የግጭት መሠረታዊ መንስኤዎች እና አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች

በመላኩ አዳል (ዶ/ር)

ግጭት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መካከል በፍላጎት፣ በአመለካከት፣ በአላማ፣ በታሪክ፣ በእሴትና በባህል አለመስማማት የሚከሰት፣ በሰው ተወዳዳሪነትና በተፈጥሮ ሃብት ውስንነት ምክንያት የሚመጣ ማህበራዊ መስተጋብር ነው። ግጭቶች አሉታዊም፣ አውንታዊም ጎን አላቸው። በአውንታዊነት ችግሮችንና የችግሮችን መንስኤ ለመለየት፣ የአንድን ፓርቲ ህልውና ለመለካት፣ ፖሊሲዎችንና ሰትራቴጂዎችን ለመፈተሽና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ይጠቅማል። በአሉታዊነቱ ደግሞ ለሰው ሞት፣ የሰላም መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት መውደም፣ የግንኙነት መበላሸትና ለሀገር አንድነትና ህልውና ስጋት ይሆናል።

የግጭት መንስኤዎች

በየቦታው ለሚታዩ ግጭቶች መንስኤዎች ብዙ ናችው። የሕገ-መንግስቱና እሱን ተከትሎ የመጣው የቋንቋ ፌደራል መንግስቱ አወቃቀር አንድ የሚያደርጉንን አጉልቶ በክልሎች መካከል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድድር በማድረግ ሀገርን መገንባት ሳይሆን፣ ቋንቋን መሠረት አድርጎ ማንነትን ከመሬት ጋር አጣብቆ የግጭት መሠረት ሆኗል። የዘር ፖለቲካው፣ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከምና የጋራ እሴትና ርዕዮት እንዳይኖር መሠራቱ፣ ኢትዮጵያዊነት ማንነት ከዘውግ ማንነት እንዲያንስ መሠራቱ፣ ከክልሉ ነዋሪዎች ውጭ የሆኑት ዜጎች መጤ መባላቸውና የመብት ጥሰት ናቸው። በተጨማሪም የግጦሽ መሬት፣ ሐብትና መሬት ፍለጋ፣ ግልፅ የሆነ ደንበርና ስርዓት አለመኖር፣ የአካባቢው ብልሹ አስተዳደርና በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት አለመስፈን፣ የውይይትና የመደራደር ባህል ማነስ፣ የግለሰብና የቡድን መብት አለመከበር፣ ድንቁርና፣ የእውቀት ማነስና የተሳሳተ መረጃ ናቸው።

በሃገራችን በህወሓት አገዛዝ የተማረረ ህዝብ ባደረገው ትግል ለውጥ እየተካሄደ ነው። የለውጡ ዋና መሪዎች የሆኑት ደግሞ የኢሕአዴግ አባል በሆኑት ኦህዴድና ብአዴን ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ናቸው። ነገር ግን የለውጡ ደጋፊዎች በሆኑት ኦህዴድና ብአዴን መካከል መተማመኑ ባለመኖሩ በሀገራችን አንድነት አደጋ እያንዣበበ ነው። በተጨማሪም በህውሓትና በኦነግ የተዘራው የዘውግ ፖለቲካ አውድ ለሀገራችን አንድነትና ለውጡን ለዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ እንዳንጠቀምበት እንቅፋት እየሆነ ነው። ይህም ህዝብን የለውጡ አምጪና ጠባቂ እንዲሆን፣ ብሎም በህገ-አራዊት የሚመራ የመንጋ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር አድረጓል።

የወቅታዊው አለመረጋጋት መንሰኤው ዋናው መንስኤ የሃይል በየቦታው መበተን (diffused power) ማለትም የሕወሓት መሪዎች ከንዴታቸው ያለመውጣትና በፌዴራል መንግስቱ ከልብ አለመሳተፍ፤ በኦሮምያ ያለው የሃይል ሚዛን በየቦታው በኦዴፓ፣ በኦነግና በቄሮ መበተኑ፤ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ፣ የጋራ ርዕዮት አለመኖር፣ አንዳንድ የወታደሩ፣ ደህንነቱና ፖሊሱ አባላት ለመንግስት ታዛዥ አለመሆን ወይም በለውጡ ለተገፉ ሃይሎች መወገንና በመንግስት ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ኦነግነት ማመዘን፤ የሚዲያ ሰዎችና አክቲቪስቶች ብፈልግ አሁኑኑ ክልሌን መገንጠል እችላለሁ፤ የመንጋ ስብስብ ሰው በየቦታው መጨፍጨፍ፤ ፓረቲዎች ከህግ ውጭ አዲስ አበባ የኛ ናት፤ ተፎካካሪ ፓረቲ ወታደሬ ትጥቅ አይፈታም ሲባል እያየን እየሰማን ነው። አሁንም በኦሮምያ፣ በአማራና በትግራይ የሚታዩ የተጋነኑ የጎሰኝነት ስሜቶች ለሀገር አንድነትና ዕድገት ተግዳሮት ናቸውና የሚመለከታቸው አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ከአደገኛ ድርጊታቸው ሊይታቀቡ ይገባል። የሚካሄደው አክቲቪዝም የአማራ፣ የኦሮሞና የትግሬ ብቻና በጉልበት የታገዘ ነው። የቀሩት ብዙሃን ጎሳዎች ጥያቄ ወደ ጎን የተገፋ ይመስላል።

