የኦሮማራ ጥምረትና አዙሪት ያስከተለው ሀገራዊ ስጋት

ከዘመናዊው የኢትዮጲያ ታሪክ ጅማሮ (ከ1855 እ.አ.አ) አንስቶ ተቆራርሳ የነበረችውን ኢትዮጲያን አንድ የማድረጉና ሀገርን የመገንባቱ ጉዞ በአጼ ቴውድሮስ ተጀምሮ ከብዙ መደናቀፎች በኃላ በአጼ ሚኒሊክ ሲጠናቀቅና የዛሬዋ ኢትዮጲያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ስትፈጠር የዘመኑ የኦሮሞና የአማራ (ኦሮ-ማራ) ጥምረት ትልቁን ድርሻ ተወቷል፡፡ አፄ ሚኒሊክ ከአፄ ቴውድሮስ እጅ ከመቅደላ አምልጠው ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ጉዟቸውን የጀመሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቅደላ በኃላ ካረፉበት ከአዳው ኦሮሞ ከቡታ ቤተሰቦች አንስቶ ኦሮሞዎችን ካማከሩና አስቀድመው ከኦሮሞዎች ጋር ማለትም ከነ የሜታው ባላባት ቢራቱ ጉሌን፣ የቱለማው ባላባት ጎበና፣ አቢቹና ከመሳሰሉት ጋር ከተስማሙና የእነርሱንም ድጋፍ እንደሚያገኙ ካረጋገጡ በኃላ ነበር፡፡

የታሪክ ጸሐፊው ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ሚኒሊክ” በሚለው መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት ሚኒሊክ ከኦሮሞዎች “ያሳደጋጅሁኝ ልጃችሁ አብረን ያደግን ባልንጀራችሁ ነኝና በአባቴ አልጋ ከተቀመጥኩኝ በፍቅር ተገዙልኝ” በማለት በፍቅር ከተስማሙ በኃላ ነው የተቀረውን ኢትዮጲያ በኦሮሞ ባላባቶች ፊት አውራሪነት አንድ የማድረጉን ፕሮጀክት የጀመሩት፡፡ ጀርመናዊው ተመራማሪ ኤሪክ ስሚዝ “The 21stc Ethiopia፡ The Paradox and Truth” በሚለው መጣጥፉ እንደጠቀሰው በ19ኛው መ.ክ.ዘ አጼ ሚኒሊክ አንዲት ጠንካራ ሀገርን የመገንባት ህልማቸው ከኦሮሞ ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ የሚኒሊክ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት ፈተና ውስጥ ወድቆ እስከናካቴው ላይሳካ ይችል ነበር፡፡

ኦዴፓ-አዴፓ የኦሮማራ ጥምረት Vs የኦሮሞና አማራ አክቲቪስቶች ጥምረት

የራሺያውን የዛር ንጉሳዊ አገዛዝን ግብአተ መሬት ያበሰረውን የቦልሸቪክ አብዮትን የመራው ሌኒን በአንድ ወቅት እንዳለው “በሰው ልጅ ህይወት አንዳንዴ ምንም የማይከሰትባቸውና ለውጥ ያልታየባቸው አስርት አመታቶች አሉ አንዳንዴ ግን በሳምንት ውስጥ የአስርት አመታት ክስተትና ለውጥ ይፈጠራል”፡፡ ህውሃት ለ27 አመታት ስልጣኑን አደላድሎ ለመግዛት ያስቻለው በዋነኝነት የኦሮሞንና የአማራን ህዝቦች በማቃረን ነበር፡፡ ነገር ግን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰቱት “ጣናን ኬኛ”፣ የጎንደሩ ሰልፍና “የኦሮሞ ደም የኔ ደም ነው” የሚለው መፈክር እንዲሁም የለማ የባህርዳር ጉብኝት የህውሃትን የበላይነት የመጨረሻ ዘመን ያበሰረና ህውሃት በግልጽ በጌታቸው ረዳ በኩል “ስራ አልሰራንም ማለት ነው… እሳትና ጭዶቹ እንዴት ሊስማሙ ቻሉ…” እስከማለት ያደረሰ እንቅስቃሴ ነበር፡፡

አሁን ያለውን የለውጡን ኃይል ወደ ስልጣን ያመጣው በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጠንካራ የነበረው በዋነኝነት በህውሃት ላይ ያነጣጠረው የእንቢተኝነት እንቅስቃሴ በኦሮሞና አማራ አክቲቪስቶችና በኦህዴድና ብአዴን መካከል ህውሃትን ያስደነገጠ ጥምረት (alliance) ፈጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የጥምረቶቹ (alliance) አይነትና ባህሪይ የተለያየ እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡

