ኢህአዴግ አልተግባብቶም፦ መግባባት በሌለበት ውህደት!

የዛሬ አመት የኢህአዴግን ም/ቤትን ስብሰባ መላው የሀገራችን ህዝብ ብቻ ሳይሆን አለም በጉጉት ሲከታተለው እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡አሁንም የዚህን አመት የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ እንዲሁ በጉጉት እንድንጠብቀው የሚያደርጉት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡

አልተግባብቶም

የህውሃት ማህከላዊ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ ለተመለከተ እና የአዴፓን እና ኦዴፓን ሁኔታ ላጤነ በኢህአዴግ ም/ቤት ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ህወሃት በመግለጫዋ እንዳለችው ሀገሪቱ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳለችና በጌታቸው ረዳት በኩል በትግራይ ቲቪ እንደገለጸቸው መፍትሔውም የሀገሪቱን ችግር ውስጥ መግባት ማመን እንደሚያስፈልግ ዘርዝራለች፡፡ ይህንን ደግሞ የኦዴፓ ሰዎች በተለይ ጠ/ሚንስትሩ በቀላሉ የሚቀበሉት አይመስልም፡፡

ፎቶ ከቀኝ ወደ ግራ፦ ጠ/ሚ አብይ አህመድ እና ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

ለኦዴፓና ህውሃት ያለፈው 28 አመት ትርጉም ለየቅል ነው፡፡ ኦዴፓ ያለፈው 27 ዓመት ጨለማ ነው ስትል ህውሃት ደግሞ ያለፈው አንድ አመት የመፈናቀል፣ የብጥብጥ፣ የህገ-መንግስት ጥሰት የታየበትና እና የረብሻ ነበር ትላለች፡፡ ህውሃት በ27 ዓመት የተከሰተውን ችግር እምብዛም እንዲጠቀስ አትፈልግም ኦዴፓ ደግሞ የአንድ አመት ጉዞውን ክፋት ሳይሆን ጭብጨባውን መስማት ብቻ ነው የምትሻው፡፡ ዶ/ር አብይ የተማመኑበትን የአንድ ፓርቲ ምሰረታም እንዲሁ ህውሃት በመግለጫዋ የማልቀበለው ነው መጀመሪያ እኛ እንግባባ ብላለች (እውነት አላት፤ ሳትግባባ ወደ አንድነት ጉዞ…)፡፡

በአማራ ብሔርተኞች መቆሚያ መቀመጫ ያጣው አዴፓ አሁንም በአህአዴግ ቤት የት እና ከማን ጋር እንሚቆም ግራ ገብቶታል፡፡ በኦዲፒ ተከድቻለው እያለ ሲያለቅስ የከረመው አዴፓ ምንም እንኳን ከዶ/ር አምባቸው መምጣት በኃላ ከትግራይ ጋር ያለው እሰጣ ገባ ረገብ ያለ ቢመስልም ከህወሃት ጋር ምንም አይነት (ታክቲካልም ሆነ ስትራቴጂካል) ግንኙነትና ጥምረት ቢፈጥር ገደል እንሚገባ ስላሚያውቀው በኢህአዴግ ም/ቤት ግራ የገባው አቋም ይዞ መግባቱ አይቀርም ፡፡

ኦዲፒ በውስጥም በውጭም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከገባች ሰንበትበት ብላለች፡፡ አሁንም የኦሮሞ ልሂቃን ቄሮ የታገለለት አላማ (ለምሳሌ ቋንቋና የአዲስ አባባ ጉዳይ) ግቡን አልመታም፤ ቲም ለማም ለኦሮሞ ህዝብ መብት በሚገባው ልክ አልሰራም የሚል ከስ ይቀርብበታል፡፡ ምንም እንኳን ከላይ ያለው የኦዲፒ አመራር አንድነት ጠንካራ ቢመስልም ከዞን ጀምሮ ያለው አመራር ግን በኦዲፒ ቅሬታ እንዳለው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች አዴፓ፣ ህውሃት እና የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች በኦዴፓ ላይ ጫናቸውን አበርትተዋል፡፡