ለችግሮቻችን የመፍትሄ ሃሳቦች ፦

 • 1) የለውጡን ቀጣይ ሂደት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት እና ተስማምቶ ወደ ቀጣይ ስራ መግባት፣
 • 2) ህገ-መንግስቱን በማሻሻል፣ በቋንቋ የተማከለውን የክልል ፌደራሊዝም በማስተካከል፣ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች በርዕዮተ-ዓለም መሰረት በማዋሃድና ብሔራዊ ፓርቲዎች እንዲሆኑ በማድረግ ለቀጠይ ሀገር ደህንነት መስራት፤
 • 3) ማዕከላዊነቱና አንድነቱ፣ እራስን ከማስተዳደሩና ብዝሃነቱ ጋር ሚዛኑን እንዲጠብቅ መስራትና የትም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብትን ማስከበር፤
 • 4) መንግስትም መሰረታዊ የመንግስት ግዴታዎች

4.1) ህግና ስርአትን ማክበርና ማስከበር፤ ብሎም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣
4.2) የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ፣
4.3) ዜጎች ሀገራቸውን “ሀገራችን” ብለው ይጠሩ ዘንድ የዜግነት ስሜትን እንዲፈጥሩና እንዲያዳብሩ ማድረግ፣
4.4) መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና ሀገራዊ ሀብትን በፍትሀዊነትና በእኩልነት ተመስርቶ ለዜጎች እንዲደርስ ማድረግና
4.5) ከሌብነትና ከወገናዊነት የፀዳ የአስተዳደር መዋቅር እንዲኖር ማድረግ፤

 • 5) ብሔራዊ እርቅን በተገቢው መንገድ ማከናወን፣ ያለመግባባትን በንግግር፣ በውይይት፣ በድርድር፣ በሕግ መደበኛ በሆነ የአለምና የሀገር ህጎችንና ተሞክሮዎችን መሠረት አድርጎ በመንግስት ደረጃና በኢ-መደበኝነት በባህላዊ ሽምግልና የማህበረሰቡን ነባር ባህሎች፣ ህጎችና እሴቶች ተከትሎ እንዲፈታ ማድረግ፤
 • 6) ለዲሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት፤ በመንግስት እንዲቋቋሙ ወይም እንዲጠናክሩ መስራት፤
 • 7) መንግስትን የሚመራው ኢሕአዴግ በተለይም ሕውሓት፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ በመፍታት ለሃገር አንድነትና ለሕዝብ ደህነት መስራት ይኖርበታል፤
 • 8) ይህንን በህገ-አራዊት የሚመራ የመንጋ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጠባብ የሆኑ፤ በሰላም ሀገር ውስጥ እንታገላለን ብለው የገቡ ወይም ሀገር ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ለራሳቸው አላማ እያነሳሱትና እየተጠቀሙበት ላለመሆኑ መንግስት ክትትል ሊያደርግ ይገባል፤
 • 9) የህዝብንና የፓረቲን ልዩነት ማወቅ፣ ሕዝብ ሁሌም በጎ መሆኑን መረዳት፤ ነገር ግን መጥፎ ግለሰቦች በማነኛውም ሕዝብ ውስጥ እንደሚኖሩ አውቆ ሁሉንም ወደሕዝብ ከማጠቃለል መቆጠብና ያም ሕዝብ ደህንነት እንዲሰማው ማድረግ ያስፈልጋል፤
 • 10) ትናንትና በሌሎች በመበደላችን ዛሬ ሌሎችን ለመበቀል መሞከር፣ በዳዮችም በፍርሃት ቆፈን ውስጥ በመግባት ለሀገር አንድነት መሰናክል መሆን፤ ለችግሮቻችን መቀጠል መንስኤ መሆኑን አውቀን ከዚህ ድርጊት መቆጠብ ይኖርብናል፤
 • 11) ፍትሕ ፈላጊ ማህበረሰብ ሕጎች እንዲወጡለትና እንዲሻሻሉለት የመጠየቅ፤ ሕገ-ወጦችን ለሕግ አሳልፎ የመስጠትና በሕግ የመመራት መብት ቢኖረውም፤ ሕግን የመተግበር ስልጣን የፖሊስና የፍርድ ቤቶች መሆኑን አውቆ በሕግ የበላይነት ማመንና ከሕግ ጥሰት መቆጠብ አለበት፤
 • 12) ክልላዊ መሠረት ያላቸውም ሆነ ሌሎች አገር አቀፍ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች በሚዲያ ህግ መሠረት እንዲሠሩ ማድረግ፣ አክቲቪስቶችም ከመጠን ያለፈ እንቅስቃሴ ለሀገር አደገኛ መሆኑን አውቀው ህዝብን በእውቀት ማንቀሳቀስ፣ የህግን የበላይነት ማወቀና ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፤
 • 13) የምናቃጥላቸው የግለሰብ፣ የፓረቲ ወይም የመንግስት ንብረቶች የኛውና የሀገር መሆኑን አውቀን ከዚህ ድረጊት ራሳችንን ማቀብ ይኖርብናል፤
 • 14) ጥሩ የትምህርት ስርዓት፣ የመጸሐፍት ህትመት፣ ላይብራሪዎች፣ ሚድያና የሚድያ ሕግ እንዲኖር በማድርግ ካለንበት ድንቁርና የሚያወጣ ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል፤
 • 15) በየአካባቢው ያሉ ስራ አጥ ወጣቶችን ለወንጀል በሚያነሳሱና በገንዘብ ወንጀል በሚያሰሩ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና የደህንነት ሰዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ፤
 • 16) ወጣቱን የስራ እድል የሚያገኝበትን ሁኔታ አመቻችቶ በተቻለ አቅም የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሩን እንዲፈታ ማድረግ፣
 • 17) በየክልሉ ሕገመንግስታዊ መሠረት ሳይዙ የተደራጁትን ልዩ ሃይሎችን በሕግ ማፍረስ፤ የልዩ ሃይል አባላትንም ወደ አገር መከላከያ ሰራዊት ወይም ወደ ሌላ የጸጥታ አካላት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ፣
 • 18) የመሳሪያ አያያዝ እና አጠቃቀምን በተመለከተ ሕግ አውጥቶ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት፣
 • 19) ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ የሰላም ማረጋጋት ስራ የሚሰራ ከህዝቡ የተውጣጣ የሰላም አስከባሪ አካል እንዲዋቀር ማድረግ ፤ ስራውንም የፌዴራሉ መንግስት በበላይነት እንዲመራው ማድረግ፣
 • 20) ይህ ተደርጎ መፍትሔ ካልሆነ የሃይል አማራጭ ጠረፔዛ ላይ መሆን አለበት። ያለዚያ ግን የሀገራችን ሰላም፣ አንድነትና ህልውና አደጋ ውስጥ ይሆናል።

