቄ የሚያስቀድሙ ፓርዎች አስደንጋጭ የምርጫ ውጤት ሲያመጡ ለተመለከተ የማንት ፖለቲካ ምን ያህል ተቀባይነት እያገኘ እንደሆነ መታዘብ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ዜግነትን መሰረት ያደረገ አካሄድ በአለም ላይ ተቀባይነቱ ቀንሷል ማለት አይደለም፡፡

ማስታረቅ አለብን?

የዜግነት ፖለቲካንና የማንነት ፖለቲካን አንዳንዶች እንደሚሉት የግድ ማስታረቅ ወይም አንዱና ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች እንደኛ ሀገሮቹ ፓርቲዎች አሸን ናቸው፡፡ የዜግነት ፖለቲካ እና የማንነት ፖለቲካ ሁለቱም በሰው ውስጥ ያሉ ማንነቶች ነጸብራቅ ናቸው፡፡ ሁለቱም ባይታረቁም አብረው መኖር ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰለጠነ ማህበረሰብና የዳበረ ዲሞክራሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁለቱም ጨቋኞች ናቸው (በተለይ የማንነት ፖለቲካ)

የማንት ፖለቲካ በሀገራዊ ጣራ ውስጥ ሆኖ የራስን ቡድን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅና ለማጎልበት ከጣረና ከሌላ ይበልጥ ሳይሆን በእኩል ልታይ የሚል ጥያቄን ይዞ ከተነሳ፣ በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎች እንደምናየው “ከእኛ ውጪ ወደ ውጪ” የሚል እሳቤ ካልያዘ ለሀገርም ለዲሞክራሲያዊ ግንባታው መልካም ነገርን ማስገኘቱ አይቀርም፡፡ በተቃራኒው ልክ እንደ ህውሃት የጠላት ትርክትን ይዞ ከተነሳ፣ ባለፈው ስለተበደልን አሁን ከሌላው ይበልጥ እንጠቀም፣ ለውጡን እኛ ስላመጣነው ይበልጥ ነገር ይገባናል የሚል ሃሳብ ካነሳና ሀገራዊ ስህሉን ከዘነጋው አደጋው የከፋ ነው፡፡

ፀሃፊ ዳንኤል መኮንን፣ በወልቂጤ ዩኑቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር

One thought on “የማንነት ፖለቲካ Vs የዜግነት ፖለቲካ

  1. የዚህ ሁሉ ችግር ኃለቀርነታችን ። ጥግ የያዘውም ፖለቲካ የጭቆና ውጤት ነው። አሁን ደግሞ ፖለቲከኞቹ ና መንግሥት እራሡ ለ ድጋፍ ከዚህ በረት አለመውጣቱ ። ወጣቱ ምን እንደሚጠይቅ ምን እንደሚቀወም አለማወቁ ። ምሁርም ችግር አለበት ። ሀገርቷ በሥልጣን ፈለጊዎች ጥቂት ግለሰቦች እየታመሰች ነው። ሁሉም በብሔረሰቡ ጓዳ ገብቶ ያምሳል። በእውነት ግን የዚህ ህዝብ ችግሮች economy ነው ። including unemployment and others. Nobody talks about this. We need peace for economic development. On contrary, we block roads, dislocate people. See how savage we are. We have to ignore politicians and think how to feed ourselves.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