ክልሉን በተገቢው መልኩ ማስተዳደረም ሆነ መምራት ያልቻለውና በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ያለው ደኢህዴን ከ30 ሚሊዮን በላይ ህዝብና ሰፊ ክልልን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ተጽህኖ ፈጣሪነት አግልሎ ያኔ የህውሃት መጠቀሚያ እንደሆነው ሁሉ ዘንድሮም የባለ ወንበሩን (ኦዲፒ) አጀንዳን ማራመዱን መቀጠሉ አይቀርም፡፡

ልዩነት፤ የስጋት ምንጭ

ታዋቂው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር መሐመድ አዩብ “sub altern realism” ብሎ በጠራውና የሶስተኛው አለም ሀገራትን (ታዳጊ ሀገራት) ደህንነት በተነተነበት ጽንሰ ሀሳብ መሰረት በታዳጊ ሀገራት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የደህንነት ስጋት የሀገሪቱም የደህንነት ስጋት ነው ይላል፡፡ እንደ አዩብ ትንተና በድሀ ሀገራት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለህልውናው ስጋት ከገጠመው ሀገሪቱም ትልቅ ስጋት ውስጥ ትገባለች፡፡

ኢህአዴግ በታሪኩ ከምንጊዜውም በላይ የተከፋፈለበት ወቅት ላይ ይገኛል፡፡ አራቱም የግንባሩ ድርጅቶች በአይዲዎሎጂ፣ ለችግሮች በሚሰጡት መፍትሄ፣ በእይታ እና በአስተሳሰብ እጅጉን የተራራቁ ናቸው፡፡ በአራቱም የግንባሩ ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ አለመተማመን እና ጥርጣሬ አለ፡፡

ወደድንም ጠላንም በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢህአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው ልዩነት ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ ልዩነት በፍጥነት ካልተፈታና መፍትሄ ካልተበጀለት አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ወይም ኢህአዴግ እንደ ከዚህ ቀደሙ አንድ ነን እያለ ልዩነት እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ወስኖ ከወጣም ዘመነ መሳፍንት ጥንት አይሆንብንም፡፡

ኢህአዴግ የፓርቲ ዲሲፒሊኑን ሊያከብርና ሊያስከብር ይገባል፡፡ ባለፈው አንድ አመት የተሰሩ ስህተቶችንም ማመንና ለማስተካከል መጣር መፍትሄ ይመስለኛል፡፡ ህውሃት ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ታደርግ እንደነበረው ችግሮችን መካድና የበሩትን መብራቶች ለማሳየት ብቻ መጣር መፍትሔ አልነበረም አይሆንምም፡፡ አራቱም ድርጅቶች በብስለትና በተረጋጋ መንፈስ ስለ ሀገርና ህዝብ ሲሉ ኩራታቸውን፣ ክብራቸውን፣ ግላዊ ፍላጎታቸውንና ቂማቸውን ትተው መመካከርና ለችግሮችና ልዩነቶች መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለዶ/ር አብይና ቲም ለማ ታሪክ እና ፈጣሪ በአለም ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ ውድ የሆነችውን ኢትዮጲያን በእጃቸወ አስቀምጦላቸዋል፡፡ ይህች ውድ ሀገር ከእጃቸወ እንዳትጠፋ በጥንቃቄ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ከነ ልዩነታቸው ከወጡ ግን ከፊታችን ድቅድቅ የፖለቲካ ክረምት ይጠብቀናል

ፈጣሪን ኢትዮጲያ ይጠብቅ

2 thoughts on “ኢህአዴግ አልተግባብቶም፦ መግባባት በሌለበት ውህደት!

 1. ”የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ“
  ውድ ዳንኤል በደብሳሳው መጩው የኢህኣዲግ ስብሰባ ያለህን እይታና ግምትህን ያስቀመጥክበት መነገድ ከፊልም ቢሆን እምስማማበት ቢሆንም፤ ከፅሁፍህ ኣንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር ኣሁንም ኣመክንዮ እውነታ በሌለው ህወሓትን ለመወረፍ የተጠቀምክበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ነው፤ ማሳያዎቹ ቆይቼ ምን ያክል የተሳሳት መሆንህ እግልፅልሃለሁ።
  ሆኖም ግን በቀጥታ ይቺ ኣገር ኣሁን ያለችበት ሁኔታ ኣተኩረህ መልእክትህ በግልፅና ቀጥታ ለሚመለከታቸው ይደርስ ነበር ግን ኣልሆነም፤ ምክንያቱም ኣሁን ያለው መንግስት ለሚሰራው ስህተት በተሳሳት መንገድ “ያው ነው ህወሓት ሲለውና ሲያደርገው እንደነበረ ነው” ብሎ እንዲዘናጋ በር የመክፈት ያክል ነው የተሰማኝ።

  ማሳያዎቹ፦
  1)“ህውሃት በ27 ዓመት የተከሰተውን ችግር እምብዛም እንዲጠቀስ አትፈልግም” ፍፁም የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ድምዳሜ፤ ምክንያቱም እንደ ህወሓት ችግሩን ፊት ለፊት ተናግሮ የሚጋፈጥ ድርጅት የለም ጌታቸው ረዳ እንዳለው “በሹል ቀንድ እንጂ በጭራው ችግርን ይዞ መጫወት የማይወደና ባህሉ ያልሆነ ድርጅት ነው። ይልቅኑም ከጠ/ሚንስትሩ ጀምረው ሁሉም የበኣድንና ኦሆዲድ ባለስልጣናት ኮሽ ባለ ቁጥር የችግራቸው ሁሉ ማራገፍያ ምክንያት ህወሓት የሚያደረጉት መክሮ ወደውስጣቸው እንዲያዩ ማድረግ በተሻለ ነበር።
  ይባስኑ የህወሓት ችግር የተነሳችበት የትግራይ ችግር ትታ የሃገር ችግር ለመፍታት ለተፈጠረው ሁሉ ችግር ሲያሸክምዋት ሰምታ እንዳልሰማች መሆንዋ ነው። ኣንድም ሁሉ የተሰራውንም ኦፊሴላዊ እውቅና ስጡዋትና ስህተትኑም እንቀበላቹህ። ኣልነበርንም ለማለት ሂልና ካለ ማለቴ ነው።

  2)“ደህዲን …. የህውሃት መጠቀሚያ እንደሆነው” ይህም ትልቅ የኣረዳድ ክፍተት ሦስቱም ድርጀ ቶች (ኦሆዲድ፣ በኣድንና ደህድን)ፈጣርያቸው ህወሓት እንደነበር ለማንም ግልፅ ሆኖ ሳለ በዚህ ኣጋጣሚ ሲደረግላቸው ለነበር ድጋፍ “መጠቀምያ” የሚል ተቀፅላ የሚሰጣቸው ከሆነ ይህም ትልቅ ማስተዛዘብያ ነው፤ እዚህ ላይ ዳንኤል የተናገርከው ሃቅ ኣለው ሊባል ከሆነ ድርጅቶቹ ወደየ ህዝባቸው ሲቀርቡ እንደማስታረቅያ ይዘውት የቀረበ ነገር ቢኖር የህወሓት “ጣልቃ ትገባብን ነበር” የሚል እርድ ስለነበር ኣንተም የደገምከው ያው ነው። ሆኖም ግን ኣንተም እንደምሁር በራስህ መንገድ ነገሮችን ማየት ይጠብቅብህ ነበር፤ ይህ ሲሆን ነው ደግሞ ያንተ ምክረሃሳብ የሚጠቅማቸው፤ ኣለበለዝያማ እሱን እማ እነሱ ራሳቸው እየተናገሩት ነው።
  3)“ህውሃት ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ታደርግ እንደነበረው ችግሮችን መካድና የበሩትን መብራቶች ለማሳየት ብቻ መጣር መፍትሔ አልነበረም አይሆንምም” ይህ ሃሳብ ከ ተቁ (1) ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ኣንድ ነገር ማመን የሚገባህ ነገር ቢኖር ህወሓት ሰሎኝ 35 ቀናት የሚባል በሩን ዘግቶ በጥልቅ ግምግሞ ሃገራዊና ክልላዊ ችግሮች በየፈርጁ ኣስቀምጦ ይመለከተኛላ ባለው ልክ በሃገር ደረጃ ለተፈጠሩት ችግሮች ከእህት ድርጅቶች ጋር በክልል ደረጃ ለተፈፀሙ ስህተቶች ሙሉ በሙሉ ሃላፊነት ወስዶ እንደተለመደው ለህዝቡ ዝቅ ብሎ ይቅርታ የጠየቀ። በተመሳሳይ ሌሎች ድርጅቶች ግማሹ ለብለብ ኣድርጎ ግማሹ ኣንጠልጥሎ የገመገመውንይዞ ስብሰባ ኣዳራሽ እንዲገኝና ኢህኣዲግን ለ17 ቀናት ቁጭ ብሎ ገምግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያደረገው ህወሓት መስሎኝ።
  በፍፁም መማር ሚዛናዊነትና መጠበቅና እውነትን እንድንናገር ካላገዘን ምኑ ተማርነው ምኑንስ ተነተንነው፤ ተወደደም ተጠላም ጨለምተኝነት ካልሆነ በስተቀር ህወሓት ላለፉ 27 ዓመታት ለበሩትም ለጠፍቱም እኩል እያስተናገደች ሃላፊነት ስትወስድ ነው የመጣችው። እናማ ያንተ ምክረሃሳብ ለኦሆዲድ ይሁን ለቲሙ የሚጠቅመው ችግሮችን ልክ እንደ ህወሓት እንዲጋፈጡና መፍትሄ እንዲያመጡ ኣግዛቸው።

  Like

 2. ተግባቡ አልተግባቡ አያገባኝም። እንደፈለጉም ሆነው የለውጥ ቡድኑ እስከ ምርጫ ያድርሰን። ካኮ ኮላ እየቆሸሸ ደግመህ አትጠጣውም፣ በፔፕሲ ትቀይረዋለህ። ስለዚህ ፓርቲ ማላዘን መተው አለብን። በጸሎት እንዳይቀየር እንኳን አምላክ ስለሱ መስማት ሰልችቶታል። የአገራችን ኢኮኖሚ የዉዱቀው እኮ ተማሪ፣ ገበሬ፣ ግንበኛ፣ ደላላ፣ መምህር፣ ባንከር፣ ኡንጁነር፣ ዶክተር፣ ወዘተ ሁሉን ስራ ትተው ይህ ቆመ ቀር ፓርቲ በፈጠረው ቀውስ ፊታቸውን ወደ ፓለቲካ በማዞራቸው ነው። አምላክ አልሰማ ያለው እኮ ቄሶችና ሼኮች የሃይማኖት ስራቸውን ትተው ይህ ዘራፊ ፓርቲ የፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሰላም ኮሚቴ ምናምን እያሉ ስብሰባ ስላበዙም ነው። በዚህ ፓርቲ ምን ያልደረሰብን ነገር አለና ነው ስለሱ ስብሰባ ተጨንቀን የምናወራው።

  ለህዝባችን እና አገራችን የሚጠቅመው ከአንድ ፓርቲ ቅኝ ግዛት መላቀቅ ብቻ ነው። ታደስን፣ ተለወጥን በሚል ማምታቻ ሃያ ሰባት አመት ሙሉ አንድ አይነት ሰዎችና ስሞችን በቴሌቪዥንና ራዲዮ መስማት አልሰለቻችሁም??? ወንድሞች ስለ እሱ ባወራን ቁጥ ሌላ ምርጫ የለም በሚል ለዳግም ዘረፋና ህዝባችን ላይ ሰቆቃ እንዲደርስ መጋበዝ ነው። እያጠፉ የሚማሩም ቢሆን አዲስ አገራዊ ፓርቲን ማሰብ አለብን። እነዚህ ቆሞ ቀሮች ታደስን፣ ተለወጥን እያሉ ይሰሩብን የነበረውን ድራማ ወደ ተዋሃድን ቲያትር እንዲያሻግሩ እድል መስጠት አይገባም። ምርጫ በሌለው በተመሳሳይ ሰዎች ለዳግም ቅኝ ግዛት መገዛት እድል መስጠት የለብንም።

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