ጠባብ ብሕርተኞች የሆኑት ሕወሓትና ኦነግ ያሉበትን ሀገር አረጋግቶ፣ ሰላሙንና ደህንነቱን ጠብቆ፣ ወደ ዲሞክራሲ ማሻገር በጣም ፈታኝ እየሆነ ነው። ፖለቲከኞቻችን ለጋራ ሀገራዊ ርዕዮትና ወሳኝ ችግሮቻችን ለመፍታት ካልሰሩና ጥቃቅኖቹን ከባቢያዊ ችግሮች ለመፍታት ጉልበታቸውን ካባከኑ ከችጋራምነታችን አንወጣም። ሕወሓትን ገፍቶ ከብዙኀኑ ለማስወጣት እየተሞከረ ቢሆንም የሚሞሉት ግን የኦነግ ፅንፈኞች ናቸው፣ አልሸሹም ዞር አሉ፣ ከድጡ ወደ ማጡ አየሄድን ነው። በአንድ ሀገር እየኖርንና በአንድ መንግስት እየተዳደርን፣ ነገር ግን የራሳችን ትርክቶች ይዘን በተለያየ ሀገር እንደሚኖሩ የማይተዋወቁ ህዝቦች አየሆንን ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየን የጋራ የሆነ ርዕዮተ-አለም እንዲኖረን እንዳልስራን፣ ማህበራዊ በሆነው ትስስርና የብሄር-ምስረታው እንዳልገፋን፣ የታሪክና የጥቅም ሽሚያው ላይ ሁሉንም ሃይላችን እያዋልነው መሆኑንና የትናንቱ መጥፎ ታሪክን ወደሚቅጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ እያደረግን መሆናችንን ነው።

ከታሪክና ስልጣን ሽሚያው ወጥተን፤ አገራዊ ነፃ ተቋማትን ገንብተን፤ በጠራ ርእዮተ-ዓለም ብቻ የምትመራ የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ። ለዚህም ግፊት እናድርግ። አለበለዚያ ግን ኢትዮጵያ በጊዜአዊ ጉልበት ብቻ ስልጣን የሚያዝባት፣ የተወሰነ ቡድን የሚጠቀምባት እና ብዙሃኑ የሚጎዳባት ሀገር እንዳትሆን እሰጋለሁ።

ዶ/ር መላኩ አዳል