ከ2008 ዓ.ም የጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ በኃላ ለ27 አመታት ታይቶ ያልነበረ ህብረትና እንደ እሳትና ጭድ ከመተያየት አብሮ የመታገል ፍላጎትና ሂደት በአማራና ኦሮሞ ልሂቃን (አክቲቪስቶች) መካከል ተፈጥሮ ነበር፡፡ የሁለቱም ወገን አክቲቪስቶች በተለያዩ ጉዳዮች አብረው በመስራት ህውሃት ከተቆጣጠረው ስልጣን እንዲያፈገፍግና ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን እንዲመጣ የአንበሳውን ድርሻ ተወተዋል፡፡ የአማራና ኦሮሞ አክቲቪስቶች ጥምረት በዋነኝነት ተመሳሳይ ጠላትን (ህውሃትን) በማስወገዱ ላይ የተመሰረተ ጊዜያዊ ጥምረት (Tactical alliance) ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡

ህውሃት ተሸንፎ መቀሌ ከተመልሰ በኃላ ዝምታን መምረጡና ሁለቱን አንድ የሚያደርግ ተመሳሳይ አጀንዳ መጥፋቱ ሁለቱም ወደ 27 አመት ነቆራቸው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ህውሃት ተሸንፏል ተብሎ የለውጡ መሪ የተባሉት ዶ/ር አብይ ስልጣን ከያዙ አመት እንኳን ሳይሞላ የሁለቱም ወገን አክቲቪስቶች ወደ ቀድሟቸው መበሻሸቅና ንትርክ ተመለስዋል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ፣ በባንድራ ጉዳይ፣ በፌዴራሊዝሙ ጉዳይ ወደ ቅራኔ ሲገቡና እርስ በርስ ለማጣጣም የሚከብዱ አሳቦችን ሲያራምዱ እየታዘብን ነው፡፡

በተለይ ደግሞ የአማራ አክቲቪስቶች ከለውጡ በኃላ ለአማራ ለውጡን ለማምጣት በታገለው ልክ ተገቢው ቦታ አልተሰጠውም፣ ለውጥ የተባለው ከህውሃት የበላይነት ወደ ኦዲፒ የበላይነት ነው የተቀየረው የሚለው ቅሬታቸው፣ ከፍተኛ ደጋፍ ይሠጡት የነበረውን የአብይን መንግስት ተቃውሞ መጀመራቸውና የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ጥያቄያቸውን ሲያጣጥሉ መመልከቱ የጥምረቱን ጊዜያዊነት ያሳያል፡፡ ታዋቂው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር የታሪክ ተመራማሪ ጀምስ ስቶኪ እንዳለው ተመሳሳይ ጠላትን ለማስወገድ ተብሎ የሚፈጠር ጥምረት የማያዋጣና ጊዜያዊ ነው ፡፡

በሌላ በኩል ከአመት በፊት በለማና በገዱ የተፈጠረው ጥምረት የ19ኛው ክፍለ ዘመንን የሚኒሊክና የጎበና ጥምረት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጎበናና ሚኒሊክ የተበታተነችውን ኢትዮጲያ ህልውና እንደመለሱት ገዱና ለማ በጥምረታቸው ህልውናዋ አደጋ ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጲያ ታድገዋል ማለት ይቻላል፡፡

ምንም አንኳን በኦዴፓና አዴፓ መካከል ከአመት በፊት የነበረው አይነት የመናበብ፣ የልብ አንድነት እና አብሮ የመስራት መንፈስ የተዳከመ ቢመስልም አሁንም የአዴፓና ኦዴፓ ጥምረት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ጠላትን ከመታገል የዘለለና ነው፡፡ ከ2008 ጀምሮ ኦዴፓና አዴፓ በኢህአዴግ ውስጥ በጋራ እየተመካከሩ ካልሰሩና በተለያዩ አጀንዳዎች ካልተባበሩ ለሌላ ኪሳራ እንደሚዳረጉና ሀገሪቱንም ለቀውስ እንደሚዳርጋት ተረድተው ነበር፡፡

ምንም እንኳን በኦዴፓና አዴፓ መካከል ያለው ጥምረት፣ የመናበብና በጋራ የመስራት ሂደት ለሀገራዊ ለውጡ ወሳኝ ቢሆንም በአክቲቪስቶቹ መካከል ያለው ልዩነትና የፍላጎቶች አለመጣጣም በሁለቱ ፓርቲዎች ዘላቂ ጥምረት ላይ ጥላውን ማሳረፉ አልቀረም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ በቅርቡ አዴፓና ኦዴፓ በድርድር ሊፈቷቸው የሚችሏቸው ጉዳዮች (በዋነኝነት የአዲስ አበባ እና የህገ-መንግስቱ ጉዳይ) በአክቲቪስቶች መካከል ሚታረቁ የማይመስሉ ክስተቶች ሲፈጠሩ ፓርቲዎቹም ለዚሁ የአክቲቪስቶቹ ንትርክ ሰለባ ሊሆኑና ጥምረቱንም አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡

አሁን አሁን በመካከላችን ካሉ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ይልቅ ልዩነቶቻችን ሰፍተው የወጡ ይመስላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው እውነትም እንደሚባለው ልዩነቶቻችን የገዘፉና የማይታረቁ ሆነው ሳይሆን ልዩነቶቹ የብሶታችን ነጸብራቅ ስለሆኑ ነው፡፡ ለውጥ መጣ ከተባለ በኃላና የለውጡ መሪ ወደ መንበሩ ከመጣ በኃላ የሆኑት ነገሮች አንዳንዶች “ተክደናል፥ ተገፍተናል” የሚልን እሳቤ ማንፀባረቅ ጀመሩ፡፡ ይህ እሳቤ ደግሞ ተራ እና ጥቃቅን በሚመስሉ ኩነቶች ሲደገፍ ውጤቱን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ለኦሮማራ ጥምረት መዳከምና አዙሪት ትልቁ ምክንያትም ይህ ይመስለኛል፡፡

የተመሳሳይ አጀንዳ እጦት

አሁን ባላው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ መንግስት ማንኛውንም እርምጃ ቢወሰድ አንድን ቡድን ሲያስደስት ሌላኛውን ማስከፋቱ አይቀሬ እየሆነ መቷል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት እንዳየነው ማንኛውም የኦሮማራ ጥምረት ለሀገሪቱ እዳሴ ወሳኝ ነው፡፡ በተቃራኒ መለያየታቸውም እንደዛው ለሀገራችን እርግማን ነው፡፡ ኦዴፓና አዴፓ ውስጣዊ የፓርቲን ጥምረትና አንድነት ከማስጠበቅ በዘለለ በፌስ ቡክ መንደር ለሚፈጠሩ ጫጫታዎች ጆሮ ከሰጡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይልቁንስ ሁለቱም ፓርቲዎችና መንግስት ተመሳሳይ አጀንዳዎችን በመፍጠር ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኦሮማራ ጥምረት አድማሱን አስፍቶ ሌሎች ህዝቦች ጥምረት መሳብ መቻል አለበት፡፡

ትልቅ ስራ የሚያስፈልገው ሀገራዊ ምርጫ እየተቃረብን በሄድን ቁጥር እና ፖለቲካዊ ለውጡን ወደ ዲሞክራሲ ግንባታና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መሻገር በሚያስፈልገው በዚህ ወሳኝ ወቅት በሁለቱ ወገን ያሉ (የምሁራኑም፣ የአክቲቪስቶቹም ሆነ የኦዴፓና የአዴፓ) ጥምረቶች ፈተና ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህም የወደፊቱን የሀገሪቱን ሁኔታ አስጊ ያደርገዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግስት እንደ መንግስት ጥምረቶቹ የሚጠናከሩበትን መንገድ ማመቻቸት፣ በሁለቱ መካከል ጥርጣሬዎችን ከሚፈጥሩ ድርጊቶች መራቅና ማስወገድና ሁለቱ ፓርቲዎችም በፌስ ቡክ አጀንዳ ከመመራትና በፌስ ቡክ መንደር ለሚፈጠሩ ጫጫታዎች ምላሽን ለመስጠት ከመታተር መንግስትን እንደመሰረተ ፓርቲ መንቀሳቀስና ትክክለኛ መንግሰት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለኦሮማራ ጥምረት አደጋ የሆኑት ለምሳሌ በአማራ ልሂቃን በኩል የሚነሳው ተክደናል የሚለው እሳቤ፣ የዶ/ር አብይ መንግስት double standard መከተል፣ የአዲስ አባባን ጉዳይና የስልጣን ክፍፍልና ህገ መንግስቱን በተመለከተ የሚነሱ ልዩነቶች በተገቢው መልኩና በሰከነ መንገድ ሊያዙ ይገባል፡፡

2 thoughts on “የኦሮማራ ጥምረትና አዙሪት ያስከተለው ሀገራዊ ስጋት

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